ተወልዳ ያደገችው በአፋር ክልል አሳይታ አካባቢ በምትገኝ አሊስአቦ በተባለች ቦታ ነው፡፡ 16 አመቷ ነው፡፡ የስምንተኛ ክፍል ተማሪ ስትሆን ለትምህርቷ ጉጉት አላት፡፡ ነገር ግን በትምህርቷ እንዳትገፋ የተለያዩ ፈተናዎች ተጋርጠውባታል፡፡ በአካባቢው ባህል መሰረት የተገረዘችው ገና የሦስት ወር ሕፃን እያለች ሲሆን ከጋብቻ በፊት ፆታዊ ግንኙነት እንድታደርግ ከተገረዘች በኋላ ተሰፍታለች፡፡ ሳይሰፋ የቀረው  የወር አበባዋና ሽንቷ ሊወጣበት የሚችል ጠባብ ቀዳዳ ነው፡፡ ነገር ግን ቀዳዳው በጣም ጠባብ በመሆኑ የወር አበባዋንም ሆነ ሽንቷን በአግባቡ ማሳለፍ እንዳልቻለ ትናገራለች፡፡

‹‹የክብሪት እንጨት በምታህል ቀዳዳ የወር አበባ ሊወጣ አይችልም፡፡  የተያዩ የጤና ችግሮች አስከትሎብኛል፡፡ የወር አበባዬ ጊዜውን ጠብቆ አይመጣም፡፡ ሳይመጣ ወራት ይቆያል፡፡ በሚመጣበት ጊዜም ከባድ ሕመም ይሰማኛል፡፡ በተገቢው መጠን አይፈስም፡፡ ጠብ ጠብ እያለ ለአምስት ቀናት ያህል ይቆይብኛል፡፡›› የምትለው ታዳጊዋ በወር አበባ ጊዜ የሚሰማትን ከባድ ስቃይ ለመገላገል ወደ ሕክምና መስጫ  ሄዳ እንደምታውቅም ትናገራለች፡፡

 የ13 ዓመት ልጅ ሳለችም የትዳር ጥያቄ ቀርቦላት ነበር፡፡ ነገር ግን እንደ ሌሎች ጓደኞቿ የቀረበላትን የትዳር ጥያቄ አልተቀበለችም፡፡ ትምህርቷን እስክታገባድድ እንዲቆያት አድርጋለች፡፡ የመጣላት ባል በአብሱማ ባህል (የአክስትና የአጎት ልጆች የሚጋቡበት ሥርዓት) የአክስቷ ልጅ ነበር፡፡ ትምህርቷን እስክትጨርስ እየጠበቃትም ይገኛል፡፡

 እሷ ግን ከቤተሰቦቿ ትእዛዝ ውጪ ላለመሆን ብላ እንጂ  ጋብቻው ቢቀርባት ምርጫዋ ነበር፡፡ በጋብቻ ውስጥ ስለሚኖሩ አንዳንድ ጉዳዮች ስትሰማ ጋብቻዋ ደስታ ሳይሆን ስቃይ እንደሚሆንባት ታስባለች፡፡ በቅርበት የምትውቃቸውን ባለትዳር ሴቶች  በአፋር ባህል ለተገረዘች ልጃገረድ ፆታዊ ግንኙነት ማድረግ ከባድ ስቃይ መሆኑን ነግረዋታል፡፡

‹‹በጋብቻ ቀን ፆታዊ ግንኙነት ለማድረግ የተሰፋው መቀደድ አለበት፡፡ የተሰፋውን ባልየው ነው በሴንጢ  የሚከፍተው፡፡ በጣም ከባድ ስቃይ ነው፡፡ ሴቷ ለነፍሷ በምትንፈራገጥበት ወቅት ደግሞ ሴንጢው ስቶ ሌላ ገላዋን ይቀደዋል፡፡ በዚህም ብዙዎች ለፌስቱላና ለሞት ይዳረጋሉ፡፡›› ስትል በክልሉ የተለመደው የሴት ልጅ ግርዛት በሴቶች ላይ ምን ያህል ከባድ ችግር እያደረሰ እንደሚገኝ ትናገራለች፡፡

