31 DECEMBER 2014 ተጻፈ በ 

በገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግና በተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ለዓመታት የዘለቀው ግንኙነት የጠላትነት መሆኑ በገዛ ራሱ የአገር ችግር ነው፡፡

በችግርነት ተጠቃሽ የሚሆነውም እንዲህ ዓይነቱ ግንኙነት ዲሞክራሲያዊ ባህሪ የሌለው በመሆኑ ነው፡፡ የተወዳዳሪነትና የእኔ እበልጥ ፉክክሩ በመራጩ ሕዝብ ፊት ፍትሐዊ በሆነ መንገድ መከናወን ሲገባው፣ አንዱ ሌላኛውን የአገር ጠላት የማድረግ ክፉኛ የተጠናወተ መንፈስ ሰላማዊውንና ዲሞክራሲያዊውን ሒደት እያደናቀፈው ነው፡፡

በዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ውስጥ በተግባር የሚታወቀው ፖለቲካ ፓርቲዎች እንደሚከተሉት ርዕዮተ ዓለም በኩረ ሐሳብ የተለያዩ መሆናቸው ሲሆን፣ ሁሉም ፓርቲዎች ከነልዩነታቸው ዕውቅና ተሰጣጥተው ሰላማዊ ተወዳዳሪ መሆናቸው አፅንኦት ይሰጠዋል፡፡ ይህም የዲሞክራሲ ጽንሰ ሐሳብ አንዱ መገለጫ ነው፡፡ ማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ለሕዝብ ይበጃል ብሎ ይዞ የሚመጣውን ርዕዮተ ዓለም የሚቀበለው ወይም የሚጥለው መራጩ ሕዝብ ብቻ ነው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተግባር ሒደቱን ሰላማዊ፣ ነፃና ፍትሐዊ ማድረግ ብቻ ነው፡፡

በኢትዮጵያ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ ስናየው ግን የዚህን ተቃራኒ ነው የምናገኘው፡፡ ልዩነትን አቻችሎ በብሔራዊ ጉዳዮች ላይ መነጋገር አልተቻለም፡፡ አንዱ የሌላውን ድክመትና ጉድለት ከራሱ ጥንካሬ ጋር እያወዳደረ ከማሳየት ይልቅ፣ የአገርና የሕዝበ ጠላት አድርጎ መፈረጅ ይቀለዋል፡፡ ይህ ዓይነቱ የከፋ ድርጊት እየተፈጸመ ያለው ደግሞ በገዥው ፓርቲና ዋነኛ በሚባሉት ተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል ነው፡፡ ልዩነትን ማቻቻል ይቅርና በሰከነ መንገድ ለመነጋገር እንኳን ፍላጎቱ የላቸውም፡፡ በዚህም ምክንያት ሕዝብ ተስፋ እየቆረጠ ነው፡፡ በተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ ውስጥ ስለ ዲሞክራሲ መነጋገር ትርጉም የለውም፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች ቅራኔያቸውን አርግበው ለመራጩ ሕዝብ ውሳኔ ተገዥ እስካላደረጉ ድረስ ስለምርጫም ሆነ ስለዲሞክራሲ መናገር አስቸጋሪ ነው፡፡ በመካከላቸው ያለው ጠላትነት ተጠናክሮ በቀጠለ ቁጥር ለውጭ ጠላት ያጋልጣል፡፡ ለአገር ብሔራዊ ደኅንነትም አደጋ ነው፡፡ በመሆኑም የፈለገውን ያህል ችግር ቢኖርም ቅራኔው በሰላም መፈታት አለበት፡፡ ብቸኛው መፍትሔም ሰላማዊ፣ ሕጋዊና ዲሞክራሲያዊ መንገድ ብቻ ነው፡፡ ይህ መንገድ ከጠብ ይልቅ ለድርድር ቅርብ ነው፡፡

