እንግዳ ታደሰ / ኖርዌይ

sibehat

 

ያንን ገለባ ልጅ ከደጅ የወደቀው

አድራሻህ ወዴት ነው ብለህ አትጠይቀው
የነገው ነፋስ ነው መንገዱን የሚያውቀው ፡፡
በዕውቀቱ ስዩም

ጥቅምት 5 ቀን 2009 ዓ.ም የሸራተን አዲስ የላሊበላ አዳራሽ ቲያትር ቤት መጋረጃ ለተደራሾች ተገለጠ፡፡  ሁለት መቶ ሃምሳ ታዳሚዎችን ባጨናነቀ ሁኔታ የትያትር ቤቱ አዳራሽ ሞልቶ ነበር ፡፡ « በዲሞክርያሳዊ  ግንባታ ችግሮች ላይ የተሰነዘሩ ምልከታዎች » በሚል መርሃ ቃል በአቶ በረከት ሰምዖን መርሃኤ ተውኔት አዘጋጅነት፣ በልደቱ ተዋኝነት የተካሄደ ስብሰባ ፡፡ አዳራሹን ያለስሙ ቲያትር ቤት ያልኩት ጠፍቶኝ አይደለም ፡፡ ከወሎዋ ላሊበላ ምድር ፣ እስከ ሸራተኑ የላሊበላ አዳራሽ ድረስ እነኝህ ሁለት ሰዎች እንዴት እየተደጋገፉ እንደሚያቄሉን ስለገረመኝ ነው ቲያትር ቤት ያልኩት ፡፡ ይህ ጽሁፍ በአቶ ልደቱ ተደጋጋሚ የአልጋ መውደቅ ሃጢያት ላይ ጊዜውን አያጠፋም ፡፡ እሱን ለነብስ አባቱ ትተንላቸዋል ፡፡ ነብስ አባት ካለው ፡፡ እንዲሁ ግን ምንም ሳልል እንዳላልፈው  የሚመጥነውን ግጥም ከበውቀቱ የግጥም መድበል ላይ አገኘሁ ፡፡ ከመግቢያዬ ላይ የተጻፈውን ፡፡ ልደቱ እድሜ ሰጥቶት ነገ ሌላ መንግሥት ቢመጣም ንፋሱ ገፍቶት ሲያመጣው አዲስ ተዋናይ ሆኖ ከመምጣት ምንም የሚያግደው ህሊና የለውም ፡፡ ሼም የለሽ ነው የሚሉት አራዶች ፡፡

ወደ አቶ በረከት ልምጣ

    አንድ የሶቭየት ህብረት ቀልድ ትዝ አለኝ ፡፡  በጎርቫቾቭ አማካኝነተ በወጣ ጥብቅ አዋጅ መሰረት፣ ቮድካ እንደልብ በሶቭየት ከተማ ባለመገኘቱ ፣ ህዝቡ የመንግሥት ማከፋፈያ ደጃፍ ላይ ተሰልፎ ለመግዛት ተራ ይጠባበቃል ፡፡አንድ ጀብራሬ የሶቭየት ዜጋ የሰልፉን ጥምጥም በአይኑ ቃኝቶ እንዲህ በዋዛ እንደማይደረስበት በንዴት ከተረዳ በኋላ ከሰልፉ ውስጥ ጮሖ በመውጣት በምንም አይነት ይህን ሰልፍ አልከተልም ጎርቫቾቭ የሚባለውን ሰው ባገኝ እገለዋለሁ እያለ በቀጥታ ወደ ክሬምሊን ቤተ መንግሥት አመራ ፡፡ ከ-40 ደቂቃ በኋላ ይህ ሰው ተመልሶ ቀድሞ ተሰልፎበት ወደነበረበት ቦታ እየተወራጨ ሲመጣ ፣ ሰልፉ ላይ የነበሩት ሰዎች በአንድ ድምጽ ገደልከው ? የታባቱ ገላገልከን ? ይሉት ጀመር፡፡  ምን እገለዋለሁ ! ክሬምሊን ቤተ መንግሥት ስደርስ ፣ ጎርቫቾቭን ሊገድሉ የተሰለፉ ሰዎች ሰልፍ ከዚህ ሰልፍ እጥፍ ስለሚበልጥ ይኽኛው ሰልፍ ይሻላል ብየ ተመለስኩ ይላቸዋል ፡፡

