Wednesday, 30 December 2015 14:01

“የዜጎች ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶች

የመልካም አስተዳደር ቁልፍ መገለጫዎች ናቸው”

አቶ ልደቱ አያሌው

በይርጋ አበበ

አቶ ልደቱ አያሌው በዘመነ ኢህአዴግ ከታዩ የተቃውሞ ጎራው ፖለቲከኞች መካከል አንዱ ናቸው። ወሎየው ጎልማሳ በኢትዮጵያዊያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ከተራ አባልነት እስከ ሊቀመንበርነት ከዚያም የሊቀመንበርነት ዘመናቸው ከተጠናቀቀ በኋላ በማዕከላዊ ምክር ቤት አባልነት የተገደበ ስልጣን ተሰጥቷቸው ፓርቲያቸውን እያገለገሉ ይገኛሉ። በበርካታ ኢትዮጵያዊያን ዘንድ በአንደበተ ርቱዕነታቸው የሚታወቁት ጎልማሳው ፖለቲከኛ በአሁኑ ወቅት ከፖለቲካው ትግል ጎን ለጎን “ከሃያ ዓመቴ ጀምሮ ስሰራው የቆየሁት ስራ ነው” ብለው በሚናገሩለት ንግድ ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ። “ከሰላማዊ ትግል ውጭ የትኛውም የትግል ስልት እንደ መፍትሔ ሊወሰድ አይገባም” የሚሉት አቶ ልደቱ አያሌው በተለያዩ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ከሰንደቅ ጋዜጣ ጋር ቃለ ምልልስ አድርገዋል። የቃለ ምልልሱ ሙሉ ክፍል ደግሞ ከዚህ በታች ቀርቧል።

ሰንደቅ፡-ጥያቄያችንን በሰሞነኛ ጉዳይ ላይ እንጀምርና በትናንትናው እለት አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ ሁለተኛውን የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ በፓርላማ አስፀድቀዋል። (ቃለ ምልልሱ የተካሄደው ቅዳሜ ጠዋት ነበር) የመጀመሪያው እቅድ በአብዛኛው እንዳልተሳካ ይነገራል። መንግስት ደግሞ እቅዱ ያልተሳካው ተለጥጦ ስለታቀደ እንጂ አሳክቻለሁ ብሏል። እርሰዎ በዚህ ላይ ያለወት አስተያየት ምንድን ነው?

አቶ ልደቱ፡-እቅድ ሲታቀድ እንዲሁ ዝም ተብሎ መታቀድ ስላለበት ሳይሆን መሬት ላይ ባለው ነባራዊ ተጨባጭ ሁኔታ ታሳቢ በማድረግ ነው። በዚያ መልኩ እቅድ ታቅዶ ወደ ስራ መገባት ይገባል። ኢህአዴግ ግን ሁልጊዜም የሚለው እቅዱ ያልተሳካው ተለጥጦ ስለታቀደ እንጂ የታሰበውን ግብ መትቷል ነው። ይህ በፍጹም ትክክል አይደለም። የመጀመሪያውን የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ በተመለከተ ለምን አልተሳካም ሲባል እቅዱ በጣም የተለጠጠ ስለነበረ ነው ማለት ተገቢ አይደለም። ፓርላማ በነበርኩበት ወቅት ኢኮኖሚው መዋቅራዊ ለውጥ ያስፈልገዋል ብዬ ደጋግሜ ተናግሬ ነበር። ግብርናው ከዝናብ ጠባቂነት ተላቅቆ በመስኖ ማምረት መጀመር አለበት፣ ከብጥስጣሽ የአርሶ አደር ማሳ በመውጣት ወደ ዘመናዊ የተቀናጀ (ሜካናይዝድ) እርሻ ስርዓት መገባት አለበት ብዬ ተናግሬያለሁ። ከግብርና መር ወጥተን ኢኮኖሚውን አገልግሎት እና ኢንዱስትሪው ሊረከብ ይገባዋል። ነገር ግን ይህ አልሆነም።

