Posted on February 9, 2017

በኢህአዴግ ጋባዥነት ጥር 10 ቀን 2009 ዓ ም በተካሄደ ቅድመ ድርድር ውይይት በተደረሰ ስምምነት መሰረት የተቀናቃኝ ፓርቲዎች ድርድር ለመጀመር ሶስት ቦታ ተቧድነው ህብረት መፍጠራቸው ተሰማ። ኢዴፓና ቅንጅት የቡድን አባት ሆነው ” ቅድመ ሁኔታ የለንም” አሉ። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች የሚበሉት ባጡበትና አገሪቱ በጎሳ አስተሳሰብ እየተዋጠች ባለችበት በአሁኑ ሰዓት ድርድርና እርቅ እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ የሚያምኑ ወገኖች ኢህአዴግ ከመቼውም ጊዜ ይልቅ አሁን ራሱን፣ ወቅቱን፣ የሕዝብ የፖለቲካ ንቃት፣ ህዝብ የሚያውቃቸውን እውነታዎች፣ በቀደመው መልክ ነገሮች ሊቀጥሉ እንደማይችሉ፣ አካባቢያዊ ፖለቲካውንና  አገሪቱን ወደፊት ሊገጥማት የሚችለውን የፖለቲካ ቀውስ ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ከተራ የፖለቲካ እሳቤ ተላቆ ድርድሩን በሃላፊነት መንፈስ እንዲከናወን ሊያደርግ እንደሚገባ ይመከራሉ።

የመንግስት ሚዲያዎች የፓርቲዎቹን ተወካዮች ጠቅሰው እንደዘገቡት ስድስቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች መኢአድ፣ መኢዴፓ፣ ኢዴፓ፣ ኢራፓ፣ ሰማያዊ ፓርቲና ኢብአፓ ተቧድነው  ህብረት የፈጠሩት በኢዴፓ አነሳሽነት ነው።

ቅንጅት እና አንድነት ለዴሞክራሲ እና ለፍትህ ፓርቲን ያካተተ የ11 ፓርቲዎች ስብስብ ሌላው ህብረት ሲሆን ድርድር እና ውይይቱ የሚመራበትን ስርዓት፣ ድርድሩ በማን ይመራ የሚለውን እና የታዛቢዎችን ማንነት ያካተተ የድርድር ፕሮፖዛል ማቅረባቸው ታውቋል። በሌላ በኩል የመድረክ አራቱ ፓርቲዎች ራሳቸውን ችለው መቆማቸው የተጠቆመ ሲሆን የተባለውን ፕሮፖዛል ስለማስገባታቸው የተባለ ነገር የለም። በመደረክ በኩል የታሰሩ እንዲፈቱ የሚጠይቁ እንደሆነ በተናጠል የፓርቲው አመራሮች አስተያየት መሰጠታቸው አይዘነጋም።

የመድረክ አባል ድርጅት የሆነው የኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረንስ ኦፌኮ ምክትል ሊቀመንበር  አቶ ሙላቱ እንዳሉት ፓሪያቸው በየደረጃው ያሉ አመራሮቻቸው፣ ደጋፊዎችንና አባላቶቻቸው ታስረውባቸዋል። እሳቸው እንደሚሉት የፖለቲካ ድርድር የሚጀመረው እስረኞችን በመፍታትና ወደ ድርድር የሚወስደውን መንገድ በማመቻቸት ነው። እርቅ ላይ የሰሩና ችግር በነበረባቸው አገራት የሰሩ እንደሚመከሩት ከሆነ ድርድር ጎዶሎ ሆኖ አይጀመርም። እስረኞችን መፍታት ዋናና አንገብጋቢ የድርድር መርህ ድልድይ ነው።

መኢአድ እና በቅርቡ አዲስ መሪ የሰየመው ሰማያዊ ፓርቲ ከሳምንት በፊት ለቪኦኤ ፓሪያቸው የታሰሩ አባላቱና አመራሮቹ እንዲፈቱ መጠየቅ የድርድሩ ቅድመ ሁኔታ እንደሚሆን በይፋ አስታውቀው ነበር። መከኢዴፓ ጋር ህብረት ከፈጠሩ በሁዋላ “ ቅድመ ሁኔታ አናስቀምጥም” የሚለው የኢዴፓ አቋም አራማጅ ሆነዋል። ህብረቱ ስላቀረበው የድርድር ፕሮፖዛል የዘገቡ የመንግስት ሚዲያዎች “…ወይይቱ ሲጀመር ግን አንድ ርዕሰ ጉዳይ መቅረብ እንዳለበት ቢናገሩም ይፋ ለማድረግ አልፈለጉም” መባሉ ምን አልባትም የፖለቲካ እስረኞች መፈታት ጉዳይ እንደሚሆን ግምት አለ። ቀደም ሲል ዛጎል እንደዘገበው አቶ ልደቱ “ ቅድመ ሁኔታ አናደርገውም። ድርድሩን ሊያደናቅፍ ይችላል። ነገር ግን አጀንዳ እንዲሆን እንፈለጋለን” ሲሉ ጫፍ መስጠታቸው አይዘነጋም።

