Wednesday, 30 December 2015 14:04

 በሳምሶን ደሳለኝ

      በአንዳንድ የኦሮሚያ አካባቢዎች ከአዲስ አበባና የኦሮሚያ ልዩ ዞን በልማት ለማስተሳሰር ተዘጋጅቶ ከነበረው ማስተር ፕላን ጋር በተያያዘ የተነሳው አለመግባባት በተወሰነ መልኩ የመርገብና ሕጋዊ መስመር የያዘ ይመስላል። የተፈጠረውን ልዩነት ለመፍታት በየአካባቢው እየተደረጉ ያሉ ሕዝባዊ ውይይቶች ተጠናክረው መቀጠል ያለባቸው ከመሆኑንም በላይ፣ ከፍርሃት ድባብ የተላቀቀ በግልፅነት የሚመራ መድረክ መሆን ይጠበቅባቸዋል። ይህም ሲሆን አስፈፃሚው የመንግስት አካል እና ቅሬታ ያነሱ የሕብረተሰብ ክፍሎች ተወያይተው አንድ ደረጃ ላይ እንደሚደርሱ በርግጠኝነት መናገር ይቻላል።

በተለይ ችግሩ ከኦሮሚያ ክልል መነሳቱ አንድ ነገር ሆኖ፣ ችግሩን በአግባቡ መመለስ ከቻልን ደግሞ ሁሉም አትራፊ የሚሆንበት መንገድ መፈጠሩ አይቀርም። ይህም ሲባል የኦሮሞ ሕዝብ የሕዝባችን ቢያንስ አንድ ሶስተኛ ክፋይ የሚሸፍን በመሆኑ የተነሳውን ጥያቄ በአግባቡ መመለስ ከቻልን አንድ ሶስተኛ አካላችን የተረጋጋ እንዲሆንና ለተጀመረው የልማትና የዴሞክራሲ ጉዞ አዎንታዊ ሚና እንዲጫወቱ እድል ይፈጥራል። ስለዚህም ችግሩን በህግ አግባብ መመለስ አሸናፊም ተሸናፊም አይኖረውም። ሊኖር የሚችለው የህግ የበላይነት እና የጋራ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የሚያስችል ከባቢያዊ ሁኔታ ብቻ ነው።

ከኅብረተሰቡ ውጪ ያለው አስፈሪው ጉዳይ ግን ሀገሪቷን ለማስተዳደር በኢትዮጵያ መንግስት ውስጥ ሥርዓተ መንግስት ያቋቋመው ገዢ ፓርቲ፣ በውስጡ የተፈጠረውን የፖለቲካ መስመር ልዩነት በሶስተኛ ወገኖች አጀንዳ ውስጥ ሰንቅሮ ለአደባባይ መብቃቱ ነው። ከዚህ መረዳት የሚቻለው ገዢው ፓርቲ እታገለዋለው የሚለው የኪራይ ሰብሳቢ ፖለቲካ ኢኮኖሚ፣ ከቢሮክራሲ (ከኢኮኖሚ) ኪራይ ሰብሳቢነት አድጎ በስሎ ወደ ፖለቲካ ኪራይ ሰብሳቢነት በመሸጋገሩ፣ የኪራይ ሰብሳቢ ፖለቲካ ኢኮኖሚ በገዢው ፓርቲ ውስጥ ጋብቻ መፈጸሙን ገሀድ የወጣ ክስተት ነበር። እንዲሁም የተወሰነው የአስፈፃሚ አካል የኪራይ ሰብሳቢን ፖለቲካ ኢኮኖሚ ወደ ስርዓት አልበኝነት ፖለቲካ ኢኮኖሚ ለመለወጥ በመንደርደር ላይ መሆኑን ጠቋሚ ምልክት ተደርጎ የሚወሰድ ነው።

