Sunday, 05 February 2017 00:00

ኢትዮጵያ አሁንም ለድርቅ አደጋ ተጋልጣለች

Written by  አለማየሁ አንበሴ

 ኢትዮጵያ አሁንም ለድርቅ አደጋ ተጋልጣለች

 – ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የእርዳታ ጥሪ ቀርቧል
– ድርቁን ለመቋቋም 948 ሚ. ዶላር እርዳታ ያስፈልጋል
– 300 ሺ ህፃናት ልዩ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል
– የግል ባለሃብቶች እርዳታ ይፈለጋል
ኢትዮጵያ አሁንም በአየር ፀባይ ለውጥ ሳቢያ ከተከሰተው የድርቅ አደጋ መላቀቅ አለመቻሏን ያስታወቀው የተባበሩት መንግስታት የምግብና እርሻ ድርጅቱ፤ አለማቀፉ ማህበረሰብ ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ የእርዳታ እጁን እንዲዘረጋ አሳስቧል፡፡ መንግስት በበኩሉ፤ ድርቁን ለመቋቋም ከ948 ሚሊዮን ዶላር በላይ ያስፈልጋል ብሏል፡፡
በአሁን ወቅት በድርቁ የተጎዳው 5.6 ሚሊዮን ህዝብ ሲሆን የበልግ አዝመራ ጥሩ ካልሆነ የተጎጂው ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል ተሰግቷል፡፡ ድርቁ በኢትዮጵያ ሶማሌ፣ በኦሮሚያ  በደቡብ ክልል ቆላማ አካባቢዎች የተከሰተ መሆኑን ለአዲስ አድማስ ያብራሩት የፌደራል አደጋ መከላከልና ዝግጁነት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ምትኩ ካሳ፤ በአሁኑ ወቅት መንግስት አስፈላጊውን እርዳታ እያደረገ ነው ብለዋል።
ቀደም ብሎ በተወሰኑ አካባቢዎች በድርቁ ሳቢያ ከብቶች መሞታቸውን የጠቆሙት አቶ ምትኩ፤ ለከብቶች መኖ በማቅረብ ብቻ አደጋውን መቋቋም የሚቻል ባለመሆኑ፣ ከብቶች ሳይጎዱ ለገበያ ለማቅረብ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
በአጠቃላይ ድርቁን ለመቋቋም ከሚያስፈልገው 948 ሚሊዮን ዶላር ውስጥ የክልልና የፌደራል መንግስታት 75 ሚሊዮን ዶላር መመደባቸውን የገለፁት ኮሚሽነሩ፤ ለተጎጂዎች በተለያየ ይዘት የእለት እርዳታ ራሽን ክፍፍል እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ በዚህ የድርቅ አደጋ የግል ባለሀብቶች እርዳታ እንደሚፈለግ አቶ ምትኩ ጠቁመዋል፡፡
ለእያንዳንዱ ግለሰብ 15 ኪ. ግራም ስንዴ፣ ለነፍሰ ጡር ሴቶችና ህፃናት 1.5 ኪ.ግ አልሚ ምግብ በነፍስ ወከፍ እየተከፋፈለ መሆኑን ለአዲስ አድማስ የጠቆሙት አቶ ምትኩ፤ በድርቁ 3 መቶ ሺ ህፃናት እርዳታ እንደሚፈልጉ፤ አስታውቀዋል፡፡
በእርዳታ አቅርቦት ላይ መንግስት የመሪነቱን ድርሻ የሚይዝ ቢሆንም የውጭ እርዳታም እንደሚጠበቅ የጠቆሙት ኮሚሽነሩ፤ የተረጅዎች ቁጥር መጨመርና መቀነስን የሚወስነው ቀጣዩ የበልግ አዝመራ ነው ብለዋል፡፡ በደጋና ወይናደጋ የሃገሪቱ ክፍሎች በቂ የግብርና ምርት በመኖሩ አብዛኛው የእርዳታ እህል ግዢ፣ ከሃገር ውስጥ እንደሚሆንም ተገልጿል፡፡
አዲሱ የተባበሩት መንግስታት ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ፣ ሰሞኑን በአዲስ አበበ ተገኝተው በሰጡት መግለጫ፤ በኢትዮጵያ የተከሰተው ድርቅ አሳሳቢ መሆኑን በመጥቀስ፣ አለማቀፉ ህብረተሰብ የእርዳታ ርብርብ እንዲያደርግ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