31 DECEMBER 2014 ተጻፈ በ 

         አምስተኛው ዙር ጠቅላላ ምርጫ ሊካሄድ የቀሩት ጥቂት ወራት ናቸው፡፡ በዚህ ጠቅላላ ምርጫ ላይ የሚሳተፉ የተለያዩ ፖለቲካ ፓርቲዎች አሉን የሚሏቸውን የመወዳደሪያ ነጥቦችና ከገዢው ፓርቲ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) የሚለያቸውን ነጥቦች በመዘርዘር የመራጩን ይሁንታ ለማግኘት በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛሉ፡፡

የአገሪቱን አጠቃላይ የምርጫ ጉዳዮች የሚያስፈጽመውና ምርጫዎችን በበላይነት የሚቆጣጠረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጽሕፈት ቤትም ምርጫውን በሰላማዊ፣ በፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ለማሳካት ያስቹልኛል ያላቸውን ቅድመ ዝግጅቶች ማጠናቀቁን፣ ቀጣይ ሥራዎችንም እያከናወነ እንደሚገኝ በተለያዩ ጊዜያት በሰጣቸው ጋዜጣዊ መግለጫዎች አስታውቋል፡፡

ምንም እንኳን የተወሰኑት የፖለቲካ ፓርቲዎች የተቃውሞ ሐሳብ ቢያቀርቡም አጠቃላዩን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ይፋ አድርጓል፡፡ እዚህ ላይ ልዩነት ያላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች አጠቃላይ የምርጫ የጊዜ ሰሌዳው ከመውጣቱና በዚያ ላይ ውይይት ከመደረጉ በፊት አጠቃላይ የምርጫና የፖለቲካ ምኅዳሩን የተመለከቱ ጥያቄዎቻችን ምላሽ ማግኘት እንዳለባቸው፣ ከጊዜ ሰሌዳው በፊት በሌሎች ጉዳይ ላይ መወያየት አስፈላጊ ነው በማለት የሚያነሱት ጥያቄ ተጠቃሽ ሲሆን፣ ምርጫ ቦርድም ጥያቄያቸውን በሌላ ጊዜና ቦታ መወያየት እንደሚቻል፣ አሁን ግን የጊዜ ሰሌዳው ይፅደቅ ማለቱ የሚታወስ ነው፡፡

በተወሰኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች በተነሳውና ከምርጫ ቦርድ ጋር የተፈጠረው ልዩነት እንደተጠበቀ ሆኖ ቦርዱ የምርጫ ጊዜ ሰሌዳውን ይፋ አድርጓል፡፡ በጊዜ ሰሌዳው መሠረትም የታቀዱት ተግባራት በዕቅዱ መሠረት እየተከናወኑ እንደሆነ ይገልጻል፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ ምርጫ ቦርድ በያዘው ዕቅድ መሠረት የሕዝብ ታዛቢዎች ምርጫ የተከናወነ ሲሆን፣ በግል ዕጩነት ለመወዳደር የሚፈልጉ ተወዳዳሪዎች ከቦርዱ ዋና ጽሕፈት ቤት ወይም ከክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የድጋፍ ማሰባሰቢያ ቅጽ ናሙና የሚያገኙበት ጊዜ ደግሞ በዚህ ሳምንት መጨረሻ ይጠናቀቃል ተብሏል፡፡

ከዝርዝር አጠቃላይ የምርጫ የጊዜ ሰሌዳ ውስጥ ቦርዱንና በተለይም ሁለት የፖለቲካ ፓርቲዎችን እያወዛገበ የሚገኘው ጉዳይ ደግሞ ለምርጫ የሚወዳደሩ ፓርቲዎች በቦርዱ ተገኝተው የመወዳደርያ ምልክታቸውን የሚመወስኑበት ጉዳይ ነው፡፡