ይህ ፅሁፍ ግን መጠየቅ የፈለገው፣ የራሳችን ችግሮች የራሳችን ናቸው። ችግሩን መረዳትም መፍታትም በእኛው ዘንድ ያለ ነው። ሆኖም ግን ለኢትዮጵያ ፖለቲካ ሶስተኛ ወገን የሆኑ የሽብር ኃይሎች የኢትዮጵያ መንግስትና ሕዝብን በሽብር ሲያተራምሱ መክረማቸው የአደባባይ እውነት ነው። የኢትዮጵያ ሥርዓተ መንግስትን የሚያስተዳድረው ገዢው ፓርቲም የሶስተኛ ወገኖችን አፍራሽ ተልዕኮ ከማፍረስ ባሻገር ተመጣጣኝ የተባለ እርምጃዎችን ሲወስድም ተመልክተናል። የተደረገው ጥረት እንደተጠበቀ ሆኖ የሶስተኛ ወገኖች አጀንዳ የውስጥ ጉዳያችን እስኪመስል ድረስ ግን ዋጋ እያስከፈለን ይገኛል። ወደፊትም ያስከፍለናል። ይህን የተራዘመ የሶስተኛ ወገኖች አጀንዳ ከእሳት ማጥፋት ባሻገር መንግስት ከስሩ ነቅሎ ለመጣል የፖሊሲ ለውጦች ሲያደርግ አላየንም። በአንፃሩ ግን የተሸራረፉ የሚመስሉ የሶስተኛ ወገን አጀንዳዎች በየጊዜው ቅርጽ እየያዙ፣ ይዘታቸው ከፍ እያለ፣ ዋጋቸውም እየናረ ይገኛል። እስከ መቼስ ሊቀጥል ይችላል? የፖሊሲ ለውጥ ማድረግ ካልተቻለስ ችግሩን በምን መልኩ መቋጨት ይቻል ይሆን?

ከአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ጋር በተያያዘ ለተነሱ ጉዳዮች መግለጫ በመንግስት በኩል የተሰጡትን እዚህ ላይ በዋቢነት እንመልከተው። የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ በሰጡበት ወቅት እና የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር አቶ ጌታቸው ረዳ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በጽ/ቤታቸው በሰጡት መግለጫ ላይ ሁለቱም ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት የአስመራን አገዛዝ ተጠያቂ ማድረጋቸው የሚታወስ ነው። ከዚህ በፊትም ሻዕቢያ በሚከተለው የሽብር ፖሊሲ ተደጋጋሚ ውንጀላ ከቀንዱ ሀገሮች ሲቀርብበት ነበር። ሆኖም ግን ሻዕቢያ የትርምስ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲውን አጠናክሮ መቀጠሉን ሳያንስ ባልተለመደ መልኩ በአደባባይ ይፋ አድርጎ እየሰራ ነው። ለዚህም ነው፣ የፖሊስ ጥያቄ የሚነሳው።

እ.ኤ.አ. ከ1998 እስከ 2000 ከተደረገው የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት በኋላ በሁለቱ ሀገሮች መካከል “No War No Peace” የሚል ፖሊሲ ይከተላሉ። ይህ አይነት ፖሊሲ በባሕሪው ቀጥታ ወታደራዊ ግጭቶችን በማስቀረት የውክልና ጦርነቶችን (Proxy War) ለማድረግ የሚያበረታታ ነው። ይህም በመሆኑ ሻዕቢያ ከዚህ ቀደም ከሚያደርገው በበለጠ በተጠናከረ መልኩ በእጅ አዙር ጦርነቶች ኢትዮጵያን በማተራመስ ስራ ውስጥ ተጠምዶ ይገኛል። ባልተለመደ መልኩም ጦር መሳሪያ ያነሱ ሃይሎች አስመራን መቀመጫ አድርገው ጦርነት ማወጃቸውን በመገናኛ ብዙሃን አስታውቀዋል። በአመስራ ግዛት ወታደራዊ ልምምድ ሲያደርጉም መመልከት የተለመደ ሆኗል።

