19 Oct, 2016
የሚኒስትሮች ምክር ቤት መስከረም 28 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ የሚሆን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መስከረም 29 ቀን 2009 ዓ.ም. ይፋ ካደረገ በኃላ፣ ደንቡን ተፈጻሚ ለማድረግ የተቋቋመው ኮማንድ ፖስት በአዋጁ መሠረት ዝርዝር የአፈጻጸም መመርያ አውጥቷል፡፡ ቀይ ዞኖችንም ለይተዋል፡፡

በአገሪቱ የተከሰተው ሁከትና ብጥብጥን ለማስቆምና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለማስከበር ታስቦ የወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተግባራዊ ለማድረግ የተቋቋመው ኮማንድ ፖስት፣ የአዋጁ አንቀጽ 13 (2) እና የደንቡ አንቀጽ አራት በሚያዘው መሠረት ዝርዝር የአፈጻጸም መመርያ ያወጣ ሲሆን፣ ቅዳሜ ጥቅምት 5 ቀን 2009 ዓ.ም. በኮማንድ ፖስቱ ሴክሬታርያት ዋና ኃላፊና በመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ሲራጅ ፈጌሳ ይፋ ሆኗል፡፡

በዕለቱ ለአገር ውስጥ ጋዜጠኞች ይፋ የሆነው ይኼው መመርያ፣ ሦስት ዋና ዋና ክፍሎች ሲኖሩት፣ ሦስት ንዑስ ክፍሎች ደግሞ አካቷል፡፡

የመመርያው ዓላማ ቀደም ሲል በሚኒስትሮች ምክር ቤት የወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተግባራዊ ለማድረግ ነው፡፡ በመላ አገሪቱና በተወሰኑ የአገሪቱ ክፍሎች እንዳይፈጸሙ የተከለከሉ ተግባራት፣ እነዚህ ክልከላዎች ተፈጽመው ሲገኙ የሚወሰዱ ዕርምጃዎችና በተከሰተው ረብሻና ሁከት ተሳትፎ የነበራቸውን አካላት ማስተማርና ለፍርድ ማቅረብ የተመለከተ ነው፡፡

በመመርያው መሠረት በመላ አገሪቱ እንዳይከናወኑ የተከለከሉ ተግባራት ከአንቀጽ አንድ እስከ አንቀጽ 20 የተዘረዘሩ ሲሆን፣ ሁከትና ብጥብጥ የሚያስነሱ ቅስቀሳዎችና አሸባሪ ተብለው ከተሰየሙ ድርጅቶች ጋር ግንኙነት ማድረግ፣ ማናቸውም ሠልፍና የአደባባይ ስብሰባ ማድረግ፣ ሕዝባዊ፣ ሃይማኖታዊና ባህላዊ በዓላትን ማስናከልና ሌላ የፖለቲካ አጀንዳ በማናቸውም መንገድ ማራመድን ይከለክላል፡፡ እንዲሁም ሕዝብ የሚገለገልባቸውን የግልና የመንግሥት ተቋማት መዝጋት፣ ከሥራ ቦታ ያለ በቂ ምክንያት መጥፋትና ለሕዝብ አገልግሎት የሚሰጡ የትራንስፖርት ዘዴዎችን ማስተጓጎልና ማወክ የተከለከለ ነው፡፡

ከዚህም በተጨማሪ በተለይ በተለያዩ የትምህርት ተቋማትና በስፖርት ማዘውተርያ ሥፍራዎች ምንም ዓይነት አድማ ማድረግና ሁከትን የሚቀሰቅሱ ተግባራት መፈጸም፣ በመመርያው መሠረት በጥብቅ የተከለከሉ ናቸው፡፡

በግልም ሆነ በሕዝብና በመንግሥት ተቋማት፣ በመሠረተ ልማቶች፣ በኢንቨስትመንቶች፣ በሌሎች የልማት አውታሮችና በሃይማኖታዊ ተቋማት ላይ በማናቸውም መንገድ ጉዳት ማድረስም የተከለከለ ነው፡፡

