September 30, 2016

obangfeisa2

ከአንድ ወር በፊት በሪዮ ኦሎምፒክ ሁለት እጆቹን በማንሳት በኢትዮጵያ የሚፈጸመውን ግፍ የተቃወመው ፈይሣ ሌሊሣ “ሁላችንንም እንደ ኢትዮጵውያን እንድንተያይ አድርጎናል” በማለት አቶ ኦባንግ ሜቶ ገለጹ፡፡

የፈይሣን የጀግንነት ተግባር በተመለከተ አቶ ኦባንግ በሚመሩት ድርጅት ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ስም ባሰራጩት መግለጫ ላይ ነበር ይህንን ሃሳብ የገለጹት፡፡ “ኦገስት 21፤ 2016ዓም ኢትዮጵያውያን አዲስ የመንፈስ መነቃቃት ሆነላቸው” በማለት የፈይሣን አኩሪ ተግባር የገለጸው መግለጫ ይህ የኦሮሞ ወጣት ለወገኖቹ ብቻ ሳይሆን ለሁላችንም ድምጻችንን በዓለም ላይ እንዲሰማ አድርጎልናል ብሏል፡፡  ድርጊቱም የዓለምአቀፉን ሚዲያ ትኩረት በመሳብ በህወሃት የግፍ አገዛዝ ላይ ብርቱ ጡጫውን አሳርፏል፡፡

“በርግጥ ፈይሳ የኦሮሞ ሕዝብ ኩራት ነው” ያሉት አቶ ኦባንግ፤ “ነገርግን ፈይሣን በዋሽንግተን ዲሲ ላይ ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጥ በሰማሁት ጊዜ እንዲሁም በግሌ ካገኘሁት በኋላ ከብሔር ማንነቱ በላይ እጅግ ታላቅና አስደናቂ ሰው መሆኑን ለመረዳት እያለሁ” በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

“የኢትዮጵያ መንግሥት የራሱን ሕዝብ እየገደለ፣ እያሰረና እየጨቆነ ይገኛል፤ በኦሮሚያ፣ በአማራ እና በጋምቤላ ያለው ሁኔታ በጣም አሳሳቢ ነው፤ … እኔ ኦሮሞ ነኝ፤ ያደኩትም በኦሮሚያ ነው፤ የሕዝቤን ስቃይ በደንብ አውቃለሁ፤ መብታቸውን በሰላማዊ መንገድ በጠየቁ ሰልፈኞች ላይ መንግሥት ተኩስ ከፍቶ እስካሁን ከ1000 በላይ ሰዎች ሞተዋል፤ ሌሎች ደግሞ ከአገር ለቅቀው እንዲወጡ በመደረጋቸው በሊቢያ በረሃ ታርደዋል፤ ሌሎች በጣም ብዙዎች ደግሞ በሜዲተራንያን ባሕር የባህር አውሬ ሲሳይ ሆነዋል” በማለት ፈይሣ ለጋርዲያን ጋዜጣ የተናገረውን በመግለጫው ላይ ተጠቅሷል፡፡

ይህንን የፈይሣን ንግግር አቶ ኦባንግ ከራሳቸው የሕይወት ተሞክሮ ጋር አዛምደውታል፡፡ “ፈይሣ የተናገረው የራሴን ሕይወት የሚያሳይ ነው፤ ከተወለድኩበት የአኙዋክ ጎሣ በዲሴምበር 2003 ዓም 424 ወገኖቼ ከሦስት ባነሱ ቀናት ውስጥ መሬታቸውን እና የመሬት ሃብታቸውን ለመቀማት በተመኘው የህወሃት ቡድን ተጨፍጭፈዋል፤ ከዚህ አሰቃቂ ድርጊት በኋላ በሌሎች ኢትዮጵያውያን ላይ የሚደርሰውን ስመለከት የሁሉም ኢትዮጵያዊ ነጻ መውጣት እውን ካልሆነ አንድ ጎሣ ወይም ብሔር ብቻውን ነጻ መውጣት እንደማይችል፤ ይህም ደግሞ ለዘላቂ ነጻነትና ፍትሕ ወሳኝ መሆኑን ተገነዘብኩ፤ ይህም ግንዛቤዬ ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ (አኢጋን) መቋቋም በር ከፋች ሆነ፤ አኙዋኮች በመጨፍጨፍ በቀጣይ ተመሳሳይ አመለካከትን ህወሃት/ኢህአዴግ እንደሚያራምድና በሌሎች የኢትዮጵያ ወገኖች ላይ ተመሳሳይ እርምጃ እንደሚወስድ ግንዛቤ ወሰድኩ፤ ለዚህ ነው የሁሉም ነጻ መውጣት ወሳኝ መሆኑን የተረዳሁት፤ ፈይሣም እንዲሁ ህወሃት/ኢህአዴግ በፈጠረው የጎሣና የዘር ወጥመድ ውስጥ መግባት ለኢትዮጵያውያን አደገኛ ነገር መሆኑን በውል የተረዳ ነው” በማለት አቶ ኦባንግ በመግለጫው ላይ ተናግረዋል፡፡

