Dr. Aklog Birara

አክሎግ ቢራራ (ዶር)

                                ድሃ ተበደለ፤ ፍርድ ተጓደለ” ኢህአዴግ የማይቀርፈው ሙስና

አክሎግ ቢራራ (ዶር)

ድርጅታዊ ምዝበራ” ብየ የሰየምኩትን መጽሃፍ ስጽፍ ከሁሉም በላይ ያሳሰቡኝና ያስጨነቁኝ አስኳል ጉዳዮች ሶስት ናቸው፤

አንድ፤ አብዛኛው በድህነት፤ በረሃብ፤ በበሽታ፤ በሰብአዊ መብቶት ረገጣ፤ በአስተዳደር ብልሽት የሚሰቃየው ከ90 በመቶ በላይ የሚገመተው የኢትዮጵያ ሕዝብ አሰቃቂ ደረጃ ላይ መድረሱ ነው።

ሁለት፤ አስደናቂ እድገት ታሳያለች በምትባለው የምግ ጥገኛዋ ኢትዮጵያ፤ መብቱ ተገፎ፤ የስራ እድል አጥቶ፤ በአገሩ በኢትዮጵያ እየኖረ ፈጥሮና ስርቶ ራሱን የማሻሻል እድሉ ዝግ የሆነበት ከ70 በመቶ በላይ የሚገመተው የደርግና “የኢህአዴግ አዲስ ትውልድ” በገዢው ፓርቲ መገለልና መብቶቹ ሁሉ መታፈን ነው። የዚህ ተተኪ ትውልድ እጣው ለመብቱ ሲከራከር ግድያ፤ አፈናና እንዲሰወር መደረግ ነው። ባለፈው ዓመት ስንት ወጣት እንደሞተ ባይታወቅም ከሁለት ሽህ በላይ እንደሚገመት የውስጥ ተመልካቾች ይናገራሉ። ከ110,000  ያላነሰ ኦሮሞና አማራ ወጣት እንደታሰረ ይገመታል። ገዢው ፓርቲ መሰረታዊ ችግሮችን ለመፍታት ፈቃደኛ ስላልሆነና ብቃትም ስለሌለው መፍትሄው ማፈን፤ ማሰር፤ መግደል፤ እንዲሰወርና እንዲሰደድ ማስገደድ ሆኗል። በዚህ አይነት ሂደት እስር ቤቶችን ካላስፋፋ በስተቀር ያሉት እስር ቤቶች አይበቁም።

ሶስት፤ አንድ ስርዓት በሙስና የተበከለ ከሆነ ሰላምና እርጋታ አይኖርም። በዜጎች መካከል ያለው የገቢና የኑሮ ልዩነት እየተባባሰ ይሄዳል። ይህ አሰቃቂ ሁኔታ ቀስ በቀስ ለአገር መፈራረስ ዋና መንስኤ ይሆናል። ኪራይ ሰብሳቢነትና ሙስና መዋቅራዊ ሲሆን የሚያስከትለውን አደጋ በመረጃ ተደግፋ ያቀረበችው ደራሲ ሳራህ ቸየዝ “Thieves of State: why corruption threatens global security,” በሚለው መጽሃፏ አፍጋኒስታን፤ ግብጽ፤ ሶሪያ፤ ኢራቅ፤ ናይጀሪያና ሌሎች ተመሳሳይ አገሮች እንዴት በመፈራረስ ላይ እንዳሉ ታሳያለች። ዋናው ነጥቧ የፓርቲና የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ለሕዝብ ያለባቸውን አደራና ሃላፊነት ትተውና ረስተው፤ ራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ስላከበሩ አገሮቻቸው የጦርነት አውድማ ሆነዋል የሚል ነው። የሞባረክ መንግሥት የወደቀበት ዋና ምክንያት ሕዝቡን አፍኖ፤ ስልጣኑን ተጠቅሞ፤ ራሱን፤ ቤተሰቦቹን፤ ወዳጆቹንና ደጋፊዎቹን፤ ጀኔራሎቹን ጨምሮ ስላከበረ ነው የሚል ድምዳሜ አቅርባለች። በሙስና የተበከለ አምባገነን መንግሥት የመሳሪያ የበላይነትም ቢኖረው በሕዝብ አመጽ እንደሚወድቅ አሳይታለች። የሙስና አደጋው ለአገር መፈራረስ ግብአት እንደሚሆን መረጃዎችን አቅርባለች።

