(ክፍል አንድ)

ውድ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ

ለጤናዎ ባያሌው እንደምን ሰነበቱ? ድምፆቻችንን ከተሰማማን ብዙ ጊዜ ሆነን ኣይደል? እኔ ለጤናዬ እግዚአብሄር ይመስገን ደህና ነኝ፡፡ ርስዎን እንደ አላመምዎት ተስፋ አደርጋለሁ;;

የእኔን አዲስ መጽሃፍ አስመልክቶ ርሰዎ ስተለተቹት ከመመለሴ በፊት፣ የተከበሩት ሊቀ-ሊቃውንት መሪራሰ አማን በላይ ለአንባብያን አስተላልፍላቸው ዘንድ የሰደዱልኝን የአደራ መልእክት አቀርባለሁ፡፡ ከዛ በሁዋላ ወደ ራሴ ምላሽ እሸጋገራለሁ፡፡  ለአንባብያን የተላከ የመሪራሰ አማን በላይ መልእክት እነሆ—

ይድረስ ይህን ለምታነቡ ሁሉ የሃገሬ ሰዎች፣

የተወለድኩት፣ የአደግኩትና የተማርኩት በዛው በጎንደርና በጎጃም ነው፡፡ የትውልዴ ስፍራ በለሳ ነው፡፡ አባቴ መምህር በላይ ድሉ ካህን ነበሩ፡፡ ከውድ አባቴ ከ መምሀር በላይ፣ከአባ ጼሄማ በጎንድ ተክለሃይማኖት፣ ከመሪጌታ መንክር ደብረኤልያስ ጎጃም፣ ከመሪጌታ ጉባኤ በዛው በጎጃም፣ ቅዳሴን፣ ቅኔን፣ ዜማን፣ ብሉይን፣ ሃዲስን፣ የእንጨት አዋጅን (የመድሃኒት እጽዋትን)፣ የሃረግ ስእልን፣ የኢትዮጵን ታሪክ፣ አቡሻህርን (ባህረሃሳብን)እና ሌሎችንም በአድባራት እና ገዳማት የሚሰጡ የኢትዮጵያን ትምሀርቶችን በሚገባ ተምሬአለሁ;; በለተይ በቅኔ፣ በግስ ርባታ እና ሰዋስው ችሎታዬ በመምህራኔ እና የትምሀርት ባልንጀሮቼ ስሜ የተጠራ ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት በጎጃም በይስማ ደጀን በመሪጌታ መንክር ዘንድ ቅኔ አስነጋሪ ነበርኩ፡፡ ተማሪ ሳለሁና ትምሀርቴንም ካጠናቀቅኩ በሁዋላ ኢትዮጵያ ውስጥ እየተዘዋወርኩ አያሌ ገዳማትን እና አድባራትን እየጎበኘሁ በውስጣቸው የአሉትን ምሰጢራዊና ጥንታዊ መጻህፍቶቻችንን ለመመርመር እድል አግኝቻለሁ;;

የ 18 ዐመት ልጅ ሁኜ ወደ ኑበያ (ሱዳን) ተጉዤ በነበረበት ወቅት በአንድ በፈራረሰ ጥንታዊ የኢትዮጵያ ቤተክተርሰትያን ቅጥር ግቢ በተቀበረ የድንጋይ ሳጥን ውስጥ ምናልባት ኢትዮጵያ ውስጥ የሌሉ የኢትዮጵያን ታሪክ ጨምሮ ስለተለያዩ ጉዳይዎች የሚዘረዝሩ በግእዝ የተጻፉ የብራና መጻህፍትና ጥቅሎች አገኘሁ፡፡ ይህ የሆነው የዛሬ 50 ዐመት አካባቢ ነበር;፡፡ እነዛን መጻህፍት ይዤ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሼ ከነሱ ውስጥ አውጣጥቼ አሳጥሬና መጥኜ የኢትዮጵያ ትንሳኤ ታሪክ በሚል ርእስ እንድ መጽሃፍ ጽፌ ለማሳተም ሞክሬ ነበር፡፡ ሆኖም ዶክተር ኃይሉ ወልደአብ የሚባሉ ሀቀኛ ሙሁር ብራናዎቹን መርምረው፣ ይህ አንተ የጻፍከው መጽሃፍ እውነተኛው ታሪካችን በመሆኑ እሰከዛሬ የተጻፉትን ስለሚቃረን ችግር ይደርስብሃል፤ ስለዚህ አቆየው፣ ብለው መከሩኝ፡፡ እኔም ቀና ምከራቸውን ሰምቼ የደርግንም የሽብር ዘመን አሳልፌ፣ መጽሃፉን በሚስጥር አቆይቼው ኖሬ የዛሬ 24 ዐመት አካባቢ በድፍረት አሳተምኩት፡፡  ከዛ በሁዋላ በብርቅዬዎቹ ብራናዎች ላይ ተመርኩዤ አያሌ መጻህፍትን እያከታተልኩ አወጣሁ፡፡  በወቅቱ በደረሰኝ መረጃ መሰረት ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ የእኔን መጻህፍት ከማንበብ አልፈው ከነሱ ውስጥ እየጠቀሱ በአደባባይ ተጠቅመውባቸውል፡፡  ዘግይተውም ብራናዎቹን እጃቸው ለመክተት የሁለታችንም ወዳጅ የሆነውን ላይብረሪ ኦፍ ኮንግረስ የሚሠራውን አቶ ፈንታሁን ጥሩነህን እና ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳን አማላጅ ልከው እባክህ ብራናዎቹን ልመርምራቸው፣ አሉኝ፡፡

እኔ ግን ከዚህ በፊት ሌሎች ምሁራን ነን የሚሉ ሰዎች እንደዚሁ ብራናዎቹን  አሳየን ብለውኝ ባሳያቸው ሊወስዱብኝ ሞክረው ስለነበር ከስህተቴ ተምሬ ብራናዎቹን ለፕሮፌስር ጌታቸው ኃይሌ ለመስጠት አልፈቀድኩም፡፡ ደግሞም ንብረቶቹ የኔ የግሌ ስለሆኑ የራሱን ንብረት ለደቂቃስ ቢሆን ያለዋስትና ማን ለማን ይሰጣል? ከዚህም በተጨማሪ ታሪከ-ነክ እና ባህረሃሳብን ጨምሮ ፕሮፌሰሩ የጻፉአቸውን መጻህፍት ሳነብ ምንም የታሪከ አውቅት የሌላቸውና የግእዝ ችሎታቸውም ደረጃ በጣም ዝቅ ያለ ሆኖ ስለአገኘሁት፣ በባህረሃሳባቸውም ውስጥ ከባድ ስህተት ፈጽመው ስለዐየሁአቸው የእኔን የግእዝ ብራናዎች፣ ያውም በጥንታዊ ግአዝ የተከተቡትን ተረድተው ለመፍረድ በጣም እንደሚያስቸግራቸው ተከሰተልኝ፡፡  ከዚህም በላይ፣ እኚህ ግለሰብ ሊቃውንት አባቶቻችንን ኢትዮጵያውያንን ስለሚንቁና አረቦችን፣ ግሪኮችንና አውሮጵያውያንን እያወደሱ ‹‹አባቶቻችን‹‹ ስለሚሉ ለኢትዮጵያውያን የአላቸው ፍቅር እና ከበሬታ አጠራጣሪ ሆነብኝ፡፡ በመጨረሻም፣ ሰውየውን ስለማላምናቸው በቀላሉ የማይገኝ ንብረቴን ከእጄ ማውጣት ጨነቀኝ፡፡ የማላምናቸውም፣ የገቡበትን ሁሉ ድርጅት አፍርሰው የሚወጡ ናቸው፣ ሲሉ ስለሰማሁና የኑሮ መተዳደሪያቸውም ፈረንጆች በርካሽ ገዝተውም ሆነ ሰርቀው ያከማቹአቸውን የኢትዮጵያ ብራናዎችንና ቅርሶችን መመዝገብና ማቀናጅት ነው ስለተባለ ነው፡፡ ይህ በመባሉም እኔ ያገኘሁአቸውን ለትውልድ ላስተላልፍ ያቀድኩአቸውን ብርቅዬ ጥንታዊ ብራናዎች ለእኚህ ሰው ይመርምሩ ብዬ ሰጥቻቸው የደለበ ደሞዝ ለሚከፍሉአቸው ፈረንጆች እሳቸው ቢዳርጉአቸውና እነዛ ፈረንጆች በውድ ዋጋ ቢሸጡአቸው ወይም ብራናዎቹ በሚመሰክሩት የኢተዮጵያ ታላቅነት ፈረንጆቹ ቀንተው ቢያጠፉት አለዛም ለኢትዮጵያ ጠላቶች አሳልፈው ቢሰጡአቸው የማን ያለህ ልል ነው፣ በሚል ስጋት ስለተጨነኩም ነበር;;

