የኢትዮጵያ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ተፅዕኖዎችን ለመገምገም ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን ከዓመታት ቆይታ በኋላ የደረሱበት ስምምነት ራሱን የቻለ የጥናት ወሰን እንዳለው፣ በግብፅ ግብርና ላይ የሚኖረው ተፅዕኖ በጥናቱ እንዲካተት ግብፅ ስታደርስ የነበረው ጫና ተቀባይነት እንዳላገኘ ተገለጸ፡፡

የሦስቱ አገሮች ብሔራዊ የቴክኒክ ኮሚቴዎችና በህዳሴው ግድብ ላይ ሁለት የተፅዕኖ ግምገማ ጥናቶችን እንዲያካሂዱ የተመረጡት ሁለት የፈረንሣይ ኩባንያዎች፣ የጥናት ስምምነት መስከረም 10 ቀን 2009 ዓ.ም. በሱዳን ዋና ከተማ ካርቱም መፈራረማቸው ይታወሳል፡፡

ስምምነቱን በኢትዮጵያ በኩል የፈረሙት የኢትዮጵያ ብሔራዊ የቴክኒክ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት ኢንጂነር ጌድዮን አስፋው ሲሆኑ፣ የሦስቱም አገሮች የውኃ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስምምነቱን ታዝበዋል፡፡

የኢትዮጵያን ተደራዳሪ ቡድን በመምራት ስምምነቱን ታዝበው የተመለሱት የውኃ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትሩ አቶ ሞቱማ መቃሳ፣ ከሱዳን መልስ በቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት ስምምነቱን አስመልክቶ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

የተፅዕኖ ግምገማ ጥናቶቹ በግብፅ ግብርና ላይ ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት እንዲገመግሙ በግብፅ በኩል በተደጋጋሚ ሲቀርብ የነበረው ጥያቄ በስምምነቱ ተቀባይነት አግኝቶ እንደሆነ ሪፖርተር ላቀረበላቸው ጥያቄ፣ ‹‹ጥናቱ ወሰን አለው፡፡ የትኛውም አገር ስለጠየቀ የጥናት ወሰኑ ሊለጠጥ አይችልም፡፡ ስለዚህ ግብፅ በተደጋጋሚ ስታቀርብ የነበረው ጥያቄ የስምምነት ሒደቱን ቢያጓትተውም በመጨረሻ በጋራ ስምምነት ውድቅ ተደርጓል፤›› ብለዋል፡፡

የህዳሴው ግድብ እንደተጀመረ በኢትዮጵያ ጋባዥነት ለዓመት የዘለቀ ጥናት ያካሄደው ዓለም አቀፍ የባለሙያዎች ቡድን፣ በሦስቱ አገሮች መካከል የበለጠ መተማመንን ለመፍጠር ሁለት ጥናቶች እንዲካሄዱ በምክረ ሐሳብነት ማቅረቡ ይታወሳል፡፡

በምክረ ሐሳብነት የቀረቡት ጥናቶች የሚመለከቱት ግድቡ በሱዳንና ግብፅ ላይ የሚፈጥረው የአካባቢና ማኅበራዊ ተፅዕኖ ግምገማ አንደኛው ሲሆን፣ የግድቡ የውኃ አሞላልና አለቃቅ ሒደት ደግሞ ሁለተኛው መሆኑ ይታወቃል፡፡

እነዚህን በምክረ ሐሳብነት የቀረቡ ጥናቶች ለማጥናት ከተወዳደሩ ኩባንያዎች መካከል ቢአርኤል ኢንጂነርስ የተባለው ተቀማጭነቱ በፈረንሣይ የሆነ ዓለም አቀፍ ኩባንያ የጥናቶቹን 70 ከመቶ እንዲያከናውን፣ እንዲሁም ለአጠቃላይ ጥናቶቹ ሕጋዊ ተዋዋይ ተደርጐ መመረጡ ይታወሳል፡፡ ከዚህ ኩባንያ ጋር በመተባበር የጥናቶቹን 30 በመቶ እንዲያከናውን የተመረጠው አርቴሊያ የተባለ ተቀማጭነቱ በፈረንሣይ የሆነ ሌላ ዓለም አቀፍ ኩባንያ ነው፡፡

እነዚህ ኩባንያዎች የሚያካሂዱት የተፅዕኖ ግምገማ ግድቡ በግብፅ ግብርና ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት ሊጨምር ይገባል በማለት ግብፅ ያነሳችው ጥያቄ ለረዥም ጊዜ ሲያከራክር እንደቆየ ሚኒስትሩ አቶ ሞቱማ አስታውሰዋል፡፡