በአገር ላይ የሚደርሰውን አደጋ ወደ ጎን ልተወውና ወጣቱን ትውልድ በሚመለከት የሚታየው ክስተት፤ አሰቃቂ ሁኔታ ያልገጠመውና እንዳይገጥመው የፈለገው ያለው ምርጭ አንድ ብቻ ነው። ይኼውም ሌላው ቀርቶ ወደ የመን መሰደድ ነው። ባለሞያዎች ስደት የስራ እድል ማጣት ብቻ አድርገው ያዩታል። እርግጥ የሚስበው እድል ፍለጋ ነው ቢባልም፤ ዋናው ግን የሰብአዊ መብቶች አለመከበር ነው። መብቱ የተከበረ ግለሰብ እንደማንም ጥሮ ግሮ ራሱን ለማሻሻል ይችላል። የእድገቱ መርህ የሕዝብን ፍላጎት የማያሟላ ከሆነና የሕዝቡ መብት ካልተከበረ ስደት የማይቀር ነው። በአለፈው አመት ብቻ 90,000 ኢትዮጵያዊያን ወደ የመን ተሰደዋል፤ ራሳቸውን ለጦርነት ሰለባ አጋልጠዋል ማለት ነው። “አገር ቤትም ብንኖር ያለኝ እድል ተመሳሳይ ነው” የሚሉ ብዙ ናቸው። ስደት አማራጭ አይደለም የሚለው የወጣት ትውልድ አካል ደሞ፤ ከስደት ይልቅ ስርዓቱን ለመለወጥ በአገሩ ሆኖ ይታገላል፤ ይሞታል፤ ይታሰራል፤ ይገረፋል፤ ለገዢው ፓርቲ ህልውና ዋናው ተቃዋሚ ሆኗል ለማለት ይቻላል። ለማንኛውም፤ ስደት ስርዓት ወለድ ነው። ስርአቱ ካልተለወጠ ስደቱ አያቆምም ማለት ነው።

በተመሳሳይ፤ ኪራይ ሰብሳቢነት፤ አድልዎና ሙስና ስርዓት ወለድ ነው። የዚህ ትንተና መሰረተ ሃሳብ ስርዓቱ ካልተለወጠ በስተቀር፤ የፈለገው የፖለቲካ ሰበካ ቢደረግ ኪራይ ሰብሳቢነትና ሙስና ሊቀረፍ አይችልም የሚል ነው። መጀመሪያ በትርጉም እንስማማ።

ለመሆኑ ኪራይ ሰብሳቢነት ምን ማለት ነው? በአለም ባንክና በአይ ኤም ኤፍ ከፍተኛ ስልጣን የነበራትን አን ክሩገርን ጨምሮ የፖለቲካ ኢኮኖሚ ባለሞያዎች የሚሰጡት ትርጉም እንዲህ የሚል ነው። “በኢኮኖሚ ሳይንስ ኪራይ ሰብሳቢነት ማለት አንድ ግለሰብ ወይንም ቡድን ወይንም ፓርቲ ወይንም ኮርፕሬሽን የሕዝብን ኃብት/ገንዘብ ወይንም ካፒታል ከሕግ ውጭ ለግል ሃብቱ ማካበቻ ወይንም ትርፍ መሰብሰቢያ ሲያደርገው ነው።” የዚህ አሉታዊ ውጤት ምን ይሆናል? ብለን ብንጠይቅ መልሱ ግልጽ ነው። ኪራይ ሰብሳቢው ለህብረተሰቡ ሆነ ለአገሪቱ ደንታ ስለሌለው ተመጣጣኝ የሆነ ጥቅም አይሰጣቸውም ማለት ነው። ማለትም፤ አንበሳውን ጥቅም ለራሱ ብቻ ማርኮ፤ የስራ እድል፤ የገቢ እድል፤ የሃብት እድል፤ የመኖሪያ ቤት የመግዛት እድል፤ የጤና አገልግሎት እድል ወዘተርፈ ይነፍጋቸዋል ማለት ነው።

ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? ብለን እንጠይቅ። እንደ ኢትዮጵያ ባሉ በአንድ ፓርቲ የበላይነት በሚገዙ አገሮች ፓርቲው፤ መንግሥት፤ የአገር ስርዓት (State) እና ተቋማት አንድ እና ተደጋጋፊ ናቸው። State capture leads to economic capture የሚባለው ለዚህ ነው። በዚህ የምርኮኛ ስርዓት አንዱ ሌላውን ይደግፋል፤ አንዱ ሌላውን እንዳያጋልጥ ይደረጋል። መረጃን ለመደበቅ፤ ኃብትን ለማሸሽ ይደጋገፋል። ግልጽነት የሚባል ነገር አይታሰብም። ውይይት የሚካሄደው ተመሳሳይ ጥቅም ባላቸው መካከል ብቻ ነው።

ይህን የዝግ ችሎት ቀረብ ብሎ ለማየት የህወሓቶችን ስብሰባዎች መከታተል በቂ ነው። የዝግ ችሎት ድብብቆሽ ማለት ነው። ለመክበር የፈለገ ምስጢር ለማውጣት አይችልም። በሌላ አነጋገር የህወሕት የፖለቲካ ስልጣን የበላይነት ዋናው ሚና የግልና  የቡድን ኃብት ማካበቻ መሳሪያ ሆኖ እንዲያገለግል ማድረግ ማለት ነው። ተሳታፊ ታማኝነትን ይጠይቃል ማለት ነው። በዚህ ሁኔታ የስለላ፤ የፌደራል ፖሊስ፤ የፍርድ ቤት፤ የመከላከያ ቁጥጥር ሊካሄድ የሚችለው በሕዝብና በተቃዋሚው ክፍል ላይ ብቻ ነው። በእኔ ግምትና ጥናት ክትትልና አፈና ለሙስና አስፈላጊ ነው። ሕዝብ ከስርአቱ የሚደርስበትን በደል ያውቃል። ሆኖም፤ ሕዝብና ተቃዋሚ በከፍተኛ ኪራይ ሰብሳቢዎች ላይ ምንም አይነት እርምጃ ለመውሰድ አይችልም። ካልተባበረ በስተቀር! በተናጠል መረጃ መስጠትና ክስ ማቅረብ በራስ ላይ መፍረድ ይሆናል ማለት ነው። ስርዓቱ መረጃ እንዲሰጥ አይፈቅድለትም። ስርዓቱ የሚፈቅደው አቅም የሌላቸውን ግለሰቦች ከማጋለጡና ከማሰሩ ላይ ነው። ይህ የሚደረገው የበላይ ባለሥልጣናት ሙሰኞችን እንዳይጋለጡ ለማድረግ ከታች ያሉትን መክሰስና ማሰር ሕዝብን ለመሸንገል ያስችላል በሚል ስሌት ነው። ይህ ከሆነ ብዙ ሽህ ዝቅተኛና መካከለኛ ሙሰኞችን ማሰር አስፈላጊ ይሆናል ማለት ነው። ምክንያቱም፤ ጥናቶች የሚያሳዩት በዛሬይቱ ኢትዮጵያ ማንም የመንግሥት ሰራተኛ በራሱ ደሞዝ ለመተዳደር ስለማይችል ሁሉም በሙስናው ይሳተፋል። ከላይ ያሉት ሌቦች በገፍ የሚሰርቁ ከሆነ “እኔስ ለምን አልሰርቅም” ቢል አይፈረድበትም። ገዢው ፓርቲ ሁሉንም ካሰረ ደሞ የመንግሥት አገልግሎት ሙሉ በሙሉ ይቆማል። ጥላቻው ይስፋፋል። ዞሮ ዞሮ ስርዓቱ ይወድቃል ማለት ነው። እነዚህ ግለሰቦች ኪራይ ሰብሳቢ ሊሆኑ ይችላሉ፤ ናቸውም። ግን እንደ ህወሓት ያለ ወይንም ተመሳሳይ የድርጅት ተገን ያላቸውም። ሲሰርቁ ራሳቸውን አጋለጡ!

