Monday, 26 September 2016 00:00
Written by  አለማየሁ አንበሴ

ለፖለቲካዊ ችግሮች - ፖለቲካዊ ውይይት

 በአገሪቱ ለተፈጠረው የፖለቲካ ቀውስ ምሁራን፣ ፖለቲከኞች፣ ዕውቅ ግለሰቦችና የአገር ሽማግሌዎች የመፍትሄ ሃሳብ የሚሉትን መሰንዘራቸውን ቀጥለዋል።

ሃሳባቸው ጆሮ አግኝቷል ወይ ለሚለው እርግጠኛ መልስ መስጠት አይቻልም፡፡ ውጤቱን በሂደት የምናየው ይሆናል፡፡ አንድ ነገር ግን በእርግጠኝነት መናገር
ይቻላል፡፡ የመፍትሄ ሃሳቦቹ አሁንም መቀጠል አለባቸው፡፡ መንግስት በአዲሱ ዓመት አገርን ወደ ሰላምና መረጋጋት የሚያመጣ የመፍትሄ ሃሳብ ላይ ይደርሳል
ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፤ ወጣት ፖለቲከኞችንና ጦማሪያንን በወቅታዊ የፖለቲካ ችግሮችና መፍትሄ ዙሪያ
አስተያየታቸውን አጠናቅሯል፡፡
የዚህ ውይይት ዓላማ፣ በአገሪቱ ወቅታዊ የፖለቲካ ችግሮች ዙሪያ ሃሳቦችን በማንሸራሸር መፍትሄ ማፈላለግና መጠቆም ነው፡፡ በአገራችን ለተከሰተው ወቅታዊ
የፖለቲካ ቀውስ መፍትሄ የሚሆን ሃሳብ ወይም አስተያየት አለን ለምትሉ ወገኖች መድረኩ ሁሌም ክፍት ነው፡፡

‹‹ውክልና ያጣ ህዝብ
የራሱን ጥያቄ ይዞ አደባባይ
ይወጣል”
ዳንኤል ተፈራ
(የ‹‹አንድነት” የቀድሞ የድርጅት ጉዳይ ሃላፊ

የችግሩ ዋናው መንስኤ አሁን ያለው ትውልድ የሚፈልገው ስርአት አለመፈጠሩ ነው፡፡ ይህ ማለት ዘመኑ የሚፈልጋቸው የዲሞክራሲ ተቋማት አለመኖር ወይም ልፍስፍስ መሆን ነው፡፡  ህዝቡ ዲሞክራሲን እንዲለማመድና የዚያ ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተቋማት በሃገራችን የሉም፡፡ ለምሳሌ ሚዲያ አሁን አለ የሚያስብል ደረጃ ላይ አይደለም። የሲቪክ ተቋማት ነፃ አለመሆን፣ ሃሳብን እንደፈለጉ ለማንሸራሸር አለመቻሉና በአጠቃላይ ፀረ-ዲሞክራሲ ባህሪ በመኖሩ የተፈጠረ ችግር ነው። ስርአቱ ለነዚህ ችግሮችና የህዝቡ ብሶቶች ጆሮ አልባ ሳይሆን ከስር ከስር ለሚነሱ ጥያቄዎች መልስ ቢሰጥ ኖሮ የከፋ ችግር ላይ አይወድቅም ነበር፡፡
ተቃዋሚ ፓርቲ የአሯሯጭነት ሚና ብቻ እንዲወጡ መፈለጉና ከዚህ ያፈነገጡ መታፈናቸው ሌላው ችግር ነው፡፡ ውክልና ያጣ ህዝብ ደግሞ አሁን በምናየው መልክ የራሱን ጥያቄ ይዞ አደባባይ ይወጣል፡፡ ስለዚህ ተቃዋሚ ፓርቲ ላይ የተፈፀመው የማጥፋት ዘመቻ ህዝባዊ ንቅናቄ እንዲፈጠር ካደረጉ ምክንያቶች አንዱ ነው፡፡ መንግስት የወሰደው አቋም፣ ችግርን በችግር የመፍታት አይነት ነው፡፡ ህዝቡ ጥያቄውን ወደ አደባባይ ይዞ ወጥቷል፣ መንግስት ደግሞ ያንን ጥያቄ በመመለስ ፈንታ ሌላ ችግር ነው የፈጠረው፡፡ ፈጽሞ ሀላፊነት የጎደለው ነገር ነው ያደረገው፡፡ የህዝብን ጥያቄ መረዳት የሚችልና አጥጋቢ መልስ የሚሰጥ ተቋም ያስፈልግ ነበር፤ ነገር ግን ገዥው ፓርቲ ጥያቄዎች ሲነሱ መፍትሄው ጉልበት ነው፡፡ ይሄ አግባብ አይደለም፡፡ በዚህ ዘመን ጥያቄ ያቀረበ አንድም ሰው ሊገደል አይገባም፡፡
‹‹መታደስ” የሚል የውስጥ የፓርቲ ጨዋታ ለችግሮቹ መፍትሄ የሚሆን አይመስለኝም፡፡ ይልቅ ሁሉንም ባለድርሻዎች፡- ምሁራኑን፣ ፖለቲከኛውን ተሰሚነት ያላቸው ግለሰቦችንና ሌሎችን ያካተተ ሪፎርም (ልዋጤ) ነው መካሄድ ያለበት፡፡ የችግሩ ፈጣሪ የሆነ አካል ልታደስ ነው ሲል  ቀልድ ነው የሚሆነው፡፡ ቁርጠኝነት ያለው ለውጥ ያስፈልጋል። ሌላው አፋኝ የሆኑ የሚዲያ ህግ፣ የሲቪል ተቋማት አዋጅና ህጎችን ፓርላማው በድጋሚ ለመረምር ይገባል፡፡ እውነተኛ ዲሞክራሲ ለማስፈን ቁርጠኛ መሆን ያስፈልጋል፡፡
ተቃውሞ ለወጣ ህዝብ መሣሪያ ሳይሆን መፍትሄ ይዞ መቅረብ ነው የሚሻለው፡፡ በፖለቲካ አቋማቸው የታሰሩ ሁሉንም አካላት ያለ ቅድመ ሁኔታ መፍታትም የመፍትሄው አካል ነው፡፡
=============================
‹‹አገር ትበታተናለች የሚለውን ስጋት አልጋራም››
ጦማሪ አቤል ዋበላ

እንደ አንድ ወጣት ሁሉንም እንቅስቃሴዎች እከታተላለሁ፡፡ እንደሚታወቀው ከምርጫ 97 በኋላ ብዙ ህጎች ወጥተዋል፡፡ ሚዲያውን የሲቪል ማህበረሰቡን የማያንቀሳቅሱና የፀረ- ሽብር አዋጁን የመሳሰሉ የህዝብ ድምጽን የሚያፍኑ አዋጆች ወጥተዋል፡፡ አሁን የምናያቸው ተቃውሞዎች የዚህ አፈና ውጤቶች ናቸው፡፡
ህዝብ ተስፋ ቆርጧል፡፡ መንግስት ያለውን ቅቡልነት አጥቷል፡፡ ስለዚህ ህብረተሰቡ ተቃውሞውን እያካሄደ ነው፡፡ አማራው፣ አሮሞው እንዲሁም የሙስሊም ማህበረሰቡ ወደ ተቃውሞ እንዲገቡ ያደረጋቸው ህዝቡ እንደ ህዝብ የሚያቀርባቸው ጥያቄዎች ተቀባይነት በማጣታቸው ነው፡፡ ገዥው ፓርቲ የቸልተኛነቱን ውጤት እያየው ነው፡፡ ራሱም ችግር እንዳለበት እየተናገረ ነው፡፡ ለውጥ መምጣት አለበት፡፡ አሁን ግን በመሠረታዊነት እየቀረበ ያለው ጥያቄ፣ ገዥው ፓርቲ የዚህ ለውጥ አካል መሆን ይፈልጋል ወይ? የሚለው ነው፡፡ ይሄ የእነሱን ውሣኔ ይፈልጋል። አሁን በጀመሩት መልኩ ተሃድሶ በሚሉት ለውጥ ይመጣል፣ እንቅስቃሴዎቹም  ይገታሉ ብዬ አላምንም። መንግስት እየወሰደው ባለው የሃይል እርምጃ ህዝቡ በህይወትም በንብረትም ዋጋ እየከፈለ ነው፡፡ ተማሪዎች ትምህርታቸው እየተስተጓጎለ፣ ነጋዴዎች ንግዳቸው እየተሰናከለ ብዙ ችግር እየደረሰ ነው። አሁን ከገዢው ፓርቲ የሚጠበቀው ወደ ለውጡ ቁርጠኛ ሆኖ መምጣት ነው፡፡ ጥገናዊ ለውጦች ለህዝቡ ምላሽ ይሆናሉ ብዬ አላስብም፡፡