ኢኮኖሚው ላይ መዋቅራዊ ለውጥ ሳትፈጥር እና የአንድ ፓርቲ አስተሳሰብ ብቻ ተሰሚ በሆነበት ሁኔታ እቅድ ማሳካት አይታሰብም። ይህ የሚያሳየው ደግሞ በአጠቃላይ ኢኮኖሚው ላይ መዋቅራዊ ለውጥ አለመካሄዱን ነው።

ሰንደቅ፡-ከ1997 ዓ.ም ምርጫ በኋላ ኢህአዴግ የሰላማዊ ትግል መንገዶችን በሙሉ እያጠበበ ሄዷል ወይም የፖለቲካ ምህዳሩን አጥብቦታል ብለው የሚናገሩ አሉ። በዚህ ጉዳይ ላይ የእርሰዎ ፓርቲም እንደሚስማማ ቀደም ሲል አስታውቋል። ኢህአዴግ የፖለቲካ ምህዳሩን ያጠበበው የትኞቹን በሮች በመዝጋት ነው?

አቶ ልደቱ፡- ኢህአዴግ ሁለት ነገር በአንድ ጊዜ ጠልቶ መኖር እንደማይቻል ማወቅ አለበት። በአንድ በኩል የሰላማዊ ትግል በሮችን በሙሉ ዘግቶ መቶ በመቶ ተመርጫለሁ ይላል። በሌላ በኩል ደግሞ የሰላማዊ ትግል ምህዳሩን በማጥበቡ የትጥቅ ትግል የሚያነሱትን ይቃወማል። ስለዚህ ወይ ሰላማዊ ትግልን ፈቅዶ የፖለቲካ ምህዳሩን በማስፋት ሀሳቦችን ይዞ መጥቶ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር በጠረጴዛ ዙሪያ መወያየትና በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታው ማሳተፍ አለበት። አለዚያ ደግሞ በይፋ የሰላማዊ ትግሉን እንደማይፈቅድ መግለጽ ይኖርበታል። እንዲህ ከሆነ ደግሞ ነፍጥ የሚያነሳው ይበዛል።

በጦርነት ደግሞ አትራፊ የሚሆን ወገን የለም። በጦርነት ስልጣን የያዘ ቡድንም ቢሆን ምንጊዜም የደም ዋጋ ከህዝቡ መጠየቁ አይቀርም። ስለዚህ በአሁኑ ሰዓት የትጥቅ ትግል (ጦርነት) አዋጭም ተመራጭም የትግል ስልት አይደለም።

ሰንደቅ፡-ኢህአዴግ የፖለቲካ ምህዳሩን አጥብቦ የሰላማዊ ትግል በሮቹን ሁሉ በመዝጋት አገሪቱን በአንድ ፓርቲ አገዛዝ ስር የሚጥል ከሆነ በሰላማዊ መንገድ እንዴት መታገል ይቻላል?

አቶ ልደቱ፡- የትግል አስፈላጊነቱ ታዲያ ምኑ ላይ ነው? ትግል እኮ የሚያስፈልገው የሰብአዊና የዴሞክራሲያዊ መብቶች ሲታፈኑ መብቶች እንዲከበሩ፣ ህዝብ የስልጣን ባለቤት እንዲሆን እንጂ እነሱ ካሉማ (ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ከተከበሩ እና የሰላማዊ ትግሉ ፖለቲካዊ ምህዳር ከሰፋ) ለምን ትታገላለህ? ሰላማዊ ትግልን አስቸጋሪ የሚያደርገውም እኮ አምባገነን መንግስታት ሁሉንም ነገር ተቆጣጥረው ስለሚይዙ እነዚያን መንግስታት በሰላማዊ መንገድ ታግሎ ከስልጣን ማውረዱ ነው። ነገር ግን ህዝብም ሆነ ፓርቲዎች በጽናት በሰላማዊ መንገድ መታገል ብቻ ነው አማራጫቸው።