ቦርዱ ባለፈው ታኀሳስ 10 ቀን 2007 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ እንዳመለከተው፣ በዚህ ሒደት ላይ ቦርዱን ያጋጠሙት ችግሮች ቀላልና ጥቂት ነበሩ፡፡ እነዚህም በጀመሪያ የተመረጡት ምልክቶች አልፎ አልፎ መመሳሰል፣ ለሕትመት ሥራ አመቺ ያለመሆንና ግልጽነት የሚጎድላቸው እንደነበሩ አስታውቋል፡፡ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ተገቢውን ማስተካከያ እንዲያደርጉ ቦርዱ አስፈላጊውን አመራር ሰጥቷል የሚል ነበር፡፡

‹‹ሆኖም ግን በሁለተኛ ደረጃ ጠንከር ያለው ችግር የሁለት ፓርቲዎች ጉዳይ ነበር፤›› በማለት ከፓርቲዎቹ አስፈላጊውን ሰነድና የአመራሮቹን ማንነት የሚገልጽ የጠቅላላ ጉባዔ ሪፖርት ባለማግኘቱ መቸገሩን ይገልጻል፡፡ እነዚህ ሁለት የፖለቲካ ፓርቲዎች አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ (አንድነት) እና የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ናቸው፡፡

ከእነዚህ ሁለት ፓርቲዎች ጋር የተፈጠረውን ችግር በተመለከተ ምርጫ ቦርድ በመግለጫው አስታውቋል፡፡ ‹‹እነኚህ ሁለት ፓርቲዎች የመወዳደሪያ ምልክቶቻቸውን ለጊዜው በሆደ ሰፊነት እንዲያስገቡ የተደረገ ቢሆንም፣ በየፓርቲዎቹ የውስጥ ጉዳይ ምክንያት በአመራሮች መካከል መከፋፈል በመፈጠሩ የፓርቲዎቹ ሕጋዊና ትክክለኛ አመራሮች ያለመታወቅ ችግር ነበር፤›› በማለት ይገልጻል፡፡

በመኢአድ በኩል በቦርዱ ከተጠቀሱት ችግሮች መካከል በፓርቲው ውስጥ በተፈጠረ የውስጥ ዴሞክራሲ እጦት ምክንያት ከ2003 ዓ.ም. ጀምሮ የምርጫ አዋጁንና የፓርቲውን መተዳደሪያ ደንብ ባላከበረ መንገድ ጠቅላላ ጉባዔ አካሂዶ ለቦርዱ ሪፖርት በማድረግ ማፅደቅ ያለመቻል፣ በየጊዜው  ደንብ በማሻሻል አመራር በመቀየር ተመርጠናል የሚሉ አካላት መከሰታቸው ይጠቀሳል፡፡ ይህ እንደ ትልቅ ችግር ከመቅረቡም በላይ፣ ቦርዱ ትክክለኛው የመኢአድ አመራር ማን መሆኑን ለመለየት ግራ ተጋብቻለሁ ይላል፡፡

‹‹የመኢአድ ፕሬዚዳንት ማን ነው? አቶ አበባው መሀሪ? ኢንጂነር ኃይሉ ሻውል? ወይስ አቶ ማሙሸት አማረ?›› በማለት ምርጫ ቦርድ ይጠይቃል፡፡ አንድነት ፓርቲን በተመለከተ ደግሞ፣ ‹‹ቦርዱ በማያውቀውና ዕውቅና ባልሰጠው የመተዳደሪያ ደንብ ማሻሻሉን፣ አሻሻልኩ የሚለውን ደንብም ለሰባት ወራት ለቦርዱ ሪፖርት ሳያደርግ ሚስጥር አድርጎ አስቀምጧል፤›› የሚል ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም፣ ‹‹ይኼንኑ ደንብ በመጠቀም ኢንጂነር ግዛቸው ሽፈራውን (የፓርቲውን ፕሬዚዳንት) ከሥልጣን አሰናብተዋል፡፡ በምትካቸውም በፓርቲው መተዳደሪያ ደንብም ሆነ በምርጫ አዋጁ በጠቅላላ ጉባዔ መመረጥ ያለበትን ወደጎን በመተው በብሔራዊ ምክር ቤት እንዲመረጥ አድርገዋል፤›› ይላል፡፡

