ክፍሉ በትኩስ እንጀራ መዓዛ ታውዷል፡፡ በውስጡ የሚገኙት ሴቶች ከ30 በላይ በሚሆኑ የእንጀራ ምጣዶች ላይ እንጀራ እየጋገሩ ነው፡፡ መደዳውን የተደረደሩ በሊጥ የተሞሉ በርሜሎችን ለተመለከተ፣ እንጀራ ጋገራው በአንድ ጀምበር ስለመጠናቀቁ ይጠራጠራል፡፡ ከመጋገሪያው ጎን በሚገኘው ክፍልም የተጋገረውን እንጀራ እያሸጉ የሚያዘጋጁ ሴቶች አሉ፡፡

ማሸጊያዎቹ የድርጅቱን የንግድ ምልክትና አርማ፣ የእንጀራው ክብደት መጠን፣ መቶ በመቶ ግሉቲን ከተባለው ንጥረ ነገር ከፀዳው ጤፍ ስለመዘጋጀቱን የሚገልጽ መልዕክትም በማሸጊያው ሠፍሯል፡፡ በውስጡ የሚገኙ የተለያዩ ንጥረ ነገሮችም በዝርዝር ተቀምጠዋል፡፡ እንደ በርበሬ፣ ሽሮ፣ ሚጥሚጣ ያሉት የባልትና ውጤቶች የሚዘጋጁበት የተለየ ክፍልም አለ፡፡ የቅመማ ቅመሞቹ መዓዛም ከባለሙያ ወይዘሮ እልፍኝ ሲገቡ የሚሰማውን ዓይነት ስሜት ይፈጥርቦታል፡፡

በማማ ትኩስ እንጀራ ማድቤት ዕረፍት የለም፡፡ ከሳምንት ሳምንት፣ ቀን ከሌት ያለዕረፍት የተለያዩ ባህላዊ ምግቦች ይዘጋጃሉ፡፡ ኤክስፖርት ይደረጋሉ፡፡ ሥራ ከጀመረ 13 ዓመታትን ያስቆጠረው ማማ ፍሬሽ ድርጅት በእንጀራ ንግድ ይታወቃል፡፡ በተቋቋመ በመጀመሪያዎቹ ዓመታት ወቅት ምርቱን የሚያቀርበው ለአገር ውስጥ ተጠቃሚዎች ብቻ ነበር፡፡ ቀስ በቀስ የማምረት አቅሙ እየተጠናከረ ሲመጣ የኤክስፖርት ገበያውን ተቀላቀለ፡፡ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስም ወደ ውጭ የሚልኩት ምርት እንጀራ ላይ ብቻ የተወሰነ ነበር፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ አቅማቸውን በማጠናከር ከእንጀራ በተጨማሪ ልዩ ልዩ የባልትና ውጤቶችን ወደ ተለያዩ አገሮች መላክ እንደጀመሩ የኩባንያው መሥራቾች ይናገራሉ፡፡ በቅርቡ ከእንጀራና ከባልትና ውጤቶች በተጨማሪ ዶሮ ወጥና ቆጮ መላክም ጀምረዋል፡፡  አሜሪካ በሳምንት ስድስት ቀን፣ ስዊድን በሳምንት ሦስት ቀን፣ ኖርዌይ በሳምንት ሁለት ቀን፣ ኩዌት በሳምንት አንድ ቀን፣ ካናዳ በሳምንት አንድ ቀን ምርቶቻቸውን ይልካሉ፡፡ በቅርቡም ወደ ኒውዮርክ የመላክ ሐሳብ እንዳላቸው ጠቅሰዋል፡፡

‹‹ገበያው ሰፊ ነው፡፡ ገና አልተነካም፤›› የሚሉት አቶ ኃይሉ ተሰማ የማማ ትኩስ እንጀራ ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ እንደ እሳቸው ገለጻ፣ ምርቶቻቸውን የሚያቀርቡት በቂ ደንበኞች ሊያገኙ በሚችሉባቸው፣ ኢትዮጵያውያን በብዛት በሚገኙባቸው አገሮች ነው፡፡ የኢትዮጵያ ባህላዊ ምግቦች በሌሎች ሕዝቦች ዘንድ ብዙም አይታወቁም ነበርና እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ምርቶቻቸውን ይጠቀሙ የነበሩ ኢትዮጵያውያን ብቻ ነበሩ፡፡