በሌላው ምድብ ቅንጅትን ጨምሮ 11 ፓርቲዎች ተካተውበታል የተባለው የፓርቲዎች ህብረት በዙም የሚባልላቸው እንዳልሆኑ ሲፈጠሩ ጀምሮ የሚሰነዘር አስተያየት ነው። ዋናው የድርድሩ እምብርት የሚሆነው ህብረት ሲሆን ይህ ዜና እስከተዘጋጀበት ድረስ ስላቀረበው ፕሮፖዛል የተባለ ነገር የለም። አስተያየት የሚሰጡ አካላት እንደሚሉት ህብረት አካሄዱ ጥንቃቄ የተሞላበት እንዲሆን ይመክራሉ።

የድርድር ሃሳቡ በሁለት ጽንፍ በያዙ ሃሳቦች የታጀበ ነው። ፍጹም ሊሆን አይችልም የሚሉና ተስፋ ያላቸው፣ ነገር ግን ሁሉም ጉዳይ ከኢህአዴግ ቀናነትና ከተደራዳሪዎች ስበና ጋር እንደሚያያዝ በሚያምኑ። ” አይሆንም” የሚሉት ወገኖች ” ኢህአዴግ አይታመንም” የሚሉ ሲሆኑ፤ ሌላው ወገን ደግሞ ” አሁን ኢህአዴግ በቀድሞው መንገድ መቀጠል እንደማይችል ተረድቷል። ድርድር ውስጥ እንዲገባ ያደረገው ህዝብ ስለሆነ ይህንን ግፊት ማስታገስ እንጂ ማፈን አይቻልም”ethiopia-election-2015

እነዚህ ወገኖች ኢህአዴግ ህዝብ ከወቃቸውና ከተረዳቸው የተለመዱ አሰራሮቹ ሊወጣ እንደሚገባ ያምናሉ። ቀደም ሲል ከነበሩት እሳቤዎች መዳኑ በራሱ ክህዝብ ጋር የመታረቂያው ትልቁ መንገድ እንደሆነ ያመላክታሉ። አያይዘውም ራሱ ኢህአዴግም የቀደሞ አካሄዱ ያበቃ እንደሆነ ያመነ ስለመሆኑ ምልክቶች እንዳሉ ይጠቁማሉ። በዚህ መነሻ ድርድሩ ከተራ የሚዲያ ፍጆታና የቡድን ሩጫ የዘለለ ሚና ሊኖረው እንደሚገባ በየአጋጣሚው የሚናገሩ ክፍሎች “ኢህአዴግ ምርጫ ቦርድን ያፍርስ፣ አገሪቱ ላይ ያለው ደመና በአስቸኳይ አዋጅና በኮማንድ ፓስት የሚፈታ ባለመሆኑ የህዝብን ተቀባይነትና ድጋፍ ለማግኘት የሚጨበጡ ዋና ጉዳዮች ላይ መስማማት በቂ ነው ” ባይ ናቸው። በተመሳሳይም የድርድሩ አካሄድ ገና ሳይጀመር ትችትና ውግዘት የሚያወርዱትን የሚቃወሙ ጥቂት አይደሉም። ከቅድመ ትችቱ ይልቅ ቢቻል አካሄዱን የሚያጠናክሩ ልምዶችን ማካፈል ላይ የሚያተኩር ስራ እንዲሰራ ይመክራሉ።

ፋና ድርድሩን አስመልክቶ የካቲት 2 ቀን 2009 . ም የሚከተለውን ዘግቧል። ሃያ ሁለት ሀገር አቀፍ ፓርቲዎች በየራሳቸው ስብስብ ፈጥረው ከገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ጋር ለመወያየት እና ለመደራደር መዘጋጀታቸውን ገለፁ።