እንግዲህ እላይ በተጠቀሱት ምክንያቶች ብራናዎቹን ስለከለከልኩአቸው ፕሮፌሰሩ ተናደው አማን በላይ ምንም ብራናዎች የለውም፤ ይህን ሁሉ መጽሃፍ የሚጽፈው ከልቡ እያፈለቀ ነው፣ እውነት ለማስመሰልም ከኢትዮጵያ ታሪክ ያጣቅሳል፤ ብለው በሃስትና በድፍረት ውሸታምና አጭበርባሪ አድርገውኝ ስሜን አጥፍተዋል;; እሳቸው በኔ ላይ ላደረሱብኝ የስም ማጥፋት እግዚአብሄር ይበቀልልኛል፡፡ ካህኑ የእግዚአበሄር አገልጋይ አባቴ መምህር በላይም ሆነ በየደብሮቹና ገዳማቱ የነበሩት ቅዱሳን መምሀሮቼ ከቶውንም ውሸት እንዳልናገርና ለእውነት ብቻ እንድቆም በግበረገብነት እያነጹ አሳድገውኛል፡፡ ስለዚህ ልብወለድ ጽፌ የኢትዮጵያ ታሪክ ነው ብዬ አላቀርብም፡፡ የጻፍአኩቸው ሁሉ መጻህፍት እውነተኛ የኢትዮጵያ ታሪክ ናቸው፡፡  በእኔ ዘንድ የሚገኙትን ብራናዎች ግን ለደህንነታቸው አስተማማኝ ጊዜ ሲደርስ የኢትዮጵያና የዐለም ጋዜጠኞች፣ እንዲሁም ሀቀኛ የሃገራችንና ዐለምአቀፍ ምሁራን በተገኙበት ሸንጎ ላይ ለባህል ሚኒሰቴር፣ ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ወይም ለቤተመጻህፍት ወ መዘክር አስረክባለሁ፡፡  ታዲያን በዛን ጊዜ ዋሾው እኔ ልሁን ፕሮፌሰር ጌታቸው ይለያል፡፡ እግረመንገዴን ግን አንድ ነገር መግለጽ እሻለሁ;;— ከኑብያ ካገኘሁአቸው መጻህፍት ውስጥ ታሪከ-ነገሥት ዘ ኢትዮጵያን ለ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኬኔዲ ቤተመጻህፍት እና የሱባንና የግዕዝ መዝገበቃላትን ለ ቤተመጻህፍት ወ መዘክር አንዳንድ ቅጂዎች አበርክቻለሁ፡፡ ዳሩ ግን ይህን ቁምነገር ብዬ በአዋጅ አላስነገርኩም፡፡ የብራናዎቹን ቅጂዎች በመስጠቴ ቤተመጻህፍት ወ መዘክር መቀበሉን የሚያንጸባርቅ የምስክር ወረቀት ሲሰጠኝ የኬነዲ ቤተመጻሀፍት ግን አመሰግናለሁ እንኩዋን አላለኝም፡፡

የ እኔ ሳያንስ፣ፕሮፌሰር ጌታቸው ውሸታም የአደረጉትና በአደባባይ የዘለፉት ሃገሩን ኢትዮጵያን የሚወደውን፣ በጎሰኝነት ጎራ ፍጹም ተሰልፎ የማያውቀውን፣ በሰብእናው ልእልና እና በምሁርነቱ ርቅቀት እጅግ የማከብረውን ወዳጄን ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳን ጭምር ነው፡፡ ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳም ልብወለድ ወይም (ሚት) አልጻፈም;; ከኔ መጻህፍት በተጨማሪ በ 42 በተለያዩ የታሪክ ዋቢ መጻሃፍት ላይ ተንተርሶ ነው፡፡ ከዚህ በፊት አኔም ሆንኩ ሌሎች ባለታሪኮች ያልደረሱትንና ያልደረሱበትን የሀገራችንን አደገኛ ውጥረት የሚያረግብ መጽሀፍ የጻፈው፡፡ ስለዚህ የኦሮሞ እና የአማራ እውነተኛው የዘር ምንጭ የተሰኘው መጽሃፉ የርሱ የራሱ፣ ላቡን አንጠፍጥፎ፣ እውቀቱን ጨምቆ፣ የጻፈው የታሪክ መጽሃፉ ነው፡፡ ይህም እጅግ የሚያስመሰግነው ድንቅ ሥራው ከዚህ ቀደም ያልነበረ ወሪጅናል እንደሆነ በዚህ አጋጣሚ ላረጋግጥ እወዳለሁ፡፡

በመጨረሻ ለፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ፣ አማን በላይ ምንም ከሱዳን የተገኘ መጽሃፍ የለውም፣ ከልቦናው አንቅቶ ነው የሚጽፈው፤ ስለአልከው፣ ከዚህ ቀደም  ለፕሮፌሰር ፍቅሬ በፍላሽ ድራየቭ ሰጥቼው ከነበረው ኑብያ ውሰጥ ካገኘሁት ጥንታዊ የብራና መጽሃፍ ላይ ጥቂት ገጾች ለናሙና እንዲያሳይ ስለፈቀድኩለት ከኮምፒተሩ ላይ ያለችግር ከታተመለት ለአንባብያን ያቀርበዋል፡፡ በኑብያ ካገኘሁአቸው መጻህፍት መሃል በቅርብ የተገኘው ይህ ብቻ ስለሆነ ነው ለጊዜው ይሀን ለህዝብ አቅርብ ያልኩት፡፡ ሌላው ጊዜና ቦታው ሲፈቅድ ለኢትዮጵያ ህዝብ ይቀርባል;;

ፕሮፌሰር ጌታቸው አዳምጥ፣— እኔና የግዕዝ ሊቃውንት በተለያዩ ጊዜያት የግዕዝ ችሎታህን እንደገመገምነው በጣም ደካማ ነው፡፡ ከልምምድ ብዛት ያካበትከው እንጂ በቅጡ የተማርከው አይደለም፡፡ ግዕዝ ለማያውቁ ሰዎች ግዕዝ የምትችል መስለህ ትታያቸው ይሆናል፡፡ ባህረሀሳብ ባልከው መጽሀፍ ውሰጥ እንኩዋን ግዙፍ ግዕዛዊና ቀመራዊ ስህተቶች ሠርተሃል፡፡ የአንተን ባህረሀሳብ ምንነት፣ ምንጭና ስህትት አስመልከቶ የጻፍኩት ራሱን የቻለ መጽሀፍ ስለማወጣ ነቀተህ ተጠባበቅ፡፡ አሁን ለጊዜው ግን፣ በርካታ ብራናውን ተወውና እስቲ እነዚህን ፕሮፌስር ፍቅሬ ለናሙና ያቀረባቸውን የግእዝ ገጾች ወደ አማርኛ ተርጉመህ ችሎታህን አሳየን፡፡ ከዛ በሁዋላ ስለ ሌሎቹ መጻህፍት እንነጋገራለን፡፡ በመጨረሻም፣ መሪራሰ አማን በላይን እኔ ወደ እኔ ና ብዬው ሳይመጣ ቀረ ስለ አልከኝ ከኔ አንድ ነገር ለማግኘት የፈለግከው አንተ ስለሆንክ ወደ እኔ መምጣት የነበረብህ አንተ ነህ፡፡ አንተ ትፈልገኛለህ እንጂ ለእኔ አታስፈልገኝምና;; ለጊዜው በእዚሁ ልሰናበትህ፡፡

መሪራስ አማን በላይ፣

ጸሀፌ-ታሪክ

እኤአ ታህሳስ 21 ቀን 2016

 

ውድ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ፣ ከዚህ በታች የሰፈረው ደሞ እኔ ፍቅሬ ቶሎሳ ለ እርስዎ የጻፍኩት ነው;;

