28 DECEMBER 2014 ተጻፈ በ 

         ከቀኑ ስምንት ሰዓት ተኩል ገደማ ገርጂ ኢምፔሪያል ሆቴል አካባቢ ነው፡፡ ከአስፋልት መንገድ ዳር ከቆሙ መኪኖች አጠገብ መሬት ላይ በጀርባው ተዘርግቷል፡፡ አፍንጫው ይደማል፡፡

ከቦታው ላይ የነበሩት ሰዎች ግራ በመጋባት ወጣቱን ዝም ብለው ይመለከቱታል፡፡ ነገሩን ከመጀመሪያው ያዩ ወጣቱ እንዴት ከሌላኛው የመንገዱ አቅጣጫ እየተንደረደረ አስፋልቱን አቋርጦ መሬት እንደወደቀ፣ ሌሎች ደግሞ የወጣቱ ሕመም የሚጥል በሽታ ሳይሆን እንደማይቀር ይናገሩ ነበር፡፡

ወጣቱን ከበው የነበሩት ሰዎች ሊረዱት ቢፈልጉም ምን ሆኖ ይሆን? እና እንዴት እናድርግ? በሚለው ግራ ተጋብተው ስለነበር ከማየት ውጪ ማንም ምንም ሊያደርግለት አልቻለም፡፡ ምንም እንኳ ስለክብሪት መጫር ጠቃሚነት ቢነሳም የሚጥል በሽታ ነው ብለው ባመዛኙ ያመኑም እርግጠኛ ሆነው ክብሪት ሊጭሩለት አልደፈሩም፡፡ በመሀል ግራ በሚያጋባ መልኩ ወጣቱ አፍንጫ ላይ የሚታየው ደም መሆኑን የጠየቀ ሰው ሁሉ ነበር፡፡ በግዴለሽነት አልያም ልናደርግለት የምንችለው ነገር አይኖርም ብሎ በማሰብ በሚመስል ዓይናቸውን ወርወር አድርገው መሬት ላይ በጀርባው የተዘረረውን ወጣት እንደዋዛ አየት አድርገው የሚያልፉም ነበሩ፡፡

ቤተሰብ፣ ጓደኛ የማያውቁት ሰው በድንገተኛ የልብ ሕመም፣ በኤሌክትሪክ አደጋ፣ በእሳት ቃጠሎ፣ በድንገተኛ የመተንፈስ ችግርና በሌላም ቅፅበት ሕይወቱ አደጋ ላይ ሊወድቅ የሚችልበት አጋጣሚ ብዙ ነው፡፡ በእንዲህ ያለው አጋጣሚ ሕይወቱ አደጋ ላይ የወደቀው ሰው ቦታው ላይ የተገኘ የማንም ዕርዳታ እንደሚያስፈልገው ግልጽ ቢሆንም እንዴት መርዳት ይቻላል? የሚለው ግን በብዙ መልኩ የሚታይ ነው፡፡ ምክንያቱም እንዴት መርዳት እንደሚቻል ባለማወቅ ከመርዳት መታቀብም ያለምንም ዕውቀት ለመርዳት መሞከርም የተጎጂዎችን ጉዳት ይበልጥ ሊያባብስና ሕይወታቸውንም አደጋ ላይ ሊጥል ይችላል፡፡

‹‹ሰዉ እንዴት መርዳት እንዳለበት ይወቅ አይወቅ ለመርዳት ወደኋላ አይልም›› የሚለው በቦሌ ሮክ ዋና አለማማጅ የሆነው አቶ እስከዳር አቻምየለህ ከ17 ዓመታት በላይ የነፍስ አድን ሠራተኛ በመሆን መሥራቱን ይናገራል፡፡ በሥራ ያሳለፋቸውን የተለያዩ አጋጣሚዎች በማስታወስ የመጀመሪያ ደረጃ የሕክምና ዕርዳታ እንዴት እንደሚሰጥ ሳያውቁ ሰዎች ሕይወቱ አደጋ ላይ ያለን ሰው ለመርዳት ሲሞክሩ መያዝ የሌለበትን ቦታ በመያዝ የአየር ቧንቧ እንዲዘጋ የማድረግ ነገር መኖሩን ይገልጻል፡፡