ማንኛቸውንም ዓይነት የጦር መሣሪያ፣ ስለት ወይም ተቀጣጣይ ነገሮች ይዞ ወደ ገበያ፣ ሃይማኖት ተቋማትና ሕዝባዊ በዓላት አካባቢ መግባትና መገኘትም የተከለከለ ነው፡፡

አንቀጽ አንድና አንቀጽ 15 ላይ እንደተደነገገው ማንኛቸውንም ዓይነት ሁከት፣ ብጥብጥ፤ መጠራጠርና በሕዝቦች መካከል መቃቃርን የሚቀሰቅስ ይፋዊም ሆነ ድብቅ ቅስቀሳ ማድረግ የተከለከለ ነው፡፡ ፈቃድ ሳይኖር ማንኛውንም ኅትመት አገር ውስጥ ማስገባት ወይም ወደ ውጭ አገር መላክም ታግዷል፡፡ በተመሳሳይ አንቀጽ ሁለትና አንቀጽ 16 ላይ እንደተዘረዘረው በመንግሥት ሽብርተኛ ተብለው ከተሰየሙ ድርጅቶች ጋር ማንኛውም ዓይነት ግንኙነት ማድረግ ሕገወጥ ነው፡፡ የአሸባሪ ድርጅቶችን የተለያዩ ጽሑፎች ይዞ መገኘት፣ ማሰራጨት፣ ዓርማቸውን መያዝና ማስተዋወቅ ኢሳትና ኦኤምኤን የመሳሰሉ የሽብርተኛ ድርጅቶችን ሚዲያዎችን ማሳየት፣መከታተልና ሪፖርት ማድረግ ክልክል መሆኑን መመርያው አስታውቋል፡፡

መመርያው በሕግ አስከባሪና በፀጥታ ኃይሎችም ላይ ዕገዳ የሚጥል ሲሆን፣ በተለይ ደግሞ ትጥቅን ለሦስተኛ ወገን አሳልፎ መስጠት፣ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት ከሥራ መልቀቅ ወይም የዓመት ዕረፍት ፈቃድ መውሰድን ይከላከላል፡፡

የክልከላ አንቀጾች በአብዛኛው ዜጎችን የሚመለከት ሲሆኑ፣ አንቀጽ 17 እና አንቀጽ 18 ግን ስደተኞችንና የውጭ ዜጎችን የሚመለከቱ ክልከላዎች ናቸው፡፡ በዚህ መሠረት የውጭ ዲፕሎማቶች ከአዲስ አበባ 40 ኪሎ ሜትር ራድየስ ውጪ ሳያሳውቁ እንዳያንቀሳቅሱ መከልከላቸውንና ለራሳቸው ደኅንነት ሲባል መሆኑም በመግለጫው ወቅት ተገልጿል፡፡ እንዲሁም ደግሞ በካምፕ ውስጥ የሚገኙ ስደተኞች አግባብ ካለው አካል ፈቃድ ሳያገኙ ውጪ እንዳይወጡ አልያም ሕጋዊ ቪዛ የሌለው አካል ወደ አገር ውስጥ እንዳይገባ ይከላከላል፡፡

ቀይ ዞኖቹ

በመመርያው ንዑስ ክፍል አንድ የተዘረዘሩት በመላ አገሪቱ እንዳይከናወኑ የተከለከሉ ሲሆን፣ ከአንቀጽ 21 እስከ 24 (ንዑስ ክፍል ሁለት) የተዘረዘሩት ተግባራት ደግሞ በተወሰኑ የአገሪቱ አካባቢዎች (ቀይ ዞን ተብለው በተከለሉ) እንዳይፈጸሙ በጥብቅ የተከለከሉ ናቸው፡፡ በዚህም መሠረት ማናቸውንም የጦር መሣሪያ፣ ስለት ወይም እሳት የሚያስነሱ ነገሮችን ከግቢና ከይዞታ ውጪ ይዞ መንቀሳቀስ የተከለከለ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ በኢኮኖሚ አውታሮች በመሠረተ ልማቶች፣ በኢንቨስትመንት ተቋማት፣ በእርሻ ልማቶች፣ በፋብሪካዎችና በመሰል ተቋማት አካባቢ ከቀኑ 12 ሰዓት እስከ ንጋቱ 12 ድረስ ከተፈቀደለት ሠራተኛ ውጪ ማንኛውም ሌላ ሰው እንዳይንቀሳቀስ ተከልክሏል፡፡

