Monday, 26 September 2016 00:00
Written by  አለማየሁ አንበሴ

“ኢህአዴግ ብቻውን ምንም ተዓምር አይፈጥርም”

– በየትም ሀገር ቋንቋን መሰረት ያደረገ ፌደራሊዝም አይመሰረትም
– መንግስት “ችግሩን የፈጠረው የኔ ፖሊሲ ነው” ብሎ ማመን
አለበት
– የማንነት ጥያቄዎች የሚፈቱት ህዝብ የሚለውን
በማድመጥ ነው
– የችግሩ መፍቻ ቁልፍ ያለው በመንግስት እጅ ነው
አቶ የሸዋስ አሰፋ ከ“ቅንጅት” ጀምሮ በፖለቲካ ውስጥ ንቁ ተሳትፎ ነበራቸው፡፡ በመቀጠልም የ“አንድነት” ፓርቲ አመራር አባል፣ ከዚያም
“ሰማያዊ” ፓርቲን በማደራጀትና በመመስረት እንዲሁም ፓርቲውን በተለያዩ የአመራርነት ቦታዎች ያገለገሉ ሲሆን ከሁለት ዓመት በፊት
ታስረው በቅርቡ ከእስር ከተለቀቁ በኋላ ደግሞ የሰማያዊ ፓርቲ ም/ቤት ሰብሳቢ ሆነው እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ አቶ የሸዋስ በሀገሪቱ በተፈጠሩ
ተቃውሞዎች ባህሪ፣ በመንግስት ምላሽና የተሃድሶ ጉዞ እንዲሁም በመፍትሄ ሃሳቦች ላይ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር
ተከታዩን ቃለምልልስ አድርገዋል፡፡