ነገር ግን ጤፍ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከተዋወቀ በኋላ የውጭ ዜጐችም ደንበኛ ሊሆኑ ችለዋል፡፡ በተለይ በአሜሪካ በእጅጉ ታዋቂና ተመራጭ ከሆኑ ሬስቶራንቶች መካከል ኢትዮጵያውያኑ ቅድሚያ እንደሚሰጣቸው በርካታ የውጭ ዜጎች ሲናገሩ ይደመጣሉ፡፡ ለዚህም ይመስላል ‹‹ዘ ሲምሰንስ›› የተባለው ኮሜዲ የቤተሰብ ተከታታይ  ካርቱን ፊልም ውስጥ አንዱን ክፍል ‹‹ሊትል ኢትዮጵያ›› በማለት የኢትዮጵያን የባህል ምግቦች አስተዋውቋል፡፡ ይህም የኢትዮጵያ ምግቦች ይበልጥ እንዲታወቁ ማስቻሉ ይታመናል፡፡ ለስኳር ህመምተኞች የጤፍ ፍቱንነት በመረጋገጡም ይመስላል የሆሊውድ ዕውቆች አዘውታሪ መሆናቸው እየተሰማ ነው፡፡

ማማ ፍሬሽ ከሚያቀርበው እንጀራ ውስጥ እስከ 15 በመቶ የሚሆነውን ባህላዊ ምግብ የሚገዙት የውጭ ዜጐች ናቸው፡፡ የደንበኞቻቸው ቁጥር በየጊዜው ሊጨምር ችሏል፡፡ ለዚህም ይመስላል ያለ እረፍት የሚሠሩት፡፡ በአሁኑ ወቅት የድርጅቱ ዓመታዊ ገቢ 1.5 ሚሊዮን ዶላር ደርሷል፡፡ በመጪው ዓመትም ገቢውን ወደ ሁለት ሚሊዮን ዶላር ለማሳደግ ደፋ ቀና እያሉ ይገኛሉ፡፡

‹‹ዓለም አቀፍ ገበያውን ለመቀላቀል አስፈላጊውን መስፈርት እያሟላን ነው፡፡ የጥራት ማረጋገጫ ሰርተፊኬትም እየተዘጋጀ ነው፤›› ሲሉ የጥራት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት ሲያገኙ ከዚህ የተሻለ መሥራት እንደሚቻል፣ እስከዚያ ድረስ ግን ኤክስፖርት አድራጊ ድርጅቶች የሚልኩትን ምርት በጥንቃቄ ማዘጋጀት እንደሚገባቸው፣ ይህ ካልሆነ ግን በአንድ ትንሽ ስህተት ገበያው እንዳልነበር ሊሆን እንደሚችል አቶ ኃይሉ ሥጋታቸውን ገልጸዋል፡፡

ከዚህ ቀደም ገበያ ወጥቶ እንጀራና ሌሎች የባልትና ውጤቶችን መሸመት እንደነውር ይቆጠር ነበር፡፡ ካልተቸገሩ በቀር ከውጭ ገዝቶ መብላት የማይታሰብ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ነገሮች ከአቅማቸው በላይ ሆኖ የበሰለ ገዝቶ ለመመገብ የሚገደዱ ‹‹ክብራችንን ይነካል›› ብለው ስለሚጨነቁ እንዳይታወቅባቸው ይጥሩ ነበር፡፡ በእንጀራና በባልትና ንግዶች የሚሰማሩ ነጋዴዎችም ቢሆኑ በሥራው የሚሰማሩት ሌላ አማራጭ ሲያጡ ነበር፡፡