እኔ አሁን ባለው ሁኔታ ሃገር ትበታተናለች የሚለውን ስጋት አልጋራም፡፡ ማህበረሰቡም ጠንቃቃ ነው፡፡ የገዥውን ፓርቲ ዝርክርክነት አይቼ፣ ህብረተሰቡን ወርጄ ሳየው የተለየ ነገር ነው የማስተውለው፡፡ የህብረተሰቡ ሰብዕና በመተባበር ላይ የተመሰረት ስለሆነ ሃገሪቱ ትበታተናለች የሚለው ጉዳይ አያሰጋኝም፤ ነገር ግን ለውጡ የማይቀር ነው። ግን የሚያሳስበው የሚከፈለው የህይወት ዋጋ ነው፡፡ መስዋዕትነቱ  በተቻለ መጠን መቀነስ አለበት፡፡ ለዚያ ደግሞ የግድ ገዢው ፓርቲ በዚህ የለውጥ ሂደት ውስጥ መሳተፍ ይኖርበታል። ሃላፊነት ተሠምቷቸው በጥንቃቄ ሁሉንም አካላት ያሳተፈ የለውጥ ፎረም ማለትም በሃገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያሉ ተቃዋሚዎች፣ በየዘርፉ ያሉ ተሠሚነት ያላቸው ግለሰቦች፣ የሲቪል ተቋማት የሚሳተፉበት ፎረም መካሄድ አለበት፡፡ ኢትዮጵያ የታላላቅ ሰዎች ሃገር ነች፡፡ ሁሉም ሰው እድሉ ሊሰጠውና በአንድ መድረክ ስለ ሃገሩ መክሮ ባለ አደራ መንግስት ማቋቋም አለበት፡፡ የሚቋቋመው ባለ አደራ መንግስት ለገዠው ፓርቲ ዋስትና መስጠት አለበት፡፡ በጣም የተደራጀ ወንጀል የሌለባቸው የገዢው ፓርቲ አመራሮች ዋስትና ሊሠጣቸው ይገባል፡፡ የኢኮኖሚ ጥቅሞቻቸው ባሉበት ሆነው፣ሁሉም አካል ዋስትና አግኝቶ የለውጡ አካል ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ጥቅምን ማሣጣት ወደ ሌላ ትርምስ ያመራል፡፡ የባለ አደራ መንግስቱ ከተቋቋመ በኋላ ቅራኔዎቹ በእርቅ ተፈተው፣ ዘላቂው መንግስት የሚቋቋምበት ሁኔታ መመቻቸት ያለበት ይመስለኛል፡፡
=============================
‹‹ስር ነቀል ለውጥ ያስፈልጋል”
ጦማሪ በፍቃዱ ሃይሉ
ተቃውሞዎች በኦሮሚያና በአማራ ክልል የበረቱበት የራሱ መነሻ ምክንያት አለው፡፡ እየተጠራቀሙ የመጡ ብዙ ችግሮች አሉ፡፡ እነዚህ ችግሮች ናቸው ዛሬ የፈነዱት። የማህበረሰቡ ወኪል የሆኑት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጥያቄ ሲያነሱ፣ ገዥው ፓርቲ ብሶቶችን ላለመስማት ‹‹የትምክህትና የጠባብ ኃይሎች” በሚል ሲፈርጅ ስለነበር ነው ዛሬ የተቃውሞ ቋት የገነፈለው፡፡