ለህዝባዊ ተቃውሞና አመጹ መንስኤው ምንድን ነው ይላሉ?
የችግሮች ምንጭ ብዙ ቢሆኑም አሁን ለምናየው ተቃውሞ ዋናው ምንጭ ቋንቋን መሰረት ያደረገው ፌደራሊዝም ነው፡፡ እርግጥ ነው ከ20 እና 25 ዓመታት በፊት ፕ/ር አስራት ወልደየስን ጨምሮ በርካታ ምሁራን ይህ ችግር ሊመጣ እንደሚችል ተንብየው ነበር፡፡ ያ ትንበያ ነው አሁን በኦሮሚያም፣ በኮንሶም፣ በአማራ ክልልም የምናየው፡፡ ዛሬ ዝም ያሉ ሌሎች አካባቢዎችም ጥያቄዎች ያሉባቸው ናቸው፡፡ ሁለተኛው የዚህ ችግር መንስኤ በምርጫ ላይ የሚደረገው ቀልድ ነው፡፡ 96 በመቶ፣ መቶ በመቶ አሸንፌያለሁ እየተባለ መነገሩ፣ ቀጥሎ ምን ያመጣል ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ የታመቀ ነገር ምን ያመጣል ማለት ተገቢ ነው፡፡ እውቀት እየመራን አለመሆኑ ይህ ማሳያ ነው፡፡ አሁን የምናየው እንግዲህ እነዚህ ያመጡት ችግሮች ናቸው፡፡ በየትም ሀገር ቋንቋን መሰረት ያደረገ ፌደራሊዝም አይመሰረትም፡፡ የውጭም የሀገር ውስጥም ምሁራን በወቅቱ ይህ የፌደራል አደረጃጀት ሲዋቀር፣ ዛሬ ላይ እየደረሰ ያለውን ችግር እየተነበዩ ባገኙት አጋጣሚ ሲያስጠነቅቁና ሲያሳስቡ ነበር፤ ሰሚ አላገኙም እንጂ፡፡
መንግስት የችግሩን ቁልፍ አግኝቶ መፍትሄ እያበጀ ነው ብለው ያስባሉ?
መንግስት የችግሩን መነሻ በትክክል አግኝቶ ወደ መፍትሄ እየሄደ ያለ አይመስለኝም፡፡ ማንኛውም ችግር ዋና ምክንያት ከጀርባ አድርጎ የመቀስቀሻ ምክንያት ደግሞ አለው፡፡ ለምሳሌ ከማስተር ፕላኑ በፊት በኦሮሚያ ውስጥ ተቃውሞ የለም ማለት አይደለም፡፡ በአማራ ክልል ውስጥም ከወልቃይት በፊት ችግር የለም ማለት አይደለም … ወልቃይት መነሻ ሆነ እንጂ፡፡ ስለዚህ መንግስት ችግሩን በሚገባ አላገኘውም፡፡ መንግስት “ችግሩን የፈጠረው የኔ ፖሊሲ ነው” ብሎ ማመንና ለውይይት መቀመጥ አለበት፡፡ በአሁን ሰአት መቶ በመቶ የችግሩ መፍቻ ቁልፍ ያለው በመንግስት እጅ ነው፡፡ አሁን ለምሳሌ መንግስት አወያያለሁ ብሎ ነበር፤ነገር ግን የተቃወሙ ሰዎች በኦሮሚያና በባህርዳር፣ በጎንደር፣ በኮንሶ እየታሰሩ ነው፡፡ ይሄ ነው የችግሩን ቁልፍ አግኝቷል ለማለት እንዳንደፍር የሚያደርገን፡፡ እንደውም የሚወስዳቸው እርምጃዎች ነገሮችን የሚያባብሱ ናቸው፡፡
መንግስት ጥልቅ ተሃድሶ አድርጌ ችግሩን እፈታለሁ ብሏል … ሰሞኑንም የባለስልጣናት ሹምሽር እየተካሄደ ነው … ተሃድሶው መሰረታዊ ለውጥ ያመጣል ብለው ያምናሉ?
በፍፁም ለውጥ አያመጣም፡፡ አንድ ፓርቲ ብቻውን ምንም አይፈጥርም፡፡ ይሄን ጥያቄ ካነሳው ህዝብ ምን ሃሳብ ወሰደና ነው እታደሳለሁ የሚለው? አሁን በዝግ አብረው እየመከሩ ያሉት ሰዎች እኮ ለዓመታት አብረው ሲመክሩ የነበሩ የሚተዋወቁ ሰዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች ምን አዲስ ተአምር ይፈጥራሉ? ሰዎቹ ቢለዋወጡ ፖሊሲው አንድ ነው።  ስለዚህ የሰው መለዋወጥ ምንም አይፈይድም። መጀመሪያ ህዝብን ማወያየት ያስፈልጋል፡፡ በዩኒቨርሲቲ የሚደረጉ ስብሰባዎች ላይ የሚነሱ ሃሳቦችን እንሰማለን፡፡ አሁንም ይሄ ፌደራሊዝም ስጋት መሆኑ እየተነገረ ነው፡፡ እንደመታደል ሆኖ የባለዕውቀቶች ችግር የለብንም፤ እንዳለመታደል ሆኖ ግን ይሄን እውቀት አንጠቀምበትም፡፡ ይሄን ችግር ሊፈቱ የሚችሉ፤ ወደ ሰላምና እርቅ ሊመሩን የሚችሉ የእውቀት ባለቤቶች ሞልተውናል፡፡ ከነሱ ጋር መነጋገር ያስፈልጋል፡፡
ኢህአዴግ ሥልጣን ቢለቅ የሚረከብ የተደራጀ ጠንካራ ፓርቲ የለም የሚል ስጋት አለ፡፡ ይሄን ስጋት እርስዎ ይጋሩታል?