ብዙ ጊዜ የልብ ችግር፣ ስኳር፣ የሚጥል በሽታና የደም ግፊት ያለባቸው ሰዎች ዋና ላይ ችግር ሲያጋጥማቸውና ሌሎች ለመርዳት ሲሞክሩ ዕርዳታው በተገቢው መልኩ ሳይሆን፣ ጉዳት ሲያመዝን ማየቱን ይናገራል፡፡ በአንፃሩ ሰዎች ለተጎዳ ዕርዳታ ከማድረግ ሲታቀቡም ማስተዋሉን ይናገራል፡፡ እሱና መሰል ባልደረቦቹ የመጀመሪያ ደረጃ ሕክምና ሥልጠና መውሰዳቸውን ሥልጠናውም ማንኛውም ሰው የሚወስደው ሆኖ ተጨማሪ ነገሮች እንዳሉት ገልጾልናል፡፡

‹‹የመስመጥ አደጋ ደርሶበት የነበረ ሰውን መርዳት ሲታሰብ ሰውየው ውኃ ውስጥ ምን ያህል እንደቆየ መገመት ያስፈልጋል፤›› የሚለው አቶ እስከዳር፣ ሌሎችም ነገሮች ከግምት ሊገቡ የግድ ነው ይላል፡፡ የመስመጥ አደጋ የደረሰበትን ሰው መርዳት ሲታሰብ የአፍ ለአፍ ትንፋሽ መስጠት ለብዙዎች ወደ አእምሮ የሚመጣ ነገር ቢሆንም በመድማት፣ በትንፋሽ የሚተላለፉ በሽታዎች መኖርና በሌሎችም ምክንያቶች መቅረቱን ይገልጻሉ፡፡ ስለዚህም በዋና ልምምድ ላይ የአፍ ለአፍ ትንፋሽ መስጠትን ሊተካ በሚችል መሣሪያ ነው የሚጠቀሙት፡፡ ይህ መሣሪያ ከሌለስ? የሚለው ጥያቄ ግን አደጋው እንደተፈጠረበት ሁኔታ መልስ የሚያገኝ ይመስላል፡፡

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ኮሙዩኒኬሽን አስተባባሪ አቶ በቃሉ አያሌውም የመጀመሪያ ደረጃ ሕክምና አላውቅም ብሎ ዕርዳታ ባለማድረግ፣ ያለግንዛቤ በመርዳትም አደጋ የደረሰበቸው ሰዎች ጉዳት ሲከፋና ሕይወት ሲያልፍም እየታየ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡

ማኅበሩ ለሠራተኞቹና በጎ ፈቃደኝነት ለሚያገለግሉ ነፃ የመጀመሪያ ደረጃ ሕክምና ዕርዳታ ሥልጠና ይሰጣል፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ሕክምና ለመከላከል፣ ጉዳትን ለመቀነስና ሕይወትን ለማትረፍ ወሳኝ በመሆኑ ቢቻል ሁሉም ሰው ሥልጠናው ሊኖረው ይገባል የሚሉት አቶ በቃሉ፣ አደጋ ሊደርስ ይችላል ተብሎ በሚታሰብባቸውና ሰው በሚበዛባቸው እንደ ፋብሪካና ኢንዱስትሪ ባሉ ተቋማት እንዲሁም በግንባታ ሳይቶች በክፍያ ሥልጠናውን እንደሚሰጡ ያስረዳሉ፡፡

ሥልጠናው ለሠራተኞች መሰጠቱ በራሱ በቂ ስለማይሆን የመጀመርያ ሕክምና ዕርዳታ መስጠት የሚያስችለውና 35 ዓይነት የሕክምና ቁሳቁስ ያለውን የመጀመሪያ ደረጃ ሕክምና ዕርዳታ ሳጥን እንዲኖር ማድረግ የተቋማት ኃላፊነት ይሆናል፡፡ ነገር ግን በተለይም በግንባታ ሳይቶች ላይ ሠራተኞች ሥልጠና እንዲወስዱ የማድረግም በጥቅሉ የመጀመሪያ ደረጃ ሕክምና ጉዳይ የታሰበበት ነገር አለመሆኑን መታዘባቸውን ገልጸውልናል፡፡

