– የዓለም ገንዘብ ድርጅት የአገሪቱን የፖለቲካ ትኩሳት ወደ ጎን ብሎታል

የዓለም ገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) በኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ጋር በየጊዜው ይወያያል፡፡ በመስከረም ወር ጥቢ ሰሞን ያደረጉትን ውይይት በተመለከተ፣ በወሩ ማገባደጃ ወቅት ይፋ ያደረጉት ሪፖርት አገሪቱ በድርቅ አደጋ ምክንያት እንዲሁም በዓለም አቀፍ ገበያ የሸቀጦች ፍላጎትና የዋጋ መዳከም አገሪቱን በውስጣዊና ውጫዊ መንገድ እንደተፈታተኑ የገንዘብ ድርጅቱ ይፋ አድርጓል፡፡

በኢትዮጵያ ባለሥልጣናትና በገንዘብ ድርጅቱ ዳይሬክተሮች ቦርድ ከተደረገው ውይይት ባሻገር፣ በድርጅቱ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ ጉዳይ የሚከታተሉትና ድርጅቱ ተልዕኮ ኃላፊ ሁልዎ ኤስኮላኖ ሰሞኑን በሰጡት ትንታኔም አገሪቱ በአገር ውስጥ ላለፉት ሁለት ዓመታት ያሳለፈችውን የድርቅ አደጋና ኢኮኖሚው ላይ ያሳደረውን ተፅዕኖ አብራርተዋል፡፡ ከዚህ በተጓዳኝ የዓለም የሸቀጥ ገበያ መቀዛቀዝ ያስከተለውን ተፅዕኖም ተንትነዋል፡፡ በዚህ ምክንያትም አገሪቱ ላለፉት አሥር ዓመታት ስታስመዘግብ የቆየችው ባለሁለት አኃዝ የኢኮኖሚ ዕድገት ወደ ታች እያለ መምጣቱንና በዚህ ዓመትም ከመንግሥት ትንበያ በመቀነስ ወደ 6.5 ከመቶ ዝቅ መደረጉን ኤስኮላኖ ጠቅሰዋል፡፡

በኢትዮጵያ ዋናው የኢኮኖሚ ዕድገት መዘውር የመንግሥት ኢንቨስትመንት እንደሆነ የሚገልጹት ኤስኮላኖ፣ በመሠረተ ልማት መስክ በተለይም በኤሌክትሪክ ኃይል ልማትና ሥርጭት፣ በሎጂስቲክስ መሠረተ ልማት በተለይም በመንገድ ግንባታና በባቡር ትራንስፖርት የታየውን የመንግሥት ኢንቨስትመንት የአገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት እንዲመዘገብ ማገዙን ይጠቅሳሉ፡፡ ከሰሐራ በታች አፍሪካ የከተማ ባቡር ወይም ሜትሮ ሲገነባም የኢትዮጵያ ቀዳሚው እንደሆነም በምሳሌነት የሚጠቅሱት ኤስኮላኖ፣ የግብርና መስክ 40 ከመቶውን የኢኮኖሚውን ድርሻ መያዙና 80 ከመቶ በላይ የገጠሩ ሕዝብ መተዳደርያ መሆኑ፣ በምርጥ ዘር፣ በማዳበሪያ ተጠቃሚነት የሚታዩ ለውጦች ሁሉ አገሪቱ ባለፉት አሥርት ውስጥ ስታስመዘግብ ለቆየችው ዕድገት አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን በመጥቀስ አብራርተዋል፡፡ አገሪቱ ትልቅ የውስጥ  ገበያ ያላት መሆኑ፣ ይሁንና ግን ወደ ውጭ የሚላከው ምርትና አገልግሎት ከጠቅላላው የአገር ውስጥ ምርት አኳያ 10 ከመቶ መሆኑ በአንፃራዊነት ለአገሪቱ በጎ ጎኖች ተጠቃሽ መሆናቸውን የዓለም ገንዘብ ድርጅቱ ባለሙያ ይተነትናሉ፡፡

ትልቁ ፈተና

ይህ ዓመት ለኢትዮጵያ ፈታኝ የሆነባቸው አንኳር ነጥቦች እንዳሉ የሚናገሩት ኤስኮላኖ፣ የሚከተሉትን በዋና ምክንያትነት ያስቀምጣሉ፡፡ አንደኛው ምክንያት አገሪቱ በሁለት ውጫዊ ፈተናዎች መጠመዷ ነው፡፡ የዓለም የሸቀጥ ዋጋ መዋዠቅና ከሌላው ጊዜም በላቀ ሁኔታ መውረዱ ከአገሪቱ የወጪ ንግድ መዳከምና ለውጭ ምንዛሪ ግኝቷ መቀነስ ብሎም ለመጠባበቂያ ክምችቷ መመናመን ድርሻውን የያዘ ፈተና ሆኗል፡፡ በአሁኑ ወቅት አገሪቱ ያላት የመጠባበቂያ ክምችት ለ1.9 ወራት ብቻ የሚያቆያት ሆኗል፡፡

