August 3, 2019

Source: https://ethiothinkthank.com/2019/08/03/the-lack-of-infrastructure-in-amhara-region-is-the-result-of-the-2007-census/

የመፍትሄ እርምጃ ለመውሰድ በሚደረገው ጥረት የመጀመሪያው ተግባር የችግሩን መሠረታዊ መንስኤ ለይቶ ማወቅ ነው። አዲሱ የአማራ ክልል ፕረዚዳንት በተለያዩ የክልሉ አከባቢዎች በመዘዋወር ከመሠረተ ልማት አውታሮች ግንባታ እና ተደራሽነት አንፃር የከፋ ችግር መኖሩን በመጥቀስ ደረጃ በደረጃ መፍትሔ ለመስጠት እንደሚሰሩ ገልፀዋል። መልካም!ከመሠረተ ልማት ግንባታ እና ተደራሽነት አንፃር በክልሉ የከፋ ችግር መኖሩን በአካል ተዟዙረው ከተመለከቱ ቀጣዩ ነገር “የችግሩ መሠረታዊ መንስኤ ምንድነው?” የሚለው ነው። ከሌሎች የሀገሪቱ አከባቢዎች በተለየ በአማራ ክልል ከፍተኛ የሆነ የመሠረተ ልማት እጥረት ሊኖር የቻለበት ምክንያት ህወሓት/ኢህአዴግ የአማራን ህዝብ በድህነት ለመቅጣት የዘረጋው አድሏዊ አሰራር ነው። ይህ ደግሞ የ1997ቱን ምርጫ ተከትሎ በአማራ ህዝብ ላይ የተወሰደ የበቀል እርምጃ ነው።

ህወሓት የአማራን ህዝብ እንደ ታሪካዊ ጠላት እንደሚያየው ሌላው ቀርቶ የቀድሞ አገልጋዮቹ ብአዴን የዛሬው #አዴፓ ሳይቀር ገብቶታል። ይሄን ደግሞ “ህወሓት” የሚለውን የዳቦ ስም ትተው #ትህነግ ብለው በትክክለኛ ስሙ ባወጡት መግለጫ ላይ በይፋ ገልፀውታል። ሆኖም ግን አዴፓን ጨምሮ አብዛኛው ሰው ያልገባው ነገር ህወሓት/ኢህአዴግ የ1997ቱን ምርጫ ተከትሎ በአማራ ህዝብ ላይ የወሰደው የበቀል እርምጃ ነው። በእርግጥ ህወሓት በ1997ቱ ምርጫ የደረሰበትን አሳፋሪ ሽንፈት እና ውርደት ለመበቀል በአማራ ህዝብ ላይ #ዘር_ማጥፋት ፈፅሟል። በእርግጥ አብዛኛው ሰው “የዘር ማጥፋት” ሲባል የሞቱ ሰዎች አስክሬን እንድትቆጥርለት ይጠብቃል። ነገር ግን በአማራ ህዝብ ላይ የተፈፀመው የዘር ማጥፋት የተፈፀመው ረቀቅ ባለ መንገድ ነው።በአማራ ህዝብ ላይ የዘር ማጥፋት የተፈፀመው በ1999 ዓ.ም በተካሄደው ሀገር አቀፍ ህዝብና ቤት ቆጠራ ነው።

የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ በየ10 አመቱ የሚያካሂደውን የህዝብና ቤት ቆጠራ ዋቢ በማድረግ ከታች በምስሉ ላይ የቀረበውን መረጃ ብንመለከት በ1977 ዓ.ም #የኦሮሞ ህዝብ ብዛት 12.38 ሚሊዮን፣ #የአማራ_ህዝብ ብዛት 12.05 ሚሊዮን፣ #ሲዳማ 1.26 ሚሊዮን፣ #ወላይታ 1.03 ሚሊዮን፣… ወዘተ ነበረ። ይህ መረጃ የሚያሳየው በአስተዳደራዊ ወሰን ውስጥ የሚኖረውን ህዝብ ብዛት ሳይሆን በመላ ሀገሪቱ አከባቢ የሚኖሩ የአንድ ብሔር ተወላጆችን ነው። ከደርግ መውደቅ በኋላ በ1986 ዓ.ም (1994) በተካሄደው ህዝብና ቤት ቆጠራ የሀገሪቱ አስተዳደራዊ ወሰኖች ተቀይረዋል። በዚህ ምክንያት ለምሳሌ የትግሬ/ትግራዋይ ህዝብ ብዛት በ1977 ዓ.ም 4.83 ሚሊዮን የተበረ ሲሆን በ1986 ዓ.ም ወደ 3.28 ሚሊዮን ቀንሷል። በተመሣሣይ በሌሎች ብሔሮች ላይ የተደረጉትን ለውጦች አስመልክቶ ከታች በቀረበው ምስል ላይ ማብራሪያ ተሰጥቶበታል።

