Monday, 26 September 2016 00:00
Written by  አለማየሁ አንበሴ
          በአማራ ክልል በተለይ በጎንደርና  በባህርዳር ከተሞችና በአካባቢያቸው ባሉ ወረዳዎች ሠሞኑን ከቤት ያለመውጣት አድማ ሲደረግ መሠንበቱን የጠቆመው መኢአድ፤ በሌላ በኩል ወጣቶች በፀጥታ ሃይሎች እየተለቀሙ መታሠራቸው አስታውቋል፡፡

የፓርቲው ዋና ፀሃፊ አቶ ኪዳነ በጎንደር ከሠኞ መስከረም 9 ቀን ጀምሮ እስከ ትናንት ድረስ አንድም የንግድ ተቋም ሳይከፈት የቤት ውስጥ አድማ ሲደረግ መሰንበቱንና በደብረታቦር  ማክሰኞ አድማው የተደረገ ቢሆንም በሃይል ህዝቡ ወደ ስራ እንዲገባ ተደርጓል ብለዋል፡፡ ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ነዋሪዎችም ደብረታቦር መታሰራቸውን አስታውቀዋል፡፡ ጋይንት፣ ንፋስ መውጫ፣ ሊቦ ኮምኮምና አዲስ ዘመን በተባሉ የጎንደር ከተሞችም እስከ ትናንት ድረስ የስራ ማቆም አድማ አድርገዋል ተብሏል፡፡
ባህርዳር  እስከ ሃሙስ እለት የንግድ መደብሮች ዝግ ቢሆኑም የመንግስት መስሪያ ቤቶችና የትራንስፖርት አገልግሎት አልተቋረጡም ብለዋል ዋና ፀሃፊው፡፡ በወገራና ኮሶዬ በተባሉ ወረዳዎች ሠሞኑን የፀጥታ ሃይሎች ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር መጋጨታቸውን መኢአድ አስታውቋል፡፡ በሌላ በኩል፤ በባህርዳርና በወልቂጤ ዩኒቨርስቲዎች በተደረጉ የመምህራን ስብሰባዎች ለመንግስት ሃላፊዎች ጠንካራ ጥያቄዎች እንደቀረበላቸው መኢአድ አረጋግጫለሁ ብሏል፡፡ በኮንሶ አካባቢ የተከሰተው ቀውስ አለመረጋጋቱን የጠቆመው መኢአድ፤ በአካባቢው ሰዎች በየቀኑ እየተለዩ እየታሠሩ መሆኑን ገልጿል፡፡
በጎንደር  ከትናንት በስቲያ በከተማዋ የእሳት አደጋ ሊያደርሱ ነበር የተባሉ ከ6 በላይ ሰዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ምንጮች ለአዲስ አድማስ ጠቁመዋል፡፡ ፖሊስና የአካባቢው ማህበረሠብም ሌሎች ቀሪ ተጠርጣሪዎች አሉ በሚል እስከ ትናንት ድረስ አሰሳ ሲያካሂዱ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡

Leave a Reply