February 19, 2017 

ከመስከረም 28 ቀን 2009 .ም ጀምሮ በሰማያዊ ፓርቲ ተካሄደ የተባለውን “ጠቅላላ ጉባዔ” አስመልክቶ ምርጫ ቦርድ በመጫወቻ ካርድነት ሲያሽከረክረው ከቆየ በኋላ የጉባኤውን ህጋዊነት በማፅደቅ እነ አቶ የሺዋስን የፓርቲው ህጋዊ መሪዎች ማድረጉን ሰምተናል፡፡

ፓርቲዎች እግር ሲያወጡ እቆርጣቸዋለሁ የሚለውን የገዥውን ፓርቲ እምነት ለማስፈፀም ምርጫ ምርጫ ቦርድ የገዥው ፓርቲ ዋና ቁልፍ ነው፡፡ ይህ እውነት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ተደጋግሞ የተከሰተ በመሆኑ በፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ በገዥው ፓርቲ ሰርጎ ገቦችና በስልጣን ጥም በታወሩ ሰዎች አማካኝነት በፖለቲካ ፓርቲዎች ችግሮችና መከፋፈል በሚፈጠሩበት ወቅት የፓርቲዎችን ሕጋዊ ባለቤትነት ለቅጥረኞችና ለአፍራሾች በመስጠት ምርጫ ቦርድ እስካሁን በቅንጅት፣ በኦብኮ፣ በአንድነት እና በመኢአድ ፓርቲዎች ላይ የፈፀመውን ዛሬ በሰማያዊ ላይ ቢፈፅመው የማይገርም መሆኑንና ይልቁንም ሊደንቅ የሚችለው የምርጫ ቦርድ ውሳኔ ከተለመደ ተግባሩ በተቃራኒ ቢሆን ነበር፡፡

የሰማያዊ ፓርቲን ለማፍረስና ለማዳከም የተሰገሰጉ ግለሰቦችን ፓርቲ የማፍረስ ተግባራቸው እውን ለማድረግ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ ለማገዝ የቦርዱ ፅ/ቤት ጉባዔው ከመደረጉ በፊትና ጉባኤውም ተካሄደ ከተባለ በኋላም ከሕገወጥ ድርጊታቸው ጋር ተባባሪ በመሆን፡

1. በፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ አንቀፅ 26 ቁጥር 6 መሰረት በሥራ አስፈጻሚም ሆነ በብሔራዊ ምክር ቤቱ ውሳኔ መሰረት ወጭ በሚደረጉ ደብዳቤዎችና ሰነዶች ላይ መፈረም ለፓርቲው ሊቀመንበር ብቻ የተሰጠ ስልጣን ሆኖ እያለ ፓርቲ ለማፍረስ ከፈለጉ ግለሰቦች ጋር በፓርቲው ስም ደብዳቤ በመፃፃፍ የህገወጥ ድርጊታቸው ተባባሪ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ህገወጦችም ከህግ ውጭ ስብሰባ እንዲያደርጉ በሚያስፈልጋቸው ነገር ሁሉ እገዛ አድርጓል፡፡ ምርጫ ቦርድን በመወከል በህገወጡ ስብሰባ ላይ በታዛቢነት የተገኙት ግለሰብ በፓርቲያችን መተዳደሪያ ደንብ አንቀፅ 25 ቁጥር አንድ መሰረት ምልዓተ ጉባኤ መሟላቱ ይነገር፣ ይመዝገብ፣ የምርጫ ቦርድ ተወካይም ስብሰባው ለመካሔድ ህጋዊነትን ማሟላት ወይም አለማሟላቱን ያረጋግጡ እየተባለ በተደጋጋሚ ቢነገራቸውም በገሃድ የታየውን ህገወጥነት በትብብር አልፈውታል፡፡

2. በፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ አንቀፅ 26 ቁጥር 1 መሰረት ፓርቲውን በህጋዊነት የሚወክለው የፓርቲው ሊቀመንበር መሆኑና በፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ አንቀፅ 26 ቁጥር 6 መሰረት በፓርቲው ውሳኔ ወጭ የሚደረጉ ደብዳቤዎች ላይ መፈረም የሚችለው ሊቀመንበሩ መሆኑ ተደንግጎ እያለ እነዚህን የፓርቲውን አንቀፆች በመጻረር የማይመለከታቸው ግለሰቦች ከቦርዱ ጋር በመፃፃፍ ጉባኤ ለመጥራት ያደረጉት እንቅስቃሴ ህገ ወጥ ተግባር መሆኑን ቦርዱ እያወቀ የድርጊታቸው ተባባሪ ሆኖ ቆይቷል፡፡