በእነዚህና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች የተነሳም ቦርዱ ውሳኔ ለመስጠት መቸገሩን፣ የተጠቀሱትን ችግሮች በአስቸኳይ እንዲፈቱና የተጠየቁትን የሚስተካከሉ ነጥቦች በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ እንዲያቀርቡ ጠይቋል፡፡

የአንድነትና የምርጫ ቦርድ ውዝግብ 

ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ የአንድነት ፓርቲ የብሔራዊ ምክር ቤት አባልና የቅስቀሳ ዘመቻ ግብረ ኃይል ምክትል ሰብሳቢ አቶ አሥራት ጣሴ ለሪፖርተር፣ ‹‹ምርጫ ቦርድ ያወጣው መግለጫ በጣም የተሳሳተና ከእውነት የራቀ ነው፤›› በማለት ተቃውሟቸውን ገልጸዋል፡፡ ‹‹ታኅሳስ 19 እና 20 ቀን 2006 ዓ.ም. ጠቅላላ ጉባዔ አካሂደን በዚህ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ የፕሬዚዳንት ምርጫና የብሔራዊ ምክር ቤት ምርጫ ተከናውኗል፤›› ብለው፣ ‹‹ምርጫ ቦርድ ባወጣው መግለጫ መሠረትም እርግጥ ነው ሐምሌ 18 ቀን 2006 ዓ.ም. ነው ለምርጫ ቦርድ የጠቅላላ ጉባዔ የቃለ ጉባዔ ሰነድ ያስገነባው፤›› በማለት ለሰባት ወራት ያህል መዘግየቱን አምነዋል፡፡ ‹‹ነገር ግን የትኛው የአዋጅ 573/2000 አንቀጽ ነው አንድ ፓርቲ የጠቅላላ ጉባዔውን ሪፖርት በዚህ ጊዜ ውስጥ ገቢ ያደርጋል የሚለው?›› በማለት ጥያቄ አቅርበው ችግሩ የራሱ የምርጫ ቦርድ እንደሆነ ይከራከራሉ፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ ቁጥር 573/2000 ክፍል ሦስት ምዕራፍ ሁለት አንቀጽ 19፣ 20 እና 21 ሪፖርት ከማድረግ ጋር የተገናኙ አንቀጾችን የያዘ ሲሆን፣ የአዋጁ አንቀጽ 19 ሪፖርት የማቅረብ ግዴታ የሚል ነው፡፡ በዚሁ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 1 ማንኛውም በዚህ አዋጅ መሠረት የተመዘገበ የፖለቲካ ፓርቲ ቦርዱ ሲጠይቅ በሕጉ መሠረት የሚፈለገው የአባላት ቁጥር መሆኑን የሚያረጋግጥ ሰነድ የማቅረብ ግዴታ አለበት የሚል ነው፡፡ አቶ አሥራትም ምንም ግልጽ ያለ የጊዜ ገደብ የለም በማለት የሚጠቅሱት ይህንኑ አንቀጽ ነው፡፡

ቦርዱ ሲጠይቅ የሚለው አባባል መቼ ጠየቀ የሚለውን ጥያቄ ያስነሳል በማለት ሪፖርተር ያነጋገራቸው አንድ የፖለቲካ ተንታኝ ገልጸው፣ እንዲያውም ይህን መመለስ መቻል በጉዳዩ ላይ ለመነጋገር በር ይከፍታል ይላሉ፡፡ ከዚህ ባለፈ ግን ይህ ድፍን ያለ በመሆኑ ለተለያዩ ትርጓሜዎች የተጋለጠ ነው በማለት ይመልሳሉ፡፡ ሌላኛው የዚሁ አዋጅ አንቀጽ 21 የሚገልጸው ነገር አለ በማለት የሁለቱም ወገኖች አስተያየት ጥያቄ ውስጥ የሚገባ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡

የአዋጁ አንቀጽ 21 ማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ አዲስ የአመራር አባላትን የመረጠ እንደሆነ ወዲያውኑ ለቦርዱ ማሳወቅ አለበት ይላል፡፡ በዚህም መሠረት ሁለቱን ፓርቲዎች በሚመለከት የተነሳው ችግር የሚያርፈው እዚህ ላይ ነው በማለት የፖለቲካ ተንታኙ ያብራራሉ፡፡