እንደ ኤስኮላኖ ማብራሪያ በጣም ወሳኙና ፈታኙ ክስተት በአገሪቱ የተከሰተው ድርቅ ነው፡፡ በ30 ዓመታት ምናልባትም በአንዳንድ ተንታኞች እንደሚባለው ላለፉት 50 እና 60 ዓመታት ያልታየ ከባድ ድርቅ አገሪቱን መምታቱን በዓብነት ተጠቅሰዋል፡፡ አገሪቱ በእነዚህ ውጫዊ ምክንያቶች ሳቢያ ስታስመዘግብ የቆየችው ኢኮኖሚያዊ ዕድገት እያሽቆለቆለ መምጣቱን ይጠቅሳሉ፡፡ ባለፈው በጀት ዓመት ድርቁ በተንሰራፋበት ወቅት የነበረው ትንበያ 4.5 ከመቶ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡

የመንግሥት ዕርምጃዎች

መንግሥት ለአሁኑና ለወደፊቱም ጭምር የድርቁ አደጋ የኢኮኖሚውን ዕድገት ይባስ እንዳይጫነው ዕርምጃ እየወሰደ እንደሚገኝ፣ አደጋው የተባባሰ ጉዳት እንዳያስከትልም ከውጭ በሚያገኘው ድጋፍ በመታገዝ ጭምር መሯሯጡን አይኤምኤፍ ጠቅሷል፡፡

የድርቁ ሁኔታ በሰዎች ኑሮ ላይ ያደረሰው ጉዳት ምንም እንደማያሻማ ያብራሩት ኤስኮላኖ፣ 10 ሚሊዮን ሰዎች በድርቁ መመታታቸውን ዋቢ አድርገዋል፡፡ ይሁንና ድርቁ እሴት በሚጨመርባቸው ምርቶች ላይ ያሳረፈው ተፅዕኖ ከዚህ ቀደም ያደርስ ከነበረው ጫና ይልቅ ዝቅተኛ ሆኖ መገኘቱንም ጠቅሰዋል፡፡ ይሁንና በከፍተኛ መጠን ለድርቅ ተጎጂዎች ከውጭ የተገዛው ስንዴ ከሌላው ጊዜ ይልቅ በእጥፍ የጨመረ እንደነበርም ሳይጠቁሙ አላለፉም፡፡ ይህ መሆኑ ደግሞ መንግሥት ከውጭ ከሚያገኘው ይልቅ ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት ያወጣው ገንዘብ ከፍተኛ እንዲሆን በማድረግ የንግድ ሚዛን ጉድለትን ጨምሮ የከረንት አካውንት ጉድለትን እንዲያስተናግድ አስገድዶታል ብለዋል፡፡ የወጪ ንግድ አፈጻጸም በዓለም ከሚታየው ፍላጎት መቀዛቀዝ አኳያ ቀንሶ መገኘቱ፣ በዋጋ ደረጃም እንደ ቡና፣ ሰሊጥና የመሰሳሰሉት ምርቶች በእጅጉ ቅናሽ ማሳየታቸው የወጪ ንግድ ሚዛን ጉድለትና የከረንት አካውንት ጉድለቱ ከፍተኛ ክፍተት እንዲፈጥር አስተዋጽኦ መፍጠራቸው ታይቷል፡፡

በአንፃሩ ከፍተኛ የገቢ ንግድ መጠን መጨመር መከሰቱ ለድርቁ ተጎጂዎች የሚውል እህል ግዥ ሲታከልበት አገሪቱ ለሁለት ተከታታይ ዓመታት ከባድ የከረንት አካውንት ጉድለት በማስተናገድ ላይ ትገኛለች በማለት ኤስኮላኖ ትንታኔቸውን አጠናክረዋል፡፡ ይሁንና በአሁኑ ወቅት የድርቁ ጫና በመቀነሱ ከመንግሥት እፎይታ አስገኝቶለታል፡፡ ይሁንና የኢኮኖሚውን የዕድገት ጉዞ ለማስቀጠል ከፍተኛ የመንግሥት ኢንቨስትመንትና ወጪ መታየቱ ግን አገሪቱ የብድር ዕዳ ውስጥ ይበልጥ እንድትዘፈቅ አድርጓታል ተብሏል፡፡ የዓለም የገንዘብ ድርጅት ስለዚህ ሥጋት ይህን ብሏል፡፡

