April 30, 20190

Source: https://zaggolenews.com/2019/04/30/66723/

በአገራችን ልማድ ሆኖ ብዙ የሚነገርለት ሲሞት ነው። ነጋሶ ማለፋቸው ከተሰማ ወዲህ የሚአውቋቸው ሲናገሩ መስማት በዛሬ ዘምን ካለው መሰሪነት ጋር ተዳምሮ ያማል። ምስክሮቻቸው በሙሉ ከሴራ የጸዱ፣ ቀና፣ ደግ፣ አሃሜት የሚባል የማያውቁ፣ ፊትለፊት ተናጋሪ፣ የመርህ ሰው፣ እንደ ሌሎች ባለስልጣናት ከህዝብ የሚለዩ ሳይሆኑ ህዝብን የሚቀርቡ፣ ለጥቅም የማይደለሉ፣ ከፕሬዚዳንትነታቸው ሲለቁ አንድ መኪናና መኖሪያ ቤት እንዲሁም ገንዘብ ያልነበራቸው፣ በታክሲ እየተጋፉ የሚጓዙ አሳዛኝ ነገር ግን አስደናቂ ባለ ጀዝም ነበሩ። ቢቢሲ አማርኛ ከአቻቸው መቶ አለቃ ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ ጋር አመዛዝኖ ኦክቶበር ፫ ቀን ፳፩፯ ላይ ይህንን ጽፎ ነበር። ለትዝብትና ለትዝታ ይሁን!!

የቀድሞ ፕሬዝዳንቶች ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳና ግርማ ወ/ጊዮርጊስ የተለያየ የኑሮ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ። በቀድሞ ሁለት ፕሬዝዳንቶችን መኖሪያ ቤት ተገኝተን ባነጋገርናቸው ወቅት የሚገኙበት የኑሮ ሁኔታ ሰፊ ልዩነት ያለው መሆኑን ለመረዳት አላዳገተንም። በኑሯቸው ብቻም አይደለም፤ ግንኘነታቸውም ያን ያህል እንደኑሯቸው የተራራቀ ነው።

ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንት ነበሩ።

አቶ ግርማ ወ/ጊዮርጊስ ደግሞ መንበረ ሥልጣኑንን ከዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ በመቀበል ሃገሪቷን ለ12 ዓመታት በርዕሰ ብሔርነት አገልግለዋል።

ዛሬ ላይ በምን አይነት ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ?

ዶ/ር ነጋሶ ሃገሪቷ የምትመራበት መንገድ ሳያስማማቸው ቀርቶ ስልጣን በራሳቸው ፍቃድ ከለቀቁ አስራ ስድስት ዓመታት አልፈዋል። የመጀመሪያዎቹን አራት ዓመታት መጸህፍት በማንበበ እንዳሳለፉና ከዚያም በኋላ በተለያዩ የማህበራዊና ፖለቲካዊ አንቅስቃሴዎች ውስጥ ለረጅም ዓመታት ንቁ ተሳትፎ እንደነበራቸው ይናገራሉ።

በ 1997 ዓ.ም በተካሄደው ሃገራዊ ምርጫ በግል ዕጩነት የሕዝብ ድምጽ አግኝተው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል እንደነበሩም ይታወሳል።

ዶ/ር ነጋሶ እንደሚሉት ከሆነ ከሶስት ዓመታት በፊት ከፖለቲካ ፓርቲያቸው ጋር በተፈጠረ አለመግባባት ሙሉ በሙሉ ፖለቲካን እርግፍ አድረገው እንደተዉ ይናገራሉ።

ዶ/ር ነጋሶ እንደነገሩን በአሁኑ ሰዓት ብቸኛው የገቢ ምንጫቸው ለተለያዩ አካላት ስርተው የሚያቀርቧቸው ጥናታዊ ጽሁፎች ናቸው።

አጭር የምስል መግለጫ
አቶ ግርማ በንጉሱ ዘመንም በተለያዩ የስልጣን እርከኖች ላይ ህዝብና ምንግሥትን አገልግለዋል
በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት ዘመን የፓርላማ አባል የነበሩት የቀድሞው ፕሬዝዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ አሁንም ቢሮ መግባታቸውን አላቆሙም።

ግርማ ወ/ጊዮርጊስን የሚያሳይ ምስል

በቅርቡ ዘጠና ሁለት ዓመት የሚሞላቸው አቶ ግርማ፤ ”ከፕሬዝዳንትነት በኋላ ላለፉት አራት ዓመታት ሕዝብን ይጠቅማሉ ብዬ ያሰብኳቸውን ሥራዎች ስሰራ ቆይቻለው” ይላሉ።