በክልሉ ባህል አንዲት ሴት ልጅ በተወለደች በሰባት ቀን ውስጥ መገረዝ ይኖርባታል፡፡ በተለያዩ አጋጣሚዎች ሳትገረዝ ብትቆይም ባል ከማግባቷ በፊት በአስራዎቹ የድሜ ክልል ውስጥ ሳለች መገረዝ ግድ ይላታል፡፡  ከተገረዘች በኋላ ከቁርጭምጭሚቷ ጀምሮ እስከጭኗ ድረስ በገመድ ተጠፍራ ትታሠራለች፡፡ በዚህ መካከልም የተቆረጠው የአካል ክፍሏ ለወር አበባና ለሽንት መውጫ የሚሆን ጠባብ ቀዳዳ እስኪቀር ድረስ እርስ በርሱ ይጣበቃል፡፡ ቁስሉ እስኪድንላት ድረስ የታሰረው እግሯ አይፈታም፡፡ ሽንቷን መሽናት ቢያስፈልጋት እንኳን ቁስሏን በቶሎ ያደርቀዋል የሚል እምነት ስላላቸው እዚያው ላይ እንድትሸና ይደረጋል፡፡ ይህ የአፋር ሴቶች ዕጣ ፋንታ እስኪመስል ለዘመናት ሲተገበር የቆየ ባህል ነው፡፡ ህይወታቸውም በስቃይ የተሞላ ዕንዲሆን አድርጎታል፡፡ ክብረ ንፅህናዋን ወደፊት ለምታገባው ባለቤቷ ጠብቆ ማቆየት የበለጠ ቦታ ስለሚሰጠው የሴቷ ስቃይ ቦታ አይሰጠውም ነበር፡፡

የግርዛቱ ቁስል ከዳነ በኋላም የሚቀረው ቀዳዳ በጣም ጠባብ በመሆኑ ሽንት ለመሽናትና የወር አበባ ለማስወጣት ከባድ ይሆናል፡፡ በመሆኑም የወር አበባና ሽንት በአግባቡ ሳይወገድ በማህፀናቸው ውስጥ በመከማቸት ለከፋ የጤና ችግር እንደሚዳርጋቸው ሴቶቹ ይናገራሉ፡፡

ከ2000 ዓመታት በፊት ጀምሮ እንደነበረ የሚነገርለት የሴት ልጆች ግርዛት በ27 የአፍሪካ አገሮች፣ በኢንዶኔዥያ፣ በኢራቅ፣ በየመንና በሌሎችም የእስያ አገሮች  ይፈጸማል፡፡ እ.አ.አ በ2016 ዩኒሴፍ ባወጣው አንድ ጥናት መሠረት በአሁኑ ወቅትበአለም ላይ  የሚገኙ 200 ሚሊዮን ሴቶች የዚህ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ሰለባ ናቸው፡፡አባዛኛዎቹም በኢትዮጵያ እንደሚገኙ ይነገራል፡፡ ከአመታት በፊት የወጣ አንድ ጥናት እንደሚያመለክተው ደግሞ በአገሪቱ ከ23.8 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሴቶች የተገረዙ ናቸው፡፡

በአገሪቱ ከሚገኙ 82 ብሔር ብሔረሰቦች  መካከል 46 የሚሆኑት ይህንን ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት እንደሚፈፅሙ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ አፋርና ሶማሌ ክልሎችም ድርጊቱን በመፈፀም በግንባር ቀደምነት ይጠቀሳሉ፡፡ ሴት ልጅ ከተገረዘች በኋላ የምትሰፋበት ባህል ያለውም በእነዚህ ሁለቱ ክልሎች ነው፡፡

በሴቶች ላይ እያደረሰ ባለው  ዘርፈ ብዙ የጤና ችግር ምክንያት ከዓመታት በፊት በአለም አቀፍ ደረጃ ተግባሩን በኢሰብዓዊ ድርጊትነት በመፈረጅ በየትኛውም የአለም ክፍል እንዳይፈፀም የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጥና ፖሊሲ የመቅረፅ  ሥራዎች ሲሠሩ ቆይተዋል፡፡ በዚህም የማይናቅ ለውጥ ማምጣት ተችሏል፡፡ ይሁንና በአንዳንድ የአለም ክፍሎች በተለይም በኢትዮጵያ እንደ አፋርና ሶማሌ ባሉ ክልሎች የታሰበውን ያህል ለውጥ ለማምጣት አለመቻሉ ይነገራል፡፡