ከእነዚህ አንቀጾች ይልቅ የቦርዱን ኃላፊነት በሚዘረዝረው የአዋጁ አንቀጽ ላይ ያተኮሩት አቶ አሥራት ጣሴ፣ ‹‹እንዲያውም ከዚህ በተቃራኒ በአዋጁ አንቀጽ 9 ንዑስ አንቀጽ 11 ላይ እንደተገለጸው፣ በዚህ አዋጅ አንቀጽ 12 ንዑስ አንቀጽ 2 መሠረት በፖለቲካ ፓርቲ የቀረበለትን የሰነድ ማሻሻያ መርምሮ መቀበል አለመቀበሉን በ30 ቀናት ውስጥ ለፓርቲው ያሳውቃል ይላል፤›› ብለዋል፡፡ በዚህ አንቀጽ መሠረትም ‹‹ሐምሌ 18 ቀን ለጻፍንለት ደብዳቤ ምርጫ ቦርድ ጉዳዩን አዘግይታችኋል የሚለው 30 ቀናት ካለፉት በኋላ ነው፤›› በማለት መልሰው ምርጫ ቦርድን ይከሳሉ፡፡

በፓርቲውና በምርጫ ቦርድ መካከል የተፈጠረው ልዩነት የአዋጁ አንቀጾች በአግባብ አልተተገበሩም ከሚለው መከራከሪያ በተጨማሪ፣ ‹‹የመግለጫው ምንጭ አንድነት ፓርቲ በአሁኑ ጊዜ ጥሩ መሠረት ላይ በመቆሙና በመጪው ጠቅላላ ምርጫ ለመሳተፍ ራሱን በጥሩ ሁኔታ እያዘጋጀ በመሆኑ፣ እንዲሁም የምርጫ ማኒፌስቶ ዝግጅታችንን ጥሩ ደረጃ ላይ እየደረሰ በመሄዱ ኢሕአዴግን ክፉኛ ስላስደነገጠው ነው፤›› በማለት ምርጫ ቦርድንና ገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግን ከመኮነን ባለፈ የተሰጠው መግለጫ፣ ‹‹የ2007ን ምርጫ ለማበላሸት የተሠራ ደባ ነው፤›› ይላሉ፡፡

የምርጫ ቦርድ ጥያቄና የመኢአድ ምላሽ

የመኢአድ አመራር ማን እንደሆነ መለየት መቸገሩን ለሚገልጸው የቦርዱ ጥያቄ የመኢአድ ፕሬዚዳንት አቶ ማሙሸት አማረ፣ ‹‹ምርጫ ቦርድ ያውቀናል፡፡ እንደሚያውቀንም ማረጋገጫው ጠቅላላ ጉባዔአችንን በሁለት ታዛቢዎቹ አማካይነት መታዘቡንና ከዚህም በላይ የምርጫ ምልክታችሁን በአስቸኳይ እንድታስገቡ የሚል ደብዳቤ መላኩ ነው፤›› በማለት ቦርዱ ያወጣው መግለጫ እውነታን መሠረት ያላደረገና መራጩን ኅብረተሰብ ውዥንብር ውስጥ የሚከት ነው፤›› በማለት ይከራከራሉ፡፡

በምርጫ ቦርድ በፓርቲው ውስጥ የተከሰቱ አዳዲስ ክስተቶችን በወቅቱ አለማሳወቅን በተመለከተ ከሪፖርተር ጥያቄ የቀረበላቸው የፓርቲው ፕሬዚዳንቱ፣ ‹‹አሁን ያለው የመኢአድ አመራር ጥቅምት 29 ቀን 2007 ዓ.ም. በጠቅላላ ጉባዔው የተመረጠው አካል ነው፡፡ ይህንንም እንዲያውቅና እንዲቀበል የጠቅላላ ጉባዔውን አባላትና ቃለ ጉባዔውን ለቦርዱ አስገብተናል፡፡ እስካሁን የዘገየበትን ምክንያት ቦርዱም የሚያውቀው ነው፤›› በማለት ገልጸዋል፡፡