በሌላ በኩል የመንግስት ወይም የአስተዳደራዊ ወሰን ለውጥ በአማራ፣ ኦሮሞ፣ ሲዳማና ወላይታ ህዝብ ብዛት ላይ የፈጠረው ተፅዕኖ የለም። በ1986 (1994) ዓ.ም በተካሄደው የህዝብና ቤት ቆጠራ መሠሰት ኦሮሞ = 17.08 ሚሊዮን፣ አማራ = 16.01 ሚሊዮን፣ ሲዳማ = 1.84 ሚሊዮን፣ ወላይታ = 1.27 ሚሊዮን ነው። በ1977ቱ ህዝብና ቤት ቆጠራ ከአጠቃላዩ የሀገሪቱ ሕዝብ ብዛት፤ ኦሮሞ 29.1%፣ አማራ 28.3%፣ ሲዳማ 3.0%፣ ወላይታ 2.4% ነበር። በ1986ቱ ህዝብና ቤት ቆጠራ ከአጠቃላዩ የሀገሪቱ ሕዝብ ብዛት፤ ኦሮሞ 32.5%፣ አማራ 30.5%፣ ሲዳማ 3.5%፣ ወላይታ 2.4% ሆኗል። የ1997ቱን ምርጫ ተከትሎ በ1999 ዓ.ም በተካሄደው ህዝብና ቤት ቆጠራ፤ የኦሮሞ ህዝብ 25.3 ሚሊዮን፣ አማራ 19.8 ሚሊዮን፣ ሲዳማ 2.9 ሚሊዮን ሲሆን ወላይታ ደግሞ 1.6 ሚሊዮን መሆኑ ተገልጿል። በዚህ መሠረት በ1999ኙ ህዝብና ቤት ቆጠራ ከአጠቃላዩ የሀገሪቱ ሕዝብ ብዛት፤ ኦሮሞ 34.4%፣ አማራ 27.0%፣ ሲዳማ 4.0%፣ ወላይታ 2.3% ሆኗል። ለምሳሌ በኦሮሞ ህዝብ ብዛት እና አማራ ህዝብ ብዛት መካከል የነበረው ልዩነት ብቻ ነጥለን ብንመለከት፤ በ1977ቱ ቆጠራ= 332,400 ነበር፣ በ1986ቱ ቆጠራ = 1,072,900 ነበር፣ በ1999ኙ ቆጠራ= 5,485,600 ሆኗል። የአማራ ህዝብ ብዛት ከ1977 እስከ 1986 ዓ.ም ባሉት አመታት ባደገበት 2.2% ቢያድግ በ1999 ዓ.ም የአማራ ሕዝብ ብዛት 21,271,588 ይሆናል። ከአጠቃላይ የሀገሪቱ ህዝብ ውስጥ ከዚህ አንፃር በ1999 ዓ.ም በተካሄደው ህዝብና ቤት ቆጠራ 1,393,388 የሚሆን የአማራ ህዝብ #ጠፍቷል። በዚህ መሠረት 6.55% በሚሆነው የአማራ ህዝብ ላይ የዘር ማጥፋት ተፈፅሟል ማለት ይቻላል።

የጠፋው ህዝብ አሁንም በ2.2% ቢያድግ ዛሬ ላይ ከ1.85 ሚሊዮን በላይ ይሆናል። ይሄ ማለት ህወሓት/ኢህአዴግ የ1997ቱን ምርጫ ተከትሎ በ1999 ዓ.ም በተካሄደው ህዝብና ቤት ቆጠራ በእውን እያለ፣ በክልሉ ውስጥ እየኖረ “የለም” የተባለው የአማራ ህዝብ ብዛት አሁን ካለው #አፋር_ክልል ህዝብ ብዛት ጋር እኩል ነው። ይሄ ህዝብ ላለፉት 12 አመታት በጀት ተመድቦለት አያውቅም። በመሆኑም በክልሉ የመሠረተ ልማት አውታሮች ተደራሽ ሊሆን አይችልም። ከዚህ በተጨማሪ በቀጣዩ የ2012 በጀት አመት የፌደራል መንግሥት ለአማራ ክልል በሰጠው የበጀት ድጎማ እና የዘላቂ ልማት ማስፈፀሚያ በጀት አልተመደበለትም።

በ1999ኙ ህዝብና ቤት ቆጠራ ወቅት የጠፋው የአማራ ህዝብ አሁን ካለው የአፋር ክልል ህዝብ ጋራ ከሞላ ጎደል እኩል እንደመሆኑ መጠን በ2012 የበጀት አመት የፌዴራሉ መንግሥት ለአፋር ክልል የሰጠው የበጀት ድጋፍ ለአማራ ክልል ሊሰጠው ይገባል። በ2012 የፌዴራሉ መንግስት ለአፋር ክልል የሚሰጠው የበጀት ድጎማ 4.17 ቢሊዮን ብር፣ ለዘላቂ ልማት ማስፈፀሚያ ደግሞ 181 ሚሊዮን ብር መድቧል። በዚህ መሠረት የአማራ ክልል በ2012 ዓ.ም ከተመደበለት 29.83 ቢሊዮን ብር በተጨማሪ 4.17 ቢሊዮን ብር፣ በጠቅላላ 34 ቢሊዮን ብር የበጀት ድጎማ ሊደረግለት ይገባል። በተመሣሣይ ለዘላቂ ልማት ከተመደበለት 1.29 ቢሊዮን ብር በተጨማሪ 181 ሚሊዮን ብር፣ በጠቅላላ 1.47 ቢሊዮን ብር ሊሰጠው ይገባል። ይህ እንዲሆን ግን በቅድሚያ የአማራ ክልላዊ መንግስት፣ በተለይ አዴፓ ከላይ በተጨባጭ ማስረጃ የቀረበለትን እውነት አምኖ መቀበል አለበት። ስለዚህ የአማራ ክልል ያለበትን የመሠረተ ልማት ችግር በዘላቂነት መፍታት የሚችለው በ1999 ዓ.ም በአማራ ህዝብ ላይ ዘር ማጥፋት መፈፀሙን አምኖ መቀበል ሲችል ብቻ ነው።