የፖለቲካው ሙስና ለገንዘብ ሙስና መሰረት ነው

እኔ ብቻ ልግዛ ማለት እኔ ብቻ ልብላ፤ እኔ ብቻ ልክበር ማለት ነው። ኪራይ ሰብሳቢነትና ሙስና የገንዘብ ብቻ አይደለም። ኪራይ ሰብሳቢነትና ሙስና ብዙ ዘርፎች አሉት። በዚህ ትንተና ለማጠናከር የምፈልገው ግን ከገንዘብ በላይ አስከፊው ሙስና የፖለቲካው መሆኑን ነው። መቶ በመቶ አሸነፉ ሲባል መቶ በመቶ ኢኮኖሚውን ለመቆጣጠር መሰረት ጣልኩ ማለት ነው። የፖለቲካውን የበላይንት እንደ ግል ኃብት የያዘ ቡድን ከኪራይ ሰብሳቢነትና ከሙስና ሊጸዳ አይችልም። እንዲያውም የበላይነቱ አስከፊ የሚሆነው የፖለቲካ የበላይነት ለግልና ለቡድን ጥቅም ዋና መሳሪያ ስለሆነ ነው። ሕገ መንግሥት መኖሩ፤ ተቋሞች መፈጠራቸው ሁኔታን አያሻሽለውም። ሙሰኞች መሬት የሚነጥቁትና የሚሰርቁት ከሕግ ውጭ መሆኑን ያውቃሉ፤ ሆኖም ተቆጣጣሪ የለባቸውም። ከሕግ በላይ ናቸው ማለት ነው።  የጋምቤላን ሕዝብ ለም መሬት ሲነጥቁ ሕጉን ጣሱ ማለት ነው። ወልቃይትን ሲነጥቁ ሕጉን ጣሱ ማለት ነው። አዲስ አበባን እናስፋፋ ሲሉ ሕጉን ጣሱ ማለት ነው ወዘተርፈ። የፈለገው ተቆጣጣሪ ተቋም ቢመሰረት ይህ ስርዓት ወለድ ግፍ አይቆምም።

ተጻራሪውን እንይ። በማንኛውም በሕግ የበላይነት በሚገዛ ስርዓት አንድ ግለሰብ፤ አንድ ባለሥልጣን፤ አንድ ፓርቲ ሲባልግ ወደ ወህኒ ቤት ይገባል። የሰረቀው ወይንም ያሸሸው ሃብት እንዲመለስ ይደረጋል። ይህ ሊሆን የሚችለው ባለሥልጣናት ተጠሪነታቸው ለሕዝብ ሲሆን ብቻ ነው። ስለሆነም፤ በኢትዮጵያ ይህን የመሰለ ፍትሃዊ ነገር ለማድረግ የሚቻለው ሕዝብ የፖለቲካው ባለሥልጣን ሲሆን ብቻ ነው። ያኔ ስደት ይቀንሳል፤ ሙና እየጠፋ ይሄዳል።

የፖለቲካ ስልጣን የበላይነት (State Capture) ለግልና ለቡድን የመሬት ነጠቃ፤ የንግድ፤ የጉምሩክና ሌላ አጭበርባሪነት፤ የውጭ ምንዛሬ ማራኪነት፤ የባጀት አመዳደብ፤ የብድር፤ የኮንትራት አከፋፋይነት ወዘተርፈ እድሎች ያበረክታል። ይህ የግልና የቡድን ጥቅም አካባችነት በሚዘገንን ደርጃ፤ በስፋትና በጥልቀት የሚካሄደው በህወሓት የበላዮችና ደጋፊዎች መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ። ይህ ከፖለቲካ ስልጣን የበላይነት ጋር የተያያዘ ብልግና በቀረው ኢህአዴግ ጥረት፤ ግፊትና ለፈፋ ይለወጣል የሚል እምነት የለኝም።