ስልጣን ላይ ከነበርኩበት ወቅት ይልቅ አሁን ብዙ ሥራ እየሰራሁ እንደሆነ ይሰማኛል
ግርማ ወ/ጊዮርጊስ, የቀድሞ ፕሬዝዳንት
”ዲጂታል የሆነ ቤተ-መጻህፍት ለሕዝብ ገንብቻለሁ። ሥልጣን ላይ ከነበርኩበት ወቅት ይልቅ አሁን ብዙ ሥራ እየሰራሁ እንደሆነ ይሰማኛል” የሚሉት አቶ ግርማ ሆላንድ ኤምባሲ አካባቢ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ቅጥር ግቢ ውስጥ ያሰሩት ቤተ-መጻህፍት በቅርቡ ሥራ እንደሚጀምር ነግረውናል።

ኑሮ ከስልጣን በኋላ

ከሃላፊነት የተነሱ የሀገርና የመንግሥት መሪዎች፣ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች፣ የምክር ቤት አባሎችና ዳኞች የሚያገኟቸውን መብትና ጥቅሞች ለመወሰን በወጣው በአዋጅ ቁጥር 653/2001 ዓ.ም መሠረት ተሰናባች ፕሬዝዳንቶች የደሞዝ፣ የመኖሪያ ቤትና ቢሮ፣ የጤና አገልግሎት፣ የጥበቃና የመጓጓዣ አገልግሎቶችን ጨምሮ በርካታ ጥቅማጥቀሞችን የማግኘት መብት እዳላቸው ይደነግጋል።

ይሁን እንጂ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ስልጣን ከለቀቁ ከአራት ዓመታት በኋላ በፖለቲካ ውስጥ በነበራቸው ተሳትፎ የተነሳ ያገኙት የነበረው ጥቅማጥቅም እንዲቋረጠባቸው መደረጉን ይናገራሉ።

የፖለቲካ ተሳትፎ ከማድረጌ በፊት በወቅቱ የነበሩትን የምርጫ ቦረድ ሃላፊዎች አማክሬ የፖለቲካ ፓርቲ እስካልተቀላቀልኩ ድረስ በግል በማደርገው የፖለቲካ ተሳትፎ ምክንያት የማገኛቸው ጥቅማጥቅሞች እንደማላጣ አረጋግጠውልኝ ነበር ይላሉ ዶ/ር ነጋሶ።

ከዚያ በኋላ ተሻሽሎ የወጣውም አዋጅ የማገኛቸውን ጥቅማጥቅሞች ለማስቀረት እንደወጣ ይሰማኛል ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ዶ/ር ነጋሶ በመኖሪያ ቤታቸው ቅጥር ግቢ ውስጥ

አጭር የምስል መግለጫ
ዶ/ር ነጋሶ ብስራተ ገብርኤል አከባቢ ከሚገኘው መንግሥት ከሰጣቸው ቤት እንዲወጡ ቢነገራቸውም እየኖሩበት ይገኛሉ
ዶ/ር ነጋሶ በአሁኑ ወቅት ብስራተ ገብርኤል አካባቢ በሚገኝ የመንግሥት ቤት ውስጥ ይኖራሉ። ”ይህን ቤት ለቅቄ እንድወጣ ከአንድም ሁለት ጊዜ ደብዳቤ ተጽፎልኛል። አንድ ቀን መጥተው ከዚህ ቤት ሊያስወጡኝ ይችላሉ” ይላሉ።

ዶ/ር ነጋሶ የሚኖሩበት ግቢ እጅጉን ጭር ያለ ነው። ምግብ ከምታበስልላቸው የቤት ሰራተኛቸውና የተለያየ ሥራ በመስራት ከሚያግዛቸው አንድ ግለሰብ ውጪ በግቢው ውስጥ ማንም አይታይም። ጀርመናዊቷ ባለቤታቸውም አሁን በሃገር ውስጥ አይገኙም።

ከቤታቸው ጀርባ ያለው የቴኒስ መጫወቻ ሜዳም ሳር በቅሎበት ይታያል።

ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ከ1987-1994 ዓ.ም ድረስ የሃገሪቱ ርዕሰ ብሔር ነበሩ።
አቶ ግርማ ወልደጊዮርጊስ ደግሞ ከ1994 – 2006 ዓ.ም ድረስ ርዕሰ ብሔር ሆነው አገልግለዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ በቀድሞ ፕሬዝዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ መኖሪያ ግቢ ውስጥ 3 መኪኖች ቆመው ይታያሉ። የሚኖሩበት ቅጥር ግቢ እጅ ሰፊ የሚባል ነው። ከጥቂት ዓመታት በፊት ለአቶ ግርማ የቤት ኪራይ ወጪ የሚደረገው የገንዘብ መጠን ትልቅ መነጋገሪያ ሆኖ ነበር።