በስልጣን ላይ ያለው የመንግስት ስብስብ ልሂቃን፣ በጣም በሙስና የተዘፈቁ ናቸው የሚል እምነት አለኝ። አብዛኞቹ በብቃት ሳይሆን በትጥቅ ትግል ስለመጡ ብቻ ስልጣኑን ያገኙ ናቸው፡፡ ከዚያ በኋላ የመጡትም በብቃት ሳይሆን በፖለቲካ ታማኝነት ስልጣን ላይ የወጡ ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች ስራውን መስራት ስላልቻሉ ነው ሁሉም ነገር ከመሻሻል ይልቅ  እየተባባሰ አረንቋ ውስጥ የተዘፈቀው፡፡ ህዝባዊ ተቃውሞው ለምን ተነሳ የሚለውን  ጉዳይ እንኳ በአግባቡ መርምረው ምላሽ መስጠት ያልቻሉት ለዚህ ነው፡፡ የሚሰጡት ምላሽ እርስ በእርሱ የተምታታ ነው፡፡ አንዴ የመልካም አስተዳደር ችግር ነው ይላሉ፡፡ ሌላ ጊዜ ደግሞ የውጭ ኃይሎች ላይ ማሳበብና ጉዳዩን ወደ ውጪ ገፍቶ ሌላ አካል ላይ የመለጠፍ አይነት ነገር ይታያል። ይሄን ስመለከት መንግስት ችግሮቹን ለመፍታት አቅሙም ፍላጎቱም የለውም የሚል ድምዳሜ ላይ ያደርሰኛል፡፡
መፍትሄውን ብዙዎች እየጠቆሙ ነው፡፡ ለውጡ ስር ነቀል መሆን አለበት፡፡ ይህ ለውጥ እንዲመጣ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በባለቤትነት የሚሳተፍበት ገለልተኛ መድረክ መፈጠር አለበት፡፡ ያንን ገለልተኛ አካል ለመፍጠር በመጀመሪያ ደረጃ ጥያቄ በማንሳታቸው ብቻ የተገለሉ ወገኖች እድሉን ማግኘት አለባቸው፡፡ በፖለቲካ አመለካከታቸው የታሰሩትን መፍታት፣ ከሀገር የተሰደዱ ዜጎች ሙሉ ዋስትና ተሰጥቷቸው ወደ ሀገር ተመልሰው የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ ዕድሉን ማመቻቸት ያስፈልጋል፡፡ ይሄኛው አሸባሪ ነው፤ያኛው ትምክህተኛ ነው የሚለው ፍረጃ መቆም አለበት፡፡ በቀጣይም የሽግግር መንግስት የሚመሰረትበትን ውይይት ማድረግና ገለልተኛ ምርጫ ቦርድ ማቋቋም ወሳኝ ነው፡፡ ከውጭ ሀገራት ዕውቀት ያላቸው ኢትዮጵያውያንን አስመጥቶ በነሱ አማካይነት አንድ የመሸጋገሪያ ምርጫ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ እነዚህ ለውጦች ካልተተገበሩ አመፆች ለጊዜው ይታፈናሉ፤ነ ገር ግን ዘላቂ መፍትሄ አይገኝም፡፡
============================
“መንግስት ሚዲያዎችና ኪነ-
ጥበቡን ነፃ ማድረግ አለበት”