ከሕግ ውጭ ከአገር የሚሸሽው ኃብት መጠን

ቻይናዎች እንዲህ የሚል ብሂል አላቸው። “አሳ የሚገማው ከራሱ ላይ ነው።” የኢትዮጵያ ድሃ ሕዝብ በድርጅታዊ ምዝበራ እየደማ መሆኑን ብዙ ጥናቶች አሳይተዋል። ለምሳሌ፤ ትራንስ ፓሬንሲ ኢንተርናሽናል፤ ግሎባል ፋይናንሽያል ኢንተግሪቲ፤ የተባበሩት መንግሥታት የልማት ድርጅት፤ በፕሬዝደንት እምቤኪ የተደረገ ጥናቶች ወዘተርፈ። በድምራቸው ሳያቸው እነዚህ ጥናቶች የሚያሳዩት የኢትዮጵያ ሕዝብ በዝቅተኛ $35 ቢሊየን ተዘርፎ ይህ ኃብት ከአገር እንደሸሸና እንደተደበቀ ያሳያል። በከፍተኛ ደረጃ ሲታይ ከአገር ተዘርፎ የሸሽው ገንዘብ ብዛት (Illicit outflow of funds$45 ቢሊየን ደርሷል። የምግብ ጥገኛዋ ኢትዮጵያ በአመት $3 ቢሊየን በላይ ይሸሽባታል። በንጥር ብናስበው ኢትዮጵያ ከውጭ ከምታገኘው የልማት እርዳታ በላይ ተዘርፋላች ማለት ነው።

ይህ እንዳለ ሆኖ የኢህአዴግ አገዛዝ የውጭ ምንዛሬ እጥረት አለ ይላል። የውጭ ምንዛሬ በገፍ ከተሰረቀና ከአገር ከሸሸ እጥረቱ ስር ዓት ወለድ መሆኑን የሚቀበል ባለሥልጣን ድምጹ አይሰማም። ይህ አርእስት ሌላ ትንተና ያስፈልገዋል። ምክንያቱም፤ የውጭ ምንዛሬ እጥረት የሚያስከትለው በደል የዋጋ መናርን ነው። ዋጋው እየናረ ሲሄድ፤ የብር ዋጋ እየቀነሰ ሲሄድ የሚጎዳው ሕዝብ ነው።

ይህ ግዙፍ ከአገር የሚሸሽ ኃብት ለፋብሪካ ስራ መስፋፋት፤ ለዝቅተኛ አምራቾች አቅም ግንባታ ግብአት፤ ለመስኖ እርሻ መስፋፋት፤ ለወጣቱ ትውልድ የስራ እድል ወዘተርፈ ቢውል ምን ያህል ጥቅም እንደሚያመጣ ለመገመት አስቸጋሪ አይደለም። ቢያንስ ቢያንስ አገራችን የምግብ ዋትና ይኖራት ነበር። ተቆርቋሪ መንግሥት፤ ሃላፊነት የሚሰማቸው ባለሥልጣናት ያስፈልጋሉ የምለው ለዚህ ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚደማው በራሱ የፓርቲና የመንግሥት ባለሥልጣናት ራስ ወዳድነት፤ ስግብግብነት ነው። እነዚህ ባለሥልጣናት የሚሰሩትና የሚከብሩት ከሕግ ውጭ ነው። ሰርቀው እንዳይከሰሱ መረጃ ይደብቃሉ። ሌሎችን ለመክሰስና ለማሰር ግን መረጃዎች በሽ በሽ ናቸው። ሰማይ ጠቀስ ፎቅ በቤተሰቦቻቸውና በወዳጆቻቸው ስም ሰርተው ለማከራየት የሚችሉበት ምክንያት የፖለቲካ ስልጣ ስላላቸው ነው። የውጭ ምንዛሬ ከአገር ለማሸሽ አቅም አላቸው። ባንኩን የሚቆጣጠሩት እነሱ ናቸው። በውጭ አገር የባንክ ሂሳብ የማቋቋም አቅም አላቸው። ኤምባሲዎች የራሳቸው የግል ኃብት ሆነዋል። ያሸሹትን ገንዘብ ተጠቅመው ቤት የመስራትና የመግዛት አቅም አላቸው። በልዩ ልዩ ስምና ዘዴ ኩባንያዎች ይመሰርታሉ። ከውጭ አገር ደላላዎች ጋር ጥሩ የጥቅም ግንኙነት አላቸው። የማስተናገድ ችሎታቸው ወደር የለውም። ይህን ሁሉ ሲሰሩ በልማት ስም ነው፤ በሕዝብ ስም ነው።

