በእንዲህ ያለው ውጥረት ሳቢያም ለዓውደ ዓመት በዓል የሚያስፈልጉ የዕርድ እንስሳት፣ እህሎችና ጥራጥሬዎች አትክልትና ሌላውንም የፍጆታ  ዕቃ ጭነው ብቅ ይሉ የነበሩ ተሽከርካሪዎች ወደ ከተማው ሲገቡ የከረሙት አቋራጭና ከዋና መንገድ ውጭ የሚገኙ መንገዶችን በመጠቀም ነበር፡፡

አጋጣሚው በተለያዩ ምርቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ እንዲፈጠር አድርጓል፡፡ ሁኔታው ሥጋት ውስጥ የከተታቸው በርካቶች የሚፈጠረው አይታወቅም በማለት እህል በረንዳን አጨናንቀው እንዲከርሙ አስገድዷቸዋል፡፡ ከወትሮው በተለየ መልኩ እንደ ጨው፣ ስኳር፣ ጤፍ የመሳሰሉት መሠረታዊ የምግብ ፍጆታዎችን በገፍ ሸምተው ለክፉ ቀን ማስቀመጡን የከተማ ነዋሪዎች ሥራዬ ብለው ይዘውት ነበር፡፡ ወፍጮ ቤቶችም ያለወትሯቸው በወቅታዊው ቀውስ በተረበሹ ደንበኞች ተሞልተው ነበር፡፡ ቀደም ብሎ 2,200 ብር ድረስ ሲያወጣ የነበረው አንድ ኩንታል ጤፍ፣ እስከ 3,000 ብር ተሸጧል፡፡ ሽንኩርትም እንዲሁ በኪሎ 25 ብር ገብቶ ነበር፡፡ ሌሎችም ምርቶች በተመሳሳይ የዋጋ ጭማሪ አሳይተዋል፡፡ ምንም ዓይነት የዋጋ ጭማሪ ያልተደረገባቸው እንደምስር ያሉ የጥራጥሬ ዘሮችም አልታጡም፡፡

ይህ በአሁኑ ወቅት በተወሰነ መልኩ መረጋጋትን እየታየ ይመስላል፡፡ በተለይም የአትክልት ዋጋ ከፍተኛ ቅናሽ አሳይቷል፡፡ ሰኞ ዕለት ወደ መርካቶ ያቀኑት ወ/ሮ ገነት ሀብቱ እንደሚሉት፣ በአትክልት ተራ በኪሎ 15 ብር ይሸጥ የነበረው ቲማቲም ስምንት ብር ገብቷል፡፡ ጥቅል ጐመንም እንደዚሁ በኪሎ አምስት ብር እየተሸጠ ይገኛል፡፡ በኪሎ 25 ብር ይሸጥ የነበረው ቀይ ሽንኩርትም፣ አምስት ብር ገብቷል፡፡ በአንፃሩ ስኳር ከገበያ ጠፍቷል፡፡ በኪሎ 60 ብር ይሸጥ የነበረው ቡናም 110 ብር ሆኗል፡፡

በሸማቾች የፍጆታ ዋጋ ጠቋሚ መለኪያ መሠረት 57 በመቶ የሚሆነው የአገሪቱ ወርኃዊ በጀት ለምግብና ለምግብ ነክ ፍጆታዎች የሚውል ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ ለጥራጥሬና ለብርዕ እህሎች የሚበጀተው አብዛኛውን ወጪ ይይዛል፡፡ በአገሪቱ ዋነኛ ምግብ ለሆነው ጤፍ የሚበጀተው ደግሞ የአንበሳውን ድርሻ ይይዛል፡፡ እንዲህ ያሉ አገራዊ ቀውሶች በሚከሰቱበት ወቅት ሕዝቡ ጤፍ በገፍ ሸምቶ ለማስቀመጥ ሲገደድ ቆይቷል፡፡ የሰሞኑ ሁኔታ ከሚፈጥረው እጥረት በተጨማሪ ሌላ ችግር እየተከሰተ ይገኛል፡፡ በግርግሩ ምክንያት የጤፍ ዋጋ በኩንታል እስከ 700 ብር ድረስ ጭማሪ አሳይቶ ነበር፡፡ አቶ ጌትነት መኮንን ከደራ አካባቢ ጤፍ በማምጣት መጠነኛ የትርፍ ሕዳግ ይዘው ለወፍጮ ቤቶች፣ ለሆቴሎችና ለደላሎች ያስረክባሉ፡፡ እሳቸው ጤፍ የሚረከቡት ደራ ከሚገኙ ነጋዴዎችና ገበሬዎች እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ከዚህ ቀደም በነበረው ገበያ መሠረት አንድ ኩንታል ጤፍ ከ1,900 እስከ 1,980 ብር ድረስ በመግዛት እስከ 2,200 ብር ድረስ ይሸጡ ነበር፡፡