በአሁኑ ወቅት ግን ነገሮች ተቀይረዋል፡፡  በራሳቸው ቤት ውስጥ ለማዘጋጀት ጊዜው አልያም ችሎታው የሌላቸው በርካቶች፣ የተዘጋጀውን ከገበያ ገዝተው ሲጠቀሙ እንደቀደምቱ የተለየ ስሜት አይፈጠርባቸውም፡፡ በርካታ ግለሰቦችና ድርጅቶችም በንግዱ አዋጭነት እየተሳቡ ቢዝነሱን እየተቀላቀሉ ይገኛሉ፡፡ እንደ ማማ ፍሬሽ ያሉ ኩባንያዎችም ከአገር ውስጥ ገበያ አልፈው ምርቶቻቸውን ወደ ውጭ መላክ ከጀመሩ ሰነባብተዋል፡፡

በተለይም ጤፍ ግሉቲን ከተባለውና የስኳር ህመምተኞች እንዳይጠቀሙት ከሚመከረው ንጥረ ነገር ነፃ መሆኑ በተለያዩ ሚዲያዎች መነገሩ፣ ጤፍን የሆሊውድ አክተሮች መመገባቸው ለእንጀራ ቢዝነስ መድራት ዓይነተኛ ሚና ተጫውቷል፡፡ ‹‹ሱፐር ግሬይን›› እየተባለ ለሚንቆለጳጰሰው ጤፍና የጤፍ ውጤቱ እንጀራ፣ ከኢትዮጵያውያን ውጭ በውጭ አገር ዜጐች ዘንድም ተወዳጅ እንዲሆን አድርጐታል፡፡ አገሪቱ በእንጀራ ንግድ የምታገኘውን የውጭ ምንዛሪ ከፍ እንዲል ቢያደርገውም ገና እዚህ ግባ የሚባል ደረጃ ላይ ግን አላደረሰውም፡፡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ ከዓመታት በፊት አገሪቱ በእንጀራ ንግድ በወር የምታገኘው ገቢ ከ10,000 ዶላር አይበልጥም፡፡ ይህ ገቢ እ.ኤ.አ. በ2011 ወደ 400,000 ዶላር አሻቅቦ ነበር፡፡

ከምግብ፣ ከመጠጥና ከፋርማሱቲካል ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የተገኘው መረጃ፣ ከእንጀራ ንግድ የሚገኘው ገቢ በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ እንደሚገኝ ያመለክታል፡፡ በ2007 ዓ.ም. ከእንጀራ ንግድ 8.5 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት ዕቅድ ተይዞ ነበር፡፡ በሰባት እንጀራ ላኪዎች አማካይነትም 6.3 ሚሊዮን ዶላር ማግኘት ተችሏል፡፡ ከተያዘው ዕቅድ 74.1 በመቶውም ተሳክቷል፡፡ በ2008 ዓ.ም. እንዲሁ 12.5 ሚሊዮን  ዶላር ለማግኘት ዕቅድ ተይዞ፣ ዘጠኝ እንጀራ ላኪዎች 10.5 ሚሊዮን ዶላር በማስገኘት የዕቅዱን 85 በመቶ ማሳካት አስችለዋል፡፡ ይህም እንጀራ ወደፊት ለአገሪቱ እንደ ቡና ሁሉ የውጭ ምንዛሪ ምንጭ እንዲሆን የሚያደርገው ነው፡፡

እንደ እንጀራው ሁሉ ሌሎች ባህላዊ ምግብና መጠጦችን ወደ ውጭ በመላክ ለአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ማስገኘት እንደሚቻል ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ ይሁንና ሌሎቹ ባህላዊ ምግቦች እንደ እንጀራ ደረጃ ባለማግኘታቸው፣ በተገቢው መጠን ባለመተዋወቃቸው እንዲሁም የማሸጊያ ችግሮች ስላሉባቸው በዘርፉ ለተሰማሩ ነጋዴዎች ፈተና ሆኗል፡፡ ብዙዎችም ተስፋ ቆርጠው ከገበያ እንዲወጡ፣ ወደ ገበያው ለመግባት ፍላጐቱ ያላቸው ደግሞ ሐሳባቸውን እንዲቀይሩ እያስገደደ ይገኛል፡፡

