August 3, 2019

Source: https://ethiothinkthank.com/2019/08/04/ejjetto-and-the-new-ethino-nationalists/

ልብ ያለው ልብ ይበል

አንድነት ይበልጣል – ሀዋሳ ሐምሌ 23 /2011

በ”11/11/11″ በሀዋሳና በሲዳማ ዞን ከተማና ገጠሮች በኤጄቶ የተፈጸመው ግፍ ሕሊና ላለው ሀሉ እጅግ ያሳዝናል፣ ያሸማቅቃል፣ ያስቆጣልም፡፡ የሲዳማ ሕዝብና መጪው ትውልድ በታሪኩ ሲያፍር ሊኖር ነው፡፡ ይህ የሚሆነው በኤጄቶ ነውረኛ፣ ዘረኛ፣ የቅጥረኛና የአረመኔ ድርጊት ነው፡፡ አሳዛኟ ኢትዮጵያ፣ የዛሬ ዓመት (ሰኔ 07/2010) ኤጄቶ በወላይታ ተወላጆች ላይ በሀዋሳ የፈጸመውን ግፍ በይቅርታና በእርቅ ወይም በሕግ የበላይነት ሳትሻገር ሌላ የዘረኝነትና የጭካኔ አዙሪት ውስጥ በድጋሚ ከተቷት፡፡ በዚህ ወቅት የተቀየሩት ሰለባዎቹ ብቻ ናቸው፤ የአሁኖቹ አብዛኞቹ ሰለባዎች የሲልጢ፣ የጉራጌና የአማራ ተወላጆች ናቸው፡፡ ከመንግሥትም በላይ እግዚአብሔር ፍርዱን ይስጥ!

አይ ኤጄቶ! እስኪ ንጹኃን፣ ከርታታና ታታሪ ዜጎችና የኃይማኖት አባቶችን ማጥቃት፣ ንብረትና ተቋሞቻቸውን (ቤተክርስቲያናትን ጭምር) ማቃጠል፣ ማውደምና መዝረፍ ከክልል ጥያቄአችሁ ጋር ምን ያገናኘዋል? ጥያቄውን የሚያስተናግዱት (የሚፈቅዱት ወይም የሚከለክሉት) እነርሱ ናቸው? ጥያቄውን የሚያስተናግደው መንግሥት መሆኑን ታውቃላችሁ፡፡ የመንግሥትንም ቢሆን ተቋማቱን ወይም ባለሥልጣናቱን በማውደምና በማጥቃት፣ ሥርዓተ-አልበኛ በመሆን ጥያቄን ማስፈጸም፣ የ21ኛው ክፍለ ዘመን ፖለቲካ፣ ነውርና ኋላቀር አድርጎታል፡፡ ታዲያ ምን እየሆናችሁ ነው?
በሲዳማ የክልል ጥያቄ ሽፋን ለሚመራው ተከታታይ የጥፋት ድርጊት እንደ ዋና መግፍኤ ሊወሰድ የሚችለው ልዩ ተጠቃሚነትን የማጣት ሥጋት ይመስለኛል፡፡

ባለፉት በርካታ ዓመታት በደቡብ ክልል፣ በሀዋሳ ከተማና በአጠቃላይ በሲዳማ ዞን፣ እስከቀበሌና መንደር ባለው መደበኛና ኢመደበኛ መዋቅር ዋናዋናውን የፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ፣ ማኅበራዊና ባሕላዊ መሪ በመዘወር በአንጻራዊ አነጋገር ክፍተኛና ልዩ ተጠቃሚ የነበሩትና አሁንም የሆኑት ከሌሎች የኢትዮጵያና የደቡብ ብሔረሰብ ተወላጆች ይልቅ የሲዳማ ተወላጆች ናቸው፡፡ የጎሣ ፖለቲካና ኢኮኖሚ፣ የጎሣ ጦርና ሜዲያ፣ የጎሣ ሰፖርት፣ የጎሣ መለያ ምልክትን ማጮኽ፣ በብሽሽቅ የተሞላ የጎሣ በዓል አከባበር የሚያስከትለው የአድልዎ ውጤት (ልዩ ጥቅምና ጉዳት) ሁሉ ከማንኛውም የክልሉ ሌላ አካባቢ ይልቅ በሀዋሳና በአጠቃላይ በሲዳማ ዞን አግጥጦ ሲታይ ዓመታት አስቆጥሮአል፡፡ በጠቅላላ መስተዳድሩን፣ “ሲቪል ሰርቪሱን” – የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችና የአገልግሎት ተቋማትን በሙሉ መቆጣጠር ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ፣ ባህላዊና ሥነልቦናዊ ትርጉሙን፣ ፋይዳውንና አንደምታውን መገመት ከባድ አይደለም፡፡ በሀዋሳ “የኮብል ስቶን” መንገድ ግንባታ የሥራ ዕድልና የከተማ መንገዶች የጽዳት ሥራ ዕድል ሣይቀር የበለጠ ተጠቃሚዎች የሲዳማ ወጣቶችና ሴቶች ናቸው፡፡

