ታዋቂው ኢትዮጵያዊ የዕፀዋት ሳይንቲስት ፕሮፌሰር ሰብስቤ ደምሰው የዘንድሮ የእንግሊዝ የሮያል ቦታኒክ ጋርደንስ ኪው (Royal Botanic Garden, Kew) ዓለም አቀፍ ሽልማት ተሸላሚ ሆኑ፡፡

ኪው ኢንተርናሽናል ሜዳልያ በያመቱ ለግሰለቦች የሚሰጥ ሽልማት ሲሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ የታወቀ ሥራን ላከናወነና ከሮያል ቦታኒክ ጋርደንስ፣ ኬው ተልዕኮ ጋር ስምም የሆነ ተግባር ለፈጸሙ የሚበረከት ነው፡፡

የኢትዮጵያን ብዝኃ ሕይወትን ለረዥም ጊዜ በማጥናትና በመመርመር ኅብረተሰቡም ሆነ አገሪቱም ከዘርፉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በዓለምም እንዲታወቅ ለማድረግ ያከናወኑት ተግባር ፕሮፌሰር ሰብስቤን ለሽልማቱ አብቅቷቸዋል፡፡

በሥነ ዕፀዋት (Botanic Science) ምርምርና ጥናት ግንባር ቀደም እንደሆኑ የሚነገርላቸው ፕሮፌሰር ሰብስቤ የኢትዮጵያ ፍሎራ ፕሮጀክትን ከ1988 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ 2001 ዓ.ም. ድረስ ከ17 የአፍሪካና የአውሮፓ አገሮች የተወጣጡ የዕፀዋት ተመራማሪዎችን በመምራት ስኬታማ ተግባር ማከናወን ችለዋል፡፡

የሽልማት ሥነ ሥርዓቱ አዲስ አበባ በሚገኘው የእንግሊዝ ኤምባሲ ጥቅምት 11 ቀን 2009 ዓ.ም. የተከናወነ ሲሆን፣ የሜዳሊያ ክብሩን የሚቀበሉት በለንደን ከተማ በመጪው ጥር ወር እንደሚሆንና ዲስኩር እንደሚያሰሙ ታውቋል፡፡ የሮያል ቦታኒክ ጋርደን ኪው የሳይንስ ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ካቲ ዊልስ በአዲስ አበባው ሥነ ሥርዓት ላይ መልዕክታቸውን ያስተላለፉት ‹‹ፕሮፌሰር ሰብስቤ በሥነ ዕፀዋት መስክ ከፍተኛ ተጽእኖ ፈጣሪና የላቁ መሪ በመሆናቸው እንደሳቸው ዓይነት ሰብእና ያለውን እውቅናና ሽልማት መስጠት እንሻለን፤›› በማለት ነበር፡፡

ፕሮፌሰር ሰብስቤ ባካሄዱት ሳይንሳዊ ምርምር ዕፀዋት በሰዎች ሕይወት ላይ ያላቸውን ሚዛናዊ ሚናና ጥቅም ማሳየት መቻላቸው ውጤታማ እንዳደረጋቸውና በአገር በቀል ዕፀዋት ላይ ያዘጋጁት ሥራ ለየአካባቢው ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረውም ዳይሬክተሩ አክለው ገልጸዋል፡፡

በሥነ ዕፀዋት ምርምር ላከናወኑት ተግባር ለዓለም አቀፍ እውቅናና ሽልማት መብቃታቸው እንዳስደሰታቸው የገለጹት ፕሮፌሰር ሰብስቤ በኢትዮጵያ የሚገኙ ዕፀዋት መልክአ ምድራዊ ሥርጭት፣ ዓይነትና መጠንን በጥልቀት የሚፈትሽ ጥናት ሠርተዋል፡፡

ፕሮፌሰሩ በግላቸው በጋራ ከሠሯቸው ከብዝኃ ሕይወት ጋር የተያያዙ የምርምር መጻሕፍት መካከል “Aloes and Other Lilies of Ethiopia and Eritrea”፣ “Aromatic Plants of Ethiopia”፣ “Atlas of the Potential Vegetation of Ethiopia”፣ “Ethiopian Orchids”፣ “Field Guide to Ethiopian Orchids” ይገኙበታል፡፡

ፕሮፌሰር ሰብስቤ በቀጣይ ከሚሠሯቸው ምርምሮች በተጓዳኝ በኢትዮጵያ የሚገኙ ዕፀዋትን በድረ ገጾች በማስተዋወቅ ረገድ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በቅንጅት ለመሥራት ፍላጎቱ አላቸው፡፡

ሽልማቱ ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገጽታ ግንባታ ዓይነተኛ ሚና እንደሚጫወት የተናገሩት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር አድማሱ ፀጋዬ፣ ፕሮፌሰር ሰብስቤ ለብዝኃ ሕይወት ልማት ያበረከቱት አስተዋጽዖ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለመላው አፍሪቃ ጭምር ነው ብለዋል፡፡

በደቡባዊ ምዕራብ ለንደን የሚገኘውና የተለያዩ ዕፀዋትን ያሰባሰበው ሮያል ቦታኒክ ጋርደንስ (ብሔረ ጽጌ) እ.ኤ.አ. በ2003 በዩኔስኮ (የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት) በዓለም ቅርስነት የተመዘገበ ነው፡፡

እ.ኤ.አ. በ1759 የተመሠረተውና በአበቦችና ዕፀዋት መናኸርያነቱ (ብሔረ ጽጌ) እንዲሁም በቱሪስት መዳረሻነቱ የሚታወቀው ሮያል ቦታኒክ ጋርደንስ ከ18ኛው እስከ 20ኛው ምእት ዓመት ድረስ የነበሩና ያሉ አትክልትና ዕፀዋት ተሰባስበው ይገኙበታል፡፡