እንደ በርማ አምባገነን መንግስት አልነበረም። አሁን ግን በርማዎች በሰላማዊ ትግል አምባገነኑን መንግስት ከስልጣን ማውረድ ችለዋል። ይህ የሰላማዊ ትግል ውጤት ነው። በአገራችንም አንድ ተጨባጭ የሰላማዊ ትግል ውጤት ልንገርህ። በ1997 ምርጫ ከ200 በላይ ወረዳዎችን ከአምባገነን ስርዓት ነጻ ማውጣት ችለናል። በትጥቅ ትግል ግን ባለፉት 24 ዓመታት ከአምባገነን መንግስት ነጻ የወጣ አንድ ወረዳ የለም።ለዚህ ነው የትጥቅ ትግል አማራጭም ተመራጭም ያልሆነ የትግል ስልት ነው ያልኩት።

ሰንደቅ፡-ኢህአዴግ (መንግስት) በአገሪቱ በሰላማዊ መንገድ ከሚታገሉ ፓርቲዎች ጋር አብሬ እሰራለሁ ሲል ደጋግሞ ቢናገርም የእርስዎን ፓርቲ (ኢዴፓ) ጨምሮ መንግስት ቃሉን እንዳልተገበረ ሲናገሩ ይሰማል። በፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ቆይታቸውም ደስተኛ አለመሆናቸውን ተናግረዋል። ለመሆኑ መንግስት ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር እንደተናገረው በተግባር አብሮ እየሰራ ካልሆነ ምክንያቱ ምንድን ነው?

አቶ ልደቱ፡-ኢህአዴግ ፓርቲዎችን አሳትፋለሁ፣ አብሬ እየሰራሁ ነው የሚለው እርዳታ እና ብድር ለሚሰጡት አገራት ማደናገሪያ ነው። በተግባር ግን ከቀበሌ ምክር ቤት ጀምሮ እስከ ፌዴራሉ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአንድ ፓርቲ አባላት ብቻ እንዲያዙ እያደረገ ነው ያለው። ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር አብሮ መስራት ቢፈልግ ኖሮ ሁሉንም ምክር ቤቶች በራሱ አባላት ብቻ ባልተቆጣጠረው ነበር። ከታች ጀምሮ እስከ ፌዴራል ፓርላማ ድረስ መቶ በመቶ በራሱ አባላት ተቆጣጥሮ ከተቃዋሚዎች ጋር አብሬ እሰራለሁ የሚለው ርካሽ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ነው። ይህ የግራ ዘመም ፖለቲካ ርዕዮት ዓለም ውጤት ነው፡፡

ሰንደቅ፡-በቅርቡ በአዲስ አበባ እና ዙሪያዋ የተቀናጀ ማስተር ፕላን ምክንያት በኦሮሚያ ክልል ተቃውሞ ተከስቶ ነበር። መንግስት የተነሳውን ተቃውሞ “ከድርጊቱ ጀርባ ሆኖ የራሱን ዓላማ ለማሳካት የተደራጀ ሀይል ያስነሳው እንጂ የኦሮሞ ህዝብ ተቃውሞ አይደለም” ሲል አስታውቆ ነበር። እውን መንግስት እንደሚለው ተቃውሞ ካነሳው የክልሉ ህዝብ ጀርባ ሌላ የተደራጀ ሀይል አለ ማለት ይቻላል?

አቶ ልደቱ፡- በእውነቱ ከተነሳው ተቃውሞ ጀርባ የተደራጀ ሀይል ወይም ቡድን የለም ማለት አይቻልም፣ ሊኖር ይችላል። ነገር ግን ህዝቡ ተነስና ተቃወም ስለተባለ ብቻ ተነስቶ ተቃውሞ ያሰማል ማለት አይቻልም። ተልዕኮ ከሚሰጠው ቡድን በፊት የህዝቡ የቆየ የመልካም አስተዳደርና ሌሎች ችግሮች እንዳሉበት ያሳያል። ማንም ሰው ከውስጡ ምክንያት ከሌለው ተነስና ተቃወም ሲባል ተነስቶ አይቃወምም። ለምሳሌ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎችን ተመልከት። ተማሪዎቹ የ19 እና የ20 ዓመት ወጣቶች ቢሆኑም በማስተር ፕላኑ ምክንያት ተቃውሟቸውን ገልጸዋል። ለምን ተቃውሞ አሳዩ ከተባለ ከቤተሰባቸው ያዩትን ብሶት ነው የገለጹት። ስለዚህ ዝም ብሎ ከድርጊቱ ጀርባ የተደራጀ አካል አለ ከማለት ይልቅ የህዝቡን ብሶት ማዳመጥ ይገባል። የህዝብ ጥያቄ ካልተመለሰ ነገ ምን ሊፈጠር እንደሚችል ማሰብ አለበት።