የኦሮሞ እና የኣማራ እውነተኛው የዘር ምንጭ በሚል ርእስ የከተብኩትን የታሪክ መጽሀፌን ዐፈታሪከ ነው፣ ብለው እርስዎ ለእርስዎ ድክመቶች የመሰለዎትን ነጥቦች ብቻ እየነቀሱ እና እየቆነጸሉ በማውጣት አስፍረዋል፡፡ ይህ የጻፉት ነገር ወይ ምሁራዊ ግምገማ አይደል፣ ወይ ትንተና አይባል፣ ወይ የመጽሃፍ ማስተዋወቂያ ተብሎ አይፈረጅ፣ እንዳው መላ ቅጡ የጠፋው በቂም በቀል መጽሃፉን ለማጠልሸት የተወረወረ ድንጋይ ነው፡፡ አርእስቱ ራሱ አንባቢን የሚያታልል ነው–

‹‹የፕሮፌሰር ፍቅሬ አስተዋጽኦ‹‹ ይላል፡፡ አንባቢው ወደውስጥ ሲገባ ግን አርእስቱ አንባቢን የመሳቢያ ወጥመድ እንደሆ እና ይዘቱ ሸረኛ እንደሆነ ይረዳል፡፡ እኔ ለጽሁፌ ማስደገፊያ 47 መጻህፍትን አስፍሬአለሁ፡፡ ከእነሱ ውስጥ የመሪራስ ኣማን በላይ 5 ብቻ ናቸው፡፡ እርስዎ ግን የሳቸውን ብቻ የጠቀሰኩ አስመስለው ትችቶን
ሆነ ብለው በሳቸው ሥራዎች ላይ ብቻ አቀረቡ፡፡ የእሳቸውንም መጻህፈት ቢሆን እኔ ሳልመረምር በዐይን ጭፍን አልተጠቀምኩባቸውም፡፡ በሚገባ መርምሬአቸው ከህሊናዬ ተሙዋጉቼ ሳበቃ እነሱን በሌሎቹ መጻህፍት አመሳክሬ፣ አንጥሬና አበጥሬ አሳማኝ መደምደሚ ላይ ደርሼ ነው፡፡ ሰውዬው ሊቅ ስለሆኑ የኢትዮጵያን ታሪክ ከታች እስከላይ፣ ከቀንዱ እሰከ ጭራው፣ ጠንቅቀው የሚያውቁ ናቸው፡፡ ይህም እውቀታቸው ጠሊቅ ሊሆን የበቃው እና በርካታ የታሪከና የጥበብ መጻሀፍትን ሊደርሱ የቻሉት፣ ከህጻንነታቸው ጀምሮ አድሜልካቸውን በኢትዮጵያ ትምህርት ቤቶች፣ ደብሮችና እና ገዳማት እየዞሩ አእምሮአቸውን ስለ አነጹት ነው፡፡ በዛ ላይ በጀበል ኑባ፣ ኑብያ ያገኙአቸው ብርቅዬ ብራናዎች ተደምረው ልሂቅ ባለታሪክ ለመሆን በቅተዋል፡፡ እንጂ አርስዎ አለአግባብ ጨዋነት በጎደለው መልኩ እንደሚዘልፉአቸው የአፈታሪክ ጸሃፊ አይደሉም፡፡ በእውነቱ እርስዎ ክብርን እጅግ የሚሹ ሰው ሆነው ሳሉ ሌሎች ትልልቀ ሰዎችን በድፍረት ለመዘርጠጥ የማያፈገፍጉ ሰው ነዎት፡፡ እርስዎ እንደሚሉት መሪራስ አማን በላይ የከተብዋቸው ከ ዐስር በላይ ብርቅዬ መጻህፍት የአፈታሪክ ወይም የልብ ወለድ ከሆኑ በክሀሎታቸው ከነ ሆመር፣ ከነ ዳንቴ፣ ከነሼክስፒር እና ቶልስቶይ ይበልጣሉ ማለት ነው፡፡ ሰለዚህም አንድ ሳይሆን ሁለት የስነጽሁፍ ኖቤል ፕራይዝ ሽልማቶች ይገባቸዋል፡፡  አኚህ ሰው እጃቸው ውስጥ የከበሩ ጥንታዊ ብራናዎች እንደ አሉ ርስዎም ጠንቅቀው ያውቃሉ፡፡ ለዚህም ማስረጃው የራስዎ ምስክርነት ነው;; በአንድ ወገን መሪራስ አማን በላይ ከሱዳን አገር ያገኘው ምንም ብራና የለም፣ ፈጥሮ ነው የሚደርስው ይላሉ፡፡ እሳቸው መጽሃፍ ሲያሳትሙ ግን ርስዎ ተሽቀዳድመው መጻህፍታቸውን በ እጅዎ ይከታሉ፡፡ ስለ እኔም መጽሃፍ ‹‹ልብወለድነት‹‹ ርስዎ በጫጫሩት ላይ ከፍ ብለው አማን በላይ ከሱዳን አገር ያገኘው ምንም ነገር ስለሌለው ነው እንጂ፣ ቢኖረው ኖሮ እኔ የማውቃቸው ፈረንጆች መርምረውት ምንነቱን ባረጋገጡት ነበር፣ ይላሉ፡፡ እንዳው ለነገሩ ብራናውን ሳያዩ ፈረንጆቹ እንዴት ይመረምሩታል? ቀድሞ ዐጠገቡ መች ደረሱ? ፈረንጆቹ ስለአልበሉት ምግብ ጣእም እንዴት ይመሰክራሉ? ደሞስ ለፈረንጅ ምስክርነት ማን ግድ አለው? ርስዎ እንጂ እኔና መሪራስ አማን በላይ ለፈረንጅ ምሰከርነት ግድ የለንም:: ታሪካችንን እኛ ለፈረንጅ እናስተምረዋለን እንጂ ፈረንጅ አያስተምረንም፡፡ በዛው በኔው ትችት ላይ ዝቅ ብለው ደግሞ መሪራስ አማን በላይን አንተ ያገኘከውን ታሪከ ነገሥት ለታሪክ መርማሪዎች አሳይ፣ ብለው ይመክሩአቸዋል;; ማስረጃው የርስዎ የራስዎ ቃል እነሆ፡፡ እጠቅሶታለሁ-

“በመጨረሻ፥ ለመሪራስ አማን በላይ አንድ ጥያቄ ላቅርብ፤ አንዳንድ የታሪከ ነገሥት ቅጂዎች ተገኝተው ታትመዋል፤ የታተሙት ሁሉ የየራሳቸውን አዳዲስ ነገሮች አስተምረውናል። አንተም ያገኘኸው ታሪከ ነገሥት በአድያም ሰገድ ኢያሱ ዘመን የተቀዳ ስለሆነ፥ አንዳንድ ቅጅ ለአዲስ አበባ ወይም ለደብረ ማርቆስ ዩኒቨርስቲ ልትሰጥ ትችላለህ። መሪራስ ሆይ፤ በጎውን ይምራህ።”

እላይ የሰፈረው የርስዎ ቃል ነው፡፡ ባንድ ወገን አማን በላይም አንተም የጻፋችሁት ልብወለድ ወይም አፈታሪክ (ሚት) ነው፣ አማን ምንም የብራና መጻህፍት የለውም እያሉ፣ መልሰው ደግሞ ‹‹ አንተም ያገኘኸው ታሪከ ነገሥት በአድያም ሰገድ ኢያሱ ዘመን የተቀዳ ስለሆነ፥ አንዳንድ ቅጅ  ለአዲስ አበባ ወይም ለደብረ ማርቆስ ዩኒቨርስቲ ልትሰጥ ትችላለህ። መሪራስ ሆይ፤ በጎውን ይምራህ።” ይላሉ;; እራስዎን በራስ