ከግርግሩ በኋላ ግን ነገሮች እንዳልነበሩ ሆነዋል፡፡ ‹‹ሰው ተፈራርቶ ቁጭ ብሎ ነበር፡፡ ገበሬው መንገድ ላይ ቢቃጠሉብኝስ በማለት ምርት አያወጣም ነበር፡፡ አትራፊ ነጋዴውም ቢሆን አውጥቶ የሚሸጠው ብዙ  ምርት አልነበረውም፤›› የሚሉት አቶ ጌትነት፣ የምርት እጥረት ስለተፈጠረ፣ አንድ ኩንታል ጤፍ እስከ 2,600 ብር ተሸጦ እንደነበር፣ በአሁኑ ወቅት ግን እንደ ቀድሞው ባይሆንም መጠነኛ መረጋጋት እንደተፈጠረ ይናገራሉ፡፡

እሳቸው እንደሚሉት፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከወጣ በኋላ ነገሮች በአንጻራዊነት ተረጋግተዋል፡፡ ይሁን እንጂ የአቅርቦት መጠኑም ቢሆን ከዚህ ቀደም እንደነበረው አይደለም፡፡ ምርት ለገበያ የማያቀርቡ አንዳንድ ቦታዎች አሉ፡፡ የሚሸጡበት ዋጋም በፊት ይሸጥበት ወደነበረበት ዋጋ ገና አልወረደም፡፡

እንዲህ ያለው አለመረጋጋት በእንጀራ ንግድ ሥራ የተሰማሩ ድርጅቶች ላይም አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደረ ይገኛል፡፡ ከእነዚህ ድርጅቶች መካከል የአቶ ቸርነት አብይ ድርጅት አንዱ ነው፡፡ ድርጅታቸው በቀን 4,200 እንጀራ አዘጋጅቶ በሦስት ብር ከ50 ሳንቲም ዋጋ ለሆቴሎች፣ ለሬስቶራንቶች፣ ለሥጋ ቤቶችና ለችርቻሮ መሸጫ ሱቆች ያስረክባል፡፡

ጤፍ የሚያስመጡትም ከደራ፣ ከጐጃምና ከኢየራ ነበር፡፡ አንደኛ ደረጃ ጤፍ በኩንታል 2,020፣ ሁለተኛ ደረጃ ጤፍ በኩንታል 2‚000 ብር፣ ሦስተኛ ደረጃ ደግሞ ቢበዛ እስከ 1,840 ብር ይሸጥ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡

በአሁኑ ወቅት ያለው አቅርቦት አነስተኛ በመሆኑ ግን የተገኘውን ከመግዛት ሌላ አማራጭ አለመኖሩን፣ የጤፉን ጥራት ማማረጥ የማይታሰብ መሆኑን፣ መጨረሻ ደረጃ ላይ የሚቀመጠው ጤፍ እንኳ በኩንታል 2,500 ብር ድረስ እየተሸጠ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ‹‹በገበያ መሸጥ የማይገባው ጤፍ እየተሸጠ ነው፤›› የሚሉት አቶ ቸርነት፣ ወጪና ገቢያቸውን ለማመጣጠን ሲሉም በፊት ከሚሸጡበት ዋጋ ላይ ጭማሪ አድርገው እየሸጡ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡

ከንግድ ውድድርና ሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣን የተገኘው መረጃ ደግሞ ግርግሩ በተፈጠረ ሰሞን በከተማዋ በሚገኙ በተለያዩ ገበያዎች የነበረው የአትክልትና ፍራፍሬ ዋጋ ላይ የታየውን ጭማሪ በተለየ መልኩ አስቀምጦት ነበር፡፡ በፒያሳ ገበያ ቀይ ሽንኩርት በኪሎ ከ13 እስከ 17 ብር፣ በቄራ ገበያ ከ17 እስከ 20 ብር፣ በሳሪስ ገበያ ከ17 እስከ 18 ብር፣ በሾላ ገበያ ከ18 እስከ 20 ብር ተሸጧል፡፡ ቲማቲም በፒያሳ ገበያ በኪሎ ከ15 እስከ 20 ብር፣ በቄራ ገበያ ከ20 እስከ 22 ብር፣ በሳሪስ ገበያ ከ18 እስከ 20 ብር፣ በሾላ ገበያ ከ20 እስከ 21 ብር ተሸጦ ነበር፡፡

በአሸዋ ሜዳና በቡራዩ አካባቢ የነበረው የጥራጥሬ ዋጋም በዝርዝሩ ተካቷል፡፡ ጤፍ ከ1,700 እስከ 2,300 ብር፣ ምስር ክክ ከ4,200 እስከ 5,000 ብር፣ በቆሎ በኩንታል ከ550 እስከ 750 ብር፣ ስንዴ በኩንታል ከ850 እስከ 1,200 ብር፣ አተር በኩንታል ከ1,800 እስከ 2,200 ብር ተሸጦ ነበር ብሏል፡፡

በአንፃሩ ገበያው ከተረጋጋ በኋላ በዚህኛው ሳምንት የነበረው የአትክልትና ፍራፍሬ ዋጋ በፒያሳ ገበያ ሲታይ፣ ቀይ ሽንኩርት በኪሎ ከሰባት እስከ ስምንት ብር፣ በቄራ ገበያ ከአምስት እስከ ስድስት ብር፣ በሳሪስ ገበያ ከስምንት እስከ ዘጠኝ ብር፣ በሾላ ገበያ ከሰባት እስከ ስምንት ብር ተሽጧል፡፡ ቲማቲም በፒያሳ ገበያ በኪሎ ከ14 እስከ 16 ብር፣ በቄራ ከ15 እስከ 16 ብር፣ በሳሪስ ከ16 እስከ 17 ብር፣ በሾላ ከ18 እስከ 20 ብር ተሽጧል፡፡

በመሳለሚያ እህል በረንዳ የነበረው የጥራጥሬ ዋጋም ጤፍ በኩንታል ከ1,560 እስከ 2,350 ብር፣ በቆሎ በኩንታል ከ620 እስከ 758 ብር፣ ምስር በኩንታል ከ3,600 እስከ 5,400 ብር፣ አተር በኩንታል ከ1,550 እስከ 1,600 ብር ተሽጧል፡፡

በንግድ ውድድርና በሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣን የሕዝብ ግንኙነት አስተባባሪ ኃላፊ አቶ እንዳልካቸው ፀጋዬ እንዳሉት፣ የተፈጠረው የዋጋ ውድነት በግርግሩ ምክንያት መንገዶች በመዘጋታቸው ምርት ወደ ማዕከል ለመግባት ባለመቻሉ ነው፡፡ ‹‹በአሁኑ ወቅት ግን በተሠራው የዋጋ ማረጋጋት ሥራ ነገሮች ተስተካክለዋል፡፡ እንዲያውም ቀድሞ ይሸጡ ከነበረበት ዋጋ በከፍተኛ መጠን የዋጋ ቅናሽ ያሳዩ የእህል ዘሮች አሉ፤›› ብለዋል፡፡

የጤፍ ዋጋ መጠነኛ መረጋጋት ቢያሳይም በፊት ይሸጥ ወደነበረበት ዋጋ ሊወርድ አልቻለም፡፡ ይህ ለምን ሆነ በማለት ሪፖርተር ላቀረበላቸው ጥያቄም ‹‹እንደ አጋጣሚ ሆኖ ወቅቱ የጤፍ ምርት የሚቀንስበት፣ ዋጋውም ወደላይ የሚወጣበት ነው፡፡ ነገር ግን በቅርቡ አዲስ ምርት ስለሚደርስ ይረክሳል፤›› ብለዋል፡፡ አክለውም በገበያ ላይ ያለው የጤፍ ዋጋ ከ2,400 ብር እንደሚበልጥ፣ ነገር ግን ሰዎች ከአከፋፋዮች ከመግዛት ይልቅ ከቸርቻሪዎች ስለሚገዙ እስከ 200 ብር ልዩነት እንዳለ ጠቅሰዋል፡፡