ኢዴፓ እና ሰማያዊ ፓርቲን ጨምሮ ስድስት ፓርቲዎች ባንድ በኩል ቅንጅት እና አንድነት ለዴሞክራሲ እና ለፍትህ ፓርቲን ያካተተ የ11 ፓርቲዎች ስብስብ በሌላ በኩል፥ ድርድር እና ውይይቱ የሚመራበትን ስርዓት፣ ድርድሩ በማን ይመራ የሚለውን እና የታዛቢዎችን ማንነት ያካተተ ፕሮፖዛል አቅርበዋል፡፡ 11 ፓርቲዎችን ያካተተው ስብስብም ከስዓታት በፊት መግለጫ ሰጥቷል፡፡

ፓርቲዎቹ በሶስት ስብስብ ተከፍለዋል አንደኛው በኢዴፓ አነሳሽነት የተደራጀው መኢአድን፣ ኢራፓን፣ ኢብአፓን እና ሰማያዊ ፓርቲን ያካተተው ስብስብ ሲሆን፥ ሁለተኛው ደግሞ ቅንጅት፣ ኢፍዲሀግ እና አትፓን የመሳሰሉ 11 ፓርቲዎችን የያዘ ስብስብ ነው ተብሏል፡፡

ከገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ ውጭ መድረክን ጨምሮ ቀሪዎቹ አራት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ራሳቸውን ችለው ቆመዋል፡፡ መግለጫውን የሰጡትም የአንድነት ለዴሞክራሲ እና ለፍትሕ ፓርቲ ሊቀመንበር እና የፓርቲዎቹ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ትእግስቱ አወሉ ናቸው፡፡

ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀረቡት የፕሮፖዛል ሀሳብም፥ ውይይቱ በማን ይመራ? በምን ህግ ይመራ? ጋዜጣዊ መግለጫስ ማን እና እንዴት ይስጥ? የሚለውን እያንዳንዳቸው ፕሮፖዛል እንዲያቀርቡ ተደርገው ነበር፡፡ ይህን የተናጠል ፕሮፖዛልም በመጭመቅ ነው ምክረ ሀሳቡን ያዘጋጁት፡፡ አቶ ትዕግስቱ ድርድሩ በተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች የተውጣጡ፣ ገዥው ፖርቲ በሚያቀርበው እንዲሁም ገዥው ፓርቲ እና ተቃዋሚዎች በመስማማት በሚያቀርቡት መሰረት በሶስት አደራዳዎች ቢመራ ብለዋል፡፡ ዓለምአቀፍ የውጭ ተቋማት ታዛቢዎች፣ ኢትዮጵያውያን ታዋቂ ግለሰቦች፣ የሲቪክ ማህበራትም በታዛቢነት እንዲቀመጡ ነው አስተያየታቸውን የሰጡት፡፡

በኢዴፓ ሀሳብ አመንጪነት የተዋቀሩት ስደስት ፓርቲዎችም በጋራ ሃሳብ አቅርበዋል፡፡ የኢዴፓ ሊቀመንበር ዶክተር ጫኔ ከበደ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ ስድስቱ ፓርቲዎች ድርድሩ በገለልተኛ ወገን እንዲመራ እንደሚፈልጉ ተናግረዋል፡፡ ለታዛቢነትም በውጭ እና በሀገር ውስጥ የሚኖሩ ምሁራን ያሉበት 11 ግለሰቦችን በዕጩነት ማቅረባቸውን አንስተዋል ዶክተር ጫኔ፡፡ መድረክ ከስድስቱ ፓርቲዎች ጋር የተቀራረበ ሀሳብ እንደሚኖረውም ግምታቸውን አስቀምጠዋል፡፡

እነዚህ ፓርቲዎች ውይይቱ እና ድርድሩ በማንና በምን መልኩ ይመራ? የጋዜጣዊ መግለጫው እና የሚዲያ ሽፋኑ እንዴት ይሁን? የሚለውን ሀሳብ ያካተተ ፕሮፖዛል ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጽህፈት ቤት አስገብተዋል፡፡

ፓርቲዎቹ በሀገር ውስጥ የፖለቲካ ምህዳሩን አጥብበዋል የተባሉ ህጎች እንዲሻሻሉ እና እስከ ህገ መንግስቱ ማሻሻያ ድረስ ሀሳቦችን በአጀንዳነት እንደሚያቀርቡ እና ምላሽ ለማግኘት እንደሚወያዩ ፍንጭ ሰጥተዋል፡፡ ሁለቱ የፓርቲዎች ስብስብም ወደ ውይይት እና ድርድሩ ለመግባት ምንም አይነት ቅድመ ሁኔታ እንደማያቀርቡ ገልፀው ወይይቱ ሲጀመር ግን አንድ ርዕሰ ጉዳይ መቅረብ እንዳለበት ቢናገሩም ይፋ ለማድረግ አልፈለጉም፡፡