ዎም ይቃረናሉ፡፡ እጃቸው ውስጥ ብራና ከሌለ ምኑን ነው የሚያስመረምሩት?  ስለዚህ አኚህ ሰው ጥንታዊ የብራና መጻህፍት እንዳገኙ ርስዎ ያውቃሉ ማለት ነው፡፡ ካልሆነም ያምናሉ፡፡ ሃቁ ይህ ሆኖ ሳለ፣ መሪራስ አማን ምንም አላገኘም፣ እሱ እና አንተ አፈታሪከ ነው የደረሳችሁት ብለው በላያችን ላይ ለምን ሃሰት ይነዛሉ? ርስዎን ከሚያህል እድሜ ከጠገበ ሰው ይህን የመስለ ደባ ይጠበቃልን?  እግዚአብሄር ፊት ቀርበው በምድር ላይ ሆነው ስተለተናገሩትና ስለ ሠሩት ሁሉ በእግዚአብሄር የሚጠየቁበት ጊዜ እንደቀረበ አያውቁምን? እውነተኛው የኢትዮጵያ ታሪከ አሁን በኔ መጽሃፍ ውስጥ ተንጸባርቆ በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ህዘብ፣ በተለይ አማራውና አሮሞው ለመግባባትና ለመታረቅ በሚሞከርበት ወቅት በሁለቱም ሆነ በሌሎቹ ህዝቦቻችን መሀል ደም መፍሰስ እንዲቆም ይህ መጽሃፌ በሚረዳበት ሰዐት፣ እርሰዎ በሃቅ ላይ ያልተመሰረተ በግል ቂምዎ ላይ የቆመ አፍራሽ ሃሳብ መሰንዘርዎ አሳዝኖኛል፡፡ ሌሎችም በርካታ ሰዎች በርስዎ ተንኮላዊ ድርጊት ማዘናችውን ገልጸውልኛል፡፡ ምሁርነት እንደዚህ ነውን? የመሪራስ ብራናዎች ጉዳይ ርሰዎን ለምን እንደሚያብከነክኖትና እንደሚያበግኖት ምስጢሩን ለማያውቀው አንባቢ ኣሁን አብራራዋለሁ፡፡ በውነትም መሪራስ አማን በላይ ከኑበያ፣ ሱዳን የአገኙአቸው ብራናዎች እንዳላቸው እላይ በተቀመጠው ንግግሮ ራስዎ አረጋግጠዋል፡፡ አኔም ከዚህ በታች በማስፍረው እሳቸው ከዛው ከኑብያ ከአገኙአቸው ጽሁፎች መካከል አንዱ በሆነው ጥቂት ገጾች አረጋግጣለሁ፡፡; ይህ ጥንታዊ መጽሀፍ ገጹ 333 ቢሆንም በፍላሽ ድራይቭ ከተጫነው ኮምፒተር ላይ ለማውረድ ስላልተመቸኝ ለጊዜው እታች የሰፈሩትን ኮምፒተሩ የፈቀደልኝን ቅጠሎች ብቻ  ለአንባብያን አስቀምጫለሁ፡፡ ለኔ በገባኝ አነስተኛ የግእዝ ችሎታዬ እንደምረዳውና መሪራስ አማን መጽሃፉን በሰጡኝ ጊዜ የነገሩኝን እንደማስታውሰው፣ መጽሃፉ የሚዘግበው ጌታችን መድሃኒታችን እየሱስ ክርሰቶስ ከሙታን መሃል ተለይቶ ከተነሳ በሁዋላ በነበሩት 40 ቀናት ለደቀመዛሙርቱ፣ በተለይም ለማቴዎስ፣ ለማርቆስ፣ ለዮሃንሰ ወልደዘብዴዎስ፣ ለቶማስ እና በሁዋላም ለሉቃስ ስለ ቤተክርሰትያን አስተዳዳሪዎች ስርዐት የአስተማራቸውን የሚያትት ነው፡፡ በተለይ ኤጲስቆጶሳትና ጳጳሳት ከፈለጉ ሚስት ማግባት መቻላቸውን እየሱስ ክርሰቶስ ይፈቅዳል;; ይህ መጽሃፍ፣ ንስጥሮስ ምንኩስናን ከማስተዋወቁ በፊት ይህ የጌታችን እየሱስ ከርስቶስ አስተምህሮ ወደ ኢትዮጵያ መግባቱን ይመሰክራል;; እየሱስ ክርስቶስ እነዚህን የቤተክርስትያን ሹማምንት ማግባት ከፈቀደላቸው ታዲያ ለምንድነው የማያገቡት? መነኮሳት ንስጥሮስን ነው የሚከተሉት ወይንስ እየሱስን? የሚል ጥያቄ ያስነሳል;; መጽሃፉ አነጋጋሪ ስለሆነ ይመስለኛል መሪራስ አማን ሊያሳትሙት ያልቸኮሉት፡፡ ለማንኛውም ቅጠሎቹ እነሆ፡፡ በቀላሉ ከኮምፒተሩ ላወርድ የቻልኩትን ብቻ ስለሆነ ያቀረብኩት ቅደም ተከተሉ ተዘበራርቆአል፡፡ ቅጠሎቹ በተለያዩ ጊዜያትና ብእሮች የተከተቡ ሳይሆኑ አይቀሩም፡፡ ቁምነገሩ የመጽሃፉ ይዘት ሳይሆን መሪራስ አማን በላይ ኑብያ ውስጥ ያገኙት ልዩና ብርቅዬ የብራና መጻህፍት እንደ አላቸው ማሳየቱ ነው፡፡ እታች የሚሰፍሩት ገጾች  ኮፒራይት የመሪራስ አማን በላይ ብቻ ነው፡፡

 

 

 

 

 

 

 

 

ፕሮፌሰር ጌታቸው ሆይ!

እስከከዛሬ ድረስ ስለ አኢትዮጵያውያን ማንነት፣ ስለ ንግሥተ-ሳባና በጠቅላላው ስለኢትጵያ ታሪክ እርስዎ የሚያሰራጭዋቸውን ስህተች በሚመለከት አድሜዎን በማገናዘብ እና ርስዎን በማከበር በአደባባይ ስምዎን ጠርቼ ተናግሬ አላውቅም፡፡ እንደ አላየ ዐይቼ አልፎት ነበር፡፡ አሁን ግን ራስዎ ነገር ፍለጋ ወደ እኔ ስለመጡ የርሰዎን ችግር ለማጋለጥ እገደዳለሁ፡፡ ችግርዎ ራስዎን ከማንም በላይ አዋቂ ማድረግ እና በእኔ እጅ ውሰጥ ያላለፈ እና በኔ ያልተባረከ የብራና፣ የቤተክርስትያን፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ ጉዳይ ዋጋ የለውም፣ አፈታሪክ ነው፣ ማለትዎ ነው፡፡ ቸሩ እግዚአብሄር ግን ለሁሉም ሰው አእምሮ ለግሶአል፡፡ ስለዚህ ሁሉም ሰው በየደረጃው ነገሮችን የመርመር አቅም አለው፡፡ የሰው ልጅ ሁሉ አይናቅም፡፡ እውቀትን ደግሞ ማንም በሞኖፖሊ አልያዛትም፡፡

ትዝ እንደሚልዎት፣የዛሬ 6 ወይም 7 ዐመት አካባቢ ዋሺንግተን ዲሲ ስብሰባ ላይ ተገናኝተን መሪራስን ለማገዝ ስል የሳቸውን መጽሃፈ ዐብሪህትን እና ሌሎችንም መጻህፍቶቻቸውን ሸጨልዎት ሳለ በመሪራስ እጅ ውስጥ የሚገኙትን ብራናዎች እየመረመሩ ወደ እንገሊዝኛ ተርጉመው ለዐለም ሀዝብ እንዲገልጹ መሪራስ አማን በላይ ፍቃደኛ መሆናቸውን ልጠየቅልዎት ወይ ብዬዎት ርስዎም ይህን ቢሆን እንደሚደስቱ አረጋግጠውልኝ ነበር፡፡ ይህን ሃሳብ ራሴው ያቀረብኩልዎት በነዚህ አስደናቂ ብራናዎች ምክንያት ሃገራችን እንድትከበር በጎውን አስቤ ነበር፡፡ ወደ ካሊፎርኒያ እንደተመለሰኩ አኔም ይህን ሃሳብ ለመሪራስ አማን አካፈልኩአቸው፡፡ እሳቸውም ሃሳቡ ቸር ነው፣ ፕሮፌሰር ጌታቸውን ግን በደንብ አላውቃቸውም፡፡ ከዚህ በፊት ሌሎች ምሁራን ልከ እንደሳቸው ብለውኝ እውነት መስሎኝ ብራናዎቹን ከአሳየሁአቸው በሁዋላ እኔን በማግለል ብራናዎቹን ሊወስዱብኝ ስለሞከሩ መጠንቀቅ አለብኝ፣ ስለ አሉ ነገሩ ሳይሳካ ቀረ፡፡ ከዛ ም ርስዎ አቶ ፈንታሁን ጥሩነህን (ላይብረሪ ኦፍ ኮንግረስ የሚሠራውንና መሪራሰ ብራናዎቹ እንዳላቸው አምኖ አንዳንዶቹን የመሪራስን መጻሃፍት ለህትመት የአረመው) ወደ መሪራስ አማላጅ ልከው ብራናዎቹን ለመመርመር ቢሞክሩም አልተሳካልዎት፡፡ ስለዚህ ተበሳጭተው ቂም ይዘው አማን ውሸቱን ነው፣ በእጁ ምንም ብራና የለም፣ የኢትዮጵያ ታሪክ ብሎ የሚጽፈው ሁሉ ልብ-ወለድ ነው፤ እያሉ ርስዎ ማውራት ጀመሩ;; ንግግርዎ የብስጭት እና የእልህ ነው፡፡ ርሰዎ የፈለጉት ተሳክቶሎዎት ቢሆን ኖሮ የኔንም ሆነ የመሪራስን ሥራ ዛሬ አፈታሪከ ነው ባላሉም ነበር;; ለደንታዎ ሲሉ እውነተኛ ታሪክ ነው እያሉ ምስራቹን በነዙት ነበር;;