ለማስረጃም ይህንን ጠቅሰዋል፤ ከላይ ፈይሣ መግለጫ በሰጠበት ጋዜጣ ላይ የሚከተለውን ብሎ ነበር፤ “አሁን ያለው ሁኔታ (ብሔርን እየለዩ የማጥቃት እርምጃ) በዚሁ ከቀጠለ የኢትዮጵያ ሁኔታ አደገኛ እንደሚሆን አልጠራጠርም፤ ዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ ጣልቃ በመግባት በዚያች አገር ላይ ለውጥ እንዲመጣ መርዳት አለበት፤ እኔ በግሌ ሁኔታው በዘር ላይ ወደማነጣጠር እንዳይሄድ እፈራለሁ፤ ሁኔታው ወደከፋ ደረጃ ሳይደርስ ዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ ጣልቃ መግባቱ የግድ ነው” ብሏል፡፡

“በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ውስጥ የጠፋው ነገር ሰብዓዊነት ነው፤ በፊታችን የተጋረጠው ጦርነት እንደ እውነት የተዘራውን ውሸት መፋለም ነው” ያሉት አቶ ኦባንግ ላለፉት 25 ዓመታት ህወሃት በኢትዮጵያ ውስጥ የነዛው ጥላቻ፣ ዘረኝነት፣ መከፋፈል፣ … በብዙዎቻችን ዘንድ ሥር ሰድዶ ከሰብዓዊነት በፊት ጎሣን፣ ዘርን፣ ብሔርን፣ … በሚያስቀድም አዙሪት ውስጥ እንድንወድቅ አድርጎናል ብለዋል፡፡ ይህንን እንደምናሸንፈው የተናገሩት ኦባንግ እንደ ጋምቤላ፣ እንደ ኦሮሞ፣ እንደ አማራ፣ እንደ ሶማሊ፣ … ሆነን ሳይሆን እንደ አንድ ባለዓላማ ኢትዮጵያዊ ሆነን ህወሃት የደገሰልንን ጥፋት አልፈን መሻገር እንችላለን ብለዋል፡፡

እንዲህ እንድንሰባሰብ የፈይሣ ድል ያደፋፍረናል ያለው መግለጫ ፈይሳ ሁለተኛ ሆኖ በማሸነፍ የድል መስመሩን ሲያልፍና እጁን አጣምሮ ድምጻችንን ከፍ አደርጎ ሲያሰማልን በኢትዮጵያ ላይ የሰፈረው ጭለማ ተገፈፈ፤ የብርሃን ጭላንጭል ታየን፤ ድምጻችን ጎልቶ በዓለም ተሰማልን፤ የፈይሣ የጀግንነት ተግባር አዲስ ተስፋ በልባችን ውስጥ ፈነጠቀ፤ የውድድር መስመሩን አልፎ ድል ሲጎናጸፍ ለአንድ ወገን ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ኢትዮጵያዊ በህወሃት/ኢህአዴግ የተመሠረተውን የዘረኝነት መሠረት አናወጠው በማለት መግለጫው ፈይሣ ለኢትዮጵውያን ያስገኘውን ድል ይጠቅሳል፡፡

ከዚህ ባለፈ መልኩ በብዙዎቻችን ላይ የተደፋውን እና አሜን ብለን የተቀበልነውን የህወሃት/ኢህዴግን የዘረኝነት ማታለያ ፈይሣ እምቢ በማለት ነጻ ሰው መሆኑን ማሳየቱ ብዙዎቻችንን ከታሰርንበት የዘር ፖለቲካ ወጥተን ለኅብረት እንድንቆም ያደፋፈረን ነው ብዬ እንዳምን ተስፋ ሰጥቶኛል በማለት አቶ ኦባንግ የግል ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡ በዚህ ብቻ አላቆሙም “ከዘርና ብሔር ልዩነታችን ባሻገር ፈይሳ ለእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ጀግና ነው፤ ባለፈው ዋሽንግተን ዲሲ ላይ ባገኘሁት ጊዜ አገር ወዳድ፣ ትሁት፣ ተወዳጅ፤ የዓላማ ሰውና ደፋር መሆኑን ለማወቅ ችያለሁ” ብለዋል፡፡