‹‹በአሁኑ ወቅት የሚታየው የከረንት አካውንት ጉድለትና እየተከማቸ የመጣው የብድር ዕዳ መጠን ወደፊት አገሪቱ መሸከም ከምትችለው በላይ ሊሆን እንደሚችል ከባለሥልጣናቱ ጋር ተነጋግረናል፡፡ ይህንን አለመመጣጠን ማስተካከል እንደሚገባቸው ተነጋግረናል፡፡ የአገር ውስጥ ምንጮችን (የሚሰበሰበውን የታክስ ገቢ መጠን በማስፋፋትና ቁጠባን) በመጠቀም፣ ከዚህም ባሻገር የግሉን የኢኮኖሚ ዘርፍ ይበልጥ በማሳተፍ መሥራት እንዳለባቸው እነሱም ያምናሉ፡፡ በአምስቱ ዓመት ዕቅዳቸውም ይህንኑ አስቀምጠዋል፡፡ የመንግሥት አስተዳደራዊ አቅምና ብቃት መሻሻል፣ በመንግሥት ተቋማት በኩል ግልጽነት ማስፈን አበክሮ እንዲተገብራቸው የሚጠበቁ ናቸው፡፡ የውጭ ኢንቨስትመንትን መሳብና የአገር ውስጥ ባለሀብቶችን ማገዝ የመንግሥት ተግባራት ናቸው፤›› ያሉት ኤስኮላኖ፣ በጊዜዊነት በተለይ ከውጭ በሚገባ የጥሬ ዕቃ ላይ የተመሠረቱ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንቶች የተቀዛቀዘ አፈጻጸም እንደሚኖራቸው፣ የውጭ ኢንቨስትመንቱ ተጠቃሚነትም በጊዜያዊነት እንደሚቀዛቀዝ ይጠበቃል ሲሉ አብራርተዋል፡፡ ይህ ግን አገሪቱ በውጫዊ በኩል ያለባትን ጉድለት እስክታሻሽል እንደሚሆን ጠቅሰዋል፡፡ በመካከለኛው ጊዜ ይህ ሊሻሻል እንደሚችል በተለይም በመሠረተ ልማት መስክ የሚደረጉ ኢንቨስትመንቶች ከፍተኛ ገቢ ሊያስገኙ እንደሚችሉ የአይኤምኤፉ ባለሙያ ያምናሉ፡፡

የቻይና ኢኮኖሚ መቀዛቀዝ በኢትዮጵያ ላይ ያለው ተፅዕኖ

ኢትዮጵያ የንግድ ሸሪኮቿ ከሆኑት አገሮች ይልቅ ከፍተኛውን የገቢ ንግድ እንቅስቃሴዋን ቻይና እንደያዘች ይታመናል፡፡ በበርካታ መስኮች ቻይና ለኢትዮጵያ ታላቅ አጋር መሆኗን የሚያስገነዝቡት ኤስኮላኖ፣ ትልቁን የገቢ ንግድ ቻይና መቆጣጠሯንም አስረግጠዋል፡፡ በኢንቨስትመንት መስክም የቻይና ተሳትፎ እ.ኤ.አ. በ2003 ከባዶ ተነስቶ እ.ኤ.አ. በ2013 ከ800 ሚሊዮን ዶላር በላይ ያስመዘገቡ ልዩ ልዩ የቻይና ኢንቨስትመንቶች በኢትዮጵያ መመዝገባቸውን አጣቅሰዋል፡፡ ቻይና ትልቋ የፋይንስ ምንጭ በመሆንም የኢትዮጵያን መንግሥት በገንዘብ እየደገፈች የምትገኝ አገር መሆኗም ትኩረት ተሰጥቶታል፡፡ በኃይል ማመንጨት፣ በቴሌኮምና በመሳሰሉት መስኮች ቻይና በኢትዮጵያ ጉልህ ሥፍራ በመያዟ፣ በቻይና የሚታየው የኢኮኖሚ መቀዛቀዝ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ ሊሳድር የሚችለው ተፅዕኖ በእነዚህ ምክንያቶች የተነሳ ግልጽ መሆኑን ኤስኮላኖ ያምናሉ፡፡

የኢኮኖሚ ትንበያ

በድርቁና በዓለም የሸቀጥ ገበያ መቀዛቀዝ በዋጋ መቀነስ ሳቢያ የአገሪቱ ኢኮኖሚ በ6.5 ከመቶ ከሰኔ ጀምሮ እንደሚያድግ ወደፊት ወደ 7.5 ከመቶ እንደሚያድግ እንዲሁም አገሪቱ ከፍተኛ ዕድገት ከሚያስመዘግቡ አገሮች ተርታ እንደሚመደቡ፣ በዘላቂነትም የኢኮኖሚውን ዕድገት በማስጠበቅ፣ የድህነት ቅነሳ መታየቱ የመሳሰሉት ከአፍሪካ ባሻገር በዓለም ደረጃ አገሪቱን በመልካም እንደሚያስነሳት ኤስኮላኖ አስታውቀዋል፡፡