የህዳሴው ግድብ በዓባይ ወንዝ ላይ መገንባቱ በታችኛው የዓባይ ተፋሰስ የውኃ ፍሰትን በመጉዳት የተፋሰሱ ብቸኛ ተጠቃሚ በመሆን ለዘመናት በቆየችው ግብፅ የግብርና እንቅስቃሴ ላይ ጉልህ ጉዳት እንደማያደርስ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት የተለያዩ የሥራ ኃላፊዎች ለግብፅ አቻዎቻቸውም ሆነ ለተለያዩ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ሲያረጋግጡ መቆየታቸው ይታወቃል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት ይህንን አቋሙን እንደማይቀይር የሚናገሩት አቶ ሞቱማ፣ ጥናቶቹን የሚያካሂዱት ኩባንያዎች ከተፈቀደላቸው ወሰን እንደማያልፉ፣ ነገር ግን ወደፊት እንዳስፈላጊነቱ በግብፅ የግብርና ሥጋት ላይ ሦስቱ አገሮች ሊወያዩ እንደሚችሉ ጠቁመዋል፡፡

ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሀብቷ ላይ የፈለገችውን ልማት የማካሄድ መብቷ የተጠበቀ መሆኑን ያወሱት ሚኒስትሩ፣ የኢትዮጵያ ታላቁ የህዳሴ ግድብም ለኢትዮጵያውያን ካለው የላቀ የልማት ፋይዳ አንፃር የተጀመረ እንጂ በማንም ላይ ጉዳት ለማድረስ አለመሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በግድቡ ላይ የሚደረጉት እነዚህ የተፅዕኖ ግምገማ ጥናቶችም በግብፅና በሱዳን መንግሥታት ላይ መተማመንን መፍጠር ዋነኛ ዓላማ መሆኑን አስረግጠው ተናግረዋል፡፡ የጥናቶቹ ሒደት ከግንባታው ሒደት ጋር ጎን ለጎን እንደሚከናወን፣ የጥናቱ ውጤትም በግድቡ ዲዛይን ላይ የሚያስከትለው ለውጥ እንደማይኖር ተናግረዋል፡፡

ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ የሪፖርተር ምንጮች እንደገለጹት ከሆነ፣ ጥናቶቹን የሚያካሂዱት ኩባንያዎች ለጥናቶቹ አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎችን በራሳቸው መሰብሰብ የማይችሉ በመሆናቸው፣ ለጥናቶቹ አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎች በአጥኚ ኩባንያዎቹ ጥያቄ ሦስቱ አገሮች የሚያቀርቡት ስለሆነ ለሦስቱ አገሮች ቀጣይ ፈተና ይሆናል፡፡

ሦስቱ አገሮች የሚሰጡትን መረጃ በጥናቱ ለሚፈልጉት ውጤት እንዲመች አድርገው ሊያቀርቡ እንደሚችሉና በመረጃዎቹ ትክክለኝነት ላይ ሦስቱ አገሮች እንዴት ሊግባቡ ይችላሉ የሚለው ትልቅ ሥጋትን ያዘለ ጥያቄ፣ እንዲሁም ቀጣይ የውዝግብ ርዕስ ሊሆን እንደሚችል ገምተዋል፡፡

ሦስቱ አገሮች ለጥናቶቹ የሚያቀርቧቸው መረጃዎችን ትክክለኛነት እንዴት ማረጋገጥ እንደሚቻል ሪፖርተር ላቀረበላቸው ጥያቄ አቶ ሞቱማ ሲመልሱ፣ የሦስቱ አገሮች ብሔራዊ የቴክኒክ ኮሚቴዎች ከኩባንያዎቹ ጋር ጎን ለጎን በጥናቱ እንደሚተባበሩ፣ አገሮቹ የሚያቀርቧቸው መረጃዎች የየአገሮቹን ነባራዊ ሁኔታ የሚገልጽ ስለመሆኑ በጋራ ስምምነት ሳያረጋግጡ ለኩባንያዎቹ እንደማያቀርቡ አስረድተዋል፡፡ ጥናቶቹን ለማካሄድ ለኩባንያዎቹ የሁለት ወራት ቅድመ ዝግጅት ጊዜ መሰጠቱንና ጥናቶቹን ማከናወን በጀመሩ በ11 ወራት ጊዜ ውስጥ አጠናቀው እንዲያስረክቡ የጊዜ ገደብ ተወስኗል፡፡ ለኩባንያዎቹ 4.5 ሚሊዮን ዩሮ በጥቅሉ የሚከፈል ሲሆን፣ ወጪውን ሦስቱ አገሮች በእኩል ድርሻ እንደሚሸፍኑት ታውቋል፡፡