እንዳው ለነገሩ፣ እንድ ጥያቄ ላቅርብልዎትና በዛን ጊዜ ርስዎ ራስዎ የመሪራስን መጻህፍት የኢትዮጵያ ትንሳኤ ታሪክ የተባለውን ጨምሮ ገዝተው አንብበው ከውስጣቸው ጥቅሶች ነቀሰው አውጥተው በአደባባይና በጽሁፍ አልተጠቀሙባቸውም?  ሃቁ ለምን ብራናዎቹ እጄ አልገቡም ብለው ተቆጭተው አይደል መጻህፍቱን ተረት የሚሉት? ዳር ግን፣ ተረት ከማለት በቀር ተረት ስለመሆናቸው አንድም እንኩዋን ማስረጃ አላቀረቡም፡፡ በሌላው እንኩዋን ቢቀር በ እድሜዎ ትልቅ ሰው አይደሉም እንዴ? አገራችን ላይ እሳት እየነደደ እና ኢትዮጵያችን ልትበጣጠስ እያሰጋት ባለችበት ወቅት ለችግራችን መፍትኄ የሚሰጥ እውነተኛ ታሪካችን ሲወጣ እሰየው እንደማለት በግል ኢጎዎ ተነሳስተው እንዴት እንዲህ ያደርጋሉ? ነውር አይደለም እንዴ ? ተሳስቼም ከሆነና እውነት ከልብዎ ቀና ካሰቡ ድካሜን እና ጥረቴን አደባባይ ወጥተው ከማጠልሸት ለምን ለእኔ ስልከ ደውለው አላናገሩኝም?

እኔ በመጽሃፌ ውስጥ በርካታ ቁምነገሮችን አንስቼ ሳለ ርስዎ ስለነዚህ ቁምነገሮች ምነው ትንፍሽም አላሉ? ከዚህ በፊት ያልተባሉ እንዳንድ የቆዩ የታሪክ እሳቤዎችንና ግንዛቤዎችን እኔ ውድቅ አላደረግኩምን? ለምሳሌ እንግሊዛዊው ኡሉንዶርፍ ኦሮሞዎች ለኢትዮጵያ ስልጣኔ ምንም አላበረከቱም ብሎ ሲዘባርቅ እኔ ኦሮሞዎች ያበረከቱትን ሁሉ ዘርዝሬ በማስረጃ አላቀረብኩምን? ታዲያ ስለ እሱ ምነው ጸጥ አሉ? አማራ የገዢ መደብ ተብሎ በሃሰት ተፈርጆ እየተዋከበና እየተገደለ ሲኖር  አማራው እንደ ስርው-መንግሠት የገዢ መደብ ሆኖ ገዝቶ እንደማያውቅ አዲስ ማስረጃ ኮልኩሌ አማራው የገዢ መደብ እየተባለ ግፍ የሚፈጸምበት አግባብ እንዳልሆነ ስለ እሚመሰክረው አዲሱ ግኝቴ ምነው ዝም አሉ? ከዚህ የላቀስ የቀድሞውን እሳቤ ፉርሽ የሚያደርግ ምን አለ? ስለጎሳ፣ ስለ ነገድ፣ ስለዘር እና ስለ ብሄር ልዩነቶች ከዚህ በፊት ያልተባለውን እኔ አዲስ ትንታኔ አቅርቤ ስለዚህ እንዳይናገሩ ምላስዎ ለምን ተያዘች? ኦሮሞዎች በላቲን ከሚጽፉ ይልቅ በኢትዮጵያ ፊደላት ቢከትቡ በዙ ጥቅም እንደ አለው በማስረጃ ስለ ጠቆምኩትስ ምነው አንድም ቃል አልተናገሩ? ከዚህ ሁሉ በላይ፣ ንግሥተ-ሳባን አረብ ነች ወይም ቢልቂስ የምትባል የአረብ ንግሥት ነች እያላችሁ እርስዎና መሰልዎችዎ መሳሳታችሁን በዘርዋ ሃረግ እና በተዘዋዋሪ የአመክንዮ ማስረጃዎች ቆልዬ በ 53 ገጾች ስለመዘገብኩት አዲስ ክስተት ምነው አድናቆትዎን አልገለጹም? አንድ እውነተኛ ምሁር ይሀን የቀድሞውን ግንዛቤ ማድነቁ እንኩዋን ቢቀር አንባቢን ለውይይት አይጋብዝምን? ርሰዎ ግን አንባቢውን በመናቅ ቅጥፈት ያሰራጫሉ;; የዛሬ ዘመን አንባቢ ግን የረቀቀ ስለሆነ የኔ መጽሃፍ እውነተኛ የሃገራችንን ታሪከ እንደሚያንጸባረቅ ማስረጃዎቼን አመዛዝኖ ያለነጋሪ ይገነዘባል፡፡ ባለፉት 4500 ዐመታት ኢትዮጵያ ውሰጥ የተከሰቱት ስርወመንግሥታት የኩሽ፣ የኢትዮጵ፣ የሰለሞን፣ እና የዛጉዌ ብቻ እንደሆኑ እኔ በማስረጃ አቅርቤአለሁ;; የትግሬም ሆነ የኦሮሞ ወይም የአማራ ስርወ-መንግሥት እንዳልነበረ፣ የኦሮሞ ዝርያዎች ግን በውንድሞቻቸው በአማራዎች የጦርሰራዊት እርዳታ ከኦሮሞዋ ከ ሃዊ ጊፍቲ መንዲያ ልጅ ከተስፋኢየሱስ (ይኩኖዐምላክ) ጀምሮ በጋብቻ እ ሰለሞን ስርወ-መንሥት ውስጥ ‹‹ሰርገው ገብተው‹‹፣ እስከ አጼ ኃይለሥላሤ ድረስ በንጉሠነገሥትነት እና በንግሥተነገሥታትነት ኢትጵያን እንደመሩ፣ በዘመነ መሳፍንትም ደሞ ከትንሹ እሰከ ትልቁ ራስ አሊ ኢትዮጵያን እንደገዙ በአዲስ ማስረጃ አስደግፌ አቅርቤአለሁ;; ይህም አዲስ ትንተና መሪራስ አማን በላይን ከመተዋዎቄ እና መጻህፍታቸውን ከማንበቤ በፊት ባለፉት 27 ዐመታት Ethiopian Review በተባለው መጽሄት በጻፍኩአቸው መጣጥፎቼ ውሰጥ ተንጻባርቀዋል;; እነሱም ከብዙ በጥቂቱ የሚከተሉት ናቸው—

Nobles of Oromo Descent Who Ruled Ethiopia,

Oromo Contribution to Ethiopian Civilization,

Amara Contribution to Ethiopian Civilization,

Tigre Contribution to Ethiopian Civilization,

Common Factors Uniting the People of Ethiopia,

Nigusse Negest, Balemulu Siltan Enderassie, Emperor, Prime Minster.