በዚሁ መግለጫ ላይ አቶ ኦባንግ ፈይሳን ሊገጥሙት ከሚችሉት አስቸጋሪ ሁኔታዎች ዋንኛውን ጠቅሰዋል፤ “ፈይሣን ህወሃት/ኢህአዴግ ባስቀመጠለት የዘር ሳጥን ውስጥ እንዲገባና ለብዙዎቻችን የትግል ተስፋ እንዳይሆን ይበልጡኑም በኦሮሞነቱ እንዲወሰን ሊያደርጉት ይሞክሩ ይሆናል፤ ሆኖም ማወቅ የሚገባን ነገር ማነው ማንነታችንን የሚወስንልን? ይኼ ነህ ብሎ የሚነግረን ወይም በዚህ የዘር ሣጥን ውስጥ ግባ ብሎ የሚደርገን ማነው? ህወሃት ያመጣው የዘር ፖለቲካ በርካታ ኢትዮጵውያንን በዚህ ዓይነት የዘር ሣጥን ውስጥ እንዲገቡ አድርጓቸው ከሰብዓዊነት ወደ ዘር ዝቅ ብለዋል፤ ይህንን በማድረግ ህወሃት ተሳክቶለታል ሊባል ይችላል፤ ኢህአዴግን በአንድ ዓመት የሚበልጠው ፈይሣ ለ25 ዓመታት የተዘራውን የዘር ፖለቲካ አልፎ በመውጣት ቢሳካለት አገሩ ነጻ ሆና ወደ አገሩ ተመልሶ በሩጫ ለመወዳደር እንደሚፈልግ መስማት የህወሃት የዘር ፖለቲካ ያላሰከራቸው በርካታ ፈይሣዎች እንዳሉ ያሳየ ጉልህና ተስፋ የሚሰጥ ተግባር ነው፡፡”

የፈይሣን አኩሪ ተግባር የተከተሉ በርካታዎች እየመጡ መሆናቸውን የጠቀሰው መግለጫ ከፈይሣ ሌሊሣ የድል ተግባር በኋላ ኤቢሣ እጅጉ በኪዩቤክ ካናዳ ማራቶን፤ በሪዮ ፓራኦሎምፒክ በ1500 ሜትር የነሐስ ሜዳሊያ አሸናፊ ታምሩ ደምሴ፤ እንዲሁም በማርሻል አርትስ የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሌላ ኢትዮጵያዊ ካሣ ይመር፤ በድፍረት እጃቸውን አጣምረው በማንሳት ለአገራቸውና ለወገናቸው ድምጽ ሆነዋል ብሏል፡፡

በማጠቃለያም “በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ እንደነዚህ ዓይነት ልጆች ያስፈልጓታል፤ የሞራል ልዕልናቸው የላቀ፤ ሰውን ሁሉ በሰብዓዊ ፍጡርነት የሚያዩና የሚያከብሩ አዲስ ለምንመሠርታት ኢትዮጵያ ያስፈልጉናል፤ ከጎሣ ይልቅ ለሰብዓዊነት ቅድሚያ የሚሠጡ፤ የሌላው ህመምና ሥቃይ የራሳቸው አድርገው የሚወስዱ፤ የወገናቸውን መከራ በሚችሉት ሁሉ ለዓለም ለማሰማት በሕይወታቸው የሚደፍሩ ያስፈልጉናል” በማለት በአኢጋን መግለጫ ላይ የተናገሩት አቶ ኦባንግ ፈጣሪ እነ ፈይሣ፣ ኤቢሳ፣ ካሣ፣ እና ታምሩ ሕዝባቸውን የሚያገናኙ ድልድዮች ሆነው እንዲሰሩ እንዲረዳቸው ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡

ይህ መግለጫ የተዘጋጀው በአኢጋን የሚዲያ ክፍል ሲሆን በኢሜይል አድራሻችን media@solidaritymovement.org ወይም አቶ ኦባንግ ሜቶን Obang@solidaritymovement.org ኢሜይል ሊያገኙ ይችላሉ፡፡

Leave a Reply