ስለዚህ አጀንዳውና ርዕሱ ምንም ይሁን ምን፣ እንዴትም ይቅረብ፣ በሲዳማ እየቀረበ ያለው ጥያቄ የጥቂት ባለሥልጣኖች፣ ባለኃብቶች፣ ባለዲግሪዎች፣ አክቲቪስቶችና ወጣቶች ጥያቄ አድርጎ ማቅረብ ችግሩን አቅልለን እንድናይ ያደርገናል፡፡ የችግሩን ባህርይ፣ ስፋትና ጥልቀት በቅጡ አለመረዳት ዋጋ ያስከፍላል፤ በመፍትሔ አሰጣጡ ላይ ለከፍተኛ ስህተት ይዳርጋል፡፡
እኔ እንደሚገባኝ ለመጎልበት በትንቅንቅ ላይ ያለው ለውጥ ዓላማው ለሁሉም እኩል መብት ማጎናጸፍና እኩል ዕድል ማመቻቸት እንጂ በአጠቃላይ የሲዳማ ተወላጆችን ከጨዋታ ውጪ ማድረግ አይደለም፡፡ እየታሰበና እየተሞከረ ያለው ለውጥ የሲዳማን ሰፊ ሕዝብ ሊያስፈራ አይገባም፡፡

እርግጥ ነው፣ በሀዋሳና በሲዳማ ዞን (እንደ ሐረሪ ክልልና እንደድሬደዋ አስተዳደር እንዲሁም እንደሌሎች ብዙ ክልሎች) ባለፉት በርካታ ዓመታትና እስከዛሬም ድረስ የሲዳማ ተወላጆች በአንጻራዊ አነጋገር ከሌላው ኢትዮጵያዊ የተሻለ ተጠቃሚ ሆነው ቆይተዋል፡፡ ከዚህ አንጻር የለውጡ ዓላማ መሆን ያለበት (አንዳንዶች እንደሚነዙት) ሲዳማን እንደሕዝብ በተራው መግፋት ሳይሆን፣ እስካሁን ወደዳር ተገፍተው የቆዩ ሌሎች ብዙኃን ዜጎችም እኩል ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ማሻሻያና ዕድል መፍጠር ብቻ ነው፡፡ ጉዳዩ በጣም ጥንቃቄን፣ መስከንን፣ አስተዋይነትን ሚዛናዊነትንና ሩቅ ተመልካችነትን ይጠይቃል።

አንድነት፣ ፍትሕ፣ “ሁሉም መብቶች ለሁሉም”፣ ዕኩል ዕድል፣ ፍትሐዊ የኃብት ክፍፍልና ተጠቃሚነት፣ የሕግ የበላይነትን የመሳሰሉት ሰብዓዊና ሐገራዊ ዓላማና መርሆዎች የጥቂቶችን ኢፍትሐዊ ተጠቀሚነት ያስቀራሉ፤ ምናልባትም ተጠያቂነትን ሊያስከትሉ ይችላሉ፤ ይህን መደበቅ አይቻልም፡፡ ከነዚህ ውጭ ግን የሲዳማም ሰፊ ሕዝብ ለውጡ የመጣለት እንጂ የመጣበት ሊሆን አይችልም፡፡ ይህን በመረዳት የሲዳማ ሰፊ ሕዝብ ለውጡን በአፍም በተግባርም መደገፍ ይኖርበት ነበር፡፡ የተረጋጋ ሁኔታ ተፈጥሮ የሲዳማ ሕዝብ ነጻና ሰፊ ውይይት ሊያደርግበትና ውሳኔ ሊሰጥበት የሚገባው ጥያቄ የሚከተለው ነው – የሲዳማ ሕዝብ ዕውነተኛና ዘላቂ ጥቅሙ የሚጠበቀው ዕውነተኛ ዴሞክራሲን በማዋለድና በማስፈን ነው ወይስ ዞንን ክልል በሚያደርግ መዋቅራዊ ለውጥ ነው?