ይህን ስርዓት ወለድ የጥቅም ሴራ ለመቋቋም አይቻልም። ምክንያቱም የበላይ ባለሥልጣናት ሙሰኞች በራሳቸው ላይ እንዲፈረድባቸው ስለማይፈቅዱ። የኢህአዴግ አገዛዝ ከአሁን በኋላ በብቸኛነት የሕዝቡን አመጽ ሊቋቋም እንደማይችል የተገነዘበ ይመስላል። አስቸኳዩ አዋጅ እርጋታ የፈጠረ ቢመስልም መሰረታዊው የአገዛዝ ችግር አልተፈታም። ከ94 በመቶ በላይ የሚገመተው ሕዝብ በልቡ አምጿል ለማለት እደፍራለሁ። የሕዝቡ እምቢተኛነትና አመጽ ለጊዜው የተዳፈነ እሳት ይመስላል እንጅ አስቸኳዩ አዋጅ ሲያልቅ መነሳቱ አይቀርም። ጥገናዊ ለውጥ አያበርደውም ማለቴ ነው።

ጠቅላይ ሚንስትር  ኃይለማሪያም ደሳለኝ ስለ ፓርቲና የመንግሥት የበላይ ባለሥልጣናት ኪራይ ሰብሳቢዎችና ሙሰኞች ሲጠየቁ ችግሩ መኖሩን በተደጋጋሚ አምነዋል። ሆኖም፤ የሚሉት “መረጃ የለም” ነው።  ይህ አባባል በሕዝብ ላይ መቀለድና ወይንም አሉባልታ መፈጠር አለበት። በስለላና በመረጃ ቀልጣፋነት ከህወሓቶች ጋር ለመወዳደር አይቻልም። ህወሓት የሚታወቅበት መስፈርት በአገር ቤትም ሆነ በውጭ የስለላና የመረጃ ክንዱ ረዢም መሆኑ ነው። ስለዚህ ጠቅላይ ሚንስትሩ “መረጃ የለም” ሲሉ ህወሓቶች መረጃ ለመስጠት አይፈቅዱም ከማለት አይለይም። ይህ ሊሆን የቻለበት ዋና ምክንያት የመሳሪያውን ኃይል በእጁ የያዘው በጥቅም የተሳሰረው የህወሓት ቡድን ስለሆነ ነው።  ባለ ጉልበቱ ህወሓት መረጃውን የመደበቅ፤ ቢጠየቅም አልሰጥም የማለት አቅም አለው ማለት ነው። በዝቅተኛና በመካከለኛ ሙሰኞች ላይ የተገኘው መረጃ በከፍተኛዎቹ ሙሰኞች ሊገኝ የሚችልበት ሁኔታ አለ። ለምሳሌ፤ የሸሸው ኃብት በመጠኑም ቢሆን በባንኮች ሊፈተሽ ይችላል። ግዙፍ ህንጻዎች መረጃ አያስፈልጋቸውም፤ የማን እንደሆኑ ለማወቅ ቀላል ነው። ለስኳር ፋብሪካ ፈሰስ የሆነው ካፒታል መሰረቅ አከራካሪ አይደለም፤ ማን እንደሰረቀውና እንዳሸሸው ለማወቅ ይቻላል። ደፍሮ የመወሰን አቅም ጥያቄ ነው።

