April 28, 2019

“እዚህ አገር ያለን የፖለቲካ ድርጅቶች 50 ዓመት ሙሉ ስንቃወም ነው የኖርነው:: ከመቃወም ውጭ ሌላ ነገር አናውቅም&… April 292019

“ሲራራ” ሞሪንጋ ያነሳት የጋሞዋ ፀሐይ April 29, 2019

Make Justice a Priority in Ethiopia’s Transition

“እዚህ አገር ያለን የፖለቲካ ድርጅቶች 50 ዓመት ሙሉ ስንቃወም ነው የኖርነው:: ከመቃወም ውጭ ሌላ ነገር አናውቅም” ዶክተር ፍቅሩ

“እዚህ አገር ያለን የፖለቲካ ድርጅቶች 50 ዓመት ሙሉ ስንቃወም ነው የኖርነው:: ከመቃወም ውጭ ሌላ ነገር አናውቅም” ዶክተር ፍቅሩ

April 29, 20190

አንድ እስረኛ እንዴት ጓደኛውን እሳት ውስጥ ይከታል? እኔ ልንገርህ፣ ፍቅርን ያየሁት እዚያ እስር ቤት ውስጥ ነው:: በክስ ሂደቱ ለምስክርነት ይመጡ የነበሩት ወታደሮች አንዴ 40 ሺ ሌላ ጊዜ ደግሞ 45 እና 50 ሺ ብር «የእርሳቸው ዘመድ አምጥቶ በምሳ እቃ አድርጌ ይዤ ገባሁ» ይላሉ:: አለቃቸው ደግሞ መጥቶ «ምሳ እቃ ይፈተሻል ወይ» ተብሎ ሲጠየቅ «በደንብ ነው የሚፈተሸው» ይላል:: ሌሎች እስረኞችንም እየደበደቡ በእኔ ላይ እንዲመሰክሩ ያስገድዱ ነበር::

ተወልደው ያደጉት አዲስ አበባ በፈረንሳይና ጣሊያን ኤምባሲ መካከል በሚገኝ ጉራራ በሚባል ሰፈር ውስጥ ነው:: የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን ኮከበ ጽባህ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል:: የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አሰላ በመምህርነት የተመደበ ታላቅ ወንድማቸው ጋር በመሄድ ራስ ዳርጌ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተምረዋል::

ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁም ወደ አየር ኃይል በማቅናት ስድስት ዓመታትን በጄት አብራሪነት አገልግለዋል:: በንጉሱ ዘመን መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት በማሰብ በአጼ ኃይለስላሴ ላይ አመጽ ሲነሳ ከአስተባባሪዎቹ መካከል አንዱ ነበሩ::

በኋላ እነ ኮሎኔል መንግስቱ ስልጣን ለመያዝ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ መቃወማቸውን ተከትሎ ሊታሰሩ እንደሆነ ከውስጥ አዋቂ መረጃ ስለደረሳቸው ከደብረ ዘይት ወደ ሱዳን ጠረፍ ሸሹ:: ከሀገር ለመውጣት የተለያዩ ጥረቶች እያደረጉ ስድስት ወራትን ከቆዩ በኋላ ተሳክቶላቸው ሱዳን ገቡ:: እርሳቸው ያመለጡት ደርግ ሁለት ወንድሞቻቸውን በቀይ ሽብር ገድሎባቸዋል::

ሱዳን የመኪና ጋራዥ ውስጥ እየሰሩ ዘጠኝ ወራትን ቆይተው በስዊዲን ጋዜጠኞች እገዛ በ1967 ዓ.ም ስውዲን ገቡ:: በስውዲን ቆይታቸው ፖስታ ቤት በደብዳቤ ዘርዛሪነት እየሰሩ የአገሩን ቋንቋ ተምረዋል:: ከአንድ ጓደኛቸው ጋር በመሆንም ካፍቴሪያ ከፍተው የነበረ ሲሆን ስላተሳካላቸው ዘጉት::