እርግጥ ነው ገዢው ፓርቲ ገና በቅጡ ባላራገፋቸው ጸረ ለውጥ አባላቱ ውስጣዊ ሻጥርም ምክንያት በቃሉ ልክ ለመፍጠንና መሥመሩን ጠብቆ ወደፊት ለመጓዝ ሲቸገር ይታያል፡፡ በተለይ በደቡብ ክልል፣ ከደኢሕዴን አመራር ገና አለመጠናከርና ከሲዳማ ጥያቄም መጠለፍና መስመር መሳት ጋር ተያይዞ፣ ለውጡ ገና አልተጀመረም ማለት ይቻላል፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ፣ ቃል የገባውን ማሻሻያ ዕውን ለማድረግ በመፍጨርጨር ላይ ያለ (ማዕከላዊ) መንግሥትን ከመጠን በላይ ማጨናነቅ፣ አየር ማሳጣትና አላሠራ ማለት፣ ከተቻለም ለመጣል መሞከር የማን አጀንዳ ይመስላችኋል? የወያኔን ማንነት፣ ምንነት፣ ታሪክና ሥልት ኤጄቶዎች አታውቁም እንዳንል፣ ታላላቆቻችሁን (ለኛም ወንድሞቻችን ናቸው) ጨፍጭፎ፣ የቆየ ጥያቄአችሁን ጨፍልቆና በሲዳማም ሕዝብ ተሳልቆ ንቀቱን አሳይቶአችኌል (1994)፡፡ ዛሬ ግን ወያኔ (ጃዋርን ጨምሮ)፣ ወዳጅ መስሎ፣ በአብዛኛው ግን ራሱን ሰውሮ ይዘውራችኋል፣ ይጫወትባችኋል፡፡ እባካችሁ ንቁ!
ሁሉንም በአንድ ቅርጫት ውስጥ ማጎር ቢከብድም፣ ኤጄቶ በአዲስ ፍቅር የወደቃላቸው እነዚህ የኮንፌዴሬሽን ብሔራዊ ንቅናቄዎች (ወላይታ ብን፣ ሐዲያ ብን፣ አማራ ብን ወዘተ) በአንድ ጊዜና በአንድ ላይ መፍላታቸው ድንገተኛና ተራ አጋጣሚ ብቻ ይሆን እንዴ? የኢንፎርሜሽን ዘመን ልጆች ናችሁና ቢያንስ ቫይረስ፣ ስፓይ ዌርና ማልዌር ደብቀውና ተሸክመው ስለሚገቡ “የትሮይ ፈረሶች” ታውቃላችሁ፤ የትሮይ ፈረስንስ ታሪክ ታውቁ ይሆን? እነ ወ፣ ሐ፣ ብን የወያኔ የትሮይ ፈረሶች ይመስሉኛል፡፡

የነዚህ አዳዲስ ብሔራዊ ንቅናቄዎች አንዳንዶቹ መሪዎቻቸው ትናንት በወያኔ-ኢሕአዴግ መዋቅር ውስጥ እንደነበሩ ይታወቃል፡፡ ይህ በራሱ ችግር ላይኖረው ይችላል፡፡ አብዛኞቹ አባሎቻቸው ግን ትናንት በትንቅንቁ ጊዜ የት እንደነበሩ እንኳ አይታወቅም፡፡ ዛሬ እንዲቋቋሙና እንዲቃወሙ ያስቻላቸውንና በመራራ ትግል የተፈጠረውን ምሕዳርና የዴሞክራሲ ጭላንጭል በደም ለማጨማለቅና አፈር ለማልበስ የሚሠሩ ናቸው፡፡ 27 ዓመት ሙሉ የተዘራውንና የተጠራቀመውን፣ እናም ዛሬ መርዘኛ ፍሬውን ያፈራውን የወያኔ በደል፣ ግፍና ምዝበራ ዛሬ ከለውጡ ጋር እንደመጣ መዓት አድርገው ለማሳየት ይጮሃሉ፡፡ መቀሌ እንደመሸጉት እንደወያኔ ጽንፈኞች ማለት ነው፡፡ እባካችሁ ንቁ!