መርሃኤ ተውኔት በረከት ሰምዖንም ባስመዘገብነው የኢኮኖሚ እድገትና ፣ የዲሞክራሲ ባህል መጎልበት የተነሳ የህዝባችን ንቃተ ህሊና በማደጉ የተፈጠረ ተቃውሞ እንጂ ፣ ህዝባችን ፌዴራላዊ አስተዳደራችንን በመቃወም ያደረገው ህዝባዊ አመጽ ቤተመንግሥቱን ለመናድ አልነበረም  ፡፡ ስለዚህ እንደ ጀብራሬው የቮድካ ሰልፈኛ ቅጥፈት ከዚያኛው ሰልፍ ይኽኛው ይቀላል አይነት የመሸወጃ ቲያትሩን የዚያ ሁሉ አመጽ ልማታችን ያመጣው እድገት ነው በሚል ምንት-እፍረት ባጣ የፖለቲካ ተራክቦ ብልግና ስብሰባውን መርቷል ፡፡ በዚህ የበረከትና የልደቱ ቲያትራዊ ጨዋታ ላይ የ – EMF ድረ ገጽ አዘጋጅና አምደኛ አቶ ክንፉ አሰፋ የሄደበትን ትንታኔ በዚህ ድረ ገጽ ላይ አንብቤአለሁ ፡፡ በአብዛኛው አቶ ክንፉ ያነሳቸውን ነጥቦች ብጋራም በአንዳንዶቹ ተሳታፊ ሰዎች ላይ ግን ልዩነት አለኝ ፡፡

  • የሸራተኑ ጉባኤ እንዴትና ለምን ዓላማ ተዘጋጀ ?
  • በአባ ዱላ አማካኝነት ይህ ጉባኤ ለምን በገሃድ እንዲከፈት ተፈለገ ?
  • ጉባኤው ሲዘጋጅ ታዳሚና አድማቂ ሆነው የተመረጡት ሰዎች ፣ በምን መስፈርት ተመረጡ ?
  • ፕሮፌሰር መረራና ኢንጅነር ይልቃል በግል ነው የተጋበዙት ወይስ የሚመሩትን ፓርቲ ወክለው ?
  • አቦይ ዘባርቀው ነው ወይስ ሆን ብለው መረራና ይልቃል ጓደኛሞች እንጂ ፓርቲ የላቸውም ያሉት ?
  • ታውቆና ታስቦበት ነው ከመጀመርያው ተርታ ሰልፍ ላይ አቦይ ወንበር ያልተሰጣቸው ?
  • ሰምሃልስ እንደተረሳ የቤት ልጅ ከመጨረሻው ረድፍ ላይ ለምን ተወረወረች ?