ተምረው ነጥባቸውን በማሻሻል ስቶኮልም ዩኒቨርሲቲ በመግባት አስተማሪ ለመሆን ሁለት ዓመት ተኩል ሒሳብና ፊዚክስ ተምረዋል:: ስዊዲን ሀገር ለጥቁር ሰው አስተማሪ መሆን አስቸጋሪ ስለነበር «ካሮሊንስካ ኢንስቲትዩት» የህክምና ትምህርት ቤት ገብተው ትምህርታቸውን በጥሩ ውጤት አጠናቀዋል:: በውጭ አገር በነበራቸው ቆይታ ረጅም ዓመታት በልብ ሀኪምነት ከማገልገል ባለፈ በአውሮፓ የኢህአፓ መሪ በመሆን በፖለቲካው ዓለም ንቁ ተሳታፊ ነበሩ::

ፖለቲካውን እርግፍ አድርገው በመተው በሙያቸው አገራቸውን ለማገዝ የወሰኑት በ1991 ዓ.ም. የስውዲን ልዑኩን በመምራት በኢትዮጵያ በሚካሄደው የኤች አይ ቪ ኮንፍረንስ ላይ ለመሳተፍ መጥተው አገራቸውን ከተመለከቱ በኋላ ነው:: ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው አነስተኛ ክሊኒክ ከፍተው ሦስት ዓመታት ከሰሩ በኋላ ከስውዲን መንግሥትና ከሌሎች በለሀብቶች ጋር በመሆን አዲስ የልብ ህክምና ሆስፒታልን በ1998 ዓ.ም አቋቁመው ህክምና ከመስጠት ባለፈ ኢትዮጵያውያንን ወደ ስውዲን ሀገር በመላክ በልብ ሐኪምነት እንዲሰለጥኑ በማድረግ ላይ ናቸው::

የህክምና መሳሪያዎችን ያለቀረጥ አስገብተዋል በሚል በ2005 ዓ.ም በተመሰረተባቸው ክስ 4 ዓመት ከስምንት ወር ቢፈረድባቸውም ጠቅላይ ፍርድ ቤት ክሱን ውድቅ አድርጎት በነጻ አሰናብቷቸዋል:: በኋላም ቂሊንጦ እስር ቤት በእሳት እንዲነድ አድርገዋል በሚል በሽብርተኝነት ተከሰው ተጨማሪ ወራትን በእስር አሳልፈው ከአምስት ዓመታት እስር በኋላ ለውጡን ተከትሎ ከእስር ተለቀዋል::

የስዊድን መንግሥት ከእስር እንደተለቀቁ ተቀብሎ ወደ ሀገሩ ቢወስዳቸውም ከአምስት ሳምንት በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው አገራቸውንና ህዝባቸውን ማገልገላቸውን ቀጥለዋል:: እኚህ ባለታሪክ የልብ ሐኪሙ ዶክተር ፍቅሩ ማሩ ናቸው::

ዶክተር ፍቅሩ ከእስር ከተለቀቁ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ስለተመሰረተባቸው ክስ፣ ስለ ፍርድ ሂደቱና በእስር ቤት ውስጥ ስለተፈጸመባቸው በደል ለአዲስ ዘመን ተናግረዋል:: በተጨማሪም ስለለውጡና ተያያዥ ጉዳዮች የግል ምልከታቸውን አካፍለውናል ፣ መልካም ቆይታ::

አዲስ ዘመን:- በእርስዎ ላይ የተመሰረተው የመጀመሪያው ክስ «የህክምና መሳሪያዎችን ያለቀረጥ አስገብተዋል» የሚል ነው:: የክሱ ምክንያት ምንድን ነው ?

ዶክተር ፍቅሩ:- የልብ ቀዶ ጥገና የሚደረግላቸው ስምንት ታካሚዎች ነበሩን:: አጋጣሚ አገር ውስጥ የደረሰልን ለሦስት ሰዎች ብቻ የሚሆን አላቂ ዕቃ ነበር:: ቀዶ ጥገና በሚደረግበት ጊዜ ልብ ይቆማል በዚህ ጊዜ የልብንና ሳንባን ሥራ ተክቶ የሚሰራ ማሽን አለ:: ይህን መሳሪያ ከልብ ጋር የሚያያይዙ ቲዩቦች ከሌሉ ህክምናውን ማከናወን ስለማይቻል ለተቀሩት አምስት ሰዎች በአራት ሻንጣዎች እነዚህን መሳሪያዎችና ጓንቶች ይዤ መጣሁ:: ጉምሩክ ስደርስ ለድንገተኛ የመጣ ነው ብዬ ሰጠኋቸው:: ደረሰኝ ስለሚያስፈልገው ይዘህ አትገባም አስፈቅደህ ማምጣት ነበረብህ ሲሉኝ ትቼው ገባሁ::

