ለማይግሪን የሚያጋልጡ ምግቦች

       የምንመገባቸው ምግቦችና መጠጦች ለከፍተኛ ራስ ምታት (ማይግሪን) መንስኤ ሊሆኑ ይችላሉ። በራስ ምታት የመያዝ አጋጣሚዎች በተለያዩ ምክንያቶች (በአየር ፀባይ መለዋወጥ፣ በጠንካራ ሽታዎች፣ በከፍተኛ ብርሃን፣ በሌሎች በሽታዎች ሳቢያ፣ በካፌይን ሱሰኝነት ወዘተ) የሚያጋጥመን ቢሆንም የምንመገባቸው ምግቦችና ወደ አንጀታችን የምንልካቸው የተለያዩ መጠጦችም ለከፍተኛው ራስ ምታት (ማይግሪን) ሊያጋልጡን እንደሚችሉ የአሜሪካ ተመራማሪዎች አስታውቀዋል፡፡ ኔቸር በተሰኘው የምርምር ጆርናል ላይ ተመራማሪዎቹ ይፋ እንዳደረጉት፤የምንመገባቸው ምግቦች ከጭንቅላት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸው ታይራሚንስና ናይትሪ የተባሉ ኬሚካሎችን በስፋት ይይዛሉ፡፡ እነዚህ ኬሚካሎች ደግሞ የደም ዝውውር ሂደትን በማወክ፣ የራስ ምታትንና የዓይን አካባቢ ህመምን ያስከትላሉ፡፡
ሣይንቲስቶቹ በምርምር አረጋግጠናል ካሏቸውና ከፍተኛ የራስ ምታትን ያስከትላሉ በማለት ከዘርዘሯቸው የምግብና የመጠጥ ዓይነቶች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፡፡
ቀይ የወይን ጠጅ
ቀይ ወይን ለራስ ምታት ህመም የሚያጋልጡ ኮንጀነርስና ታይራሚን የተባሉ ንጥረነገሮችን በብዛት ይይዛል፡፡ ስለዚህም ከሌሎች አልኮል መጠጦች ሁሉ የራስ ምታት ህመምን በማነሳሳት በእጅጉ ይታወቃል። የችግሩ ከፍተኛነት በወሰድነው የቀይ ወይን መጠንና በሽታን በመከላከል አቅማችን የሚወሰን ቢሆንም ቀይ ወይን መጠጣት ለከባድ የራስ ምታት ህመም የሚያጋልጥ መሆኑን አረጋግጠናል ሲሉ ተመራማሪዎቹ ገልፀዋል፡፡ ቀይ ወይን ለራስ ምታት ህመም እንድንጋለጥ የሚያደርገን በአልኮልነቱ ሳይሆን በነጭ ወይን ውስጥ የሌለና በቀይ ወይን ውስጥ ብቻ በሚገኘው ተፈጥሮአዊ ውህድ መነሻነት እንደሆነም እነዚሁ ተመራማሪዎች ጠቁመዋል፡፡
ቸኮሌት
ቸኮሌትን አብዝቶ መመገብ ለከፍተኛ ራስ ምታት ያጋልጣል፡፡ በተለይም ጠቆር ያለውና ቡናማ ቀለም ያለው የቸኮሌት አይነት ህመሙን በማባባስ ለከፍተኛ ስቃይ የሚዳርግ መሆኑን የጠቆሙት ተመራማሪዎቹ፤ ከካካዋ ቅቤ የሚሰራው ነጭ ቸኮሌት ከራስ ምታት ህመም ጋር የሚያገናኘው ምንም ነገር አለመኖሩን በጥናታቸው ማረጋገጣቸውን ገልፀዋል፡፡
አይስክሬምና ሌሎች ቀዝቃዛ ምግቦች
እንደ አይስክሬም ያሉ በጣም የቀዘቀዙ ምግቦችን በምንመገብበት ወቅት በአፋችን ውስጥ የሚፈጠረው ከፍተኛ ቅዝቃዜ ለከባድ ራስ ምታት ያጋልጠናል፡፡ ለዚህም ምክንያቱ በአፋችን ውስጥ የተፈጠረው ቅዝቃዜ እስከ ጭንቅላታችን ድረስ ስለሚሰማን እንደሆነም አሜሪካዊያን ተመራማሪዎቹ ጠቁመዋል፡፡
ካፌን
ቡና እና ኮካ መሰል መጠጦች ውስጥ የሚገኘው ካፌን ሱስ የማስያዝ ባህርይ አለው። ይህንን መጠጣት በምናቆምበት ወይንም ሳንጠጣ በምንቆይበት ጊዜ ከባድ የራስ ምታት ህመም ያጋጥመናል፡፡ ካፌይን መውሰድ ያቆሙ ሱሰኞች ለድብርት ስሜት፣ ለመጫጫንና ለከባድ ራስ ምታት ህመም የተጋለጡ ናቸው፡፡ ካፌይኑ የአንጐላችንን ኤሌክትሪካል ሲስተም በማዛባት ሰውነታችን ተጨማሪ የቤታ ንዝረቶችንና አነስተኛ የቴታ ንዝረቶችን እንዲለቅ ያደርገዋል፡፡ ይህ ደግሞ በአንጐላችን ውስጥ የሚካሄደውን ኤሌክትሪካል እንቅስቃሴ በማዛባት ለከፍተኛ የራስ ምታት ህመም እንድንጋለጥ ያደርገናል፡፡
ካፌይን ነክ የሆነ መጠጦችን በጠዋት የመጠጣት ልምድ ያላቸው ሰዎች ካፌይኑ በሕብለ ሰረሰራቸው ውስጥ የሚገኙትን የደምቅዳ ቧንቧዎች በማጥበብ ደም በበቂ መጠን ወደ አንጐል እንዳይገባ ያደርጋል። በዚህ ሣቢያም ከባድ የራስ ምታት ህመም ያጋጥመናል ሲል ተመራማሪዎቹን ዋቢ አድርጐ ኔቸር ዘግቧል፡፡

Leave a Reply