በተወሰኑ የአገሪቱ አካባቢዎች እንዳይፈጸሙ ከተደረጉ ክልከላዎች ከተደረጉባቸው መካከል ቦታዎቹን ኮማንድ ፖስቱ በየጊዜው የሚያሳውቅ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ በሁሉም የአገሪቱ ድንበሮች 50 ኪሎ ሜትር ወደ ውስጥ ገባ ብሎ የሚገኝ አካባቢና በዝርዝር የታወቁ ዋና ዋና የአገሪቱ መንገዶች ላይ 25 ኪሎ ሜትር ወደ ግራና ወደ ቀኝ ተግባራዊ እንደሚሆኑ፣ የኮማንዱ ፖስቱ ሴክሬታርያት ዋና ኃለፊ ይፋ አድርገዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል

ከአዲስ አበባ ጅቡቲ፣

ከአዲስ አበባ ሻሸመኔ ደሎ፣

ከአዲስ አበባ ሻሸመኔ ሞያሌ፣

ከአዲስ አበባ ሐረር፣

ከአዲስ አበባ አሶሳ፣

ከአዲስ አበባ ጋምቤላ፣

ከአዲስ አበባ ገብረ ጉራቻ የሚወስዱ መንገዶች፣

እንዲሁም ከጎንደር ወደ መተማና

ጎንደር  ሑመራ የሚወስዱ መንገዶች የቀይ ዞን አካባቢዎች ተብለው ተለይተዋል፡፡

የሚወሰዱ ዕርምጃዎች

በመመርያው የተዘረዘሩት የተከለከሉ ተግባራትን ተላልፎ የሚገኝ ግለሰብ ወይም ድርጅት ላይ ዕርምጃ እንዲወሰድ የመመርያው ክፍል ሁለት ይፈቅዳል፡፡ የተጠረጠረውን አካል ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ በቁጥጥር ሥር ማዋል፣ ብርበራ ማካሄድ፣ ኮማንድ ፖስት በሚወሰነው ቦታ እንዲቆይ፣ ማድረግ ተገቢውን ትምህርት እንዲያገኝ አልያም ለፍርድ እንዲቀርብ ማድረግ፣ በማናቸውም የግንኙነት ዘዴዎች የሚተላለፉ መልዕክቶችን መቆጣጠርና መገደብ፣ እንዲሁም ማናቸውም ሁከት ይፈጥራሉ ተብለው የተጠረጠሩ አካላት ወይም ጉዳት ይደርስባቸዋል ተብሎ የታመነባቸው አካላት ወደተወሰነ ቦታ እንዳይገቡ፣ አልያም በአንድ ቦታ ብቻ እንዲቆዩ ሊያደርግ ይችላል፡፡

እንዲሁም ሕግ አስከባሪ አካላት በትምህርት ተቋማት ውስጥ አድማ የሚያደርጉ ሰዎች በቁጥጥር ለማዋል እንዲገቡ የተፈቀደላቸው ሲሆን፣ አስፈላጊም ከሆነ በአካባቢው ለመቆየት ይችላሉ፡፡

በንዑስ ክፍል ሦስት ውስጥ መረጃ የመስጠትና የመተባበር ግዴታ ተጥሏል፡፡ አንድ አከራይ ያከራየውን ክፍል፣ ዕቃ፣ ቦታ ወይም ሌላ መገልገያና የተከራዩን ማንነት በጽሑፍ በአቅራቢያው ለሚገኘው ፖሊስ ጣቢያ የማሳወቅ ግዴታ አለበት፡፡ በአጠቃላይ በማናቸውም ተቋማት ወይም ግለሰብ ላይ ለሕዝብ ፀጥታና ደኅንነት ሲባል ለሕግ አስከባሪ ማናቸውም መረጃ የመስጠት ግዴታን ይጥላል፡፡