በ2004 ዓ.ም. የተቋቋመው ዜድኤልኤን ልዩ ልዩ ቅመማ ቅመሞችና ባህላዊ ምግቦችን አዘጋጅቶ ወደ ውጭ ከሚልኩ ድርጀቶች መካከል የሚመደብ ነው፡፡ እንጀራ፣ ቆጮ፣ ሽሮ፣ በርበሬ፣ ዶሮ ወጥና ቅመማ ቅመሞችን በሳምንት ስድስት ጊዜ ወደ አሜሪካ፣ ኖርዌይ፣ ፊንላንድና አምስተርዳም ይልካል፡፡ በዋናነት የሚልከውም ደረጃ የወጣለትን እንጀራ ነው፡፡ ገበያው አስተማማኝ ባለመሆኑ ሌሎቹን የባልትና ውጤቶች የሚያዘጋጀው ትዕዛዝ  ሲኖር ብቻ ነው፡፡

‹‹እንጀራ ደረጃ ወጥቶለታል፡፡ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ አያስቸግርም፡፡ ሌሎቹ ግን ገና ደረጃ አልወጣላቸውም፡፡ እነሱን መላክ አስቸጋሪ ነው፤›› የሚሉት የዜድኤልኤን ባለቤት ወ/ሮ ገነት በርሄ፣ ከእንጀራ ውጪ ላሉ የባህላዊ ምግቦች ደረጃ አለመውጣቱ እንደ እሳቸው ላሉ ነጋዴዎች ፈተና መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ወደ ውጭ የሚላኩ ምግቦች ከፍተኛ ጥንቃቄ ይሻሉ፡፡ ደረጃውን በጠበቀ ማሸጊያ ማዘጋጀት ግድ ይላል፡፡ ስለምግቡ አዘገጃጀት የሚያሳይ እንዲሁም በውስጡ ስላካተታቸው ንጥረ ነገሮች ዝርዝር መረጃ ማስቀመጥም ይጠበቃል፡፡ ይህንን ለማድረግ ግን ነገሮች ቀላል አልሆኑም እየተባለ ነው፡፡

ስለዚህም ወደ ውጭ የሚልኩትን ምርት ሊከሰቱ የሚችሉ ማንኛውንም ዓይነት ችግሮች በመቀበል ኃላፊነት ወስዶ የሚረከባቸው ደንበኛ ሊኖራቸው ይገባል፡፡ አለዚያ ግን በፕላስቲክ አሽገው የሚልኩትን ምግብ ደፍሮ የሚገዛ አይኖርም፡፡ የዓለም አቀፍ ገበያውም ይህንን አይፈቅድም፡፡ በአጠቃላይ ባህላዊ ምግቦችን ሁሉ ወደ ውጭ ለመላክ የጥራት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት ካልተገኘ ነገሮች ፈታኝ ይሆናሉ፡፡

‹‹እኔ የላኩትን ዶሮ ወጥ የተመገበ አንድ ግለሰብ ቢታመም፣ ወጡን ያዘጋጀሁት እኔ ስለሆንኩ የምጠየቀው እኔው እሆናለሁ፡፡ ይህም የሚሆነው ግን የጥራት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት ሲኖረኝ ነው፤›› የሚሉት ወ/ሮ ገነት፣ የጥራት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት የሌላቸው ምግቦችን ኃላፊነት ወስዶ ለመቀበል አስቸጋሪ መሆኑን፣ ይህም እንደ እሳቸው ላሉ ባህላዊ ምግብ አቅራቢዎች ፈተና መሆኑን ይናገራሉ፡፡

ባህላዊ ምግቦችን ወደ ውጭ በመላክ አገሪቱ የማይናቅ የውጭ ምንዛሪ እያገኘች ትገኛለች፡፡ ነገሮች ባልተመቻቹበት ሁኔታ እየሠሩ ከሚገኙ እንደ ዜድኤልኤን ካሉ ተቋማት በዓመት ከሁለት ሚሊዮን ዶላር በላይ ይገኛል፡፡ ከእንጀራ ውጪ ያሉ ባህላዊ ምግቦችና መጠጦች ተገቢው ደረጃ ቢወጣላቸው ደግሞ በርካቶች ንግዱን ሊቀላቀሉ እንደሚችሉ፣ አገሪቱ የምታገኘውን የውጭ ምንዛሪ እንዲጨምር እንደሚያደርገው ይናገራሉ፡፡