በሌላ ጊዜ ወደ ስዊዲን ስመለስ ይዘህ ሂድ አሉኝ:: እዚህ ቁጭ ብሎ ከሚበላሽ አስፈቅጄ እመጣለሁ ብዬ ይዤ ልወጣ ስል ለእያንዳንዱ ሻንጣ 175 ዶላር መክፈል አለብህ አሉኝ:: ልከፍል ሄጄ ክፍያውን በቪዛ ካርድና በማስተር ካርድ ልክፈል ስል ሲስተሙ አይሰራም አሉኝ:: ካልሰራ አውሮፕላን ከሚያመልጠኝ እኔን ልትሸኘኝ የመጣች አንድ ልጅ አለች ወደ ጉምሩክ እንድትመልሰው ለሷ ስጧት ብዬ «ፖርተር» ለሚገፉ የአየር መንገድ ሠራተኞች ሰጥቼ እነርሱ ይዘውት ወጡ:: በኋላ የጉምሩክ ሰዎች እየሮጡ መጥተው «ከአገር ይውጣ የተባለ እቃ ወደአገር ውስጥ በኮንትሮባንድ ልታስገባ ነው» ብለው እዛው አሳደሩኝ:: ስምንት ቀን ታስሬ ከአገር እንዳትወጣ ተብዬ ስምንት ወር

ያህል ፍርድ ቤት ስመላለስ ቆየሁ::

የፀረ ሙስና ኮሚሽነር የነበሩት አቶ አሊ ሱሌይማን ታካሚዬ ስለነበሩ ቢሮ ሄጄ እነዚህ ሰዎች ከሰሱኝ ብዬ ምክንያቱን አስረዳኋቸው:: እኔው ፊት ደውለው ምክትሉን አቶ ገብረዋህድን «ይህ ሰው መርካቶ ወስዶ ሊሸጥ ነው ? የሚያሳፍር ሥራ እንዴት ትሰራለህ ይህን ነገር ተው» ብለውታል:: አቶ ገብረዋህድን ተመላልሼ ለማናገር ብሞክርም ምንም መፍትሄ አላገኘሁም:: ችግሬን ላስረዳው አቶ መላኩ ፈንታን ለማግኘት ተዳጋጋሚ ጥረት ባደርግም አልተሳካልኝም::

በሌላ ጊዜ በሥራ አጋጣሚ በወቅቱ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር የነበሩትን ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖምን አግኝቼ ሁኔታውን አስረድቻቸው ስመለስ ቤቴ ሳልደረስ ደውለውልኝ «ሰኞ ጠዋት አቶ መላኩ ጋር ሂድ» አሉኝ:: ስሄድ አቶ እሸቱ ወልደሰማያት ከተባለ የህግ አማካሪው ጋር ጠበቀኝ:: ተቀምጬ ሶስታችን ሰላሳ ደቂቃ ያህል ካወራን በኋላ «ኢንቮይስ ማምጣት ነበረብኝ» ብለህ ደብዳቤ ጻፍና ክሱ ይሰረዝ ብለውኝ ጽፌ አስገባሁ:: በቀጠሮ ቀን ፍርድ ቤት ስሄድ አቃቤ ህጉ ክሱን አንስቻለሁ ብሎ ክሱ ተቋረጠ::