እነዚህም ከአጽናፍ እስከ አጽናፍ ኢትዮጵያውያን ያነበቡዋቸው መጣጥፎች እኔ ታሪካችንን ባልተለመደ መልኩ የማቅረብ ክህሎት እንደ አለኝና አያሌ  ሙሁር-ተብዬ ሁሉ በታሪክ ውዥንብር ውሰጥ ተዘፍቆ፣ እናት ኢትዮጵያን ክዶ በየጎሳው ሲወሸቅ እኔ የማያወላዳና ቀጥ ብሎ የወጣ የኢትዮጵያዊነት አቁዋም እንደነበረኝ ይመሰክራሉ;; ለታሪክም ጸሃፊነት እኔ አዲስ እንዳልሆንኩ እማኝ ይሆናሉ፡፡ ቀደም ሲል እንደ ገለጽኩት፣ ርስዎ ራስዎ እላይ በተጠቀሱት እና በሌሎቹም መጣጥፎቼ የተነሳ አድኖቆትዎን በወቅቱ እንደቸሩኝ ዛሬ አሌ አይሉም፡፡

 

ውድ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ፣

 

ሌላው የርስዎ ችግር ኢትዮጵያውያንን መናቅና ማጣጥል አረቦችን፣ ግሪኮችን እና ሌሎች ነጮችን ማምለክ ነው፡፡ ንግግርዎችዎ እና ጽሁፍዎችዎ ሁሉ ሲፈተሹ ይህን እውነት ይፈነጥቃሉ;;  ለምሳሌ ንግሥተ-ሳባ የኢትዮጵያ ንግሥት መሆንዋን እንኩዋር አንኩዋር አዳዲስ ማስረጃዎች (በ 53 ገጾች) በመጽሀፌ ውስጥ አቅርቤልዎት ማስረጃዎቹ ዐይኖችዎ ላይ እያፈጠጡ የርስዎን የተሳሳተ ድምዳሜ ስለ  እፈረስኩብዎት ርስዎ ሳባን ስምዋን ቀይረው ‹‹ቢልቂስ‹‹ ብለው፣ በሃሰት ሳባ የኛ ቢልቂስ ናት ለሚልዋት ለአረቦች ደይሸልሙዋታል፡፡ ደሞም ባሕረሃሳብ ብለው  ባቀነባበሩት መጽሃፍዎ በገጽ 67 ላይ እኛ ኢትዮጵያውያን ከሌሎቹ ክርስትያኖች ተለይተን የእየሱስ ክርሰቶስን ልደት በ 7 ዐመት ወደ ሁዋላ ቀርተን ለምን እንደምናከብር እየጠየቁ እየሱስ ክርስቶስን በ 7 ዐመት ወጣት ልናደርገው ነውን በማለት ያወቁ የበለጡ መስሎዎት በራሳችን ላይ እያሾፉና እየተሳለቁ ይህን ያደረግነው እኛ ኢትዮጵያውያን ቀን አቆጣጠርን ባለማወቃችን እንደሆነ አድርገው ይዛለፋሉ፡፡ ርስዎ ስለራስዎ እንደሚመሰከሩት እወነት የታሪከ አጥኚ ቢሆኑ ኖሮ ምክንያቱን ባወቁ ነበር፡፡ ምክንያቱ ግን እኛ አላዋቂ፣ ፈረንጆች አዋቂ ሆነው ሳይሆን ፈረንጆች የጌታችንን የእየሱስ ክርስቶስን ልደት መቁጠር የሚጀምሩት የዚያን ጊዜው የሮማን ኢምፓየር ቄሳር የነበረው አውጉሰቶስ ቄሳር፣ እየሱስ ከመወለዱ ከ 7 ዐመታት አስቀድሞ እንደ እግዚአብሄር ይመለክ ስለነበር የራሱ ልደት እንዲከበር ስለ አወጀ ከዛን ወቅት ጀምረው አውሮፓውያን ቀን ስለቆጠሩ እና እኛ ደግሞ ራሱ እየሱሰ ክርስቶስ ከተወለደበት ቀን አንስቶ መቁጠር ስለጀመርን ነው፡፡ ስለዚህ እኛ የህያዉን የእግዚአብሄርን ልጅ ትክክለኛውን ልደት እናከብራለን እንጂ የጨካኙን አረመኔ ቄሳር ልደት አንዘክርም፡፡ ስለዚህ ትክክለኛው የዘመን አቆጣጠር የኛ ርስዎ የሚያሾፉበቱ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ፣ የዘመን አቆጣጠርን ዘዴ ርስዎ ‹‹አባቶቻችን‹‹ ከሚሉዋቸው ክግብጾች፣ ከሶረያውያን እና ከግሪኮች እንደቀዳን እያተቱ ይሳለቁበናል;; ሃቁ ግን የግብጾቹና የሌሎቹ ቤተክርሰትያናት የዘመን አቆጣጠር ከኛው ጋር በምንም አይገናኝም፡፡ ካንዳቸውም ጋራ የኛው አንድነት የለውም፡፡ አይመሳሰልምም፡; እውነት እኛ የቀንን እና ዘመንን አቆጣጠር የቀዳነው ከነሱ ከሆነ ለምን የነሱ ከኛው ጋር ዛሬ የማይገጥም ሆነ? አሁንም ሃቁ የኛን የዘመን አቆጣጠር የኛው ሊቃውንት ፈልስፈው ያቆዩልን ነው፡፡ እነሱም በአቀማመር እና በስሌት የረቀቁ ነበሩ እንጂ እርስዎ በዚሁ በባህር ሃሰብ መጽሃፍዎ እንደሚሰድቡዋቸው እና እንደሚያዋርዱአቸው ሰኞና ማክሰኞ ን እንኩዋን የማይለዩ መሃይማን አልነበሩም;;  እግረ-መንገዴን አንድ ጥያቄ ልጠይቆትና፣ እነዚያን ግብጻውያን ‹‹አባቶቼ፣ አባቶቼ‹‹ የሚሉአቸው ለርስዎ በግብጽ ሀገር ስኮላርሺፕ ክመስጠት በተረፈ ሊቃውንታችንን ከማስገደል፣ አንዳንዴም ስውር ሙስሊም ሆነው መስጊድን ከመገንባት የዘለለ ለኛ ለኢትዮጵያውያን ምን ፈይደውልናል? አረቦች ሊያደርጉን ከማሻጠር በቀር ቅኔ አስተምረውናል ወይስ ዜማ፣ ወይስ አቁዋቁዋም ወይስ ብሉይና ሃዲስን አስጠንተውናል? ራሳቸው አማርኛ ወይም ግዕዝ አይናገሩ አይጋገሩ;; አብዛኞቹ ተንቀሳቃሽ ሃወልቶች ብቻ ነበሩ;;  ከባድ የወርቅ ዋጋ እየተከፈላቸው ለ 1500 ዐመት ያህል በኛ ሲያላግጡ ኖረው ሃገራችንን አፈራረስዋት;; እና ርስዎ እነዚህን የእምዬ ኢትዮጵያን ጣውንቶች አባቶቻችን ይላሉ;; ይሄ ፌዝ ነው;; የኔ እና የመሪራስ አባቶች ግን ጠቢባኑ ኢትዮጵያውያን እንጂ አረቦችና ግሪኮች አይደሉም;; የእርስዎን አባቶች ግብጻውያንን ደግሞ ፈርኦን ንጉሦችና ህንደኬ ንግሥቶች ሆነን የገዛናቸውና ያሰለጠናቸው እኛው ኢትዮጵያውያን ነን እንጂ በመንፈሳዊነትም ሆነ በቁሰ-አካል ስልጣኔ ከኛ በታች የሆኑት ግብጻውያን እኛን አላሰለጠኑንም;; በእውኑ እርስዎ የኢትዮጵያን ታሪክ የሚያውቁ ቢሆኑ ኖሮ ሆነ ብለው ካልካዱት በቀር ይህን በተገነዘቡት ነበር፡፡

 