ብዙ ጥያቄዎችን የዕለቱን የስብሰባ አዳራሽ ድባብ በመመልከት መጠየቅና ግምቶችን መስጠት ይቻላል ፡፡ ገራሚው ጉዳይ ግን « ተከልከይ ባዋጅን » አሽሞንሙኖ ባወጀበት ማግስት ፣ በዲሞክርያሳዊ ግንባታ ችግሮች ላይ የተሰነዘሩ ምልከታዎች በሚል ባዶና ቱሻ መፈክር ውስጥ የተገኙት ጎምቱ ተቃዋሚዎች፣ በተበላ እቁብ ውስጥ አድማቂ ሆነው መገኘታቸው ነው አጠያያቂው ፡፡ ቢያንስ እነኝህ ሁለት ሰዎች በዚህ ጉባኤ ላይ እንዲገኙ ሲመረጡ ፣ የዕለቱን ጉባኤ የወደቁ ሰማእቶችን በማሰብ በህሊና ጸሎት ጉባኤው እንዲጀመር ያለማድረጋቸው ፥ ለሃገሪቱ መጻኢ ሁኔታ ለሰላምና መረጋጋት ሲባል የታሰሩ የህሊና እሰረኞች ነጻ እንዲወጡ እንኳ ሳይጠይቁ በረከት ቀድሞ ሊጫወትባቸው ባዘጋጀው የዲሞክራሲ እድገታችን ያመጣው ቁጣ ነው ጨዋታ ተጠልፈው ያላቸውን ካርታ ተኩሰውና ጨርሰው በተቃዋሚነት ጨዋታ ለአሜሪካ ምክር ቤትና ለአውሮፓ ህብረት ፓርላማ ለሚቀርብ ካሜራ ገጭ የሳሎን ቤት ጨዋታ ተበልጠው ሩጫቸውን ጨርሰዋል ፡፡ ይህ ጉባኤ ሲዘጋጅ ታስቦበት ፣ በረከት ቅድመ ሴራውን ጎዝጉዞበት እንደሆነ የሚታወቀው ፣ ጉባኤው የተከፈተው በአገሪቱ ፓርላማ አፈጉባኤ መሰረት መሆኑ ነው ፡፡ ይህ ለፈረንጆች ታላቅ ምልከታ ነው ፡፡ ፈረንጆች በየሃገራቸው የፓርላማ አፈ ጉባኤዎችን የክብር ቦታ ያውቁታል ፡፡ በዚህ ጉባኤ ላይ ካሜራው በደንብ እንዲታዩ ያደረጋቸውና በተቀዋሚነት ማማ ላይ ወጥተው እንዲጎሉ ያደረጋቸው በቅርቡ በሰሜን አሜሪካ የአሜርካን ኮንግረስ አባላቶችን በቅርበት በጋር ሲያናግሩ የከረሙት እና በጋራም በአንዳንድ የአሜሪካ ግዛቶች ለኢትዮጵያውያን ስብሰባ ሲጠሩ የነበሩ ሁለቱ ተቃዋሚዎች እንደሆኑ ወያኔ ስለምታውቅ ነው ፡፡ ይህን ጨዋታ ወያኔ ጠንቅቃ ስለምታውቅ ካሜራ ላይ ሞልተው እንዲታዩላት በደንብ ሠርታቸዋለች ፡፡

በሌላ በኩል ምንም እንኳ ለአባላቶች እና ደጋፊዎች ግልጽ ባይሆንም ፣ ከሰሜን አሜሪካ መልስ በኢንጅነር ይልቃል ላይ ባልተገኙበት መፈንቅለ መንግሥት ተደርጎባቸው በምትካቸው አቶ የሺህዋስ አሰፋ መመረጣቸው በአደባባይ ተነግሯል ፡ይህን የምርጫ ስነ ስራት የመራው ደግሞ የምርጫ ቦርድ ጭምር እንደሆነ በግልጽ በተነገረበት ወቅት ፣ እንዴት ኢንጅነር ይልቃል በዚያ ስብሰባ ላይ ተገኙ ? ሰማያዊውን ወክለው እንዳንል የምርጫ ቦርዶቹ መሪዎች ፕሮፌሰር በቃና እና ዶክተር አዲሱ ባሉበት ነው ኢንጅነር ይልቃል በሰማያዊ ፓርቲ ስም ክርክር ውስጥ የገቡት ፡፡ አይ ! በግል ነው እንዳንል ደግሞ አቦይ ስብሃት በመረራ ላይና በይልቃል ላይ የሰነዘሩት ሂስ አንድ ነገር ያሳብቃል ፡፡

ጽሁፌን ለማጠቃለል እንደ ቀድሞው ደርግ መፈክር እኛም አልረሳናችሁም አይነት መፈክር ያረሳኋቸውን ሁለት ሰዎች ጠቅሼ ጽሁፌን ላጠቃልል ፡፡ ወደ ሰምሃል ስመጣ