የቢዝነሱን አዋጭነት የተመለከቱ ጥቂቶች ሐበሾች በብዛት ወደሚኖሩባቸው አገሮች ምርቶቻቸውን እየላኩ ይገኛሉ፡፡ እንደ እንጀራ፣ ዶሮ ወጥ፣ ሽሮና በርበሬ ካሉት በተጨማሪ እንደ ጠጅና አረቄም ያሉት ባህላዊ መጠጦችም ከአገር አልፈው ለውጭ ገበያ እየቀረቡ ይገኛሉ፡፡ ነገር ግን መጠጦቹን ወደ ውጭ መላኩ ባህላዊ ምግቦችን ከመላክ በተለየ ከባድ ነው፡፡

ለመጀመሪያ ጊዜ ጠጅ ኤክስፖርት ለማድረግ የተሞከረው በ1996 ዓ.ም. ነበር፡፡ በወቅቱ የነበሩና በጠጅ ንግድ ሥራ ላይ የተሠማሩ ነጋዴዎች ብርዝ፣ መካከለኛ ጠጅ፣ ደረቅ ጠጅ፣ ፊልተር ጠጅ የተባሉ የጠጅ ዓይነቶችን በማዘጋጀት ወደ ደቡብ አፍሪካ፣ ካናዳ፣ አሜሪካ፣ ጣሊያንና ዱባይ ልከው ነበር፡፡ በወቅቱ ከደረጃ መዳቢዎች ኤጀንሲም አስፈላጊው ትብብር ተደርጐላቸዋል፡፡ ምርቶቹ ከአገር ሲወጡም ደረጃ ተሰጥቷቸው ነበር፡፡

‹‹በወቅቱ በጐ ምላሽ አግኝተን ነበር፡፡ በተለይም ከወደ ዱባይ በብዛት እንድንልክላቸው ጥያቄ ያቀረቡልን ድርጅቶች ነበሩ፡፡ እኛም ደግመን ለመላክ ደረጃ መዳቢዎች የተለመደውን ትብብር እንዲያደርግልን ጠየቅን፡፡ ነገር ግን ፈቃደኛ ሊሆኑ አልቻሉም፤›› የሚሉት በወቅቱ ምርቶቻቸውን ከላኩት መካከል የነበሩት የአስቴር ጠጅ ባለቤት ወ/ሮ አስቴር ሰይፈ ናቸው፡፡

ጠጅን በማስተዋወቅና ለውጭ ገበያ በማቅረብ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ማግኘት እንደሚቻል በጠጅ ንግድ የተሰማሩ ነጋዴዎች ይናገራሉ፡፡ በዘርፉ የተሰማሩት ወ/ሮ ሙሉመቤት ገበየሁ እንደሚሉት፣ ምንም እንኳ ለጠጅ ደረጃ ስላልወጣለት ለውጭ ገበያ ማቅረብ ባይቻሉም በተለያዩ መንገዶች ወደ ጣሊያን፣ ጀርመን፣ ካናዳ፣ ስፔን ድረስ የወይዘሮ አስቴር ጠጅ እየተዳረሰ ይገኛል፡፡ ደንበኞቻቸውም ዳያስፖራ ኢትዮጵያውያንና የውጭ ዜጐች ናቸው፡፡ አንድ ሊትር ጠጅ በ70 ብር ይሸጣሉ፡፡ ‹‹ጠጃችንን የቀመሱ የውጭ ዜጐች ይወዱታል፡፡ በሻንጣቸው ደብቀው አገራቸው ይወስዱታል፤›› ሲሉ በስፋት ገበያ ላይ ቢቀርብ ለዓለም ማስተዋወቅና ጠቀም ያለ የውጭ ምንዛሪ መሰብሰብ እንደሚቻል ይናገራሉ፡፡ ወይዘሮዋ ጠጅ ደረጃ ወጥቶለት በሰፊው ወደ ዓለም ገበያ እንዲቀርብ ለማድረግ ብዙ ጥረዋል፤ ነገር ግን አልተሳካላቸውም፡፡