እኔን፣ አንተ የስነጽሁፍ ሰው እንጂ ባለታሪክ አይደለህም፣ ስለአሉት ርስዎም የቁዋንቁዋ ተመራማሪ እንጂ ከቶውንም ባለታሪክ አይደሉም፡፡ ታሪክን አስመልከቶ አባ ባህሪይ ስለ ኦሮሞ ጽፈውት ርስዎ ከግእዝ ወደ አማርኛ በተረጎሙት የአባ ባሀርይ ድርሰቶች መጽሃፍ ላይ ተርጉዋሚ እንጂ ባለታሪክ እንዳልሆኑ አምነዋል;;  ታዲያ በየትኛው የታሪክ እውቀትዎ ላይ ተመርኩዘው ብቁ ሆነው ነው የእኔን እና የመሪራስ አማን በላይን የታሪክ መጻህፍት ልብውለዶች ናቸው ለማለት የደፈሩት? እንደ እውነቱ ከሆነ የኔን እና የመሪራስን የታሪክ መጻህፍት ለመፈረጅ ብቃት የለዎትም፡፡  እኔ ግን ምንም በታሪክ ትምሀርት ዲግሪ ባይኖረኝም (በነገራችን ላይ ብዙዎች ባለታሪኮች የታሪክ ዲግሪ አልነበራቸውም፡፡  እነ ክቡራን ተክለጻድቅ መኩሪያ፣ ጳውሎስ ኞኞ፣ ይልማ ደሬሳ፣ አቤ ጎበኛ፣ አስረሰ የኔሰው እና ሌሎችም ለአብነት ይጠቀሳሉ;; ) የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤትም ሆነ የኮሌጅ ተማሪ ሆኜ በታሪከ ትምህርት አልበለጥም ነበር፡፡ በዚሁ የታሪክ ችሎታዬ በመምሀራኖቼ ተመልምዬ ገና የ 11 ኛ ክፍል ተማሪ ሳለሁ የማታ 8ኛ ክፍል የአደጉ ተማሪዎችን በእንግሊዝኛ ቁዋንቁዋ ታሪክ እያስተማርኩ ገንዘብ ይከፈለኝ ነበር.;; በመስኮብ አገር የዩኒቭርሲቲ ተማሪ ሳለሁ በርካታ የዐለም ታሪክ ኮርሶችን ተከታትያለሁ;; በጀርመን ሃገርና በአሜሪካ በዩኒቨርሲቲ ደረጃ የአፍሪካን ታሪክ፣ የኢትዮጵያን ጨምሮ አስተምሬአለሁ፡፡ በማስተምርም ጊዜ ራሴ እማርና እመራመር ነበር፡፡ ምን አለፋዎት ስለ እኔ የታሪክ ችሎታ ከእርስዎ ከራስዎ እና ከፕሮፌሰር መስፍን በላይ ማን እማኝ አለኝ? የዛሬ 15 ዐመት ገደማ በሎአንጅለስ ከተማ በአድዋ ድል በአል ስብሰባ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ በግንባር ስንገናኝ የአሉኝ ይታወሶታል? ኢትዮጵያን ሪቪው ገና ሲወጣ ፈጥኜ የማነበው የአንተን ጽሁፍ ነው፣ ነበር የአሉኝ፡፡  ታዲያ በዛን ወቅት እኔ በብዛት እከትብ የነበረው እንደዛሬው ሁሉ ስለ ኢትዮጵያ ህዝብ እና የኢትዮጵያ ታሪክ ነው፡፡ አዎን በደጉ ጊዜ የእኔን የታሪክ እውቀት ራስዎ አድንቀውልኝ ነበር;;  ዛሬ ግን ምላስዎን አጠፉት;;

 

በርካታ ህብረተሰባዊ መጻህፍትን የከተቡት፣ ለሰብአዊ መብት የሚሙአገቱት እና በድፍረትና በግልጽነት የሚናገሩት አንጋፋው ሙሁር ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም አዳፍኔ በተባለው መጽሃፋቸው ውስጥ እና በቃላቸውም ሰለ እኔ የታሪክ እውቀት መስክረዋል;; ዶክተር ፍቅሬ ቶሎሳ፣ የኢትዮጵያን ታሪከ፣ በተለይ የኦሮሞን ታሪክ ጠንቅቆ ሊጽፈ የሚችል ነው፣ ብለው ስለ እወነት መስክረዋል; እኔም አላሳፈርኩአቸውም;; ይሀን ዮኦሮሞ እና የአማራ እውነተኛው የዘር ምንጭ የተሰኘውን ከእርስዎና ከመሰሎችዎ በቀር ድፍን አገር የወደደውን መጽሃፍ ጽፌ አኮራሁአቸው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ካንዴም ሁለቴ ተገናኝተን ስለመጽሀፉ ስንወያይ በፈገግታ እያዩኝ ‹‹አንዳንድ ሶዎች፣ አንተ አማራ የለም ብለሃል፣ ወዳጅህ ፍቅሬ ቶሎሳ ግን አለ ብሎ ጽፎአል፣‹‹ ከአሉኝ በሁዋላ ‹‹ድሮ የምናውቀውን ታሪከ ገለባብጠህ ጽፈሃል፣ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ አብዮት አካሂደሃል፣ አንተ የጻፈከውን አዲስ ታሪክ በአዲስ መልክ እያገናዘብን ማንነታችንን እንደገና መመርመር አለብን፣‹‹ በማለት የሃቀኛ ምሁርን እውነተኛ አስተያየት ከልባቸው ገልጸዋል;; ቀጣፊ እና መሰሪ ምሁር ቢሆኑ ኖሮ የኔን የቀድሞ ሃሳብ የሚያፈርስ

አዲስ ሃሳብ አመጣ ብለው አፍረው እና ተናደው መጽሀፌን ባጣጣሉት ነበር;; አዎን፣ ሃቀኛ ምሁር የቀድሞ እሳቤውን የሚሽር አዲስ ትክክለኛ እሳቤ ሲመጣ የኔን የድሮውን ይሽርብኛል ብሎ ከድሮው ጋር ሙጭጭ ብሎ፣ ዐይን አውጥቶ፣ ሃሰት እያዛመተ ገር አንባቢን አያሳስትም፡፡

 

እርስዎ ግን ታሪከ አውቃለሁ እያሉ መሃይም እንኩዋን የማይሠራውን ታሪካዊ ስህተት ፈጽመዋል;; እንዴት ማለት ደግ ስለሆነ እንዴት ይበሉ፡፡ ስለ አማራው በከተቡት አንድ መጽሔት ላይ በሸዋ የሰለሞንን ስርወመንግሥት ስለተከለው ስመ-መንግሥቱ ይኩኖዐምላክ፣ ወላጆቹ ያወጡለት ስም ተስፋእየሱስ ስለተባለው ንጉሥ ሲጽፉ የልጁን እና የአባቱን ስሞች አምታተው ገለባብጠው መዝግበዋል;; የተስፋእየሱስ አባት ስም እድምአሰግድ ነበር፡፡ እርስዎ ግን ልጁን እድምአሰግድ፣ አባቱን ተስፋእየሱስ ብለው አፋልሰው አስፍረዋል፡፡ ይህ የስህተት ስህተት ነው፡፡ የሚያሳፍርም ነው፡፡ የታሪክ አላዋቂነትዎ ተጋልጦ እንዳያፍሩ አስቤለዎት ከዚህ ቀደም በትዝብት ብቻ አልፌዎት ነበር፡፡ ይህንን አሳፋሪ ስህተት ርስዎ ሊሠሩ የቻሉት ርስዎ እንደ ጣኦት ከሚያመልኩዋቸው ኢትዮጲስት-ተብዬዎች አንዱ የነበረው ኮንቲ ሮሲኒ በመንደርተኞች መረጃ ላይ ተንተርሶና ተሳስቶ አባቱን ልጅ፣ ልጁን አባት አድርጎ ስቶሪያ ዴ ኢትዮጵያ ብሎ በጻፈው መጽሃፍ ውስጥ በስህተት ያስቀመጠውን ርሰዎ ምንጩን ሳያጣሩ በቀጥታ ከተክለጻድቅ መኩሪያ የኢትዮጵያ ታሪክ ከአጼ ይኩኖአምላክ እስከ አጼ ልብነድንግል መጽሃፍ ላይ ስለገለበጡ ነው፡፡ ስለ ተስፋእየሱስ እናት ማንነት ይሄው ጣልያናዊ የዘባረቀውን እርስዎም በዛው ፅሁፍዎ እንደገደል ማሚቶ አስተጋብተዋል; ; ርሰዎ ኢትዮጵያውያን ባለታሪኮችን ስለሚንቁ እንጂ (ኢትዮጵያውያንን ሲንቁ ራሰዎንም እንደናቁ ይገንዘቡ) ኢትዮጵያውያን ባለታሪኮች ያኖሩትን ሸዋ የተደበቁትን የአክሱም ነገሥታት ዝርያዎች የስም ዝርዝር ቢመለከቱ ኖሮ ይህን ግዙፍ ስህተት ባልፈጸሙ ነበር;;

እሱውም ክላይ ወደታች እንደሚከተለው ነው—

ድልነአድ፣ አግባጽዮን፣ ጽንፈአርእድ፣ነጋሺ ዛሬ፣ አስፍሃ፣ያእቆብ፣ ባህር-ሰገድ እና እድም-አሰግድ ናቸው;; የመጨረሻው የተስፋእየሱስ (የኩኖአምላክ) አባት ነው;; ለወደፊቱም ይህን ሃቅ እወቁት;;