አማራጭ እንዳይኖር ያደረገው ራሱ ገዥው ፓርቲ ነው፡፡ እኛ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ነን፤ ሃሳብ አለን፤ ሃሳብ ሳይኖረን አንሰባሰብም፡፡ በዚያ ሃሳብ ዙሪያ የተሰበሰበ ሰው የራሱ መፍትሄ አለው። መምራት ይችላል፡፡ ቅንጅት ተቃዋሚ የለም በተባለበት ወቅት ነው እነዚያን የመሠሉ ሰዎች አመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ያሰባሰበው፡፡
ስለዚህ እዚህ ሃገር ውስጥ እውቀት ያላቸው ሰዎች ችግር የለብንም። የግዴታ ተቃዋሚ መሆን አይጠበቅበትም፡፡ በመንግስት ውስጥም ጥሩ እውቀት ያላቸው ቀና ሰዎች አሉ፡፡ ለጉልበት ሳይሆን ለእውቀት ቅድሚያ እንስጥ የምንለው ለዚህ ነው፡፡ መንግስት ችግሩን ሊያባብሰውም ሊያስተካክለውም የሚችልበት ቁልፉ በእጁ ነው፡፡ ሃገሪቱ የሰው ድሃ አይደለችም፤ ብዙ ልሂቃን አሏት። በፓርቲ ላይደራጁ ይችላሉ፤ ግን ሃገር ለመምራት፤ ሃሳብ ለማዋጣት የግዴታ በፓርቲ መደራጀት አያስፈልግም። ተቃዋሚዎችም እንደሚባለው ሳይሆን በቂ ሃይል አላቸው፡፡ ህዝቡ ሠላምን ስለሚፈልግ ወደዚያ መሄድ አይከብደንም።
አሁን እየተነሡ ያሉት የማንነት ጥያቄዎች በምን አግባብ ነው መፈታት ያለባቸው?
በዲሞክራሲ አስተሳሰብ ነው መፈታትና መመለስ ያለባቸው፡፡ ያ ማለት ህዝብ የሚለውን ማዳመጥ ነው፡፡ ህዝብ እንዲህ ነን ካለ በቃ መብቱ ነው፤ መከልከል አይቻልም፡፡ ከብዙ አመታት በፊት ይሄን የማንነት ጉዳይ ያመጡት እንደ ሩስያ ያሉ ሃገራት፣ ልክ ጥያቄው ሲበዛባቸው፤ “የማንነት ጥያቄ መልሰን ጨርሰናል” ነው ያሉት፡፡ ነገር ግን የማንነት ጥያቄ የሚያልቅ አይደለም፡፡ በየጊዜው የሚፈጠርም ጭምር ነው፡፡ ስለዚህ ህዝቡ የሚለውን ማዳመጥና በህዝቡ ፍላጎት መፈታት አለበት፡፡
ለችግሮቹ የተለያዩ የመፍትሄ ሃሳቦች እየቀረቡ ነው፡፡ በእርስዎ በኩል አሁን ያለውን ችግር ለመፍታት የሚያስችሉ መፍትሄዎች ምንድን ናቸው ይላሉ?
የመጀመሪያው መንግስት ለይስሙላ ሳይሆን ከልቡ ችግሩን መቀበል አለበት፡፡ የተለያዩ የአገር ውስጥና አለማቀፍ ምሁራን የሚሉትን ማድመጥ ይኖርበታል፡፡ ቀጥሎ ጓዳ ውስጥ ከሚደረግ ሹክሹክታ ወጣ ብሎ ችግሩን ከሚመለከታቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር መነጋገር አለበት። የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪክስ ማህበራት፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሃገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶች አሉ፡፡ የሰው ችግር የለብንም፤ ከእነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር መወያየት ይገባዋል፡፡ ከውይይት በኋላ የመፍትሄ አማራጮች ይመጣሉ፡፡ እነዚያን በሚገባ መጠቀም ነው፡፡
የታጠቁ ሃይሎች ጭምር የያዙትን መንገድ ትተው በውይይቱ እንዲሳተፉ መጋበዝ ያስፈልጋል፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ እኮ ሠላም እስካሁን እንደናፈቀው ነው ያለው፡፡
ሙሉ ታሪካችን የጠመንጃ ነው፡፡ ስለዚህ ለሠላም ህዝቡ ማንኛውንም ነገር ይከፍላል። ውይይቶች የእውነት መሆን አላባቸው፡፡ ራሳቸው ያበላሹት ሰዎች ተወያይተው የሚያመጡት ለውጥ አይኖርም። የሚያስፈልገው መሰረታዊ ለውጥ ነው።

አዲስ አድማስ

Leave a Reply