በዚህ ሰፊ ግቢ ውስጥ የመኖሪያ ቤት፣ ቢሮዎች፣ የመሰብሰቢያ አዳራሾች፣ ቤተ-መጻሓፍት፣ ማዕድ ቤቶች እንዲሁም የሰራተኛ መኖሪያ ክፍሎች ይገኛሉ።

የአቶ ግርማ መኖሪያ ቤት

አጭር የምስል መግለጫ

የአቶ ግርማን ህይወት ቀላል የሚያደርጉ የተለያዩ ወጪዎችን መንግሥት ይሸፍናል
መኖሪያ ቤታቸው 24 ሰዓት ጥበቃ ይደረግለታል። ግቢያቸውም እጅግ ንጹህና ያማረ ነው።

ምንም የቀረብኝ ነገር የለም። መንግሥት የሚያስፈልገኝን ሁሉ አሟልቶልኛል
ግርማ ወ/ጊዮርጊስ, የቀድሞ ፕሬዝዳንት
”ምንም የቀረብኝ ነገር የለም። መንግሥት የሚያስፈልገኝን ሁሉ አሟልቶልኛል። በህግ የተሰጠኝን መብት ሙሉ በሙሉ እየተጠቀመኩበት ነው። ከዚህ በላይ ደግሞ ምንም አልፈልግም” ይላሉ አቶ ግርማ።

ይህ ሁሉ ልዩነት ለምን?

ዶ/ር ነጋሶ በ1997 ዓ.ም የደምቢዶሎን ከተማ ሕዝብ በመወከል በግል እጩነት የተወካዮች ምክር ቤት ወንበርን ካገኙ በኋላ ያገኟቸው የነበሩት ጥቅማ ጥቅሞች እንደተቋረጡባቸው ይናገራሉ።

”መጀመሪያ ላይ በቤቱ ውስጥ የሚረዱኝ ሦስት ሰዎች፣ አትክልተኛና ሁለት መኪኖች ከአሽከርካሪ ጋር እንዲሁም ሁሉን የሚያቀናጅልኝ አንድ ሰው ነበር። አሁን ግን ይህ ሁሉ የለም” ይላሉ ዶ/ር ነጋሶ።

አጭር የምስል መግለጫ
ስልጣን ከለቀቁ በኋላ መንግስት ለኔ ምንም የሚበጅ ነገር እያደረገልኝ አይደለም ይላሉ
ዶ/ር ነጋሶና አቶ ግርማ ተገኛኘተው ያውቁ ይሆን?

”ብዙም አንገናኝም” ይላሉ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ግርማ።

ዶ/ር ነጋሶም ተመሳሳይ መልስ ነው ያላቸው፤ ከዚህ በፊት ቢበዛ ለሦስት ጊዜ ያክል ብቻ እንደተያዩ ያስታውሳሉ። ከአቶ ግርማን ጋር ለመጨረሻ ጊዜ የተገናኘነው ፕሬዝዳንት ሳሉ ነበር።

”በአዋጁ ምክንያት የተቋረጠብኝን ጥቅማጥቅም ለማስመለስ ፕሬዝዳንት ግርማን ባማክራቸውም ሳይሳካልኝ ቀርቷል።” የሚሉት ዶ/ር ነጋሶ፤

”በጥያቄዬ እንደማይስማሙ ነገሩኝ ከዚያም በኋላ ተስፋ በመቁረጥ ሳልጠይቃቸው ቀርቻለሁ” ይላሉ ዶ/ር ነጋሶ።

የሚገባኝን ጥቅማጥቅም ለማስመለስ ለህዝብ ተወካዮች መክር ቤት አፈ-ጉባኤ ሶስት ግዜ ደብዳቤ ብጽፍም መልስ አላገኘሁም የሚሉት ዶ/ር ነጋሶ ጥቅማጥቅሞቼ እስኪመለሱልኝ ድረስ አስፈላጊውን ጥረት አደርጋለው ብለዋል።

ሁለቱ የቀድሞ ፕሬዝዳንቶች ሃገሪቱን በተመሳሳይ የሃላፊነት ቦታ ላይ ያገለገሉ ቢሆንም ከሥልጣን በኋላ በሚያገኙት ጥቅም ግን ተለያይተዋል