ቆይቶ እነመላኩ ፈንታና ገብረዋህድ በታሰሩ ማግስት እሁድ ጠዋት አሥራ ስድስት ፌዴራል ፖሊሶች ቤቴን ከበቡት:: ይዘውኝ ቤቴን ከበረበሩና ሥራዬ ቦታ ከወሰዱኝ በኋላ ማዕከላዊ ወስደው አሰሩኝ:: የታሰርኩበትን ምክንያት ሳላውቅ አንድ ሳምንት ካለፈኝ በኋላ ነው መጥተው ያናገሩኝ:: በምን ምክንያት እንደታሰርኩ ስጠይቃቸው «ለመላኩ ጉቦ መስጠትህን እናውቃለን አንተ እንድታምን ነው የምንፈልገው» አሉኝ:: አትቀልዱ ማስረጃ ካላችሁማ አቅርቡ። ለምን ትጠይቁኛላችሁ አልኩኝ::

አዲስ ዘመን:- በማዕከላዊ ቆይታዎ እንዴ ነበር የተያዙት ?

ዶክተር ፍቅሩ:- ማዕከላዊ አራት ወራት ቆይቻለሁ:: እርግጥ አልደበደቡኝም። ነገር ግን እያሰሩ ያውሉኝና ይሰድቡኝ ነበር:: በተጨማሪም ሞራሌን ዝቅ ለማድረግ ሞክረዋል:: ዓላማቸው ስለገባኝ እኔ ምንም አልመሰለኝም::

አዲስ ዘመን:- የፍርድ ሂደቱ ምን ይመስል ነበር ?

ዶክተር ፍቅሩ:- ወደ ቂሊንጦ ከገባሁ በኋላ ክሱ ተመሰረተ:: ጉቦ ሰጠህ እንዳይሉ ተቀብያለሁም ሰጥቻለሁም የሚል ሰው ጠፋ:: የጥቅም ግንኙነት አለህ በሚል ጥፋተኛ ነህ ተከላከል አሉኝ:: ምን እንደምከላከል እንኳን አላውቅም:: የመሰከረብኝ አንድ ሰው ነው:: በቅርብ የማውቀውና ዋሽቶኝ የተጣላሁት ማህሊ የሚባል ሰው «ክሱ የተሰረዘላቸው ቀን ዶክተር ደውለው ጠሩኝና መኪና ውስጥ ሆነው እኔኮ ለገብረዋህድና መላኩ ለእያንዳንዳቸው 2 መቶ ሺ ብር ሰጥቼ ነው ክሱን ያሰረዝኩት» ብለው ነግረውኛል ብሎ ነው የመሰከረው:: በመሃል ሀሙስ ቀን በጣም ታምሜ ሳንባዬ ፈንድቶ ወደ ጥቁር አንበሳ ወስደውኝ ወዲያውኑ ቀዶ ጥገና ተደረገልኝ:: ቆይቼ ክሱን አልከላከልም አልኩኝ::

በዚህ ጊዜ ፍርድ ቤቱ (ችሎቱ) የተኛሁበት ሆስፒታል ድረስ መጣ:: ሦስቱ ዳኞች፣ ጠበቃ ፣ አቃቢ ህግና ፖሊስ ሆስፒታል ውስጥ መጥተው አስር ደቂቃ አናግረውኝ 4 ዓመት ከ8 ወር ፈርደውብኝ ሄዱ:: ዳኛ በሪሁ በመጀመሪያው ክስ ሰው አገናኝቶኝ አማክሬው «እንዲህ ብለህ መከራከር ትችላለህ አያስከስስህም» ያለኝ ሰው ነው::

ጉዳዩን እያወቀ እኔን ሲዳኝ ነበር:: የዚህን ሰው ጉዳይ ስለማውቀው አልዳኝም ብሎ ራሱን ማግለል እንጂ የመሃል ዳኛ ሆኖ መቅረብ አልነበረበትም:: ከስዊዲን ሶስት ዶክተሮች መጥተው ቀዶጥገና ተደርጎልኝ ከሆስፒታል ድኜ ከወጣው በኋላ ጠቅላይ ፍርድ ቤት አቤት አልኩኝ:: ፍርድ ቤቱም ክሱን ውድቅ አድርጎት በነጻ አሰናበተኝ ::