ዲሞክራሲ የተለያዩ አስተሳሰቦችና ፍላጎቶች በነፃነት የሚስተናገዱበት እስከሆነ ድረስ ሁለቱም ወገኖች ከጠላትነት ይልቅ ተፎካካሪነት፣ ባወጣ ያውጣህ ተባብሎ ለጠብ ከመፈላለግ ይልቅ ተደራዳሪነት፣ አማራጮችን ከማጥበብ ይልቅ ለፖለቲካው ሥነ ምኅዳር መስፋት አስተዋጽኦ ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡ አሁን ግን የምናየው ልዩነቶቻቸውን የማይታረቁና የማይደራረሱ በማድረግ በጠላትነት መቀጠላቸውን ነው፡፡

ገዥው ፓርቲና ተቃዋሚዎች በጎ ነገሮች ያሉት በየራሳቸው ዘንድ እንደሆነ፣ ተቃራኒያቸው በእኩይ ባህርያት መታጨቁንና አንዱ ሌላውን የአገርና የሕዝብ ጠላት በማድረግ ሥጋትና ጥላቻ እንዲፈጠር ያደርጋሉ፡፡ ሁለታችንም ተሳስተን ቢሆንስ? ትክክለኛው ነገር ከሁለታችን ውጭ ቢኖርስ? መልካሙና መጥፎው በሁለታችንም በኩል አንድ ላይ ይኖር እንደሆነስ? የሚል አመለካከት አይታይባቸውም፡፡ ይልቁንም አንዱ የሌላውን መልካም ነገር ቢናገር ትልቅ ፖለቲካዊ ሽንፈት ሆኖ ይቆጠራል፡፡ ይህ ፈጽሞ ለአገር የሚበጅ አይደለም፡፡

ገዥው ፓርቲ አገርን የመምራት ትልቅ ኃላፊነት ተሸክሞ ከተቃዋሚዎች ጋር በሰላማዊ መንገድ ለመነጋገርና ለመደራደር ፍላጎት የለውም፡፡ ለታይታ ያህል ፍላጎት እንዳለው ቢገልጽም በተግባር አይታይም፡፡ ውይይቱን ወይም ድርድሩን በቅድመ ሁኔታ ያጥረዋል፡፡ ከዚያ አልፎ ተርፎ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎችን እንቅስቃሴ በተለያዩ ምክንያቶች ያደናቅፋል፡፡ በሕገ መንግሥቱ ዋስትና ያገኙትን የመደራጀት፣ የመቃወምና ሐሳብን  በነፃነት የመግለጽ መብቶች የሚፃረሩ ድርጊቶችን እየፈጸመ ለሥነ ምኅዳሩ መጥበብ የራሱን አሉታዊ ሚና ይጫወታል፡፡ በተለይ በአመራር ደረጃ ያሉ ሰዎች ይህንን ዓይቱን ድርጊት የማስቆም ኃላፊነት አለባቸው፡፡ የዲሞክራሲ ሒደቱን እየተፈታተነ ነውና፡፡ ለአገር ህልውና አይበጅምና፡፡

ተቃዋሚ ፓርቲዎችም ከገዥው ፓርቲ ጋር በሚያደርጉት ፉክክር የራሳቸው ችግር አለባቸው፡፡ እስከዛሬ የመጡበትን መንገድ በቅጡ የፈተሸና መጪውን ጊዜ ጥርት ባለ ፖሊሲ የገመገመ አካሄድ ሳይኖራቸውና እዚህ ግባ የሚባል አማራጭ ሳይዙ ጥላቻ ውስጥ ይነከራሉ፡፡ የትግል ሥልታቸው ተደጋጋሚና አሰልቺ ከመሆኑ የተነሳ ሕዝቡ ምን እንደሚፈልጉ እንኳ በቅጡ የተረዳቸው አይመስልም፡፡ ‹‹የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው›› እና ‹‹የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው›› በሚባል አዘናጊ ተረቶች ውስጥ ሆነው ለዘመኑ ፍላጎት የሚመጥን ነገር ይዘው መቅረብ እያቃታቸው ነው፡፡ በውስጣቸው ካለው ሽኩቻ መረዳት የሚቻለውም ይህንኑ እውነታ ነው፡፡ ይህንን በፍፁም መካድ አይቻልም፡፡ ውስጥን ሳያጠሩ በአሮጌ መፈክር የትም መድረስ የማይቻልበት ዘመን ላይ ነን፡፡ ውጤት የሚገኘው ከጥላቻ ሳይሆን ከድርድር ብቻ ነው፡፡