ብዙዎች በሰሞኑ በፌስ ቡክ ላይ  ሽንት አስፈንጥሮ ከመሽናት ፎቶ ባሻገር ፣ እስከ የጆሮግንድ የጺም አወራረድ ጆንትራ ቮልታ ፎቶዎቿን ጭምር በማምጣት ሃሳቧን ሲተቹ አይቻለሁ ፡፡ በኔ በኩል ሰምሃል ያጠፋችው ጥፋት  አልታይ ብሎኛል እንደ አቦይ ከመድረኩ ርዕስ ወጥታ! ባገኘችው ዕድል ግን ራሱ ህወሃት ያወጣውን መመርያ ራሱ እየበላው የኋሊት እንደሄደ ያጋለጠችበት መድረክ ነው ፡፡ ከመለስ አንጻር ልጅቷን ጭምር በመጥላት ሳይሆን የምንቃወማት፣ ያደረገችው ንግግር በህወሃት የስልጣን ማማ አወጣጥ ላይ ችግር እንደገጠማት  የሚያሳይ ነው ፡፡ በነማን ላይ ቂም እንዳላት ያባቷ ልጅ ሳታፍር ፈርጠም ብላ ተናግራለች ፡፡  እዚያ ማዶ ጭስ ይጨሳልና አጭሳም ይሁን አንጀቷ ጨሶ በቡሄ መልክ አውርዳለች ፡፡ የስልጣን ቡጥቡጥ ጭምር እዚያ ቤት እንዳለ የሚያሳይ ጭምር ነው ፡፡ መለስ ሲሞት ይቅርታ ሲሰዋ  አቦይ ስብሃት በአደባባይ ወጥተው በአሜሪካን ድምጽ ሬድዮ ፣ ድርጅቱ እስካለ ድረስ መለስ ሞተ ! ፋጡማ መጣች የሚመጣ አደጋ የለም ፣ የሚፈጠር ቫክዩምም የለም እስካሉ ድረስ ፣ ለምን የተገለላችሁት የህወሃት አዛውንቶች ድርጅቱ እስካለ  ድረስ ተመልሳችሁ ወደ ስልጣን መጣችሁ ? እኛ ተተኪ ወጣት ልጆቻቸው እያለን ነው ያለችው ! ዋሸች እንዴ ?

ጋዜጠኛ ሳምሶን ማሞ በሚመለከት መድፊያዬን በቀድሞዋ ሶቭየት ህብረት አምባገነን መሪ ስታሊን ላይ በተቀለደው ቀልድ ዙርያ በማጠንጠን ወደ ሳምሶን ማሞ አለፍኩ ፡፡ ስታሊን ፊልም ቤት ሄዶ ! የያዘውን ዱካክ በሳቅ ካስወገደ በኋላ ያን የመሰለ አስቂኝ የቲያትር ገቢርን በብቃት የተወጣውን ኮሚክ አክተር ካደነቀ በኋላ አስጠርቶ የአድናቆቱ ማሰርያ ያደረገው ያን ድንቅ ኮሚክ አክተር አሁኑኑ ወስዳችሁ ረሽኑት ማለቱ ያሳዘናቸው የቲያትር ቤቱ ኃላፊዎች ቢያንስ ከላይ ከንፈሩ ላይ ልክ እንደ ስታሊን ያጎፈረውን  የከንፈሩን ጺም ይላጭና ይትረፍልን ብለው ስታሊንን ቢማጸኑት ፣ ይሁን ! ጺሙን ላጩና ረሽኑት እንዳለው ፣ ሳምሶንም የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ በጌታቸው ረዳ የሚተርፍ አይመስለኝም ፡፡ ሳምሶን የራሱን ተክለ ሰውነት አጉልቶ ለማሳየት ሲል ፣ የበረከትን ቢሮ በስድብ እበት ለቅልቆ እንደሚወጣ ራሱን አጀግኖ ተናግሯል ፡፡ በረከትን አድንቆ ፥ የጌታቸው ረዳን መዋቅር አኮሦሶ መናገሩ ከተሰመረው 40 ኪሎሜትር ቀይ መስመር ውስጥ ያለፈ ይመስለኛል ፡፡ አዲሱ አስገዳጅ ወይም አስገዳይ አዋጅ ደግሞ ከአፍንጫው የረዘመ « የአሊ ባባን ጫማ አይነት » የተጫማ ሰው ደብረዘይት ጁስ ቤት ላይ ካልቆመ አልፌ ቢሾፍቱ እሄዳለሁ ቢል ቢያንስ ጫማው እንደ-ምድር ዘላይ ሰው ጫማ ከተሰመረው መስመር አልፎ ቢሾፍቱ/ ደብረዘይት ስለሚደርስ አዲዮስ ነው ፡፡ ሳምሶናችን !! በለፈለፉ በአፍ ይጥፉ ነውና ከሰሞኑ የኮሚኒኬሽን ጽ/ቤትን ውሳኔ እንሰማለን ፡፡

Leave a Reply