ቢኒያም ወርቁ (የፊልምና የቴአትር ባለሙያ)
የአገራችን ወቅታዊ ችግርና የምናየው የምንሰማው ነገር በጣም አሳሳቢ ነው፡፡ ጉዳዩ ብዙ ነገሮችን እንድናስብ ያደርገናል፡፡ ለምሳሌ በዚህ በዘረኝነት ጉዳይ ላይ በግልጽ እያየነው ያለው ነገር በጣም አስቸጋሪና አሳሳቢ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ ምንም እንኳን የፖለቲካ ሰው ባልሆንም እንደ ኪነ-ጥበብ ባለሙያነቴ ነገሮችን ስመለከት፣ ችግሩን የወለደው በነፃነት የመናገር መብት አለመከበር ነው። በነፃነት መነጋገር መወያየት ቢለመድ፣ የሚዲያና የኪነ-ጥበብ ነፃነት ቢኖር አሁን ያለንበት ችግር ላይ አንደርስም ነበር፡፡ በኪነ-ጥበቡ፣ በሚዲያውና በአጠቃላይ ማህበረሰቡ ላይ ያለው ሀሳብን በነፃነት የመግለፅና የመናገር አፈና ችግሩን ወልዶታል ባይ ነኝ፡፡
በአጠቃላይ በአሁኑ ወቅት ከየአቅጣጫው የሚሰማውና እየሆነ ያለው ነገር አገርን የሚገነባ ሳይሆን የሚያፈርስ ነው፡፡ ወደ አንድነት የሚያመጣ ሳይሆን ወደ መለያየት የሚወስድ ነው፡፡ ይሄ እንደ ማንኛውም ዜጋ ያሳስበኛል፡፡ ህዝብ ጥያቄ ሲያነሳ በጥይት መትቶ የሚገድል ወታደርም፣በዘረኝነት ጥላቻ ተተብትቦ ጎረቤቱን የሚያጠቃ ሰውም ለእኔ አንድ ናቸው፡፡ በሌላ በኩል በህዝብም በመንግስትም በኩል ትልቅ የስነ-ምግባር ችግር አያለሁ፡፡ ሰው በሰውነቱ መከበር አለበት ሲባል ከእነ ሀሳቡ ነው የሚከበረው፡፡ ሀሳብ የሌለው ሰው ደግሞ ሰው አይደለም ማለት ነው፡፡ የሰዎችን ሀሳብ ያለማክበር፣ ጥያቄን ተቀብሎ መልስ ያለመስጠት፣በመንግስት በኩል ያለ የስነምግባር ችግር ነው፡፡ የሚጠየቀው ጥያቄ ሌላ፣ የሚመለሰው ሌላ፡፡
ሌላው ሰዎች ባላቸው አመለካከትና በፖለቲካ አቋማቸው እንዲፈሩና እንዲሸማቀቁ ማድረግ ምን ማለት ነው? ይሄ እጅግ አሳሳቢ ነው፡፡ በህዝብ በኩል የስነ ምግባር ጉድለት የምለው ለምሳሌ አንድ ክልል ውስጥ የሚኖሩ የሌላ ክልል ተወላጆች በወገኖቻቸው ይባረራሉ ይፈናቀላሉ፡፡ ይሄ ማለት የስነ ምግባር ችግር ነው፡፡ ወንድም ወንዱም ማባረርና ማፈናቀል የለበትም፡፡ ይሄ ሁሉ ያሳስባል፡፡ ትልቁን የአገር ታሪክ ትተን የምናነሳቸው ጥያቄዎች ያንሱብኛል፡፡