የሌሎች አገሮችን ተሞክሮ በመጥቀስ ሁሉም ሰው ባይሆን እንኳ በተለያየ ምክንያት ሠራተኞች ለአደጋ ተጋላጭ ይሆናሉ ተብሎ በሚታመን የሥራ ዘርፍ የተሰማሩ የመጀመሪያ ደረጃ ሕክምና ሥልጠና እንዲወስዱ ማድረግ አስገዳጅ ሊሆን ይገባል የሚል አቋም ቢሯቸው እንዳለው አቶ በቃሉ ይገልጻሉ፡፡ ‹‹ይሄ መከላከል ላይ ከሚያተኩረው የአገሪቱ የጤና ፖሊሲ ጋርም የሚሄድም ነው›› ይላሉ፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ሕክምና ልክ እንደ ጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም ትኩረት ሊያገኝ ይገባል ብለው ያምናሉ፡፡

በተለያዩ ቦታዎች በግንባታ ሳይቶች ላይ ተዘዋውረን ለማየት እንደሞከርነው የመጀመሪያ ደረጃ ሕክምናን በሚመለከት ያገኘነው ነገር የለም፡፡ አንዳንድ ቦታዎች ላይ እንዲያውም የመጀመሪያ ደረጃ ሕክምና ምንድን ነው? በሚል ጥያቄያችን በጥያቄ ተመልሷል፡፡ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽንና ኢንዱስትሪ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ዘገየ ኃይለ ሥላሴ 95 በመቶ በሚሆኑ የግንባታ ሳይቶች የመጀመሪያ ደረጃ ሕክምና ቦታ እንዳልተሰጠው ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ምንም እንኳ በአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ ላይ የሠራተኛው የሥራ ላይ ደኅንነትን በሚመለከት በግልጽ የተቀመጠ ነገር ቢኖርም በግሉ ዘርፍ በመንግሥትም በሚካሄዱ ግንባታዎች የመጀመሪያ ዕርዳታ ሕክምና ቦታ እንዳልተሰጠው፣ ሠራተኞች ግን ዕለት ከዕለት ከሚያጋጥማቸው ነገር በመነሳት ስለመጀመሪያ ደረጃ ሕክምና ዕርዳታ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ሥልጠና፣ ቁሳቁሶችም እንዲሟሉላቸው እንደሚጠይቁ ገልጸዋል፡፡ ቀላል ጉዳት ብቻ ሳይሆን፣ ከስካፎልዲንግ (የግንባታ መወጣጫ) መውደቅ በተደጋጋሚ በሚታይበት በዚህ ዘርፍ ለመጀመርያ ደረጃ ሕክምና ቦታ አለመሰጠቱ ግን ይገርማል›› ይላሉ፡፡

ከመኪና አደጋ፣ በግንባታ ሳይቶች ላይ ከሚደርስ ጉዳት፣ ከመውደቅና ራስን ለማጥፋት ከሚደረጉ ሙከራዎች ጋር በተያያዘ አደጋ ደርሶ ወደ ሆስፒታሉ ከሚሄዱ ሰዎች ሁኔታ በመነሳት በኅብረተሰቡ ዘንድ ስለመጀመርያ ደረጃ ሕክምና ግንዛቤ አለመኖሩን በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝ ሆስፒታል የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስትና የድንገተኛ ሕክምና ክፍል ኃላፊ ዶ/ር አክሊሉ አዛዥም ይናገራሉ፡፡