ሰንደቅ፡- ኢህአዴግ የመልካም አስተዳደር ችግር እንዳለበት ደጋግሞ ይናገራል። በዚህ ጉዳይ ላይ ትኩረት ሰጥቶ በተደጋጋሚ ሲናገር ቢሰማም ተጨባጭ ለውጥ ግን ማምጣት እንዳልቻለ ይታወቃል። ለመሆኑ ኢህአዴግ በመልካም አስተዳደር ላይ ለውጥ ማምጣት ያልቻለው ለምን ይመስልዎታል?

አቶ ልደቱ፡- መልካም አስተዳደር ፈርጀ ብዙ እና በአጠቃላይ በመንግስትና በህዝብ መካከል ያለውን ግንኙነት የሚመለከት ጽንሰ ሀሳብ ሆኖ እያለ ኢህአዴግ ግን የአገልግሎት አሰጣጥ ጉዳይ ብቻ አድርጎ ነው የሚመለከተው። የዜጎች ዴሞክራሲያዊና ሰብአዊ መብቶች የመልካም አስተዳደር ቁልፍ መገለጫዎች ሆነው ሳለ በኢህአዴግ ግን ለአፍታም ቢሆን እንዲነሱ የሚፈለጉ ርዕሰ ጉዳዮች አይመስሉም። ሰብአዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብት ባልተከበረበት መልካም አስተዳደር ሊኖር አይችልም። ስለዚህ ኢህአዴግ የመልካም አስተዳደር ችግርን ከልቡ መፍታት ከፈለገ የችግሮቹን ምንጭ እና የመፍትሔውን አቅጣጫ ከአገራችን የሰብአዊ እና ዴመክራሲያዊ መብት ሁኔታ ጋር አያይዞ ሊፈትሽ ይገባል። በተለይ ፖለቲካዊ ሙስናዎችን ሊዋጋ ይገባል። ፖለቲካው በሙስና ከተሸነፈ ኢኮኖሚያዊ ሙስና መኖሩ አይቀርም።

በአገሪቱ የመንግስትና የፓርቲ መዋቅር ተደበላልቋል። ሆን ብሎ በማቀድ የመንግስትንና የኢህአዴግን መዋቅር እንዲደባለቅ በማድረግ በመንግስት መዋቅር ውስጥ የእርስ በእርስ ቁጥጥርና ክትትል እንዳይኖር አድርጓል። በመንግስት የተለያዩ መዋቅሮች መካከል ቁጥጥርና ክትትል ሳይኖር ነው ኢህአዴግ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመዋጋት ተነስቻለሁ የሚለው። በሌላ በኩል ደግሞ ህዝቡ አቅም እንዳይኖረው (አቅመ ቢስ እንዲሆን) ተደርጓል።

የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ተዋግቶ ማሸነፍ ያለበት ህዝቡ ቢሆንም ህዝቡ ግን በቢሮክራሲው እና በሙሰና የተሸነፈ አቅመ ቢስ ሆኗል። ዜጎች ጉዳያቸው በአግባቡ አልፈጸም ሲላቸው ወይም በደል ሲደርስባቸው ለበላይ አካል አቤቱታ አቅርበው የሚያገኙት መፍትሔ እንደሌለ ስለሚያውቁ ችግሩ እንዲፈታ ከመታገል ይልቅ የችግሩ አካል ሆነዋል። ህዝብ ተገቢውን ጉልበት አግኝቶ የለውጥ ሀይል የሚሆነው ዴሞክራሲያዊና ሰብአዊ መብቱ ተከብሮ እውነተኛ የፖለቲካ ስልጣን ሲኖረው ነው።