በአጠቃላይ ይበጃል የምለው፣ መወያየትን ባህል ማድረግ ሲሆን በነፃነት እንድንወያይም መንግስት መፍቀድ አለበት፡፡ መፍቀድ ብቻ ሳይሆን የምንወያይበትን መድረክ ሁሉ ማመቻቸት አለበት። መመቻቸት ካለባቸው መድረኮች አንዱና ዋነኛው ደግሞ ሚዲያ ነው፡- ሬዲዮ፣ ጋዜጣ፣ ቴሌቪዥን—–የህዝብ መወያያ መድረክ መሆን አለባቸው፡፡ አሁን ያሉት ውስን ሚዲያዎች ናቸው፡፡ በየሬዲዮው ኳስና መዝናኛ ነገሮች ብቻ ነው የምንሰማው፡፡ ጋዜጣማ ሊጠፋ ምንም አልቀረውም፡፡ ከ10 እና ከ15 ዓመት በፊት የነበረውን ሚዲያና አሁን ያለውን እንኳን ብናወዳድር፣ አሁን ምንም የለም ማለት ይቻላል፡፡ ከነፃነት እጦት ጋር እየተመናመነ መምጣቱ እሙን ነው፡፡ አሁን ለተፈጠረው ችግር፣ ጋዜጠኞች ቦታው ድረስ ሄደው ለመዘገብ እንኳን አልቻሉም፡፡ ህዝቡም ወጥቶ ሀሳቡን ለመግለፅ ይፈራል፤ይሸማቀቃል፡፡ ይሄ መቅረት አለበት፡፡
ይሄን ሁሉ ነፃነት ባጣ ቁጥር ህዝቡ ወደ አመፅና ንብረት ወደ ማውደም ይገባል፡፡ ህዝቡ በነፃነት የመናገር መብቱ ተከብሮለት ቢሆን ኖሮ፣ መንግስት ከራሱ አቋም የተለዩ ሃሳቦችን መስማት ለምዶ ቢሆን፣ አሁን ላለንበት ችግር አንደርስም ነበር፡፡ ችግሩ ቢከሰት እንኳን በለመድነው የንግግር ባህል መፍታት እንችል ነበር፡፡ በጥይት የሰው ህይወት አያልፍም፤ ንብረትም አይወድምም ነበር። ስለዚህ መንግስት የመናገር ነፃነትን መፍቀድ፣ የተለዩ ሀሳቦችን ማዳመጥና ምላሽ መስጠት፣ የህዝቡ የውይይት መድረክ የሆኑትን ሚዲያዎችና ኪነ-ጥበቡን ነፃ ማድረግ አለበት፡፡
=============================
“ችግሮች በሰለጠነ መንገድ መፈታት አለባቸው”
ዳዊት ይፍሩ (የሙዚቃ ባለሙያ)
እኔ እንግዲህ ፖለቲከኛ አይደለሁም፤የሙዚቃ ባለሙያ ነኝ፡፡ በተለይ የእኛ የሙዚቀኞች ማህበርና አባላት በፖለቲካ፣ በዘርና በሃይማኖት ጉዳዮች ላይ መሳተፍ አንችልም፤ሙያችንም አይፈቅድም። በአገሪቱ ላይ የተከሰተው የወቅቱ ችግር ግን ሁሉንም ኢትዮጵያዊ የሚመለከት ነው፡፡ በኪነ ጥበብ ውስጥ ያለን ሰዎች ደግሞ ከምንም በላይ ሰላምን እንናፍቃለን፡፡ ምክንያቱም ሰላም ከሌለ ኪነ-ጥበብ ትርጉም አይኖረውም፡፡ ኪነ-ጥበብ ደግሞ ፕሮሞት የሚያደርገው ፍቅርን፣ ሰላምን፣ አንድነትንና እኩልነትን ስለሆነ ሰላም ሲደፈርስ የፈጠራ ስራም አይኖርም፤ቢኖርም ሰላም ከሌለ የትም ለማንም አናቀርበውም፡፡ በፈጠራ ስራችንም ተጠቃሚ አንሆንም፡፡ ይሄ ደግሞ ህብረተሰቡንም አገሪቱንም ይጎዳል፡፡ በመሆኑም አገሪቱ ላይ የተከሰተው ችግር እንደ አርቲስትነቴም የህብረተሰቡ አካል እንደመሆኔም ያሳስበኛል፡፡