ከፍተኛ ጥረት የተደረገ ቢሆንም ዛሬም የአምቡላንስ ሕክምና አገልግሎት ባልተዳረሰበት የአገሪቱ ሕክምና ዘርፍ የመጀመርያ ደረጃ ሕክምና ግንዛቤ ዋጋው ከፍተኛ ነው የሚል እምነት አላቸው፡፡ ‹‹አደጋ የደረሰበት ሰው በትክክል ከወደቀበት ካልተነሳ፣ መሸከሙም ሆነ መኪና ላይ መጫኑም በተገቢ መንገድ ካልሆነ አከርካሪ፣ አንገት ወይም ጭንቅላት ላይ የባሰ አደጋ ይደርሳል፡፡ የአየር መስመርንም የመዝጋት ነገር አለ›› ብለዋል ዶ/ር አክሊሉ፡፡

እንደ አቶ በቃሉ የሌሎች አፍሪካ አገሮችን ተሞክሮ በማንሳት በተወሰኑ ሁኔታዎች ውስጥ የመጀመርያ ደረጃ ሕክምና ዕርዳታን አስገዳጅ ማድረግ ተገቢ ነው ብለው የሚያምኑት ዶ/ር አክሊሉ፣ ለምሳሌ የመጀመርያ ደረጃ ሕክምና መስጫ ቁሳቁስ መኪናዎች ውስጥ ማኖር ሾፌሮችም ሥልጠናው እንዲኖራቸው ግዴታ ቢደረግ፤ ይህን የማያደርጉ አሽከርካሪዎች ደግሞ የሚቀጡ ቢሆን ይላሉ፡፡ ከዚህ ሲያልፍ ደግሞ በትምህርት ቤቶችም ሥልጠናው እንደ አንድ የሥርዓተ ትምህርት ክፍል ሆኖ ቢሰጥ ጥሩ መሆኑን፣ ሥልጠናው የ36 ሰዓታትና አጭር በመሆኑ ተግባራዊ ማድረጉም ከባድ አይሆንም ይላሉ፡፡

ዶ/ር አክሊሉ እንደሚሉት፣ በአገሪቱ እየተካሄደ ካለው የግንባታ ሁኔታ፣ የትራፊክ አደጋና ሌሎችም እውነታዎች አንፃር ዜጎችን የመጀመሪያ ደረጃ ሕክምና ግንዛቤ ያላቸው ማድረግ ከመቼውም የበለጠ ወሳኝ ነው፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ሕክምና ግንዛቤ ያለው ኅብረተሰብ ደግሞ አደጋን የሚከላከልም ጭምር መሆኑ ተጨማሪ ጥቅም ነው፡፡ አስተያየታቸውን የሰጡት ባለሙያዎች ባሉት ደረጃ ባይሆን በኅብረተሰቡ ዘንድ በተወሰነ መልኩ እንኳ ስለመጀመሪያ ደረጃ ሕክምና ግንዛቤ ቢኖር በብዙ ሰው ተከቦ ነገር ግን አንድ ሰው እንኳ እንዳልረዳው ወጣት ያሉ ብዙዎች ሕይወታቸው ከአደጋ ይተርፋል፡፡

ዓለም አቀፍ የቀይ መስቀል ፌዴሬሽን የመጀመሪያ ደረጃ ሕክምና ላይ ከዓለም አቀፍ ተቋማት ቀዳሚው ሲሆን፣ እ.ኤ.አ. የ2011 መመሪያው እንደሚያስቀምጠው፣ የመጀመሪያ ደረጃ ሕክምና ለታመመ ወይም ድንገት ጉዳት ለደረሰበት የሚሰጥ አፋጣኝ የሕክምና ዕርዳታ ነው፡፡ መመሪያው እንደሚያሳየው በ2009 በዓለም አቀፍ ደረጃ ሰባት ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች ዕውቅና ያለው የመጀመሪያ ደረጃ ሕክምና ዕርዳታ ሥልጠና ወስደዋል፡፡ በተመሳሳይ ዓመት 36,000 አሠልጣኞችና 770,000 በጐ ፈቃደኞች በስፋት የተንቀሳቀሱ ሲሆን፣ 46 ሚሊዮን ለሚሆኑ ሰዎች የመጀመሪያ ደረጃ ሕክምና ዕርዳታ ተደራሽ ሆኖ ነበር፡፡

Leave a Reply