የመልካም አስተዳደር ችግር ፈጣሪ እኮ ራሱ ኢህአዴግ ነው። ከስልጣን ሹመት በተጨማሪ የስራ ቅጥርም ቢሆን በሙያ እና በትምህርት ብቃት ሳይሆን በፓርቲ ታማኝነት ላይ የተመሰረተ በማድረግ ነው መልካም አስተዳደር እንዳይኖር ያደረገው።ያ ሀይል ነው አሁን በመንግስት መዋቅር ውስጥ ገብቶ የህዝብን ብሶት የፈጠረው።ኢህአዴግ አሁን በመልካም አስተዳደር ችግር ላይ ሁለት አማራጮች ብቻ ፊቱ ላይ ቀርበውለታል። በካንሰር የተበከለ አካላቱን (በመልካም አስተዳደር ችግር ሰንሰለት ውስጥ የገቡትን አባላቱን) ቆርጦ መጣል ወይም ከእነ ካንሰሩ አብሮ መኖርና ህልውናውን ማሳጠር።

ሰንደቅ፡- ላለፉት ረጅም ዓመታት ሲያነጋግር የቆየው የኢትዮጵያ እና የሱዳን ድንበር አከላለልን በተመለከተ የሱዳን መገናኛ ብዙሃን እና የተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች በስፋት ሲዘግቡት ታይተዋል። የኢትዮጵያ መንግስት ግን ጉዳዩን ከማስተባበል የዘለለ ያለው ነገር የለም። ይህን እንዴት ያዩታል?

አቶ ልደቱ፡- ጉዳዩ (የድንበር ማከለሉ) ሲነሳ የአሁኑ የመጀመሪያ አይደለም። ላለፉት 24 ዓመታት በተደጋጋሚ ጊዜ በየዓመቱ እየተነሳ ሰሞነኛ የውይይት ርዕስ ሆኖ እንደገና ይጠፋል። በዚህ ጉዳይ በተደጋጋሚ ጊዜ ጥያቄዎች ይቀርቡልናል፤ ተመሳሳይ መልስ ነው የምንሰጠው። ነገር ግን መንግስት ለምን ዝምታን መረጠ? በሚለው ላይ መንግስት አሰራሩን ለህዝብ ግልጽ ማድረግ አለበት። የሁለቱን አገራት የሚዋስነውን ድንበር ለመገናኛ ብዙሃን በማስጎብኘት ለህዝብ ግልጽ ማድረግ አለበት። መንግስት ነገሩን አፍኖ ከተቀመጠ እና ለሚነሳው ወሬ ትክክለኛ መልስ ካልሰጠ በህዝብ ላይ ውዥንብርን ይፈጥራል።

ድንበሩ የሚካለል ከሆነ ደግሞ መሆን ያለበት ሁለቱንም አገራት ተጠቃሚ የሚያደርግ ወደፊት ሰላማዊ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን በማያበላሽ መልኩ መሆን አለበት እንጂ አንደኛውን አገር ብቻ ተጠቃሚ ማድረግ የለበትም። እኔ በግሌ የኢትዮጵያን መሬት ለሱዳን አሳልፎ መስጠትም ሆነ የሱዳንን መሬት ወደ ኢትዮጵያ ማካለል ተገቢ ነው አልልም።

 

ሰንደቅ፡- ፓርላማ በነበሩበት ወቅት የአገራችን የህዝብ ቁጥር በአሳሳቢ ደረጃ እየጨመረ መሆኑን ተናግረው በዚህም መንግስት የስነ ህዝብ ፖሊሲውን መፈተሽ እንዳለበት አሳስበው ነበር። አሁን በአገሪቱ በደረሰው ድርቅ ምክንያት ከ10 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የአስቸኳይ የምግብ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሆኗል። በዚህን ያህል ደረጃ በአገራችን ላይ የምግብ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ዜጎች ቁጥር የጨመረው የስነ ህዝብ ፖሊሲው ስላልተፈተሸ ነው ማለት ይቻላል?