አቶ አሊ ሱሌይማን ክሱ በማን እንደተሰረዘ እያወቁ «ጉቦ ሰጥቶ ነው ያሰረዘው» ሲባል ዝም ማለታቸው አልበቃ ብሏቸው ጭራሽ በቴሌቪዥን «የነቀዙ ህሊናዎች» ብለው የእኔን ፎቶግራፍ እያሳየ ዘጋቢ ፊልም መልቀቁ እጅግ በጣም አሳዝኖኛል:: ዶክተር ቴዎድሮስም አቶ መላኩ ፈንታን በስልክ አናግረው ክሱ እንዲሰረዝ ማድረጋቸውን ኃላፊነት ወስደው ባለመመስከራቸው አዝኜባቸዋለሁ::

እነዚህን ሰዎች አግኝቼ ባናግራቸው ደስ ይለኛል:: እኔ አገር ልርዳ ብዬ የመጣሁ ሰው ነኝ:: ውጭ ሀገር ተጨማሪ ሰዓት ስሰራ በሳምንት 14 ሺ ዶላር ይከፈለኛል:: እዚህ ግን በቀን 2 መቶ 50 የኢትዮጵያ ብር ነው ሚከፈለኝ:: ለገንዘብ ብሎ ጓንትና አላቂ እቃዎች ሊሸጥ መጣ ብለው ሲከሱኝ ዝም ማለት አልነበረባቸውም::

አዲስ ዘመን:- ሁለተኛው ክስ በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ከተነሳው እሳት ጋር በተያያዘ በሽብርተኝነት የተከሰሱበት ነው:: የተመሰረተብዎ ክስ ዝርዝር ሁኔታና የፍርድ ሂደቱ ምን መልክ ነበረው ?

ዶክተር ፍቅሩ:- እኔ ታምሜ ሐሙስ ዕለት ሆስፒታል ገብቼ ቅዳሜ ነው ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት የተቃጠለው:: የተኛሁበት ሆስፒታል መርማሪዎች መጥተው «ገንዘብ ሰጥተህ ፤ አደራጅተህ አንተህ ራስህን ለማዳን ቸኮላት በልተህ ሳንባህን አፈንድተሃል» አሉኝ:: ሳንባና ጨጓራን ምን አገናኘው? 38 ሰዎች ተመርጠን ገድለዋል አቃጥለዋል ተብለን ነው በነብስ የተጠየቅነው::

አንድ እስረኛ እንዴት ጓደኛውን እሳት ውስጥ ይከታል? እኔ ልንገርህ፣ ፍቅርን ያየሁት እዚያ እስር ቤት ውስጥ ነው:: በክስ ሂደቱ ለምስክርነት ይመጡ የነበሩት ወታደሮች አንዴ 40 ሺ ሌላ ጊዜ ደግሞ 45 እና 50 ሺ ብር «የእርሳቸው ዘመድ አምጥቶ በምሳ እቃ አድርጌ ይዤ ገባሁ» ይላሉ:: አለቃቸው ደግሞ መጥቶ «ምሳ እቃ ይፈተሻል ወይ» ተብሎ ሲጠየቅ «በደንብ ነው የሚፈተሸው» ይላል:: ሌሎች እስረኞችንም እየደበደቡ በእኔ ላይ እንዲመሰክሩ ያስገድዱ ነበር::

በዚህ ሁኔታ ላይ እያለሁ ለውጡ መጣ ተለቀቅን:: ቂሊንጦ እያለሁ በተለይ አሁን በእስር ላይ የሚገኙት የማረሚያ ቤት ኃላፊዎች ምግብ በመከልከል፤ መድኃኒትና ህክምና እንዳላገኝ በማድረግ ፤ ጥቁር አንበሳ በተኛሁበት ወቅትም እዚያ የምትሰራው ልጄ እንዳታክመኝ በማድረግ በብዙ መንገድ ታግለዋል:: እነርሱም ታስረዋል አሁን ትክክለኛ ፍርድ ቢሰጣቸው ጥሩ ነው::

አዲስ ዘመን:- የእርስዎ እስር ፖለቲካዊ ነው የሚሉ ወገኖች አሉ:: ትክክል ናቸው ?