ሰላም ሰፍኖ አገሪቱ ወደቀድሞ ሰላሟ እንድትመለስ እመኛለሁ፡፡ በአሁኑ ወቅት ህዝቡ የመብት ጥያቄ እያነሳ ነው፤ይሄ ደግሞ መብት ነው፡፡ መብቱን የሚጠይቅን ሰው ተኩሶ መግደል በየትኛውም መልኩ አግባብ አይደለም፡፡ በሰላማዊ መንገድ ጥያቄ ያቀረበ ሰው ፍትህ ማግኘት እንጂ መሞት የለበትም፤ይሄ ግልፅ ነው፡፡ ማንኛውም ሰብአዊ ፍጡር አይደግፈውም፡፡ እኔም እንደ ግለሰብ አልደግፈውም፤ አግባብም አይደለም፡፡ ጠያቂው ህዝብም፣ ተጠያቂው መንግስትም በሰላምና በውይይት ችግሮችን መፍታት አለባቸው፤ይሄ አማራጭ የሌለው መፍትሄ ነው፡፡ ሰላም በሌለበት አገር፣ መንግስትም ህዝብም ሊኖሩ አይችሉም፡፡ ስለዚህ በሁለቱም በኩል መብት መከበር አለበት፡፡ አንዱ አጥቂ ሌላው ተጠቂ ከሆነ፣ አጥቂው ማንን ነው የሚመራው?  መንግስት ለተነሱ ጥያቄዎች መልስ መስጠት አለበት፡፡ ከህዝቡ ጋር በመወያየት አገሪቱ ወደ ሰላም መምጣት አለባት፡፡ አሁን የስልጣኔ ዘመን ስለሆነ ከዘመኑ ጋር መጓዝና ስልጣኔን መልመድ አለብን እላለሁ፡፡
=============================
“የርዕዮተ ዓለምም ሆነ የፖሊሲ ጥገናዊ ለውጥ መኖር አለበት”
ዳንኤል ብርሃነ (ጦማሪ)
የችግሩ መነሻ ምክንያት የብሄርተኝነትና የኢኮኖሚያዊ ችግር ቅልቅል ነው፡፡ የብሄርተኝነቱና ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም አስተዳደራዊ ችግሮች ተደበላልቀው የፈጠሩት ችግር ነው፡፡ የፖለቲካ ችግሮችን ሃላፊነት በተሞላው መልኩ ተንትነው የሚያቀርቡ አካላት አለመኖራቸው አንዱ ችግር ነው፡፡ የጎንደር የኢኮኖሚ እድገት የሚጎተተው በዚህ ምክንያት ነው ወይም የአምቦ ኢኮኖሚ የተጠበቀውን ያክል ያላደገው በዚህ ምክንያት ነው ብሎ የሚተነትን አካል ባለመኖሩ ቀላሉ ችግር ይወሳሰባል፡፡ የኛ የብሄር ተወላጅ እዚህ ቦታ ላይ ባለመኖሩ ነው እንዲህ እየተደረግን ያለነው የሚለው አመለካከት በዚህ መነሻ ይዳብርና የብሄር ቅርፅ እየያዘ ይመጣል፤ከዚያም የአሁኑን አይነት ችግር ይፈጥራል፡፡
መንግስት ደግሞ ችግሩን ለመፍታት በሚያደርገው እንቅስቃሴ የመቀናጀት ችግር አለበት፡፡ ፖለቲካዊና የፀጥታውን ስራ በየራሱ መንገድ ማስኬድ አለበት፡፡ ወረዳው ከዞኑ፣ ዞኑ ከክልሉ፣ ክልሉ ከፌዴራል እየተቀናጁ ነው ችግሩን መፍታት ያለባቸው እንጂ ወረዳው ሌላ ነገር ሲል ዞኑ ሌላ እያለ መሆን የለበትም፡፡ እንዲያ ሲሆን ለችግሩ ያልሆነ ትርጉም ያሰጣል፡፡ እርግጥ ነው በአንዳንድ ቦታዎች ሃይል አስፈላጊ ነበር፤ነገር ግን ሃይል አስፈላጊ ባልሆነባቸው ቦታዎችም ያለ አግባብ የመጠቀም ችግር ነበር፡፡ ሃይል አስፈላጊ በሆነባቸው አካባቢዎችም ከሚያስፈልገው በላይ የመጠቀም ችግር የነበረ ይመስለኛል፡፡ ለአንዳንድ በቀላሉ መፍትሄ ማግኘት ለሚችሉ ችግሮች ዘግይቶ መፍትሄ የመስጠት ነገርም አለ፡፡ ይሄ የተቀናጀ አሰራር ያለመኖሩ ያመጣው ነው፡፡ ዘግይቶ መልስ እስኪሰጥ ድረስ ሌላ ጥያቄ ተወልዶ ይጠብቃል፡፡