ሌሎቹ ባህላዊ ምግቦችና መጠጦች በሚቀርቡበት መንገድ ጠጅን ለዓለም ገበያ ማቅረብ አስቸጋሪ ነው፡፡ የሚዘጋጅበት መንገድ ኋላቀር ነው፡፡ ቴክኖሎጂ ቀመስ አይደለም፡፡ ጠጅ የሚዘጋጀው በበርሜል ውስጥ በእጅ ታሽቶ ነው፡፡ ይህም የዓለም ገበያው ካስቀመጠው መስፈርት ውጪ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡ በሌላ በኩልም ጠመቃው ከየትኛውም መጠጥ የተለየ ነው፡፡ ለረጅም ጊዜ መቆየት ቢችልም የመፍላት ባህሪ አለው፡፡ ይህም በፕላስቲክ ታሽጐ ወደ ውጭ ገበያ በሚቀርብበት ጊዜ ፕላስቲኩ እየፈነዳ አስቸግሯቸዋል፡፡

ጠጅን በጠርሙስ ለማቅረብ ደግሞ በጠርሙሱ ላይ የምርቱን ባለቤት የሚያሳዩ መረጃዎች ሊኖሩ ይገባል፡፡ ይህንን ለማድረግ ደግሞ የግድ ደረጃ መውጣት ይኖርበታል፡፡ ጠርሙስ በተመጣጣኝ ዋጋ የሚያመርት ተቋም ማግኘትም ሌላው ፈታኝ ነገር ነው፡፡ ሁኔታው የአገሪቱን ባህላዊ መጠጦችን ኤክስፖርት የሚያደርጉና ፍላጐቱ ያላቸውን ተስፋ ቆርጠው ከገበያ እንዲወጡ እያደረጋቸው ይገኛል፡፡

ወ/ሮ ሰላማዊት ባየለየኝ ‹‹እኔ ነኝ ያለ›› የሐበሻ አረቄ በማምረት ይታወቃሉ፡፡ የማር፣ የነጭ ሽንኩርት፣ የኮሶ፣ የግብጦና መደበኛ እየተባለ የሚመደብ አምስት ዓይነት አረቄ ያዘጋጃሉ፡፡ ሥራውን ከጀመሩ ሦስት ዓመታትን አስቆጥረዋል፡፡ ምርታቸውን ወደ ውጭ ለመላክ ጥረት አድርገው ያውቃሉ፡፡ ይሁንና አልተሳካላቸውም፡፡ ለዚህም የማሸጊያ ችግር ዋናው ነው፡፡ አረቄውን የሚያዘጋጁበት ገብስ ከዘረ መል ምህንድስና ነፃ መሆኑን ማስጠናት ሌላኛው የተጠየቁት መስፈርት ነበር፡፡ ይህንን ለማድረግ አቅሙ የላቸውም፡፡ ስለዚህም አረቄ ኤክስፖርት የማድረግ ሐሳባቸውን ወደ ጐን ብለው ለአገር ውስጥ ገበያ በማቅረባቸው ቀጥለዋል፡፡

በሉላዊነት ሰበብ የተለያዩ አገሮች ባህላዊ ምግብና መጠጦች በዓለም ዙሪያ እየተለደመዱ ይገኛሉ፡፡ በአንድ ወቅት በተወሰኑ አካባቢዎች ብቻ ይታወቁ የነበሩ እንደ ፓስታ፣ ቴላቴሊ፣ ላዛኛ፣ ፒዛ፣ በርገር ያሉ የምግብ ዓይነቶች መደበኛ ምግብ እስኪመስሉ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች በስፋት ለምግብነት እየዋሉ ይገኛሉ፡፡ ከሩዝ፣ ከአትክልት፣ ከዓሣ ሥጋና ከመሳሰሉት የሚሰናዳው የጃፓኑ ሱሺም በበርካታ አገሮች ታዋቂና ውዱ ምግብ ሆኖ ይገኛል፡፡ የአገሪቱን ባህላዊ ምግብና መጠጦች በተመሳሳይ መንገድ ለማስተዋወቅ ወደ ሥራው የገቡት እነዚህ ምግብ ላኪ ድርጅቶች ያላቸው ፋይዳ የላቀ ነው፡፡ ድርጅቶቹ የሚልኳቸውን ምርቶች የዓለም ገበያ በሚጠይቀው መስፈርት መሠረት ደረጃና የጥራት ማረጋገጫ በመስጠት የአገሪቱን ባህላዊ ምግብና መጠጦች ለዓለም ማስተዋወቅ የውጭ ምንዛሪ ማካበት ይቻላል፡፡

ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችን ደረጃ በማውጣት ተወዳዳሪ እንዲሆኑ የሚስችለው የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲም የተለያዩ ሥራዎች እየሠራ ይገኛል፡፡ መሥሪያ ቤቱ በሁለት መንገዶች ለምርቶች ደረጃ ይሰጣል፡፡ የመጀመሪያው አስገዳጅ የሚባለው ሲሆን በብሔራዊ ደኅንነት ላይ ችግር ሊፈጥሩ የሚችሉ፣ በአካባቢ ላይ የሚያደርሱት አደጋ ሊኖር እንደሚችል የሚገመቱ እንዲሁም በሰውና በእንስሳት ጤና ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ሊኖራቸው የሚችሉ ምርቶችን ይመለከታል፡፡ ሌላው በኅብረተሰቡ ንቃተ ህሊና  ላይ ተመሥርቶ የሚሰጠው የፈቃደኝነት ደረጃዎች በመባል የሚታወቀው ሲሆን፣ ምርቶች በሰውም ሆነ በአካባቢ ላይ የሚያደርሱት አደጋ ባይኖርም ደረጃ ቢወጣላቸው የተሻለ ተዓማኒነት ይኖራቸዋል፡፡ በመሆኑም ለምርቶቻቸው ደረጃ ወጥቶላቸው በገበያ ላይ የተሻለ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመገኘት ፍላጎቱ ባላቸው ፈቃደኛ አምራቾች ጥያቄ የሚዘጋጅ ይሆናል፡፡ የባህላዊ ምግብና መጠጦች ደረጃም በዚሁ ደረጃ አሰጣጥ ሥር ይመደባል፡፡

‹‹ተመሳሳይ ደረጃዎችን የምናዘጋጀው ገበያ ላይ ከፍተኛ ፍላጐት መኖሩን በራሳችን ጥናት በማድረግና የደረጃ ይውጣልን ጥያቄ ሲኖር ነው፤›› የሚሉት የኤጀንሲው የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ይስማህ ጅሩ ናቸው፡፡ እንደ እሳቸው ገለጻ፣ ለአንድ ምግብ ደረጃ የሚሰጠው ምግቡ በውስጡ የያዛቸው ንጥረ ነገሮች፣ የአሲድ መጠን፣ በምን ያህል የሙቀት መጠን መቀመጥ አለበት የሚሉና የመሳሰሉትን መስፈርቶች በግልጽ ለይቶ ካስቀመጠና በውስጡ የያዛቸው ንጥረ ነገሮች ጠቃሚ መሆናቸውን ከተረጋገጠ በኋላ ነው፡፡

 ይህንን ለማድረግ ደግሞ ተቋማቱ የቴክኖሎጂና የአቅም ውስንነት አለባቸው፡፡ ይህም ለምርቶቹ ደረጃ ለማውጣት አስቸጋሪ ሆኖ ቆይቷል፡፡ እስካሁንም ደረጃ ወጥቶላቸው እየተሠራባቸው ያሉት እንጀራና ማር ብቻ ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን ኤጀንሲው ለሌሎች ባህላዊ ምግብና መጠጦች ደረጃ ለማውጣት እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል፡፡ ከእነዚህ መካከል ጠጅ አንዱ ነው፡፡ በጥቃቅንና አነስተኛ ተደራጅተው እንደ ሽሮ፣ በርበሬ፣ ሚጥሚጣ፣ ቅመማ ቅመሞች ያሉትን ለሚያዘጋጁ ድርጅቶችም ኤጀንሲው ዘመናዊ የአሰራር ሥርዓት እንዲከተሉ የተለያዩ የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎች  እየሰጠ ይገኛል፡፡