ዶክተር ፍቅሩ:- አዎ በሁለት መንገድ:: እኔ ድሮም ውጭ ሀገር የኢህአፓ መሪ ነበርኩ:: ከኢህአፓ ከወጣሁ በኋላም አገር ሸጣችሁ ኢትዮጵያን ያለ ባህር በር አስቀራችሁ በሚል ስለምታገላቸው ኢህአዴጎች በጠላትነት ፈርጀውኝ ነበር:: ይህ የተወሰነ አስተዋጽኦ ሳያደርግ አይቀርም:: ዋናው ነገር የሚመስለኝ ግን እነ አቶ መላኩ ፋንታን በሙስና ለመክሰስ ጉቦ ሰጠ የሚባል ሀብታም ሰው ስለሚያስፈልግ እኔን ማጣፈጫ አድርገውኛል::

በነገራችን ላይ ገቢዎች የአዲስ የልብ ህክምና ሆስፒታልን 1 ዓመት ከ 2 ወር ኦዲት አድርጎታል:: የትኛውም ድርጅት በ28 ቀን ነው ኦዲት የሚደረገው ይህን ያህል ጊዜ የወሰዱት እኔ ላይ አንዳች ነገር ለማግኘት ነበር አልተሳካላቸውም:: ስድስት ኦዲተሮች እየተቀያየሩ ኦዲት አድርገው መጨረሻ ላይ የተገኘው እንደውም እኛ ገቢዎች ላይ ዘጠና ሺ ብር እንዳለን ነው::

አዲስ ዘመን:- በእስር ላይ እያሉ ፍርድ ቤት በቀረቡ ቁጥር «ታጅቤ ወጥቼ ግማሽ ቀን እንኳን ሁለት ሶስት የልብ ህሙማን ላክም» እያሉ ይማጸኑ ነበር:: አንድ ችሎት ላይ ፍቃድ አግኝተው አንድ ቀን ካከሙ በኋላ ተከልክለዋል:: ህክምናውን መስጠት ባለመቻልዎ 20 ታካሚዎችዎ ህይወት አልፏል:: በአዲስ የልብ ህክምና ሆስፒታል የሚገኙ አሊያም ሌሎች ሀኪሞች ህክምናውን ማከናወን አይችሉም ነበር?

ዶክተር ፍቅሩ:- ብዙ የልብ ሐኪሞች ቢኖሩም እኔ ብቻ የሰለጠንኩበት የልብ ባትሪ መትከል ህክምና አለ:: ስልሳ ለሚደርሱ ሰዎች የልብ ባትሪ አስገብቼላቸዋለሁ:: ይህ ባትሪ አምስትና ስድስት ዓመት ከሞላው በኋላ ስለሚያልቅ መቀየር አለበት:: አንድ ታካሚዬ እስር ቤት መጥታ «ዶክተር ባትሪው ደክሟል ሊያልቅ ነው ብለውኛል ምን ላድርግ ?» አለችኝ:: ስታለቅስ ከማልቀስ በቀር መልስ አልሰጠውም ነበር:: ከስምንት ቀናት በኋላ ይህች ሰው ሞተች::

በወቅቱ የነበሩት ዳኞች ምንም ስሜት የማይሰጣቸው ነበሩ:: ጊዜና የሰው ህይወት የረከሰበት አገር ይሄ ነው:: 30ና 40 ደቂቃ የማይፈጅ ሥራ ሰርቼ ብመጣ ምን አለበት? እነኚህ መርማሪዎችና ዳኞች እቤታቸው ሄደው ለቤተሰቦቻቸው ምን ሰርቼ ገባሁ እንደሚሏቸው አላውቅም:: ከእስሩ የበለጠ የሚቆጨኝ፤ የሚያንገበግበኝና ከልቤ ውስጥ የማይጠፋው የእነዚህ 20 ሰዎች ሞት ነው::

አዲስ ዘመን:- እርሶን ጨምሮ በርካቶች ከለውጡ በኋላ ተፈተዋል፤ ለውጡን እንዴት ያዩታል ?

