01/19/2017

መንግስቱ ሙሴ

                                              “ድርድር” የሕወሐት አዲስ ስልት ወይንስ?

ሰሞኑን የማህበራዊ ገጾች በዚህ የወያኔ የግዜው ስልት ላይ መነጋገሪያ እርእስ አድርገውታል። በበኩሌ ዜናው ጣእም ስለሌለው ችላ ማለት ፈለግሁ ውሎ ሲያድር ሁነኛ ወረቀቶች ሲዘግቡት ማየት ደግሞ ለሁሉም የሚሰጠው ስሜት አንድ ባይሆንም ትንሽ ብየ ማለፍ ፈለግሁ።

ጥያቄ፦ ሕወሐት በእውነት አስገዳጅ ሁኔታ ስላለባት ነው ወይንስ በሰሜናዊ አማራ ከባቢወች የተጀመረውን አመጻዊ ሁኔታ እንዲሁም በኦሮሚያ ያለውን የሕዝብ መነሳሳት ለማስታገስ የታሰበ ስልት?

በግሌ እንደማምንበት ለሕዝብ ጭቆና በቃኝ ብሎ ለመነሳት አያሌ ቅድመ ሁኔታወች አሉ። እነዚህ ቅድመ ሁኔታወች የአገሪቱን የቅርጽ እና የይዘት ለውጥ። የሕወሐት አመራር አገሪቱን ያለ ባህር በር ማስቀረት። የአነሰች ኢትዮጵያን መፍጠር። ብሎም ለዘላቂው የማትኖር አገርን የማመቻቸት፣ አንቀጽ 39 የሕወሐት ቅድመ ሁኔታ መፍጠር። አገሪቱን እጅግ አደገኛ ወደሆነው በዘር፣ በቋንቋ መከለል። ዜጎችን ማፈናቀል፣ አርባ ጉጉ፣ በደኖ፣ ጉራ ፈርዳ፣ መተከል፣ ወለጋ ወዘተረፈ። ቢያንስ እንኳ በየቀኑ፣ በየሳምንቱ በየቀየው የሚጋዙት ለጋ ልጆች ጉዳይ ማንም የሚያነሳው ሲሆን። የሕዝብ ጥያቄወችን በጋዜጦች እና በብሎጎች፣ የፖለቲካ ድርጅት መሪወች እና ሌሎች ሰላማዊ ዜጎች፣ እንደነ እስክንድር ነጋ፣ አንዷለም አራጌ፣ በቀለ ገርባ፣ ዮናታን ተስፋየ በቅርብ እንኳን ገና ወራት ያላስቆጠረው የዶክተር መረራ ጉዲና ያውም የዚህ አንጋፋ ታጋይ ጥያቄ ለአመታት ለአገር እና ሕዝብ ከመቆርቆር ያለፈ እንዳልሆነ ሕወሐት የምታውቀው ጉዳይ ሆኖ ሳለ ግን ይህች በቀልተኛ ድርጅት እርሱንም ወደ እስር ወርውራዋለች።

ለመሆኑ ምን ደግ እና የተሻለ ቅድመ ሁኔታ ከሕወሐት መራሽ መንግስት ታይቶ ወይንም አሳይታ ነው የእንደራደር ቃል ያመጣችው? ከላይ የጠቀስኳቸው ሁሉም ዜጋ የሚያውቃቸው ለአመታት በግፍ የተጋዙ ሰላማዊ ዜጎች ናቸው። የሀሰት ሕወሐታዊ የቂም እና የበቀል ክስ ተሰርቶ ለእስር የበቁት እና እድሜአቸውን በጥላቻ በተመረዘ ልቦና የሚሰቃዩት። አቶ አንዳርጋቸው ጽጌም ሌላው ተጋዥ ነው። የሕወሐት የግፍ አገዛዝ የገፋው እና ወደተቃውሞው ጎራ የተቀላቀለ በግፍ ከመንገድ እና ከሌላ አገር ተጠልፎ ወደ እስር የገባ እና በሕወሐት የማሰቃያ ቤት የሚኖር። ቁጥሩ በውል የማይታወቅ አማሮች እና ኦሮሞወች በእርግጠኝነት ግን በትንሹ በመቶ ሽህ የሚቆጠሩ ዜጎች ለምን መብታችሁን በሰላማዊ ሰልፍ ጠየቃችሁ ተብለው በማሰቃያ ካምፖች የታጎሩ እና ለቶርቸር የተዳረጉ። አሁንም በየእስር ቤቶች በአገሪቱ ተበትነው የሚኖሩ። ይህን ሁሉ ዜጋ በግፍ እስርቤቶችን ሞልቶ ባለበት ሕወሐት እንደራደር የምትለውስ ከምር ወይንስ ለፌዝ?

