Thursday, 25 December 2014 10:59

በጥበቡ በለጠ

የኢሕአፓ (የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ) መስራቹና ከፍተኛ አመራሩ ውስጥ የነበረው ክፍሉ ታደሰ “ያ ትውልድ”እያለ የሚጠራው የኢትዮጵያ ወጣት አለ፤ ነበረ። እኔ ደግሞ “ይህ ትውልድ” የምለው በዚህ እኔ ባለሁበት ዘመን ውስጥ አብሮኝ የሚኖረውን፣ የማውቀውን፣ የሚያውቀኝን ኢትዮጵያዊ ወጣት ነው። ክፍሉ ታደሰ ያ ትውልድ ብሎ ስለ ራሱ ትውልድ ሦስት ተከታታይ መፃሕፍትን አሳትሞለታል፤ ዘክሮታል። እርግጥ ነው፤ እኔ ደግሞ ስለዚህ ስለ እኔ ዘመን ትውልድ በየኮሪደሩ ከማወራው በስተቀር መፅሐፍ አላሳተምኩለትም። ግን እስኪ ወግ እንጠርቅ!

“ያ ትውልድ” ውስጥ በስፋት ተንፀባርቆ ይታይ የነበረው ለአዲስ አስተሳሰብ፣ ለለውጥ፣ ወደፊት ለመጓዝ፣ ጨለማውን ሰንጣጥቆ ወጥቶ ብርሃን ለማየት ወኔ፣ ቆራጥነት አይበገሬነት ይታይበት ነበር። ከዚህ ሌላ በዓለም አቀፍ ደረጃ ይቀነቀኑ ስለነበሩ ትኩስ ፖለቲካዊ አጀንዳዎችና ፍልስፍናዎች የማንበብ የማወቅና ከዚያም የመተግበር እንቅስቃሴዎችን ያዘወትራል።

በአንጻሩ ደግሞ “ያ ትውልድ” ለዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች ቅርብ አልነበረም። በርካታ መረጃዎች በየቀኑ አይጎርፉለትም። አእምሮውን የሚያስጨንቀው የሚያስጠብበው በሚከተለው የፍልስፍና መንገድ ብቻ ነው። እንደ ጥያቄ ያነሳውን ነገር ቀጥተኛ ምላሽ ካላገኘ ራሱን ለመሰዋት የተዘጋጀ ነበር።

ከዚህ አንጻር የእኔን ዘመን ትውልድ ሳየው ብዙ ልዩነቶችን አገኝበታለሁ። እርግጥ ነው፤ በዚህ በአሁኑ ትውልድ እና በያ ትውልድ መካከል አንድ የተዘነጋ ትውልድ አለ። ይህም የደርግ ዘመን ወጣት (አኢወማ) እየተባለ ይጠራ የነበረው ነው። አ.ኢ.ወ.ማ. ማለት (የአብዮታዊት ኢትዮጵያ ወጣቶች ማሕበር) ነው። ይህ ማህበር ደግሞ በማርክሲስት ሌኒኒስት ፍልስፍና የተጠመደ፣ በግድ እነዚህን ፍልስፍናዎች እንዲያውቅ የሚደረግ፤ ደርግ ያሳትመው የነበረው “ሠርቶ አደር” እየተባለ የሚጠራውን ጋዜጣ በግዴታ የሚያነብ በአጠቃላይ ብኩን ወጣት ነበር።

ይህ ብኩን ወጣት ከክፍሉ ታደሰ “ያ ትውልድ” ምንም ነገር እንዳይቀበል ተደርጓል። ወደዚህ ትውልድ ደግሞ ያወረሰው ያስተላለፈው ነገር እምብዛም ነው። ስለዚህ ክፍተት ያለበት ቦታ ነው።