የፓርቲ፤ የስለላ፤ የፍርድ ቤት፤ የፌደራል ፖሊስ፤ የመከላከያ ወዘተርፈ ኃይል ያለው ህወሓት ነው፤ ዝቅተኛና መካከለኛ ሙሰኞት ተመጣጣኝ ኃይል የላቸውም። ሌላው ቀርቶ ጠበቃ የመቅጠር አቅማቸው ዝቅተኛ ነው። የመንግሥት ተቋማት ድጋፍ ያለው ኃይል መረጃውን የመደበቅ አቅም አለው፤ ድጋፍ የሌለው ግን መቀጣጫ ለመሆን ያለው እድል ገደብ የለውም። ዝቅተኛና መካከለኛ ኪራይ ሰብሳቢና ሙሰኛ አስሮ ድርጅታዊውን ምዝበራ ለመቅረፍ  አይቻልም የምለው ለዚህ ነው።

ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማሪያም ባለፉት ሰባት አመታት በተደጋጋሚ የፓርቲና የመንግሥት ባለሥልጣናት ያላቸውን ኃብት ለሕዝብ ይፋ ያድርጉ ሲሉ ቆይተዋል። አልቻሉም። ወደፊትም አይችሉም። ማንም ራሱን፤ ቤተሰቡንና ቡድኑን፤ ወዳጆቹንና ደላላዎቹን በመባለግ ኃብታም ያደረገ በራሱ ላይ አይፈርድም። ሊፈርድ የሚችለው የኢትዮጵያ ሕዝብ ብቻ ነው። ሕዝብ ለመፍረድ የሚችለው የፖለቲካ ስልጣን ባለቤት ሲሆን ብቻ ነው። ገዢውን ፓርቲ፤ በተለይ ህወሓትን የሚያሳስበው ይኼው ነው፤ የሕዝብ ፍርድ።

ጀኔራሎች ሚሊየኔር ሲሆኑ ምን ያሳያል?

የጥቅም ቁርኝት ስር የሰደደ መሆኑን ነው።  አንድ ጀኔራል በወር የሚያገኘው ደሞዝ 4,000-5,000 ብር ቢሆን የ10 ሚሊየን ብር ቪላ ለመስራት አይችልም፤ ካልሰረቀ ወይንም ከባንክ ያለምንም መያዣ ግዙፍ ብድር  ካላገኘ በስተቀር! አንድ ተቆርቋሪ ኢትዮጵያዊ እኒህን ጀኔራል ቢያጋልጥ በህይወቱ ላፍ ፈረደ ማለት ነው። ህወሓት ይህ መረጃ የሰጠ ግለሰብ “የፍየል ወጠጤ” ብሎ አያስረውም ወይንም አይገለውም። የሚያስረውና የሚገለው በድብቅ ነው። ስለሆነም፤ ሕዝብ ሙሰኞችን ያጋልጥ ብሎ መፍረድ ራስክን መስዋ እት አድርግ ከማለት አይለይም።