3. የጉባዔው አጠራር ፓርቲውን በህግ ከሚወክለው የፓርቲው ሊቀመንበር እውቅና ውጭ ለማካሔድ የተሞከረ ስለነበር አባዛኛዎቹ የጠቅላላ ጉባዔ አባላት ባለመገኘታቸው ከ226 የጠቅላላ ጉባኤ አባላት መካከል በዕለቱ የተገኙት 75 አባላት ብቻ መሆናቸውን ቦርዱ በታዛቢነት በላካቸው ግለሰብ አማካኝነት ያረጋገጠው ሃቅ ቢሆንም መበተን የሚገባው ህገወጥ ስብሰባ እንዲካሄድ በምርጫ ቦርድ ተወካይ በኩል ትብብር አድርጓል፡፡

4. በፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ አንቀፅ 26 ቁጥር 5 መሰረት የገንዘብ ወጭዎችን የሚያዘው የፓርቲው ሊቀመንበር መሆኑ ተደንግገ እያለ የፓርቲው ሊቀመንበር ምንጩን በማያውቀውና በፊርማው ባላፀደቀው ገንዘብ ጉባኤ ለማድረግ መሞከሩ የፓርቲውን መተዳደሪያ ደንብና የፖለቲካ ፓርቲዎችን የምዝገባ አዋጅ የሚፃረር ህገ ወጥ ተግባር በመሆኑ ለምርጫ ቦርድ እንዲያውቀው ቢደረግም በዝምታ አልፎታል፡፡


5
. ጉባኤ አድርገናል የሚሉ ግለሰቦች የፓርቲውን ማህተም ከቢሮ ሰርቆ ከጠፋ ግለሰብ ጋር በመተባበር አድራሻቸው ሳይታወቅ መሰረቁ ለበፖሊስ ሪፖርት ተደርጎ ክስ እንዲመሰረት በምርመራ ላይ ያለን ማህተም በመጠቀም ከፓርቲው ፅ/ቤት ውጭ አየር በአየር ከቦርዱም ጋር ሆነ ከሌሎች አካላት ጋር በመፃፃፍ የፓርቲውን ህጋዊ ማንነት በማንአለብኝነት በመጣስ የአፍራሽነትና የከፋፋይነት ሚና በመጫወት ላይ መሆናቸው እንዲያስቆምልን ቢጠየቅም ራሱ ተባባሪያቸው ሆኖ ቀጥሏል፡፡

6. አንድ ጉባኤ የተካሔደበት መንገድ በሕግና በአግባቡ መሆኑን መርምሮ ምርጫ ቦርድ ከማፅደቁ በፊት ጉባዔ ተደርጓል ስለተባለ ብቻ የራስን ሹመት በራስ በማፅደቅ “የፓርቲው መሪዎች እኛ ነን” በማለት በየመገናኛ ብዙሃኑ መግለጫ መስጠት የምርጫ ቦርድን ኃላፊነት የሚጋፋና ህጋዊነታቸው በሕግ እስከሚሻር ስልጣን ያላቸውን የፓርቲውን አመራሮች ስልጣን በመንጠቅ በሚፈፀሙ ህገወጥ ተግባራት ህዝብንና አባላትን ማሳሳት ኃላፊነት የጎደለው የብልግና ተግባር በመሆኑ እንዲየስቆም ቢጠየቅም በተቃራኒው ከቦርዱ ወሳኔ በፊት የቦርዱ ጽ/ቤት ኃላፊ ሳይቀር የእቅውና ትተብብር ሲያደርጉ ታይተዋል፡፡

ይህንን ዓይነት ጨዋታ ሲቆምር የቆዬ ተቋም ያሳለፈው ውሳኔ የሚጠበቅ በመሆኑ ባይገርምም ሰማያዊ ፓርቲ በህዝብ ልብ እንዲገባና ለኢትዮጵያ ሕዝብም የተስፋ ጭላንጭል ሆኖ እንዲታይ ብዙ ዋጋ የከፈሉ ወጣቶችን አሳዝኗል፡፡ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ቃል ኪዳንን በማፍረስና ጓዳዊነትን በመክዳት ብዙ ሸፍጦች ተሰርተዋል፡፡ ይህ እንደማህበረሰብ እየተራባ የመጣውን የባንዳነት አስተሳሰብ ከስሩ ካልተነቀለ በስተቀር እየደጋገምን መክሸፍና መዉደቃችን ይቀጥላል፡፡

ይህንን አዙሪት ለመስበር የሰማያዊ ፓርቲ አባላት የምናደርገው ትግል ይቀጥላል፡፡ የፓርቲው መሪነት ለትንሽ መሸጦዎች ተሰጠ ማለት ሰማያዊ አበቃለት ማለት አይደለም፡፡ እንዲያውም በኢትዮጵያ ፓርቲዎችን ለከሃዲዎች እያስረከቡ መቆዘም ማብቃት ስላለበት አባላት በምናደርገው ትግል ፓርቲውን ወደህጋዊነቱ እንደምንመልሰው በእርግጠኝነት እንናገራለን፡፡

ዛጎል