ይህ የእንደራደራለሁ ቱሪናፋ የተነሳሳውን ሕዝባዊ ትኩሳት ለማብረድ የተዘየደ መሆኑ ምንም መላምት አይፈልግም። ዜጎችን ያለወንጀል መብት ስለጠየቁ የተጋዙትን አሁንም አስሮ እና በየቀኑ እና በየቀየው አሁንም እየጋፈፉ እና ወደ እስር እየወረወሩ በጎን ለማሞኘት ታስቦ ከሆነ የበለጠ የሕወሐትን ጅልነት አመላካች እንጅ በመሬት ላይ ያለሁ ሁኔታ ይህን አያረጋግጥም። በእውኑ አለም ዜጎች አገራቸው ሰፊ እስርቤት መሆኗን ያውቃሉ። በሰላም ወጥተው መግባታቸውን እንኳን እርግጠኖች አይደሉም። እናም ቀልዱን ወደጎን ትቶ ትግሉን ማፋሙ መቀጠል የሁሉም ስራ እና ተግባር ይሁን። ሕወሀትን ማመን ቀብሮ እንጅ የሕወሐትን የእውሸት ፕሮፓጋንዳ ይዞ ማራገቡ መጃጃል ነው። ሕወሐት ከትውልድ ግዜዋ እንስከ ቤተመንግስት ያለው ታሪኳ በእውሸት፣ በቅጥፈት እና በወንጀል የተሞላ ታሪክ ነው ያላት። አዲስ ተለዋጭ። ወይንም የሕዝብ ትግል የፈጠረው ክስተት ካለ መደረግ የሚኖርበት እንደሚከተለው ነው።

ለአመታት ያጎረቻቸውን እና በመሰቃየት ላይ ያሉ ዜጎችን እስክንድር ነጋ፣ አንዷለም አራጌን እና በተመሳሳይ ግዜ የታሰሩትን መፍታት

የኦሮሞ ዜጎችን ሰላማዊ ትግልን ተከትሎ ወደ እስር የተወረወሩ የፖለቲካ እና ሲቪክ መሪወችን መፍታት

ጋዜጠኞችን፣ የብሎግ ክሪቲክ አቅራቢወችን መፍታት

ያለጠያቂ፣ እና አሳቢ በእስር ለአመታት የሚሰቃዩ ዜጎች መፍታት

የጎንደር እና የጎጃም በአጠቃላይ በአማራው የወልቃይትን ጥያቄ ተከትሎ በሰላማዊ ዜጎች የወሰደውን የግድያ፣ የእስር፣ እና ግፍ ተግባራትን በአደባባይ አቅርቦ ለህዝብ ይቅርታ መጠየቅ

በቅርብ በኦሮሚያ እና በአማራ ሰላማዊ ንቅናቄወች ሳቢያ እስከ 50 ሽህ ወይንም ከዚያ እጥፍ የሚሆን ወጣቶች ታጉረዋል። እነርሱን ያለ ቅድመ ሁኔታ መፍታት

አስቸኳይ አዋጅ በሚል የታወጀውን የሽብር ተግባር አሁንኑ ያለምንም ቅድመሁኔታ ማቆም እና የዜጎችን ሰላማዊ ኑሮ ያናጋውን ወታደራዊ የሕወሐት ንቅናቄ በአስቸኳይ መሳብ። እነዚህን አይነት እርምጃወች ሳይወስዱ የእንደራደር ጥሪ ማቅረብ አሁንም ከቧልትነት የዘለቀ እንዳልሆነ ሁሉም ሊያውቅ ይገባል።

ድርድር ከማን ጋር?

እንደሚመስለኝ ወያኔ ሐርነት ትግራይ መራሹ መንግስት በአገር ውስጥ እንንቀሳቀሳለን የሚሉትን ባሻው የሚያስተዳድራቸው እንጅ እነርሱ በፈለጉት ሌላ ቀርቶ የድርጅት ስብሰባ ለማድረግ የማይችሉ ነጻነት አልባ ስብስቦች ናቸው። እነዚህ አገርን እና ሕዝብን ነጻ ማድረግ ቀርቶ ለራሳቸው ነጻ ያልሆኑ እስረኞች በመሆናቸው ምንም አይነት አቅምም ሆነ ለሕዝብ ጥያቄ የሚያቀርቡ እንዳልሆኑ መታወቅ ይኖርበታል። ቀልዱን ወደጎን አድርጎ መደራደር የሚፈልግ ካለ ድርድር በእስር ካስቀመጡት ወይንም ልሳኑን ከዘጉት ጋር ሳይሆን ለዘመናት ይህን ስርአት አይሆንም ብለው ከምር ከሚታገሉት ከኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ አመራሮች (ኢሕአፓ ወች) እና አሁን በአመጽ ከሚታገሉ ሀይሎች ከግ7 ተወካዮች፣ ከአማራ ንቅናቄ ተወካዮች፣ከኦሮሞ ንቅናቄ ተወካዮች፣ከጋንቤላ፣ ከሶማሌ፣ ከሲዳማ እና ከአፋር ተወካዮች፣ በሰሜን ለዘመናት ሕወሐትን በትጥቅ ከሞገተው ከከፋኝ ንቅናቄ ተወካዮች፣ ይህን የበለጠ ለመግለጽ ከሁሉም በሰላምም ይሁን በአመጽ ከቆሙት ጋር።ይህ ሲሆን ሦስተኛ አለማቀፍ ዳኛ ወይንም ገላጋይ በተገኘበት። አልያም ሕወሐት ከምትቆጣጠረው ቀበሌ በወጣ እና የሁሉም አካል በነጻነት ቆመው በነጻ በእኩል አንደበት ሊሞግቱ በሚችሉት ሌላ ሀገር መሆን ነው የሚኖርበት። ይህን ያላሟላ ተግባር ፋይዳ የሌለው እጅ የመስጠት እንጅ የመደራደር ሊሆን አይታሰብም። ሕወሐት ድንበር ዘልቃ አንዳርጋቸው ጽጌን ማሰሯ የሚዘከር ነው እና።

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!

መንግስቱ ሙሴ