March 25, 2019ሐራ ዘተዋሕዶ

“ለመሪ ዕቅዱ ትግበራ ኹለንተናዊ አስተዋፅኦ ያደርጋል” /ሰብሳቢው አቶ ታምሩ ለጋ/ ~~~ በለውጡ ሽፋን ለግልና ለቡድን ጥቅም የሚደረግን የጎሠኝነት እንቅስቃሴ አጥብቆ ይቃወማል፤ የአባቶችን አንድነት የሚጎዱና ተልእኮዋን የሚያሰናክሉ ተግባራትን ይከታተላል፤ ያጋልጣል፤ ለቤተ ክርስቲያን አንድነት ሳይጨነቁ ፍላጎታቸውን ለማሳካት የሚሯሯጡትን እንቃወማቸው፤ በልዩነቶች ከመሽቀዳደም ይልቅ፣ለቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በማቅረብ መፍትሔ ይፈለግ፤ የተፈናቀሉ ወገኖችን ለመርዳት እና ወደተረጋጋ ሕይወት ለመመለስ ዜጎች ሊተጋገዙ …► ሙሉውን ለማየት እዚህ ላይ ይጫኑ

የቤተ ክርስቲያንን አስተዳደራዊ ለውጥ የማሰናከልና አንድነቷን የመጉዳት እንቅስቃሴዎችን ሕዝቡ አጥብቆ እንዲቃወም ማኅበረ ቅዱሳን ጥሪ አቀረበ

March 25, 2019 Leave a comment

“ለመሪ ዕቅዱ ትግበራ ኹለንተናዊ አስተዋፅኦ ያደርጋል”