ከዚህ ክፍተት በኋላ የተፈጠረው ደግሞ ዛሬ እስከ 35 ዓመት የእድሜ ክልል ውስጥ ያለው ወጣት ነው። ይህ የወጣት ክፍል በብዙ ችግሮች ውስጥ አልፎ የሚገኝ ነው። ለምሳሌ የነገዋን ብርሃን አሻግሮ እንዳይመለከት በ1980ዎቹ ውስጥ በሀገሪቱ አንድ አሸባሪ ክስተት ተፈጠረበት። ይህም የHIV ኤድስ ቫይረስ በስፋት መሰራጨት እና እሱን ተከትሎ ደግሞ ከየቤቱ የሚረግፈው ሰው ብዛቱ የትየለሌ ሆነ።

ከቫይረሱ በላይ ደግሞ ስለዚሁ በሽታ ማስተማሪያና ግንዛቤ መስጫ ተብሎ በየቀኑ የሚሠራጨው ማስታወቂያ፣ ማስፈራሪያ የወጣቱን ሃሳብና አመለካከት የሰለበው ይመስለኛል። በየቀኑ ተጠንቀቅ፣ እንዳትያዝ፣ ራስህን ጠብቅ፣ ውልፍጥ፣ መመናቀር፣ መንቀዥቀዥ የለም! ወዘተ የሚሉት የማስፈራሪያ ኃይለ ቃሎች በዚህ ዘመን የተፈጠረውን ወጣት የአእምሮ እስር ቤት ውስጥ የከተቱት ይመስለኛል። በነፃነት እንዳያስብ፣ የፈቀደውን እንዳያደርግ ማህበራዊ ጫና የተፈጠረበት ዘመን ነው።

ከዚህ ሌላ የሀገሪቱ ስርዓትን አስተሳሰብም ጭምር ወደ ሌላ ምዕራፍ የተገባበት ወቅት ነው። ሰዎች በአንድነት፣ በሕብረብሔርነት ሲያስቡት የነበረው ፍልስፍና ተቀይሮ ወደ ተለያዩ ጎሳና ቀበሌያዊ ተኮር ምዕራፎችም የተገባበት ዘመን ነው። ከሕብረብሔርነት ይልቅ እስኪ ማንነቴን፣ ትውልዴን፣ ቋንቋዬ፣ መንደሬን በቅድሚያ ላጥናው የተባለበት ወቅት ነው። ለጥናት ተብሎ እዚያው ቀበሌያዊ በሆነ አስተሳሰብ ውስጥ ገብቶ የተቀረበት ዘመን ነው። አያሌ የፖለቲካ ቡድኖች የተፈሩበት፣ ከዚያም አልፎ እነዚህ ቡድኖች ደግሞ ዋነኛ ትኩረታቸው ለተደራጁበት ቋንቋ እና ጎሳ መሆኑ ነው። ስለዚህ ትልቁን ሀገራዊ ስዕል ለማየት መጀመሪያ ወደ ስር ወርደን ቀበሌያችንን እንወቅ የተባለበት ዘመን ነው። ስለዚህ የዚህ ዘመን ወጣት ከያ ትውልድ አፈጣጠር የሚለይበት ዋነኞቹ ምክንያቶች እነዚህ ይመስለኛል።

ታዲያ ይህን ትውልድ እና ያንን ትውልድ ለማወዳደር እነዚህ ከላይ የጠቀስኳቸው መረማመጃ ነጥቦች እንዲያዙልኝ እፈልጋለሁ። ምን እነዚህ ብቻ ሌላም አብዮት ተከስቷል። ከ1985 ዓ.ም በኋላ አያሌ የግል የፕሬስ ውጤቶች መጥተዋል። እነዚህ ፕሬሶች ጥቅምም ጉዳትም ነበራቸው። ጥቅማቸው ልዩ ልዩ አስተሳሰቦች በነፃነት እንዲንሸራሸሩ ያደርጋሉ። ያበጡ የሰው ልጆችን ስሜቶች ያስተነፍሳሉ። በመተንፈስ ምክንያት ለሌላ እርምጃ የማይዳረጉ ሰዎች ተፈጥረዋል።