እነዚህ ምግቦችን በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ለማስቻል ኤጀንሲው ከሚሰጠው ደረጃ በተጨማሪ በእያንዳንዱ ማሸጊያ ላይ የጥራት ማረጋገጫ ምልክት ሊኖር ግድ ይላል፡፡ ይህንን ለማድረግ ደግሞ የተለያዩ ችግሮች መኖራቸውን በኢትዮጵያ ተስማሚነት ምዘና ድርጅት የማርኬቲንግና የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ተክኤ ብርሃነ ይናገራሉ፡፡

‹‹የጥራት ማረጋገጫ በጣም ወሳኝ ነው፡፡ የጥራት ማረጋገጫ ያልተሰጠው ምርት ከአገር ቢወጣም ተፈትሾ ከደረጃ በታች ተብሎ ይመለሳል፤›› ያሉት አቶ ተክኤ፣ የጥራት ማረጋገጫ መስፈርቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ መቀመጡ የአገሪቱን ባህላዊ የምግብ አዘገጃጀትና ምጣኔ ጋር ተመሳሳይ አለመሆኑ ለምርቶቹ የጥራት ማረጋገጫ ለመስጠት እንቅፋት እንደሆነ ይናገራሉ፡፡

ለምሳሌ በርበሬ ሲዘጋጅ የተለያዩ ማጣፈጫ ቅመማ ቅመሞች ይጨመሩበታል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው የበርበሬ ደረጃ በሚያዘው መሠረት ደግሞ በርበሬ ማለት ምንም ሳይቀላቀልበት በቃሪያው ብቻ የሚዘጋጀው  ነው፡፡ የምርቱን ጥራት የሚፈትሸው መሳሪያም የተዘጋጀው በዚህ መሠረት ለተዘጋጁ ምርቶች ማረጋገጫ ለመስጠት ነው፡፡ በመሆኑም ምርቱን በሚፈትሽበት ወቅት በርበሬውን ለማጣፈጥ የተጨመሩ የተለያዩ ንጥረ ነገሮች በመኖራቸው ምርቱን በርበሬ እንዳልሆነ ሁሉ ባዕድ ነገር ብሎ ያነብባል፡፡ ይህ ለዘርፉ ዕድገት ትልቅ ማነቆ መሆኑን የሚናገሩት አቶ ተክኤ ምርቶቹ የሚፈተሹበት ‹‹የራሳችን ስታንዳርድ ያስፈልገናል፤›› ይላሉ፡፡

ምንም እንኳን ቁጥራቸው አነስተኛ ቢሆንም፤ ደረጃ ባይወጣላቸውም የጥራት ማረጋገጫ ተሰጥቷቸው ምርታቸውን የሚልኩ ድርጅቶች አሉ፡፡ እስካሁን የጥራት ማረጋገጫ አግኝተው እየሠሩ የሚገኙት አራት የሐበሻ አረቄ አምራቾች፣ አራት ቅመማ ቅመም ላኪዎች፣ ሦስት እንጀራ ላኪዎችና አምስት ማር አቅራቢ ድርጅቶች ይገኛሉ፡፡

የጥራት ማረጋገጫም ሆነ ደረጃ ያልወጣላቸው ነገር ግን ወደ ውጭ እየተላኩ ያሉ እንደ ጠጅ፣ ሽሮ፣ በርበሬ ያሉ ባህላዊ ምግብና መጠጦችም አሉ፡፡ እነዚህም ከማሸጊያ ጀምሮ የተለያዩ ችግሮች አሉባቸው፡፡ ይሁንና በሚቀጥለው የበጀት ዓመት ቴክኖሎጂ ለሚያስፈልጋቸው ቴክኖሎጂ በማዘጋጀት እንዲሁም የፓኬጂንግ ችግር ያለባቸው ችግሮቻቸውን በመቅረፍ ከዘርፉ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሪ ለማሳደግ ዕቅድ መያዙን በምግብ፣ በመጠጥና ፋርማሱቲካል ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያው አቶ ዳንኤል በትረ ተናግረዋል፡፡