በክልሉ በስፋት ይተገበር የነበውን የሴት ልጅ ግርዛት ለመግታት በተደረጉ ጥረቶች በአንዳንድ ቦታዎች አበረታች ለውጦችን ማየት ሲችል፤ በከፊል ለውጥ ያሳዩ አካባቢዎችም አሉ፡፡ ግርዛት ሃይማኖታዊ መሰረት እንዳለው የሚያምኑ ወላጆች ሙሉ ለሙሉ መቅረት የለበትም በሚል ሴት ልጆቻቸው የደንቡን ያህል እንዲገረዙ ነገር ግን እንዳይሰፉ ያደርጋሉ፡፡ ባገኙት ግንዛቤ ግርዛት አደገኛ መሆኑን የተረዱ ወላጆች ልጆቻቸው እንዳይገረዙ የደረጉም ጥቂት አይደሉም፡፡ እነዚህ ወላጆች ግን ‹‹ያልተገረዘችን ሴት አናገባም›› የሚሉ ያልተገረዘችን ሴት የሚያጥላሉ የማህበረሰቡ ክፍሎች በመኖራቸው፡ በውሳኔያቸው እንዲፀፀቱ ሆነዋል፡፡

የ15 ዓመቷ ሀሊማ (ስሟ ተቀይሯል) የሴት ልጅ ግርዛት ለአስከፊ አደጋ እንደሚያጋልጥ ከዚህ ቀደም ደጋግማ በወሰደቻቸው ሥልጠናዎች ተገንዝባለች፡፡ ወላጅ እኗቷም ብትሆን በቂ ግንዛቤ አላት፡፡ ለዚህም ነው እናቷ ሀሊማን ከማስገረዝ የታቀበችው፡፡ ወላጅ አባቷ ግን የሀሊማን አለመገረዝ አልሰማም፡፡ ጉዳዩንም እናትና ልጅ በሚስጥር ይዘውታል፡፡ ‹‹ወንድ ተከትላ የትም ትሄዳለች፣ ያልተገባ ድርጊት ትፈጽማለች ጋጠወጥ ትሆናለች የሚል እምነት ስላለው አለመገረዜን ቢሰማ ጦርነት ነው የሚፈጠረው፡፡ ያስገርዘኛልም ለዚህም በሚስጥር መያዝ መርጠናል፡፡ ›› ትላለች ሃሊማ፡፡

ምንም እንኳን ነገሮች በሚስጥር የተያዙ ቢሆንም ስለ አለሀሊማ መገረዝ ጥርጣሬ ያደረባቸው በሩቁ እንደሚያገልሏት ትናገራለች፡፡ ትምህርት ቤትም ሆነ በሰፈር የሚያውቋት ወንዶች ያንቋሽሿታል፡፡ ‹‹ማን ያገባሻል አንቺ እኮ ዱርዬ ነሽ›› ይሏታል፡፡ ለአብዛኛዎቹ የዕድሜ እኩዮቿ የትዳር ጥያቄ የመጣው ከሁለት እና ከሦስት ዓመታት በፊት ነው፡፡ ለሀሊማ ግን እስካሁን የትዳር ጥያቄ ያቀረበላት የለም፡፡

‹‹በአፋር የሴት ልጅ ግርዛት የተከበረ ባህል ነው፡፡ በሥራው የተሰማሩ ሰዎችም የልፋታቸውን ክፍያ አይጠይቁም፡፡ ገንዘብ መጠየቅ ነውር ነው›› የሚሉት የ32 ዓመቷ ወይዘሮ አሲያ አህመድ በአፋምቦ ወረዳ ከሚገኙ የልምድ አዋላጅና የግርዛት አገልግሎት ከሚሰጡ እናቶች መካከል ነበሩ፡፡