/ሰብሳቢው አቶ ታምሩ ለጋ/

~~~

***

***

00-5

በመሪ ዕቅድ የታገዘውን የቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ ለውጥ ጥረትን ለማሰናከል፣ የመዋቅሯንና የአባቶችን አንድነት ለመከፋፈልና ለመጉዳት፣ በአካባቢያዊነትና በጎሠኝነት እየተደረጉ ያሉ እንቅስቃሴዎችን እየተከታተለ እንደሚያጋልጥ ማኅበረ ቅዱሳን አስታወቀ፤ መላው ሕዝበ ክርስቲያንም በማስተዋልና ኦርቶዶክሳዊ ሥርዓትን በጠበቀ መልኩ አጥብቆ እንዲቃወማቸው ጥሪ አቀረበ፡፡

በማኅበሩ የዋናው ማእከል ጽ/ቤት የተዘጋጀውና ከ15ሺሕ ምእመናን በላይ የተሳተፉበት 16ው ዙር የሐዊረ ሕይወት መርሐ ግብር፣ ትላንት እሑድ፣ በሰሜን ምዕራብ ሸዋ – ሰላሌ ሀገረ ስብከት አሌልቱ ወረዳ ደብረ ኀይል ቅዱስ ዐማኑኤል እና ዘራማ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ተካሒዷል፡፡ የመርሐ ግብሩ አንዱ ዓላማ፣ ምእመናን የገጠር አብያተ ክርስቲያን ያሉበትን ኹኔታ ተረድተው የድርሻቸውን እንዲወጡ ለማመቻቸት እንደኾነ፣ በመክፈቻው መልእክት ያስተላለፉት የማኅበሩ ሰብሳቢ አቶ ታምሩ ለጋ፣ የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር እና የአባቶች አንድነት መጠበቅ እንዲሁም በይፋ የተጀመረው የመሪ ዕቅድ ትግበራ መሳካት፣ ለተጠናከረ ኹለንተናዊ ዕድገቷ ወሳኝ እንደ ኾነ አስገንዝበዋል፡፡

በአባቶች ዕርቅ የተመለሰው የቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ አንድነት፣ ኹለንተናዊ ዕድገቷን ለማጠናከር መልካም ዕድል መክፈቱንና ለዚህም ቅዱስ ሲኖዶስ እንዲተገበር የወሰነው የቤተ ክርስቲያን መሪ ዕቅድ ተግባራዊነት ወሳኝ በመኾኑ፣ ማኅበሩ በእጅጉ እንደሚደግፈው ገልጸዋል፤ ለውጤማነቱም፣ በዕውቀትም በጉልበትም ኾነ በሌሎች መንገዶች አባላቱን በማስተባበር ኹለገብ አስተዋፅኦ ለማበርከት ዝግጁ እንደኾነ አረጋግጠዋል፡፡

በመሪ ዕቅድ የታገዘው ተቋማዊ ለውጥ፥ በሰው ሀብት አስተዳደር፣ በገንዘብና ንብረት አያያዝ የሚታየውን የአወቃቀር፣ የዕቅድ፣ ትግበራና ክትትል ግዙፍ ችግሮች የሚቀርፍና ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ ተልእኮዋን በአግባቡ እንድትወጣ የሚያስችል በመኾኑ፣ ምእመናን በአጠቃላይ፣ መሪ ዕቅዱ ተፈጻሚ እንዲኾን፣ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት እስከ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ድረስ በተዋረድ በሚገኙ መዋቅሮች፣ ድጋፍና ክትትል በማድረግ እየተሳተፉ የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

12294847_757928317671846_3548580655651410115_n

በሌላ በኩል፣መላው ሕዝበ ክርስቲያን በጉጉት የሚጠብቀውን የአስተዳደር ለውጥና ማሻሻያ ሽፋን በማድረግ ሥልጣን ለማግኘትና ጥቅም ለማጋበስ በአካባቢያዊነትና በጎሠኝነት የሚካሔዱ እንቅስቃሴዎች መኖራቸውን የጠቆሙት ሰብሳቢው፣ የለውጡን አቅጣጫ በማሳት ግላዊና ቡድናዊ ፍላጎትን የማሳካት ዓላማ ያላቸው በመኾኑ ማኅበረ ቅዱሳን አጥብቆ እንደሚቃወማቸው አስታውቀዋል፡፡

የመንግሥት ለውጥን ተከትሎ በ1967 እና በ1983 ዓ.ም.፣ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ጠቃሚ ለውጦችን ለማምጣት ቅን ሙከራዎች ተደርገው የነበረ ቢኾንም፣ እንቅስቃሴዎቹ ሌላ አቅጣጫ በመያዛቸው ቤተ ክርስቲያን እንደተጎዳችበት ሰብሳቢው አስታውሰዋል፡፡ ዛሬም፣ የቤተ ክርስቲያኒቱ መዋቅራዊ አንድነት ተናግቶም ቢኾን የራሳቸውንና የቡድናቸውን ፍላጎት ለማሳካት ቅር የማይላቸው አካላት፣ ይህንኑ አሳዛኝ ታሪክ ለመድገም የሚያደርጉትን ሩጫ ሕዝበ ክርስቲያኑ ተረድቶ፣ በማስተዋልና ኦርቶዶክሳዊ ሥርዓትን በጠበቀ መልኩ በግልጽ እንዲቃወመው ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በዕርቀ ሰላም የተመለሰውን የቤተ ክርስቲያንና የአባቶች አንድነት የሚጎዱና ሐዋርያዊ ተልእኮዋን በአግባቡ እንዳትወጣ የሚያሰናክሉ ተግባራትን ማኅበሩ እየተከታተለ ለሕዝበ ክርስቲያኑ እንደሚያሳውቅ አቶ ታምሩ ገልጸዋል፡፡ ኹሉም አካላት በልዩነቶች ከመሽቀዳደም ይልቅ፣ በቅርቡ በሚካሔደው የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ላይ ጉዳያቸውን አቅርበው መፍትሔ እንዲፈልጉለት የጠየቁት የማኅበሩ ሰብሳቢ፣ በያዝነው የዐቢይ ጾም ወቅት፣ ስለ ቤተ ክርስቲያን መዋቅራዊ አንድነት መጽናትና ስለ ሕዝብ ደኅንነት መጸለይ ትኩረት እንዲሰጠው ተማፅነዋል፡፡

አገራችንም በተለያየ አቅጣጫ እያጋጠማት ባለው ፈተና፣ የውድ ልጆቿ ሕይወት እየተቀጠፈ፣ ንብረት እየወደመ፣ ዜጎች ከቤት ንብረታቸው እየተፈናቀሉ በመኾኑ፣ የተቸገሩትን ለመርዳት፣ የተራቡትን ለመመገብ፣ የታረዙትን ለማልበስ በዋናነትም፣ ከገቡበት ምስቅልቅል ኹኔታ ወጥተው የተረጋጋ ሕይወት እንዲኖራቸው እያንዳንዳችን እንድንተጋገዝ ማኅበሩ በመርሐ ግብሩ ላይ መልእክት አስተላልፏል፡፡ ጥያቄዎችና ሐሳቦች፣ በተረጋጋና በኢትዮጵያዊ ጨዋነት እንዲቀርቡና እንዲስተናገዱ፤ እግዚአብሔር አምላክ አገራችንንና ሕዝቧን በምሕረት እንዲጎበኝ በጾምና በጸሎት መትጋት እንደሚያስፈልግ ማኅበሩ የጉዞውን ተሳታፊዎች አዘክሯል፡፡

ላለፉት ሰባት ዓመታት በአዲስ አበባ እና በመላው ዓለም ሲካሔድ የቆየው የማኅበረ ቅዱሳን የሐዊረ ሕይወት መርሐ ግብር፣ ምእመናን ቃለ እግዚአብሔርን ከሊቃውንት፣ መምህራንና አባቶች አንደበት እንዲማሩና እንዲያውቁ፤ እንዲሁም በየአቅራቢያቸው የሚገኙ የገጠር አብያተ ክርስቲያን ያሉበትን ኹኔታ ተረድተው በአገልግሎት የድርሻቸውን እንዲወጡ የማመቻቸት ዓላማዎች አሉት፡፡

“የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ አገልግሎትና ኢኮኖሚያዊ አቅም ተጠናክሮ፣ የጌታችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርተ ወንጌል በመላው ዓለም ተስፋፍቶ፣ በሃይማኖት ጽኑዓን የኾኑ ምእመናን በመላው ዓለም በዝተው ማየት” በሚለው ርእዩ፣ የቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት ዓለም አቀፋዊ ለማድረግ ማኅበሩ አድማሱን በማስፋት ላይ ይገኛል፡፡

በአገር ውስጥ አህጉረ ስብከት 48 ማእከላትና 400 የወረዳ ማእከላት እንዲሁም 101 የግንኙነት ጣቢያ መዋቅሮችን፤ በውጭ አህጉር ደግሞ በኬንያ፣ በአውሮጳ፣ በሰሜን አሜሪካ እና በካናዳ 4 ማእከላት እንዲሁም በተለያዩ የዓለም ክፍሎች 22 ንኡሳን ማእከላትና 21 የግንኙነት ጣቢያዎች በመመሥረት፣ የቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት አጠናክሮ ለማስቀጠል የበኩሉን ጥረት እያደረገ እንደኾነም ተመልክቷል፡፡