የመመርያው አንቀጽ 29 ማናቸውም የሕግ አስከባሪ አካል እነዚህን ክልከላዎች ተግባራዊ ለማድረግ ሲንቀሳቀስ አደጋ ላይ የሚጥል ጥቃት ሲሰነዘርበት፣ ራሱን የመከላከል ዕርምጃ እንዲወስድ ይፈቅዳል፡፡

የመጨረሻው ክፍል ሦስት ተሃድሶና ፍርድ ቤት ስለማቅረብ የሚያትት ሲሆን፣ ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ በተከሰተው ሁከት በግልም ሆነ በቡድን ተሳትፎ በማድረግ ንብረት የዘረፈ፣ በሕገወጥ ተግባራት የተሳተፈና ድጋፍ ያደረገ፣ ሰው ከመግደል ጀምሮ ንብረትን እስከማቃጠል የሚደርስ ማናቸውም ወንጀል የፈጸመ ይህንን መመርያ በወጣ በአሥር ቀናት ውስጥ ለፖሊስ ጣቢያ ያሳወቀና እጁን የሰጠ እንደ ወንጀሉ ክብደት የተሃድሶ ትምህርት ተሰጥቶት ሊለቀቅ እንደሚችል ይደነግጋል፡፡

መመርያውን በተመለከተ አንዳንድ ጥያቄዎች ከጋዜጠኞች የቀረቡ ሲሆን፣ በተለይ ከአሸባሪ ድርጅቶች ጋር ስለሚደረግ ግንኙነትና የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀምን በተመለከተ የኮማንድ ፖስቱ ሴክሬታርያት ዋና ኃላፊና የመከላከያ ሚኒስትሩ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ከዚህ በፊት በማኅበራዊ ሚዲያ የሚደረጉ ግንኙነቶች ሊኖሩ እንደሚችሉ ጠቁመው፣ መመርያው ተግባራዊ ከሚሆንበት ጊዜ ጀምሮ ሊሆን እንደሚችልና ከአሸባሪዎች ጋር ግንኙነት ማቋረጥና ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል፡፡ የአሸባሪ ድርጅቶችን የመገናኛ ዘዴዎች መከታተልን በተመለከተ አንድ ሰው መከታተሉን እንዴት ማወቅ ይቻላል ተብሎ ለቀረበው ጥያቄም፣ ይህንን የሚመለከተው የኮማንድ ፖስቱ አካል የራሱ የሚቆጣጠርበት ዘዴ እንደሚኖረው ጠቁመዋል፡፡

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መሠረት በተለይ ያለፍርድ ቤት ተጠርጣሪን በቁጥጥር ሥር ማዋልና ብርበራ ማካሄድን በተመለከተ፣ የንፁኃን ዜጎች መሠረታዊ ሰብዓዊ መብት አይጥስም ወይ በማለት ሪፖርተር ላቀረባላቸው ጥያቄ ሚኒስትሩ በሰጡት ምላሽ፣ በአፈጻጸም ላይ ጥንቃቄ እንደሚደረግና በተዋረድ የኮማንድ ፖስት መዋቅር ሳያውቀው እንደማይፈጸም ገልጸዋል፡፡ እንዲሁም የአካባቢው የኅብረተሰቡን እምነት ለመፍጠር ዕርምጃው የሚወሰደው በአካባቢው የሚታወቅ ፖሊስና ቅርበት ያላቸው አካላት በተገኙበት እንደሚሆን፣ ስህተት ከተፈጠረም በአስቸኳይ እንደሚታረም አስረድተዋል፡፡

 ምንጭ           _             ኢትዮጵያን ሪፖርተር

Leave a Reply