የተገረዘችን ሴት በተለይም ደግሞ የተሰፋችን ሴት ማዋለድ በጣም ከባድ መሆኑን ፣ ምንም እንኳ እናቲቱ የፈለገ ብታምጥ ማህፀኗ ጠባብ በመሆኑ ልጁ እንዳይወጣ እንደሚያደርገው ፣ ብዙጊዜም ማህፀኗን በሴንጢ  በመቅደድ ለማስፋት ይሞክሩ እንደነበር ‹‹ካልተቀደደ አይወጣም፡፡ በምንቀድበት ጊዜ በስቃይ ብዛት የሚሞቱ ብዙ ነበሩ›› ሲሉ የልምድ አዋላጅ ሆነው በሰሩባቸው ጊዜያት ያጋጥማቸው የነበረውን አስታውሰዋል፡፡

ወ/ሮ አሲያ በተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናዎችን በመከታተላቸው የግርዛትን አስከፊነት ተረድተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የተባበሩት መንግሥታት የሥነ ሕዝብ ፈንድ (ዩኤንኤፍፒኤን) አለ እድሜ ጋብቻና የሴትን ልጅ ግርዛት ለማስቀረት ቀርፆ እየተገበረ  ባለው  ፕሮጀክት ታቅፈው ስለግርዛትና ስለ አለ እድሜ ገብቻ አስከፊነት እያስተማሩ ይገኛሉ፡፡

‹‹ግርዛት ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ ባህላችን ነው፣ ሃይማኖታችን ያዘናል ያልተገረዘች ሴትን የሚያገባ የለም የሚል እምነት በመኖሩ የቱንም ያህል ቢሰራ ግርዛት እስካሁን ከክልሉ ሊጠፋ አልቻለም›› የሚሉት በክልሉ ሴቶች ሕፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ የፕሮጀክቱ ተባባሪ ወይዘሮ ሣራ መሐመድ ናቸው፡፡

እንደ እሳቸው ገለፃ፣ በክልሉ ያለዕድሜ ጋብቻና የሴት ልጅ ግርዛት ሥር የሰደዱ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ናቸው፡፡ በርካታ እናቶችን ለፌስቱላና ለሞትም ዳርጓል፡፡ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ቀርፆ በመተግበር መልካም የሚባል ለውጥ ማምጣት ተችሏል፡፡ ራሱን የቻለ ህግ በማውጣትም ድረጊቱን በወንጀል የሚያሲቀጣ ማድረግ ተችሏል፡፡ ይሁንና ተመሳሳይ ፕሮጀክቶች በተወሰኑ አካባቢዎች ላይ ብቻ የተተገበሩ በመሆናቸው የተገኘው ለውጥ ክልሉን አይወክልም፡፡

‹‹አንድን አካባቢ ብቻ አፅድቶ ሌላውን መተው ዋጋ የለውም፡፡ ምክንያቱም ከአንዱ  ወረዳ ወደሌላው መልሶ ይስፋፋል፡፡ በአንድ ወረዳም እንደዚህ ዓይነት ሁኔታ አጋጥሞናል፤›› ሲሉ በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች ፕሮጀክቶች ተግባራዊ ተደርገው ጥሩ ውጤት ከተመዘገበ በኋላ የሚመለከታቸው አካላት አስፈላጊውን ክትትል እንዲያደርጉ ፣ካልሆነ ግን  የተለፋውን ልፋት ውጤት አልባ እንደሚያደርገው ተናግረዋል፡፡

ዩኤንኤፍፒኤ በአፋር ክልል በአፋምቦ በሚገኙ በሦስት ቀበሌዎች ላይ ባለፉት ሦስት ዓመታት ሲተገበር በቆየው የሕፃናት ጋብቻና የሴት ልጅ ግርዛት የማቆም ፕሮጀክት የተገኘው አበረታች ውጤት ሐምሌ 30 ቀን 2008 ዓ.ም. ይፋ አድርጎ ነበር፡፡ ፕሮጀክቱ ተግባራዊ በተደረገባቸው በአፋምቦና በሌሎች አምስት ወረዳዎች ላይ 10,000 የሚሆኑ ሴቶችን ከግርዛት መታደግ መቻሉም ይፋ ተደርጓል፡፡ በአፋምቦ ወረዳ ውስጥ የሚገኙ 3 ቀበሌዎችም ከእነዚህ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ነፃ መሆናቸውን አውጀዋል፡፡ ይሁንና ቀበሌዎቹ ነፃ ሆነዋል ተብሎ መረሳት እንደሌለባቸው፣ክትትል እንደሚያስፈልጋቸው ወይዘሮ ሳራ ተናግረዋል፡፡