በአንድ ወቅት ስለነፃ ፕሬስ በቀረበ ጥናት አንድ አስገራሚ ነገር ሰምቻለሁ። ይህም የነፃ ፕሬስ ጎጂነት ተብሎ የተሰነዘረ ሃሳብ ነው። ነፃ ፕሬስ የሰዎችን ስሜት በነፃነት ስለሚያስተነፍስ ለትግል፣ ለውግያ፣ ለጦርነት ለለውጥ የሚደራጁ የለም የሚል። ለጦርነት የሚደራጅ አለመኖሩ ጥሩ ነው። ግን ነፃ ፕሬስ ስለማያዋጋ ጎጂ ገፅታው ነው ተብሎ መጠቀሱ ገርሞኝ አልፏል። ለማንኛውም ይህ ትውልድ ነፃ ፕሬስ ስለነበረው ሁሉንም ነገር ሲያነብ ቆይቷል።

መች በዚህ ብቻ አቆመ። የኤፍ ኤም ሬዲዮ ዘመንም ወረረው። ወረረው ያልኩት አደነዘዘው ወደሚለው መስመር እንዲያስገባኝ ነው። ይህ ወጣት በእንግሊዝ ክለቦች፣ በእነማንችስተርና አርሴናል ፍቅር ተለክፎ ከጥቅም ውጭ እየሆነ ነው የሚሉ አሉ። እርግጥ ነው በየጊዜው በትውልዱ ውስጥ እየተፈራረቁ የሚመጡት የአስተሳሰብ ልዩነቶች መጨረሻ ላይ አንድ መሸሸጊያ መጠለያ ጥግ ይፈልጋሉ። ኤች.አይ.ቪ. ኤድሱ፣ የጎሣ ተኮር ፖለቲካው፣ የሬዲዮ ጣቢያዎች የትኩረት አቅጣጫዎች ባብዛኛው ለእንግሊዝ ሀገር ስፖርት መሠጠት፣ ተጨባጭ የሆነ አዳዲስ ስርዓታዊ ለውጦችን አለማየት፣ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ የወጣቱ የስልጣን ውክልና እጅግ አናሳ መሆን ተደማምሮ የዚህን ዘመን ወጣት ሁሉንም ነገር እርግፍ አድርጎ የነሩኒ እና የነ ሜሲ የየእለት ሕይወት ተከታታይ አድርጎታል።

እኔ የዚህን ዘመን ወጣት ሃጢያቱን ለመቀነስ የተጠቀምኩባቸው መንደርደሪያዎቼ ተደርገው እንዳይወሰዱብኝ ከወዲሁ አሳስባለሁ። ይህ ወጣት በቴክኖሎጂ ውጤቶችም የተከበበ ነው። የዓለም መረጃዎችን ኪሱ ውስጥ አድርጎ ከያዛት ተንቀሳቃሽ ስልኩ ውስጥ ይዞ የሚኖር ነው። የፌስ ቡክ አብዮት ፈንድቶ በተለይ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት የደረሰ ወጣት ሁሉ ግንኙነት የፈጠረበት የተሳሰረበት ወቅት ነው።

እነዚህን የዘመኑን የመረጃ ቋቶች ጥሎ በአንድ አስተሳሰብና ፍልስፍና ውስጥ ተመስጦ የሚገባ ትውልድ አሁን የለም። ይህ ትውልድ ቀደም ብዬ በጠቀስኳቸው ነጥቦች የተከበበ፣ የተሠራ፣ የዚያም ውጤት ነው። ስለዚህ ትውልዱ የተፈጠረበትን የዘመን ዘር (ቅመም) በቅጡ ማወቅ ግድ ይላል።