ሁሉንም ስህተትዎን እዚህ አልዘረዝረውም፡፡ የአማራውን መኖር ለመካድ አማራ ብለው እነዳይጠሩ ‹‹አማራ‹‹ የሚለውን ቃል ››ቤተዘመድ›› የሚል አዲስ ስም አውጥተውለት አንባቢውን ግራ የሚያጋቡትን እዚህ አልጠቅሰውም፡፡ እርስዎ የእኔ እና የአማን በላይን የታሪክ ሥራዎች ለመተቸት ብቃት እንደሌለዎት ከዚህ በላይ ምን ማስረጃ አለ? የርስዎ ሙያ የቁዋንቁዋ ጥናት ብቻ ስለሆነ ታሪክ አለማወቅዎን አዋቂዎች ሲያስታውሱዎት እኔ እኮ ብራና ስመረምር ነው የምኖረወ፣ ብለው ይከላክላሉ፡፡ መረመርኩ የሚሉዋቸው በቀጣሪዎችዎ በነጮቹ ክ ኢትዮጵያ የተዘረፉት፣ የተሰረቁትም ሆነ ያለዋጋቸው በሳንቲሞች ተለቅመው ቅጂም ሆኑ ወሪጂናሌ ወደ አሜሪካ የመጡት ብራናዎች የታሪክ ብቻ አይደሉም እንጂ የታሪክ ብቻ እንኩዋን ቢሆኑ እነሱን ካታሎግ ሲያደርጉ መዋልዎ ባለታሪክ አያስብሎትም፤ ወይም አያደርግዎትም፡፡ እውነቱነ ንገረኝ ከአሉ እነሆ፡፡

የኔ መጽሀፍ መውጣት ርሰዎን እንቅልፍ የነሳው ሌላው ምክንያት በንግሥት-ሳባ ምክንያት ነው;; አረቦች ስለ ንግሥት- ሳባ የሚዘላብዱትን ቅጥፈት እርስዎ ደግመው ጽፈው በአንድ አውሮፓ በሚታተም ጁርናል አሳትመው አንድ ኮፒ ከ ሶሰት ዐመታት በፊት ልከውልኝ ነበር;; ስልከ ደውዬለዎት ቢልቂስና ሳባ ሁለት የተለያዩ ሴቶች እንደሆኑ አስረድቼዎት፣ ‹‹ሳባ‹‹ የሚለው ቃልም ከኩሽ የወረደ የወንድ ስም፣ እንዲሁም የከተማ መጠሪያ እንደሆነ አብራርቼልዎት፣ ርስዎ በጻፉት  እንደማልስማማ ነገርኩዎት፡፡  እንግዲህ የማያውቁትን የኢትዮጵያ ታሪክ አውቃለሁ ብለው ሌላ ርስዎ የሚምታታቦት እና የሚያምታቱት የንግሥተ-ሳባ ማንነት ነው;; ንግሥተ-ሳባ የሳባ (ከተማ) ንግሥት ማለት ነው፡፡ ፈረንጆቹ ‹‹ሺቫ‹‹ የሚሉት ‹‹ሳባ‹‹ ለማለት ነው;; ርስዎ ሳባን ‹‹ቢልቂስ‹‹ ነች፣ የአረብ ንግሥት ነች፣ ይላሉ፡፡ ይህ ከስህተትም ስህተት፣ እጅግ ትልቅ ስህተት ነው;; አረቦች ተምታቶባቸው ወይም ዝና ፈልገው ነው ሳባን ቢልቂሰ የሚያደርጉት፡፡ ቢልቂሰ ማን እንደሆነች ማወቅ ከፈለጉ ግን ቢልቂስ ማለት በኢትዮጵያዊትዋ እመቤትዋ በንግሥተ-ሳባ የተሾመች የየመን ንግሥት ነበረች፡፡ ሳባ እስዋን በየመን ላይ ልትሾም የቻለችው የመን በዛን ጊዜ ከኢትዮጵያ ግዛቶች አንደኛዋ በመሆንዋ ነው፡፡ ለእርስዎ እንደሚመስልዎት አረቦች ራሳቸው የሾሙአት አንዲትም የአረብ ንግሥት በታሪክ አልነበረችም፡፡ አረቦች ሴትን ከሰው ስለማይቆጥሩ ሴትን እንኩዋን በላያቸው ላይ በቤታቸውም ውስጥ አያነግሡም ነበር፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን ግን ሴት ልጅን እና ሙሉ መብትዋን ስለምናከብር ባለፉት 3800 ዐመታት ውስጥ በርካታ ሴቶችነ በኢትዮጵያ፣ የመን፣ ግብጽ፣ሊብያና ኑብያ ግዞቶቻችን ላይ አንግሠን ነበር፡፡ ሴቶቻችን ደግሞ ደንበኛ ‹‹ንጹህ‹‹ ኢትዮጵያውያን ነበሩ፡፡ ቢልቂስም ከሳባ በታች በየመኖች ላይ የተሾመች በዘርዋ ኢትዮጵያዊ ነበረች፡፡ ይህውሎት የኢትዮጵያ ታሪክ እንደዚህ ነው እንጂ እርስዎ እንደሚያናንቁትና እንደሚሳለቁበት አይደለም፡፡ ብራና ላገላብጥ ስለምወል እኔ የታሪክ አዋቂ ነኝ፣ ማለትዎን ይተዉና በትህትና ጆሮዎንና ዐይንዎን ከፍተው አዳምጠው እና ዐይተው ገናና ታሪካችንን ይማሩ፡፡ ርስዎ እንደሚሉት ቢልቂስ ሳባ እና የአረብ ንገሥት ከሆነችስ እንደኛ አረቦች ለምን ሰሎሞናዊ ስርወ-መንግሥት አልመሰረቱም? ለምን እንደ እኛ ታቦት የላቸውም? ለምን እንደኛ በመጽፍ ቅዱስ ውሰጥ አልተወደሱም? ለምን እንደኛ ትንቢትስ አልተተነበየላቸውም? ለምን እንደ እኛ የሰለሞን ዝርያ ነን የሚሉ ለ 3000 ዐመታት የነገሡ 225 ነገሥታት የላቸውም? ነው ወይንስ የርስዎ ቢልቂስ ከሰለሞን ልጅ አልወለደችም? መልሱን እኔው እነግርዎታለሁ፡፡ አዎን አልወለደችም፡፡ እናትዋ ‹‹ኢትያኤል‹‹ ስትል በልጅነትዋ ስም ያወጣችላት የኛዋ ንግሥተ-ሳባ ግን ከንጉሥ ሰለሞን ምንይልክን ሰለወለደች እሱ ይዞት የመጣው ታቦት እኛ አለን፣ እሱ የሰለሞንን ስርወመንግሥት ኢትዮጵያ ውስጥ መስርቶ ለ 3000 ዐመታት የነገሡ 225 ነገሥታት እና ንግሥተነገሥታት ነበሩን፣ አጼ ኃይለሥላሴ የመጨረሻው ሰለሞናዊው ንጉሠነገሥት ነበሩ፣ እንላለን፡፡ አግአዝያን፣ ፈላሾችና ኦሪታዊው የአይሁዳውያን ሃይማኖትም ኢትዮጵያ ውስጥ ሊገቡና ሊኖሩ የቻሉት ንግሥተ-ሳባ የኢትዮጵያ ንግሥተ-ነገሥታት ሆና ሳለ ከኢትዮጵያ ተነስታ ወደ ኢየሩሳሌም ሄዳ፣ ከንጉሥ ሰለሞን ምኒልክን በመውለድው ነው እንላለን፡፡  አርስዎ ግን ይህን ታሪካችንን ያጣጥላሉ፤ ይክዳሉ፤ አፈታሪክ ነው ይላሉ፤ እሱንም እስከነአካቴው ለአረቦችም ይዳርጋሉ፡፡ ስለ ንግሥተ-ሳባ እና ቢልቂስ ማንነት በዚህ ርስዎ ልብወለድ በሚሉት መጽሀፌ ውስጥ ልዩ ልዩ ማስረጃዎች ደርድሬ ፍርጥርጥ እድርጌ በ 53 ገጾች አስሬዋለሁ;; ሁለተኛም ይህ ጥያቄ እንዳይነሳ የመጨረሻ ፍርድ ሰጥቼበታለሁ፡፡ የርስዎን ያውጡትና አንባቢ የርሰዎን እና የኔን አነጻጽሮ የትኛው ለህሊና እውነት እንደሆነ ይፍረድ፡፡

(ክፍል ሁለት ይቀጥላል፡፡ መጽሃፌን አስመልክቶ ስለ አሰፈሩት ተጨማሪ ነጥቦች በክፍል ሁለት ውስጥ አካትታለሁ፡፡)