ዶክተር ፍቅሩ:- ኢትዮጵያ ውስጥ እየተደረገ ያለው ከዚህ በፊት በተለይ በአፍሪካ ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ ነገር ነው:: እነ ዶክተር አብይ ያደረጉት ነገር በቤት ውስጥ ሌላ ቤት መስራት ነው::

መንግሥት እያለ በመንግሥት ውስጥ ሆነው ሌላ መንግሥት መስርተዋል:: ቀደም ሲል የነበረውን መዋቅር ይዞ እሱኑ እየተጠቀመ መቀየር ያለባቸውን ሰዎችና መዋቅር እየቀየረ ሳያፈርስ እየገነባ ያለ ለውጥ ነው:: እንዲህ ዓይነት ለውጥ ቀላልም ከባድም ነው:: «ሀ» ብሎ ተቋም ግንባታ ውስጥ መግባት አለመጠየቁ ቀላል ሲያደርገው ለውጡን የማይደግፉ ሰዎችን አቅፎ መያዙ ከባድ ያደርገዋል::

እውነት ነው አሁንም ኢህአዴግ ነው ያለው:: እኔን እኮ ያሰረኝ የኢህአዴግ መንግሥት ነው:: ነገር ግን አሁን ኢህአዴግ ውስጥ ልክ እንደ እኔ ኢትዮጵያዊነት ስሜት የሚሰማቸው እንደ ዶክተር አብይ ዓይነት ሰዎች ስላሉ ማገዝ ያስፈልጋል::

በእኔ የዕድሜ ክልል የሚገኙ ሀሳባቸው ጡረታ ያልወጣ እነሱም ጡረታ ያልወጡ ብዙ ሰዎች አሉ:: በየቴሌቪዥኑ ቁጭ ብለው ከ 50 ዓመት በፊት ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ስለነበረ የብሔርተኝነት እንቅስቃሴ ሲያወሩ ስመለከት ያሳፍረኛል:: እንዴ … ለዚህ ትውልድ እንተውለት፤ ጡረታ እንውጣ:: ካስፈለገ ምክር እንስጣቸው ምክር የሚፈልግ ትውልድ መጥቷል:: ወጣቱ አለ :: ዶክተር አብይ እኮ ለእኔ የበኩር ልጄ ነው የሚሆነው ፣ ለእሱ የአባትነት ምክር ልሰጠው እንጂ በአንተ ቦታ ሆኜ ላስተዳድር ልለው አይገባም::

እዚህ አገር ያለን የፖለቲካ ድርጅቶች 50 ዓመት ሙሉ ስንቃወም ነው የኖርነው:: ከመቃወም ውጭ ሌላ ነገር አናውቅም:: 40ና 50 ዓመታት የቆዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች አንዲት ቀበሌ አስተዳድረው የማያውቁና ሲቃወሙ የኖሩ ናቸው:: አሁን ሊቃወሙት የማይችሉት አስተሳሰብ ያለው ሰው ሲመጣ ካልተቃወሙ መኖር ስለማይችሉና ድጋፍ ስለማያገኙ መቃወም ይጀምራሉ።

ምክንያቱም መደገፍን አልተማሩም:: አንድ ሰው አንድ ድርጊት ሲፈጽም ድርጊቱን በሰከነ መንገድ ሳንመረምር አብሮ መሰለፍን ስለለመድን እነዚህ ሰዎች ተከታይ አያጡም:: ዶክተር አብይ የሚመሩት መንግሥት አንዳንድ ጉዳይን ይስከን በሚል ተወት ማድረጉ ትክክል ይመስለኛል::

አዲስ ዘመን:- ከእስር ተፈተው ወደ ስዊዲን ካቀኑ ከአምስት ሳምንታት በኋላ ወደ ኢትዮጵያ መመለስዎ የስዊዲን መንግሥትንና ህዝብን እንዳስገረመ ነግረውኛል:: እኔንም ገርሞኛል እስኪ ምክንያትዎን ይንገሩኝ፡

ዶክተር ፍቅሩ :- በመሰረቱ በሀገርና በህዝብ ላይ ቅያሜ የሚባል ነግር ሊኖር አይችልም:: ሀገርህንና ህዝብህን ከተቀየምክ ራስህን ተቀይመሃል ማለት ነው:: እኔን ያሰረኝ ስርዓቱ ነው:: ስርዓቱን የተወሰኑ ሰዎች ጥቅም ለማግኘት ተጠቅመውበታል:: በኢትዮጵያ ደስተኛ ነኝ፤ ትልቅ ተስፋም አለኝ:: ተስፋ ባይኖረኝ ኖሮ ተመልሼ አልመጣም ነበር::

