• በሀ/ስብከቱ÷ 55 ከእስልምና 115 ከሌሎች እምነቶች በጥምቀተ ክርስትና ተመልሰዋል

 

 

በመካከለኛው ምሥራቅ(በሊባኖስ እና የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ) ሀገረ ስብከት፣ በዱባይ ከተማ ቤሪያ በተባለ አካባቢ፣ በቤተ ክርስቲያን ስም የሚነግዱ የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ምንደኞች ከቅዱስ ሲኖዶስ ዕውቅና ውጭ ስለከፈቱት ኮሌጅ ውሳኔ እንዲሰጥ ሀገረ ስብከቱ ጠየቀ፡፡

ሀገረ ስብከቱ፣ ዛሬ ሦስተኛ ቀኑን በያዘው የመንበረ ፓትርያርክ የሰበካ አስተዳደር አጠቃላይ ጉባኤ 34ኛ ዓመታዊ ስብሰባ የቀትር በፊት ውሎ፣ በሥራ አስኪያጁ አማካይነት ባቀረበው ሪፖርቱ እንደገለጸው፤ የተወገዙት “የዱባይ ሚካኤል” መሪዎች፣ አኹንም ኮሌጅ ከፍተው ምእመናን ለማደናገር በዝግጅት ላይ ናቸው፡፡

የሦስት ወራት የማሠልጠኛ ተቋማት እንኳ ከቅዱስ ሲኖዶስ ዕውቅና ውጭ ሊቋቋሙ እና ሊሠሩ እንደማይችሉ በሪፖርቱ ያስገነዘበው ሀገረ ስብከቱ፣ ቅዱስ ሲኖዶስ መፍትሔ እንዲሰጠው በአጠቃላይ ጉባኤው ፊት በአጽንዖት ጠይቋል፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ፣ “ገለልተኛ ቤተ ክርስቲያን መኖር የለባትም ብለው” መመሪያ በሰጡበት ወቅት፣ መሪው ተስፉ እንዳለ መንበረ ፓትርያርኩ ድረስ በመምጣት “ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን አንድነት እገባለኹ” ብሎ የነበረ ቢኾንም ከተመለሰ በኋላ በቅዱስ ሲኖዶስ ፊት የገባውን ቃል ማጠፉ ተገልጧል – “ውግዘቱ ሊደርስብኝ አይችልም፤ በማለት በእኩይ ተግባሩ ቀጥሎ ይገኛል፡፡”

ሪፖርቱ፣ “የኑፋቄ መናኸርያ” ሲል በገለጸው “ዱባይ ሚካኤል”፣ በፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ምንደኛ መሪዎች የሚሰጠውን ከርቱዕ ትምህርተ ሃይማኖት፣ ሥርዐተ እምነት እና ክርስቲያናዊ ትውፊት ያፈነገጠ ኑፋቄ በመገንዘብ ተጸጽተው ወደ አማናዊቷ ቤተ ክርስቲያን በንስሐ የሚመለሱና በሥጋ ወደሙ ተወስነው የሚኖሩ ምእመናን ከጊዜ ወደ ጊዜ መበራከታቸውን ጠቅሷል፡፡

በ2007 ዓ.ም. በሀገረ ስብከቱ በተደረገው የስብከተ ወንጌል እንቅስቃሴም፤ 55 ከእስልምና፣ 115 ደግሞ ከሌሎች የተለያዩ እምነቶች ወደ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ሃይማኖት ተመልሰው የቤተ ክርስቲያን ልጆች እንደኾኑ በሪፖርቱ ተመልክቷል፡፡

የሀገረ ስብከቱ ሪፖርት እንዳወሳው፣ የ“ዱባይ ሚካኤል” መሪዎች ቤተ ክርስቲያን ለመትከል በተነሡበት ወቅት፣ ሊቀ ጳጳሱ የማያውቁትና ያልባረኩት ሥሪትና አካሔድ ትክክለኛ እንዳልኾነ ከጅምሩ ተነግሯቸዋል፤ በማስከትልም ተደጋጋሚ ምክርና ተግሣጽ ቢሰጣቸውም ሊመለሱ ባለመፍቀዳቸው በሊቀ ጳጳሱ ቃለ ውግዘት ተላልፎባቸዋል፡፡ ከመንበረ ፓትርያርኩ ከአንዴም ኹለቴ በተላኩ ልኡካን ችግሩን ለመፍታት ቢሞከርም ሊፈታ ስላልቻለ ውግዘቱ ጸንቷል፡፡

 

Leave a Reply