እነዚህ ሁለት ጽንፍ የረገጡ የጠላትነት ስሜቶች ለአገር አደጋ ናቸው፡፡ በሰላም መፈታት ያልቻለው የውስጥ ሽኩቻና የመጠፋፋት አባዜ ከጎረቤትና ከሩቅ ባላጋራዎች ጋር ሲሸረብ አደጋ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ኃይሎች የአንደራረስም ሻካራ ግንኙነት ሊያደርስ የሚችለው ጉዳት በዋዛ መታየት የለበትም፡፡ ለምሳሌ ሻዕቢያ ጥቃት ሊፈጽም የሚችለው በዋናነት ከጎረቤት አገሮች ጋር በማጋጨት ሥልት ሳይሆን፣ የአገር ውስጥ የተቃውሞ ትግል አጋዥ በመምሰል ነው፡፡ አልሸባብን የመሰሉ ጽንፈኞች ኢትዮጵያን ለማጥቃት ዘዴ የሚያውጠነጥኑት የውስጥ ትግሉን መራራ ጎን በመጠቀም ሊሆን ይችላል ብሎ ማሰብ ክፋት የለውም፡፡

የኢትዮጵያ መጠናከርና በአካባቢው እየገነነች መውጣት የሚያስፈራቸውና ከዚህ ቀደምም የኤርትራን መገንጠል ትግል በማዳከሚያነት ሲጠቀሙበት የኖሩት ዋነኛ ተዋናይ አገሮች፣ በዚህ በተወሳሰበው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ኃይሎች ትግል ውስጥ በስውር ለመሳተፍ ያሰፈስፋሉ፡፡ በተግባር ከመፈጸምም አይመለሱም፡፡ ሌላው ቀርቶ የውስጥ ትግሉ በቅራኔ ተሞልቶ ሰላማዊ ሒደት እንዳይኖር እሳቱን ይቆሰቁሳሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ ገንዘባቸውን ይረጫሉ፡፡

የኢትዮጵያ መልማትና ማደግ ለህልውናዬ አደጋ ነው ብሎ የሚያስብ ማንኛውም የጎረቤት አገር የኢትዮጵያ ፖለቲካ የውስጥ ትግል እንዳይበርድ የበኩሉን ሚና አይጫወትም ብሎ አለመጠርጠር የዋህነት ነው፡፡ ለዚህም ነው ልዩነቶችን የማይታረቁ ቅራኔዎች አድርጎ ውጥረትን ማባባስ አያስፈልግም የሚባለው፡፡ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ውስጥ ማንም እየገባ እንዲፈተፍት መፈቀድ የለበትም፡፡ በብሔራዊ ደኅንነታችን ቀልድ የለምና፡፡

ይህ ደግሞ ተግባራዊ የሚሆነው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ኃይሎች በዲሞክራሲያዊ አግባብ መነጋገር ሲችሉ ብቻ ነው፡፡ የአገር ደኅንነትና ሰላም የሚያሳስበው ማንኛውም ዜጋ የአገሪቱ የፖለቲካ ኃይሎች እየተጓዙበት ያለውን አደገኛ መንገድ የማስቆም ኃላፊነት አለበት፡፡ ለአገር ብሔራዊ ደኅንነትና ክብር ሲባል የፖለቲካ ኃይሎች ከገቡበት የቅራኔና የጠላትነት ማጥ ውስጥ ሊወጡ ይገባል!

Leave a Reply