አዳዲሶቹ “ብሔራዊ ንቅናቄዎች”፣ በተጀመረው የለውጥ ሂደት ላይ ልዩ ልዩ አሻጥር የሚፈጽሙ አካላት በውስጣቸው የተሰገሰጉባቸው፣ ስለዚህም የውስጥ ትግል የሚያስፈልጋቸውና መጽዳት የሚገባቸው ድርጅቶች ናቸው፡፡ ኤጄቶም ስሙ ነው እንጂ መዋቅሩና ግብሩ ከነዚህ አይለይም፡፡ በተለይ እናንተ ኤጄቶዎች፣ ሕዝብና ሐገርን ባስጨነቃችሁበት ዋዜማና ማግሥት እናም የረብሻችሁን ፍሬ በምታጭዱበት በዚህ ወቅት ወያኔንና እነዚህን ድርጅቶች እንዲሁም እንደ በቀለ ገርባና ሕዝቅኤል ያሉ ሰዎችን የሚያንጫጫቸው ምን ይሆን? የኮንፌዴራሊስቶች የትግል አጋርነት? በነገራችን ላይ እንደ ኤጄቶ ሁሉ የወላይታና የሐዲያ አዳዲስ ብሔራዊ ንቅናቄዎች በአንድ ዓይነት ቃልና ድምጸት እየነገሩን ያሉት ጎሳቸው ከ130 ዓመት በፊት የራሱ መንግሥት የነበረው ነጻ ሐገር የነበረ መሆኑን ነው፡፡ “ኢትዮጵያ በድላናለች” ሲል በቴሌቪዥን ሰሞኑን ሰምቸዋለሁ፣ አንዱን የጎሳ ንቅናቄ መሪ፡፡ መቀሌ የመሸጉ የወያኔ ጽንፈኞችና ከ”የሐገሩ” የተጓጓዙት እንግዶቻቸው እየለፉ ያሉት የነዚህን ነጻ ሐገሮች ነበሩ የምትሏቸውን የዞን መስተዳድሮች ትብብር ዕውን የማድረጊያ ማለትም የኮንፌዴሬሽን የማቋቋሚያ ሰነድ ለማዘጋጀት ይሆን እንዴ? እና ኢትዮጵያ የበደለቻችሁን ለማከም መሆኑ ነው! ክልልነታችሁን በጉልበትም ቢሆን እንድታውጁ ያደፋፈራችሁ ጃዋርስ ምነው ጠፋ ብላችሁ አልጠየቃችሁም? ቢያንስ ሰፊ አባሎቻችሁ እባካችሁ ከእንቅልፋችሁ ንቁ!

አንዳንዶቻችሁ እያወቃችሁት፣ ብዙዎቻችሁ ደግሞ ሳይገባችሁ የወያኔ ጽንፈኞች ከነተላላኪዎቻቸው እንዲሁም ኦነግ፣ ጽንፈኛ ቄሮ/ጃዋር በውስጣችሁ፣ በጀርባችሁና በኋላችሁ ተሳፍረው ይነዷችኋል፡፡ የትሮይ ፈረስ ማለት እንዲህ ነው፡፡ የወያኔን ባህርይ ለሚያውቅ ይህ እንደሚሆን መገመት አይከብድም፡፡ የወያኔ ጽንፈኛና ጃዋር በጋራም ይሁን በተናጠል እንደየጊዜውና እንደየሁኔታው የሚለዋወጥ አጀንዳ ቀርጸው ያሸክሟችኋል፤ ሠነድ ያዘጋጁላችኋል፤ የረብሻ ሥምሪት ሥልት ይነድፉላችኋል፤ ያሰለጥኗችኋል፣ የሜዲያና የፕሮፓጋንዳ ሽፋን ይሰጧችኋል፡፡ ገንዘቡም ቢሆን፣ ከክልልና ዞን በጀት እንዲሁም ከሌባ ነጋዴዎች የምታገኙት መዋጮ ለዚህ ትልቅ የጥፋት ፕሮጀክታቸው/ችሁ አይበቃም፡፡ ስለዚህ የወያኔ ሌቦች ለሦስት አሰርታት ከዘረፉት ሐብት ላይ ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ መመደባቸው አይቀርም፡፡ ዶላሩን ሲያጓጉዙ ካልተጠነቀቁ ግን በውጭ ምንዛሪ እጥረት እየተቸገረች ላለች ሐገር የሚኖረው ፋይዳ አይናቅም፡፡ እባካችሁ ንቁ!!

ከመሥመሩ እንዳይወጣ መጠበቅና መታገዝ የሚገባውን ለውጥ ለማደናቀፍ እንቅልፍ ያጣችሁትን ዘረኞች፣ በገንዘብም የተገዛችሁትን ጨፍጫፊዎች ግን እግዚአብሔር የሥራችሁን ፍርድ ይስጣችሁ፣ ይህ ደግሞ የማይቀርና በቅርብ ጊዜ ውስጥ የምናየው ነው፡፡ እድሜ ብቻ ይስጠን፡፡ በቀደሙት ዓመታት የጌዴዖ ዘረኞች (በዲላ፣ ይርጋጨፌ፣ ቡሌ ወዘተ) የፈጸሟቸው ተከታታይ ግፎችና በአጠቃላይ የጎሣ ፖለቲካ ሕዝቡን እንዴት በእጥፍ ዋጋ እንዳስከፈሉ አትመለከቱም? ከዚህስ እንዳትማሩ ምን ዓይነት ሰይጣን (ወይስ ጥቅም) ጋረዳችሁ? የእግዚአብሔር ፍርድና እርምጃ ከመንግሥትም ወቅታዊ እርምጃ ሚሊዮን ጊዜ ይብሳል፡፡

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይጠብቅ!!