አሁን አራቱ ድርጅቶች ተሃድሶ እያደረጉ ነው። ተሃድሶው የተሟላ እንዲሆን የርዕዮተ-አለምም ሆነ የፖሊሲ ጥገናዊ ለውጥ መደረግ አለበት፡፡ ሰው መቀየር ብቻውን መፍትሄ አይሆንም፤ነገር ግን ሰዎችም መቀየር አለባቸው፡፡ ፖለቲካ በግለሰቦች የሚዘወር ነው፡፡ ግለሰቦች ሲቀየሩ ብዙ ነገሮች ይቀየራሉ፡፡ የግለሰቦች መቀየር እጅግ አስፈላጊ ነው።
በሌላ በኩል የንግድ ማህበረሰቡ ተጠቃሚ የሚሆንበት መንገድ መፈጠር አለበት፡፡ የተወሰኑ በመንግስት የተያዙ ዘርፎች ለግል ሴክተሩ የማካፈል ነገር ቢመጣ መልካም ነው፡፡ የኢኮኖሚ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት የሚሰፋበትን መንገድ መቀየስ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ሲሆን ሌላውን ጥያቄ ለመመለስ መንግስት ፋታ ሊያገኝ ይችላል፡፡ የብሄር፣ የማንነት ጥያቄ ሁሌም የሚኖርና የማይቋረጥ ነው፡፡ በአጭር ጊዜም አይመለስም፡፡ እነዚህን በረጋ መንገድ ለመመለስ የኢኮኖሚ ሪፎርሙ አስፈላጊ ነው፡፡
ሌላው በድርጅት አባል ኮታ የሚደረግ የባለሙያ ድልድል ቀርቶ ለልሂቃን ቦታው ክፍት የሚሆንበት ሁኔታ መፈጠር አለበት፡፡ የተለያዩ ብሄሮችን የሚወክሉ ልሂቃን ሃሳብ የሚለዋወጡበት ማዕቀፍን መፍጠርም ያስፈልጋል፡፡ ይህ የፖለቲካ ምህደሩን የበለጠ ሰፋ ለማድረግ ይጠቅማል፡፡ የፌዴራሽን ም/ቤት፣የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስቴር፣ የህገ መንግስት አጣሪ ኮሚሽን በደንብ ስራቸውን እንዲሰሩ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ዋናው ቁም ነገሩ በሃገሪቱ የተለያዩ የብሄረሰብ ልሂቃን መካከል ተከታታይ የሃሳብ ልውውጥ መደረጉን ማረጋገጥ ነው፡፡ ሃገሪቱ ሊበራል ዲሞክራሲን አራመደች አላራመደች አይደለም ዋናው ጉዳይ፤ የልሂቃኑን ውይይት አስፍቶ ግጭቶች እንዳይፈጠሩ ማድረግ ላይ ነው፡፡ የኢኮኖሚው ማሻሻያ ግን አስፈላጊ ነው፡፡ ወሳኝ የኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይም ባለሙያዎች የላቀውን የሃላፊነት ድርሻ መያዝ አለባቸው፡፡

አዲስ አድማስ

Leave a Reply