በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል በተለይ በአፍዴር፣ በዳዋና በሊበን ዞኖች ድርቁ በጣም እየጠነከረ መምጣቱን፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ፡፡

ጽሕፈት ቤቱ ሰኞ የካቲት 6 ቀን 2009 ዓ.ም. ባወጣው ሳምንታዊ መግለጫ መሠረት፣ ለድርቅ ተጋላጭ የሆኑ የክልሉ አርብቶ አደሮች ከመቼውም ጊዜ በላይ እየተጎዱ ነው፡፡

በተለይ በአፍዴር ዞን የእንስሳት ሞት ቁጥር በጣም እየጨመረ መሆኑን የገለጸው ጽሕፈት ቤቱ፣ በዚህ ድርቅ ሁሉም ዓይነት እንስሳት እየሞቱ ነው ብሏል፡፡ በተለይ የበጎች፣ የፍየሎችና የቁም እንስሳት ሞት ጨምሯል ሲል አክሏል፡፡

በአፍዴር ዞን ሐርገሌ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት አቶ አብዲ አባዴ ለመስክ ጉብኝት ከወጣው የማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ባልደረቦች እንደገለጹት፣ ድርቁ ሲከሰት 25 የቁም እንስሳት የነበሩዋቸው ቢሆንም አሁን የቀሯቸው ግን ስድስት ብቻ ናቸው፡፡ ከእነዚህ በተጨማሪ አቶ አብዲ 70 በጎችና ፍየሎች እንደሞቱባቸው መናገራቸውን ጽሕፈት ቤቱ አስታውቋል፡፡

በዳዋና በሊበን ዞኖች ብቻ 40,861 እንስሳት መሞታቸውን ሪፖርት መቅረቡ ተገልጿል፡፡ በዚህ መሠረት 29,955 በጎችና ፍየሎች፣ 8,034 የቁም እንስሳት፣ 1,859 ግመሎችና 1,013 አህዮች ሞተዋል፡፡ አሁን የከፋ ድርቅ ወቅት በመሆኑ ተጨማሪ እንስሳት ሊሞቱ እንደሚችሉ ጽሕፈት ቤቱ አሳስቧል፡፡

እየተጠበቀ ባለው ከየካቲት አጋማሽ እስከ ግንቦት ያለው ደካማ ዝናብ፣ በድርቅ የተጠቁ የሶማሌ ክልል አካባቢዎችን ሁኔታ የበለጠ እንደሚያባብሰው ተገልጿል፡፡

በተመሳሳይ ከሶማሌ ክልል በተጨማሪ በኦሮሚያ ክልል በቦረና ዞንና በጉጂ ዞን፣ በደቡብ ክልል በደቡብ ኦሞ ዞን የእንስሳት ሞት ሪፖርት መደረጉን ጽሕፈት ቤቱ አስረድቷል፡፡ በቂና ወቅቱን የጠበቀ ዕርዳታ ማቅረብ ካልተቻለ ሁኔታው አሳሳቢ ነው ሲል አስጠንቅቋል፡፡

ምንም እንኳ በመንግሥትና በለጋሾች አማካይነት የሚደረገው ጥረት እየቀጠለ ቢሆንም፣ በአሁኑ ወቅት ከሚፈለገው ዕርዳታ አንፃር እየቀረበ ያለው በቂ አለመሆኑን ጽሕፈት ቤቱ ገልጿል፡፡ ሌላው ቀርቶ ድርቁ በፀናባቸው አካባቢዎች ውኃ ለማመላለስ ብቻ በሳምንት 2.7 ሚሊዮን ዶላር ያስፈልጋል ብሏል፡፡

መንግሥት ድርቁን ለመቋቋም እያደረገ ያለውን ጥረት ለማገዝ ከተለያዩ ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚሠሩ ዓለም አቀፍ ለጋሾች በማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤቱ ለሚመራው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ ፈንድ 17 ሚሊዮን ዶላር መገኘቱን አስታውቋል፡፡ ይሁንና በመላ አገሪቱ አስቸኳይ የምግብ፣ የቁሳቁስና የመድኃኒት ዕርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች 948 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ በቅርቡ በወጣ የዕርዳታ ፍላጎት ሰነድ መገለጹ አይዘነጋም፡፡