አቶ ልደቱ፡- መንግስት በምግብ ሰብል ራሳችንን ችለናል ብሎ በተናገረበት ማግስት ከ15 ሚሊዮን በላይ ህዝብ አስቸኳይ የምግብ እርዳታ ፈላጊ ሲሆን እያየን ነው። የህዝብ ቁጥር ከሚመረተው ምርት ጋር ተመጣጣኝ ካልሆነ ድርቅ ባይኖር እንኳ የርሃብ ስጋት መኖሩ አይቀርም። እንደዚህ የድርቅ አደጋ ሲፈጠር ደግሞ ችግሩ የከፋ ይሆናል። ለዚህ ነበር ፓርላማ በነበርኩበት ወቅት የስነ ህዝብ ፖሊሲ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ያልኩት።

ሰንደቅ፡- የህዝብ ብዛቱ እንዳለ ሆኖ የአሰፋፈር ሁኔታውስ ማለትም ለምሳሌ በጋምቤላ እና በቤኒሻንጉል የሚኖረው ህዝብ ቁጥሩ በጣም አነስተኛ ነው። ይህም በክልሉ ገና ያልታረሰ ባዶ ቦታ እንዲኖር ሲያደርገው በሌላ በኩል በሌሎች ክልሎች ያለው የህዝብ ብዛት መሬቱ ማምረት ከሚችለው በላይ ነው። ይህ ለድርቁ መከሰት አንድ ምክንያት አይሆንም?

አቶ ልደቱ፡- ልክ ነህ ኢትዮጵያ በጣም ሰፊ አገር ነች። ገና ያልታረሰ መሬት መኖሩም ልክ ነህ። ግን የአሰፋፈር ችግር እንዲኖር ያደረገው የፌዴራሊዝም ስርዓቱ ነው። በኢህአዴግ የፌዴራሊዝም ስርዓት የተመጣጠነ የህዝብ አሰፋፈር እንዳይኖር ፌዴራሊዝሙ የተዋቀረው ቋንቋን መሰረት ያደረገ በመሆኑ በአገር አቀፍ ደረጃ ህዝብ ማስፈር የምትችለው ከአንዱ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በራሱ ክልል እንጂ ከአንዱ ክልል ወደ ሌላው ክልል ማስፈር አትችልም። ስለዚህ እንዳልከው በድርቁ ምክንያት ለደረሰው ችግር የህዝብ አሰፋፈሩም አንዱ ምክንያት ሊሆን ነው።

ሰንደቅ፡-ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከፖለቲካ ተሳትፎውም ሆነ ከመገናኛ ብዙሃን ጠፍተዋል። ምክንያቱ ምንድን ነው ሲባል አቶ ልደቱ ፊታቸውን ወደ ኢንቨስትመንት አዙረዋል ሲባል ሰማን። እውን ፊትዎን ከፖለቲካ ወደ ኢንቨስትመንት አዙረዋል?

አቶ ልደቱ፡- ኢትዮጵያ ውስጥ ፖለቲከኛ የግል ኑሮ ያለው አይመስልም። የራሱን ኑሮ ማሸነፍ ያልቻለ ፖለቲከኛ የህዝብን ጥያቄ መመለስ አይችልም። ከፖለቲካውም ከመገናኛ ብዙሃንም ርቀሃል ላልከው አልራኩም። አሁንም የፓርቲዬ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ነኝ። ሚዲያው ወደ እኔ ስላልመጣ ከመገናኛ ብዙሃን ልርቅ እችል ይሆናል እንጂ እኔ አልራኩም። አሁንም ካንተ ጋር የተገናኘነው እኮ በፖለቲካው ነው። ከፖለቲካው ራቀ የተባለው ከፓርቲ ኃላፊነትም ሆነ ከስራ አስፈጻሚ አባል ውጭ ስለሆንኩ በሁሉም ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫ መስጠት አልችልም እንጂ ከፖለቲካ ተሳትፎ ውጭ አይደለሁም። እንደተባለው ግን ለሁለት ዓመታት ለትምህርት ከአገር ውጭ ስለነበርኩ የጠፋሁ ሊመስል ይችላል እንጂ የንግድ ስራው አላጠፋኝም። ገና ከ20 ዓመቴ ጀምሮ ስሰራው የኖርኩት ስራ ነው አሁንም እየሰራሁ ያለሁት።¾

Leave a Reply