የህወሓትን ሙሰኞች ግፍና በደል ከሕዝብ አመጽ ውጭ ለመቅረፍና ለማጋለጥ አይቻልም። አንድ ታዛቢ ያለውን ልጥቀስ። “አባይ ጽሃይ ደግሞ ከሁሉም በላይ የባሰ ሙሰኛ እንጅ ሙስናን ሊታገል የሚችል ሰው አይደለም።” ሌሎችስ የህወሓት አለቃዎች፤ የፓርቲና የመንግሥት ባለሥልጣናት የሆኑ ከፍተኛ ኪራይ ሰብሳቢዎችና ሙሰኞች? እኛ ከሕግ በላይ ስለምንሰራ አይመለከተንም ነው የሚሉት? እነ አቦይ ስብሃት ስለሙስና ሲናገሩ ራሳቸውን ከደሙ ንጹህ ነን በሚል አንደበት ነው። የራስን ቤተሰብ ባለጸጋነት ማየቱ ይበቃል። አንድ ታዛቢ ያለውን ልጥቀስ። “ አቦይ ስብሃት ነጋ ደርሶ አይኑን በጨው አጥቦ ኢትዮጵያ እንዴት በሙስና እንደምትፈራርስ ጋዜጣዊ መግለጫ ይሰጣል? ከጥፋቱ ድፍረቱ!” ይላል።  አዛውንቱ “ኢህአዴግ ሙሰኞችን ካልከሰሰ አገሪቱ ወደ ብተና ማምራቷ አይቀርም” ብሎ ተናግሯል። ያልነካው ይኼን በሽታ መዋቅራዊ ያደረገው የራሱ ፓርቲ ህወሓት መሆኑን ነው። የኢትዮጵያን የባህር በር አሳልፎ የሰጠው የራሱ ፓርቲ ነው። አገሪቱ እንድትፈራርስ ያመቻቸው የራሱ ፓርቲ ነው። የብሄር ክልል የሚል አስተዳደር የመሰረተውና ጠባብ ብሄርተኝነት እንዲነግስ ያደረገው የራሱ ፓርቲ ነው ወዘተርፈ።

ስብሃት ነጋ ከመቶ በላይ ዝቅተኛና መካከለኛ ሙሰኞች እንዲታሰሩ ቀስቅሷል። በጀ ልበል። ሆኖም፤ እነዚህ ትንንሽ አሳዎች ሲታሰሩ ታላላቆቹ አሳዎች አልተነኩም። እነ ስብሃት ነጋን የሚነካ ኃይል የለም ማለት ነው። ጠቅላይ ሚንስትሩ የእነዚህን አውራ ኪራይ ሰብሳቢዎችና ሙሰኞች ሊነካቸው አልቻለም፤ አይችልም። አዛውንቱና ግበረአበሮቹ “ከቁንጮው በኪራይ ሰብሳቢነትና በሙስና የተዘፈቁ” መሆናቸውን ተራው ኢትዮጵያዊ ያውቃል። መካሪና ተቆርቋሪ ባለሥልጣን የለም እንጅ ቢኖር ኖሮ “እስኪ እናንተ ህወሓቶች ለምትኖሩባት አገር አስቡ፤ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ህይወት ተጨነቁ። ተጨንቃችሁ በውስጣችሁ ያላውን ጉድ አጋልጡ” ለማለት አልተቻለም። ደፍሮና የሞራል ብቃት ኑሮት ይህን ምክር የሚሰጥ አዛውንት የለም። እንዲህ ለማለት የሚደፍሩ ግለሰቦች በራሳቸው ህይወት ላይ ለመፍረድ የቆረጡ ብቻ ናቸው።

ለማጠቃለል፤ ኪራይ ሰብሳቢነትንና ሙሰኛነት ስር ነቀል በሆነ ደረጃ ለመቅረፍ የሚቻለው ያለውን በዝባዢና አድካሚ ስርዓት በማባበል አይደለም። ዝቅተኛና መካከለኛ ሙሰኞችን በማሰር ስር የሰደደውን ከፖለቲካ ስልጣን የበላይነት ጋር የተያያዝ ድርጅታዊ ምዝበራን ለመቅረፍ መሞከር፤ “አባይን በጭልፋ” እንዲሉ የስልጣን ባለጌዎችን ከሃላፊነት ነጻ እንደማውጣት መታየት አለበት። ይህን ስር የሰደደ፤ ለአብዛኛው ሕዝብ ነቀርሳ የሆነ ስርዓት ወለድ በደል ለመቅረፍ የሚቻለው የፖለቲካውን ስርአት ለሕዝብ ታዛዢና ተገዢ በሆነ ስርአት መተካት ብቻ ነው። ይህ እንዲሆን ምኞትና ፍላጎት ያለን ሁሉ ጥቃቅን ልዩነቶችን ወደ ጎን ትተን ለኢትዮጵያ ሕዝብ ፍትህ ተባብረን መታገል ብቻ ነው።