በአፍሪካ ቀንድ የሽብር የውጭ ግንኙነት ፖሊሲን በእጅ አዙር የዘረጋው የሻዕቢያ አገዛዝ ዛሬ ላይ ምክንያቱ እምብዛም ባልታወቀ መልኩ ቀጥተኛ የሽብር ፖሊሲ በኢትዮጵያ ላይ ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል። ከዚህም በላይ ርቆ በመሄድ የኤርትራን ነፃ ሀገር መሆን ሲቃወሙ የነበሩ ሃይሎችን፣ በአደባባይ የኤርትራን ነፃ ሀገርነት እንደሚቀበሉ እንዲያውጁ ከማድረጉም በላይ የኢትዮጵያ መንግስትን በጋራ ለመጣል እንደሚሰሩ አስነግሯል። ወደ ተግባር ስራዎችም ውስጥ ገብተዋል።

በ“No War No Peace” ፖሊሲ የኢትዮጵያ መንግስት የሻዕቢያን የሽብር የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ለዓለም ህዝብ በተለይ ለአፍሪካ ቀንድ ሀገሮች ማጋለጥ ችሏል። እንዲሁም በተባበሩት መንግስታት በኩል በሻዕቢያ የሽብር ፖሊሲ መነሻነት ማዕቀብ በአስመራ አገዛዝ ላይ እንዲጣልበት አድርጓል። በሁለቱ ሀገሮች መካከል የነበረው የንግድ ግንኙነት እንዲቋረጥ በመደረጉ የአስመራ አገዛዝ በከፍተኛ ሁኔታ የኢኮኖሚ ድቀት  ውስጥ ተዘፍቋል። የኤርትራ ዜጎች ሀገራቸውን ጥለው እንዲሰደዱ ከመሆናቸውም በላይ የአስመራን አገዛዝ ለመጣል በተለያዩ ቦታዎች ተደራጅተው ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ። በዚህ ችግር ውስጥ የወደቀው የአስመራ አገዛዝ ግን ከነችግሩ ኢትዮጵያን ለማተራመስ ያገደው አንዳች ነገር የለም። ለዚህም ነው፣ የፖሊሲ ለውጥ ማድረጉን በአማራጭነት እየተነሳ ያለው።

በተለይ በአሁን ሰዓት በየመን እና በሳዑዲ መራሹ የዓረቦች ጥምረት ሃይል መካከል እየተደረገ ያለው ጦርነት በምስራቅ አፍሪካ በተለይ ደግሞ በኤርትራ የጂዖ ፖለቲካ የኃይል አሰላለፍ ለውጦችን አስከትሏል። የየመን ጦርነት “የሺዓ-ሱኒ” የእጅ አዙር ጦርነት ተደርጎ በዓለም ዓቀፍ ዓብይ መገናኛዎች እየተዘገበ ይገኛል። ይህን ተከትሎ ከደቡብ የመን የተነሳው በአብዛኛው የሺዓ ሙስሊም እምነት ተከታዮች የመደብ ውክልና አለው የሚባለው የአንሱርላህ የፖለቲካ ኃይል የመንን ከረጅም የትጥቅ ትግል በኋላ መቆጣጠር ችሏል። በአሁን ሰዓትም ሰንዓን እያስተዳደረ ይገኛል። ለዚህ የፖለቲካ ኃይል ጦር መሳሪያ ታቀርባለች ተብላ በስፋት የምትወነጀለው ኢራን ስትሆን፣ የጦር መሳሪያ ዝውውሩ የሚፈጸመው ደግሞ በኤርትራ አገዛዝ በኩል ነው።

ይህን የኢራን-ኤርትራ ጥምረት ያሰጋቸው ሳዑዲ ዓረቢያና ኳታር ከኤርትራ አገዛዝ ጋር ያላቸውን ግንኙነት እንደገና እንዲፈትሹ ተገደዋል። የሳዑዲው ልዑል ባቀረቡላቸው ጥያቄ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ይፋዊ ጉብኘት አድርገዋል። እንዲሁም ባሳለፍነው ሳምንት የኳታሩ አሚር በአስመራ ከተማ ይፋዊ ጉብኝት አድርገዋል። የተለያዩ የኢኮኖሚ ትብብር ሰነዶች ከሁለቱ ሀገሮች ጋር አስመራ ፈርማለች። በተለይ የአሰብ ወደብ እና ምፅዋን ለማልማት በመቶ ሚሊዮን ዶላሮች ስምምነት ተፈጽሟል። እነዚህ ስምምነቶች በቀጣይ በአስመራ እና በቴህራን መካከል ሊያሳድሩ የሚችሉትን ተፅዕኖ ወደፊት የሚታይ ነው። ለኢትዮጵያ ግን የቅርብ ስጋት መሆኑ አሻሚ አይደለም።