ተማርሬ አገር ጥዬ ለመሄድና ዳግመኛም ላለመመለስ ጫፍ የደረስኩት በቂሊንጦ እስር ሳይሆን በገቢዎችና ጉምሩክ የቢሮክራሲ ችግር ነው:: ስለታሰርኩኝ አገሬን አልከዳም ነገር ግን የማያሰራ ነገር ከመጣና አትሰራም ብሎ ከከለከለህ ምን ምርጫ ይኖርሃል ? የሚገርምህ «የውጭ ምንዛሪ የለም» ይሉናል::

እኛም እሺ አንፈልግም ብለን የሆስፒታላችን ባለድርሻ ባለሀብቶች ከውጭ ሀገር በውጭ ምንዛሪ ገዝተው እንዲልኩልን ስናደርግ ጉምሩክ የተገዛበትን ሶስት እጥፍ ቀረጥ ያስከፍለናል:: ይሄ ያስመርረኛል:: ይሄ አገር አስለቅቆ የሚያስኮበልል ነው:: አምጥተን አንሸጠው እኛ:: እንዲህ ያለ ቀረጥ ስንከፍል ኢትዮጵያዊው ላይ ነው ዋጋው የሚጨመረው ስለዚህ ሳይታከም ቀርቶ ይሞታል::

በጥቁር አንባሳ ብቻ የልብ ቫልቭ የሚቀየርላቸው 14 ሺ 8 መቶ ወጣት የልብ ታማሚዎች ተመዝግበው ህክምናውን እየተጠባበቁ ነው:: በዓመት 1 መቶ ሰው ብናክም 1 መቶ 40 ዓመት ይፈጅብናል:: ነገር ግን እንዚህ ወጣቶች ካልታከሙ 30 ዓመት ሳይሞላቸው ይሞታሉ:: እቃው እንደልብ ቢገኝ በአጭር ጊዜ ውስጥ ብዙ ወጣቶችን ማከም ይቻል ነበር::

አዲስ ዘመን:- በመጨረሻ ማስተላለፍ የሚፈልጉት መልዕክት ካለ ዕድሉን አግኝተዋል::

ዶክተር ፍቅሩ :- ሀገራቸውን የሚወዱ ብዙ ኢትዮጵያውያን በውጭ አገራት እየኖሩ ነው:: እኔ የማደርገውን ነገር ሊያደርጉ የሚችሉ ብዙ ኢትዮጵያውያን አሉ:: ኢትዮጵያ ባንረዳትም ትኖራለች:: ከረዳናት ደግሞ መኖር ብቻ ሳይሆን ትበለጽጋለች:: እነዚህን ኢትዮጵያውያን ሀገራችንን እናድናት እናትርፋት ሳይሆን ቀዳዳዋን እንድፈንላት ቁስሏን እናክምላት ነው የምላቸው::

በተለይ በህክምና ውስጥ ያላችሁ ቁጥራችሁ ላቅ ያለ ነው ግን ኢትዮጵያ ውስጥ መጥታችሁ የምትሰሩ በጣም ጥቂት ናችሁ:: ጥሪ ነው የማቀርበው ፣ በህይወታችሁ ደስተኛ የምትሆኑት ኢትዮጵያ ውስጥ መጥታችሁ አንድ ሰው እንኳን ስታክሙ ነው:: ያከማችሁት አንድ ሰው ምርቃትና አክብሮት ውጭ ሀገር 1 ሺ ፈረንጅን አክማችሁ ከምታገኙት ይበልጣል:: ስለዚህ እባካችሁ ኑ አብረን እንስራ::

አዲስ ዘመን:- ውድ ጊዜዎን ሰውተው ከእኛ ጋር ስለቆዩ እናመሰግናለን::

ዶክተር ፍቅሩ :- እኔም አመሰግናለሁ::

አዲስ ዘመን

የትናየት ፈሩ