አንዳንድ ሰዎች ይህን ትውልድ ሲወቅሱት ይደመጣል፤ ይነበባልም። የሚወቀሰው እንደ “ያ ትውልድ” ቆራጥ አይደለም፤ ራሱን አሳልፎ አይሰጥም፤ የሚያምንበት ዓላማ እና ፍልስፍና የለውም። አላማም ሆነ ፍልስፍና ከሌለው ደግሞ ተስፋ የሚጣልበት አይደለም እያሉ በተለያዩ ድረ-ገፆች ይወቅሱታል።

እኔ በበኩሌ ይህ ትውልድ ራሱን እና ቀጣዩን የሀገሩን እጣ ፈንታ እንዲረከብ፣ እንዲሰራ፣ ኃላፊነት እንዲሰማው የማድረግ ስራ በሁሉም ወገኖች ቢሰራ ነው ደስ የሚለኝ። ዛሬ በብዙ የስልጣን መንበር ላይ ያሉት ሰዎች የዚያ ትውልድ አባላት ናቸው። ዛሬ በተቃውሞ የፖለቲካ አስተሳሰብ ውስጥ ናቸው። ዛሬ በተቃውሞ የፖለቲካ አስተሳሰብ ውስጥ ያሉትም የዚያ ትውልድ አባላት ናቸው። ስለዚህ የዚህ ትውልድ እጣ ፈንታ የቱጋ እንደሆነ በቅጡና በውል አልታወቅ እያለ ነው።

ይህ ትውልድ ጨምሮ የሚቀጥለውም ትውልድ የተሻለ አስተሳሰብና አመለካከት እንዲኖረው የባሕል አብዮት መካሔድ አለበት። የባሕል አብዮት የምለው በሁሉም መስክ ነው። ለምሣሌ ትምህርታችን ላይ ትኩረት መደረግ አለበት። ኢትዮጵያዊ የሆነ የትምህርት ፍልስፍና እና አስተሳሰብ ያስፈልገናል። ዶ/ር እጓለ ገ/ዮሐንስ የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ ብለው ባሰናዱት መፅሀፍ ውስጥ እንደተጠቀሰው ትምህርታችን ኢትዮጵያዊ ግብ ያስፈልገዋል። በእንግሊዝ እግር ኳስ ጨዋታ የሚዋልል፣ የሚደባደብ፣ የሚገዳደል ትውልድ ማፍራት የለብንም።

ባሕል ስንል በሌላ መልኩ ታሪክን፣ ሃይማኖትን፣ ጥበብንም ይመለከታል። በሀገሩ ታሪክ የሚኮራ ትውልድ መፍጠር የየትኛውም ሃይማኖት ተከታይ ቢሆን ለሃይማኖቱ ታማኝ የሆነ፣ ፅናት ያለው ትውልድ ያስፈልጋል። ጥበብን ይውደድ ስል ማንበብን፣ መመራመርን፣ ማድነቅን፣ ሰውን መውደድን፣ ሀገሩን እና ሕዝቡን የሚታደግ ትውልድ ለማፍራት ዛሬ መጀመር የሚገባን ስራ አለ። ትውልድና ሀገር በሂደት ነው የሚገነቡት።

በአጠቃላይ “ያ ትውልድ” ላመነበት ፍልስፍና ብሎም አመለካት ራሱን ሰውቶ ያለፈው እኔ በበኩሌ የክብር ቦታ ሊያሰጠው ይገባዋል ባይ ነኝ። ምክንያቱም ሕይወቱን ከመስጠት ውጪ ሌላ ትልቅ ነገር የለምና ነው።

ይህ ትውልድ ደግሞ የራሱን ገመና የሚፈትሽበት ወቅት ነው። ሐገሬን አውቃታለሁ? ባህሌን፣ ታሪኬን፣ ማንነቴን መግለፅ እችላለሁ? ለሀገሬ ኢትዮጵያ እኔ ምንድን ነው ማድረግ የምችለው? በዚህች ፕላኔት ላይ ስኖር አላማዬ ምንድን ነው ብሎ እስኪ ዛሬን ያስባት። እናስባት። ሃሳቤ አላላቅም። ሣምንትም እቀጥልበታለሁ።

Leave a Reply