የተደረገው ስምምነት ግን በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ኢትዮጵያ በአስመራ አገዛዝ ላይ የምትከተለውን  “No War No Peace” ፖሊሲን ጥያቄ ውስጥ ይጥለዋል። ይህም ሲባል፣ የአስመራን አገዛዝ ከዓለም ዓቀፍ ሕብረተሰብ መነጠል እና በኢኮኖሚ ማዕቀብ ውስጥ ማቆየት የሚቻልበት እድል እየመነመነ ነው። ለምሳሌ በደቡብ የመን የሚገባውን የጦር መሳሪያ አስመራ እንዳይገባ ካደረገች፣ ከሳዑዲ አረቢያና ከኳታር መንግስታት ከፍተኛ የኢኮኖሚ ትብብር ታገኛለች። እንዲሁም በዓለም ዓቀፍ ማሕበረሰብ በኩል የዲፕሎማሲ ድጋፍ እንድታገኝ የአረብ ሀገራት ምክር ቤት አባሎች ይሰራሉ። ይህ ሲሆን፣ የኢሳያስ አገዛዝ የኢኮኖሚ አቅሙ ይጨምራል፤ ከዓለም ማሕበረሰብ የመነጠል እድሉም እየጠበበ ይመጣል። በዚህ መልኩ የሚፈጠሩ ድጋፎች በኢትዮጵያ ላይ አጠናክሮ ለጀመረው የሽብር ፖሊሲው ተጨማሪ አቅም ይሆነዋል። ዋጋውም አሁን ካለው የበለጠ ይንራል።

መሬት ላይ ያለው ጥሬ ሃቅ ከላይ የሰፈረው ነው። ይህን መሰል ከባቢያዊ ሁኔታ ከቀድሞ “No war No Peace” ፖሊሲ ሻገር ያለ አዲስ ፖሊሲ መከተል ተገቢ ነው የሚሆነው። በርግጥ የፖሊሲ አማራጮችን ለመመልከት ብዙ ከግምት የሚወሰዱ ነገሮች መኖራቸው ይታወቃል። ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ ነገሮችም ሊኖሩ እንደሚችሉ መገንዘብ ይቻላል። እንዲሁም በ“No war No Peace” ፖሊሲ የኢሳያስን አገዛዝ ለመናድ ነገሮች እየጠበቡ መሆናቸውን መረዳትም በአማራጭነት የሚታይ አቀራረብ ነው።

ለምሳሌ የአውሮፓ ሀገሮች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የኤርትራዊያን ስደተኞች ቁጥርን ለመቀነስ ሁለት አማራጮችን እየተመለከቱ ነው። አንዱ የኤርትራን አገዛዝ በአስገዳጅ ጫናዎች የዜጎቹን ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶችን እንዲያከብር እና ኤርትራዊያን በቀያቸው የልማት እገዛ እንዲደርግላቸው ማድረግ ነው። ሁለተኛ አማራጭ በአንድም በሌላ መልኩ የኢሳያስን አገዛዝ ከስሩ በማድረቅና በመጣል፣ አገዛዙን በዴሞክራሲያዊ ኃይሎች መተካትን ያካትታል። እስካሁን ድረስ ግን ወደ ሙሉ ስምምነት ላይ መድረስ ይቀራቸዋል።

በተመሳሳይ መልኩም የኢትዮጵያ መንግስት የፖሊሲ አማራጮችን መፈተሽ ይገባዋል። አስምሮ መናገር የሚቻለው ግን “No war No Peace” ፖሊሲ የኢሳያስ አገዛዝን ማብቂያ ሊያመጣ የሚችልበት እድል በጣም አናሳ መሆኑን ነው።

ምንጭ ሰንደቅ

Leave a Reply