ይህንን ሁሉ ማብራሪያ ሲያቀርቡ፣ በአገሪቱ ካለፈው ዓመት ጀምሮ ሲከሰት የቆየው ፖለቲካዊ ቀውስ ኢኮኖሚው ላይ ሊያሳድር የሚችለው ተፅዕኖ ይኖር እንደሁ ምንም ሳይጠቅሱ አልፈዋል፡፡ በአገሪቱ የሚታየው በድሃውና በሀብታሙ መካከል ያለው የኑሮ ልዩነት ከሌላው ዓለም አኳያ ሲመዘን ዝቅተኛ መሆኑ ለአገሪቱ ጥሩ ተብለው ከሚጠቀሱ ተርታ እንደሚመደብ የገለጹት ኤስኮላኖ፣ ይህም ቢባል ግን አገሪቱ የቱንም ያህል ብታድግና ድህነትን እየቀነሰችም ብትሆን አሁንም ድሃ ከሚባሉ አገሮች ተርታ ናት ብለዋል፡፡ የአገሪቱ የነፍስ ወከፍ ገቢ በአማካይ ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት አኳያ ሲታይ በቀን ሁለት ዶላር በታች ሆኖ ይገኛል፡፡ ይህም አገሪቱን አሁንም በድሃ አገሮች ምድብተኛነት አስፈርጇታል፡፡

ከአንድ ወር በፊት የአፍሪካ የዓለም ገንዘብ ድርጅት መሥሪያ ቤትን እንዲመሩ በዋና ዳይሬክተሯ ክርስቲያን ላጋርት የተሾሙት አቶ አበበ አዕምሮሥላሴ፣ ይህንን ሹመት በተረከቡ በአንድ ወራቸው ከሰሐራ በታች የአፍሪካ አገሮችን በሚመለከት አዲስ ሪፖርት ከሰሞኑ ይፋ አድርገዋል፡፡ በዚህ ቀጣና ከሚገኙ መካከል 20 አገሮች የተሻለ የኢኮኖሚ ዕድገት እያስዘመገቡ ቢሆንም በነዳጅ ዋጋ መቀነስና በሸቀጦች ዋጋ መውረድ እየተጎዱ እንደሚገኙ፣ በዚህም የአብዛኞቹ አገሮች የዕድገት ጉዞ ላይ ጫና እያሳደረ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል፡፡

በግጭትና በፖለቲካ አለመረጋጋት አገሮች ችግር ውስጥ እንደሚገኙም ጠቅሰዋል፡፡ እነዚህ አገሮች ትልቅ ፈተና ውስጥ ይገኛሉ ያሏቸውና ትኩረት የገንዘብ ድርጅቱን ክትትል ያሻሉ ከተባሉት ውስጥ አንጎላ፣ ናይጄሪያና ደቡብ አፍሪካ አይኤምኤፍ ትኩረት የሚሰጣቸውና ትልቅ የኢኮኖሚ መዋዠቅ ውስጥ የሚገኙ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡ ኢትዮጵያን በዚህ መስክ ባይጠቅሱም ሱዳን፣ ቡሩንዲ፣ ቻድና የመሳሰሉትን ጠቅሰው ቢሆንም፣ በአፍሪካ የግጭት መጠን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

መንግሥት በበኩሉ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ከስምንት ከመቶ በላይ እያስመዘገበ እንደሚያድግ ያምናል፡፡ ይልቁንም የድርቁም ሆነ የዓለም የሸቀጥ ንግድ መቀዛቀዝ በኢትዮጵያ ላይ ያሳደረው ጫና ከሚገባው በላይ ተጋኗል ይላል፡፡ በቅርቡ ይህንን ሐሳብ ያንጸባረቁት፣ የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትር ዴኤታው አቶ አህመድ ሺዴ ናቸው፡፡ አቶ አህመድ አፍሪካ ዓመታዊ ኢኮኖሚ ሪፖርት ይፋ በተደረገበት ወቅት በድርቅና በሸቀጥ ንግድ መቀዛቀዝ ምክንያት የአገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ትንበያ ወደ ታች እንዲቀንስ መደረጉን ተቃውመዋል፡፡ ይህም ሆኖ መንግሥት ያስቀመጠው ትንበያም ቢሆን ወደ 8.5 ከመቶ ዝቅ ለማድረግ መገደዱን ግን አምነዋል

SOURCE     –   ETHIOPIAN REPORTER

Leave a Reply