Wednesday, 15 February 2017 13:17
 አዲስ በካንሰር የሚጠቁ ህፃናት ቁጥር እየጨመረ እንደሚገኝ የተስፋ አዲስ ፓረንትስ ቻይልድሁድ ካንሰር ድርጅት አስታወቀ። የድርጅቱ ስራ አስኪያጅ ወ/ት ሣራ ኢብራሂም ለሰንደቅ ጋዜጣ እንደተናገሩት ከጥቂት ወራት ወዲህ በተሰበሰበ የዳሰሰ ጥናት በየወሩ ወደድርጅቱ የሚመጡ ከካንሰር ጋር የሚኖሩ ህፃናት ቁጥር በአማካኝ 30 መድረሱን ተናግረዋል።

በህፃናት ካንሰር ዙሪያ ግንዛቤን ለመፍጠር ዋነኛ አላማው አድርጎ በዓለም ለ16ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚከበረው “የህፃናት ካንሰር ቀን” ስለመዘጋጀቱም ተናግረዋል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ፤ በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ልዩ የካንሰር ህክምና ማዕከል ዛሬ (የካቲት 8 ቀን 2009 ዓ.ም) በተለያዩ ፕሮግራሞች የሚከበር ሲሆን፤ በቀጣይም የካቲት 12 ቀን 2009 ዓ.ም በ70 ደረጃ ማዘር ቴሬዛ ሆም ለማክበር በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ስራ አስኪያጇ ተናግረዋል።

በተለያየ ደረጃ የሚገኙና በካንሰር የተጠቁ ህፃናት ህክምና እንዲያገኙ ከማመቻቸት ባለፈ በድርጅቱ አማካኝነት ለወላጆችም ድጋፍ እንደሚደረግ ተጠቁሟል። በአሁኑ ወቅት በድርጅቱ ስር ከ100 በላይ ህፃናት አባል ሆነው የተመዘገቡ ሲሆን፤ ከእነዚህም መካከል 10 የሚሆኑት ህክምናቸውን በሚገባ ተከታትለው ከካንሰር ነፃ መሆናቸው ታውቋል።

ተስፋ አዲስ ፓረንትስ ቻይልድሁድ ካንሰር ድርጅት ካጋጠመው የገንዘብ እጥረት ባሻገር፤ በበርካታ ወገኖች ዘንድ ስለህፃናት ካንሰር ያለው ግንዛቤ አናሳ መሆንና በባህላዊ ህክምና ላይ ያተኮረ መሆን እንደፈተና የተጋረጠበት መሆኑንም ስራ አስኪያጇ አስረድተዋል። ይህንንም ችግር ለመቅረፍ በተለይ ከጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ጋር በመሆን በማህበረሰባችን ዘንድ የህፃናት ካንሰርን በተመለከተ ግንዛቤ እንዲሰፋ እየሰራ ይገኛል ብለዋል። ድርጅቱ የተመሰረተው በ2005 ዓ.ም ሲሆን፤ ሲጀመር በህክምና ማዕከላት ውስጥ ያሉ ታካሚዎች ህክምናቸውን እንዳያቋርጡ ድጋፍ መስጠት ላይ ያተኮረ እንደነበር ተናግረዋል። በአሁኑ ወቅት ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በጅማ የህጻናት ካንሰር ማዕከል ስራ መጀመሩን ያስታወሱት ስራአስኪያጇ በቀጣይም በሀገር አቀፍ ደረጃ ካንሰርን የተመለከተ እንቅስቃሴ እንደሚያደርጉ ጠቁመዋል።

ስንደቅ