‹‹ቦርዱ የሚያውቀው የመኢአድ ችግር ቀደም ሲል ፓርቲው ውስጥ የነበሩት ግለሰቦች ማኅተሙን ይዘውት ስለሄዱና ማኅተም ለማድረግ በምንሰጣችሁ ጊዜ ቀርፃችሁ አምጡ የሚል ምላሽ ከቦርዱ ኃላፊዎች በማግኘታችን ነው፤›› በማለት የዘገየበትን ምክንያት በመግለጽ ቦርዱ ያወጣውን መግለጫ ተቃውመዋል፡፡

እንደ አቶ አሥራት ጣሴ አቶ ማሙሸት አማረም ይህ መግለጫ፣ ‹‹ሆነ ተብሎ መኢአድን ለማጥፋት ወይም ለመዝጋት የተሠራ ሴራ ካልሆነ በስተቀር፣ አላውቃቸውም ብሎ የሚወሰንበት ምንም የሕግ መሠረት የለም፤›› በማለት ይከራከራሉ፡፡

የምርጫ ቦርድ ምላሽ

ምርጫ ቦርድ በመግለጫው ላይ የተዘረዘሩት ችግሮች እያሉ እንዴት የምርጫ መወዳደሪያ ምልክት እንዲወስዱ ዕድል ሰጣቸው ለሚለው የሪፖርተር ጥያቄ ምላሽ የሰጡት፣ የቦርዱ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ደምሰው በንቲ ናቸው፡፡

በምላሻቸውም፣ ‹‹ቦርዱ በተለይ የዴሞክራሲ ባህላችን ገና እንጭጭ ከመሆኑ አንፃርና የዴሞክራሲ ባህል እንዲዳብር ከማድረግ አኳያ በትዕግሥትና በአስተውሎት የሚያያቸው በርካታ ነገሮች በመኖራቸው ነው፤›› ብለው፣ ‹‹እያንዳንዱን ጉዳይ በዚህ መልኩ ይህንን እንዲህ አላልክም ወይም አላደረክም ብሎ ቦርዱ የሚያቆመው ከሆነ በርካታ ፓርቲዎች ባልነበሩ ነበር፡፡ ችግራቸውን ቀስ በቀስ እንዲፈቱና እንዲያስተካክሉ እየተደረገ ነው ያለው፡፡ ይህም የዚህ ሒደት አካል ነው፤›› በማለት ገልጸዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ፓርቲዎቹ የሚያቀርቡት ወቀሳ መሠረተ ቢስ ነው ይላሉ፡፡  ‹‹የወጣው መግለጫ ማንንም ከምኅዳሩ ገፍትሮ ለማስወጣት እንዲሁም ማንንም ጎትቶ ለማስገባት አይደለም፡፡ ሕጉ እንዲከበር እንጂ፤›› በማለት የፓርቲዎቹን ተቃውሞ እውነት ላይ መሠረት ያደረገ አይደለም በማለት መልሰው ፓርቲዎቹን ይወቅሳሉ፡፡

አክለውም፣ ‹‹በዚህ ጊዜ ውስጥ ያለባችሁን ጉድለት አሟልታችሁ አቅርቡ ነው የተባለው፡፡ በተሰጣቸው ጊዜ ውስጥ የተጠየቁትን ነገር አሟልተው ካቀረቡ እሰየው ነው፡፡ ካልቀረቡ ምን ይሆናል የሚለውና እንዴት ነው የሚስተናገዱት የሚለውን የሚወስነው ቦርዱ ነው የሚሆነው፤›› በማለት የመጨረሻው ውሳኔ ከቦርዱ የሚመነጭ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ በምርጫ ቦርድና በሁለቱ ፓርቲዎች መካከል ያለው ልዩነት በጊዜ ሰሌዳው መሠረት በቅርቡ ውሳኔ የሚያገኝ እንደሚሆን፣ ውሳኔው ምን ሊሆን እንደሚችል በቅርቡ እንደሚታወቅ ይጠበቃል፡፡

Leave a Reply