ዘር ኢትዮጵያ በተያዘው ዓመት መጀመርያ ላይ በይፋ የተመሠረተ ቢሆንም ላለፉት አራት ዓመታት በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የገቡ ሴት ተማሪዎችን የገንዘብ አቅም ችግር ለመፍታት ሲሠራ ቆይቷል፡፡

በአሁኑ ሰዓት ደግሞ በከፍተኛ የሥልጣን እርከን ላይ የሚገኙትን ጨምሮ 13 ሴት በጎ ፈቃድ አምባሳደሮችን መርጦ በትብብር እየሠራ ይገኛል፡፡ አቶ ያሬድ ግርማ የዘር ኢትዮጵያ መሥራች ናቸው፡፡ ምሕረት ሞገስ አነጋግራቸዋለች፡፡

ሪፖርተር፡- የዩኒቨርሲቲ ሴት ተማሪዎችን የገንዘብ ችግር ለመፍታት ‹‹ዘር ኢትዮጵያን›› መሥርተዋል፡፡ መነሻዎት ምን ነበር?

አቶ ያሬድ፡- የተነሳሁበት ዋና ዓላማ ከከፍተኛ ትምህርት መስፋፋት ጋር ተያይዞ ሴት ተማሪዎች ያገኙትን የመማር ዕድል የሚያደናቅፉ ብዙ ችግሮች መኖራቸውን በመረዳቴ ነው፡፡ ከትምህርት ከሚያደናቅፏቸው ችግሮች መካከል ሦስቱን ለይተናል፡፡ ተማሪዎች ብዙውን ጊዜ ከቤተሰቦቻቸው ጋር ከማሳለፋቸው ጋር ተያይዞ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ የሚጠብቋቸውን ተግዳሮቶችና ያሉትን ዕድሎች ካለመረዳት የተነሳ ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ሴት ተማሪዎች ይዘውት የሄዱትን ሕልምና ራዕይ ጥለው በማይሆን ሕይወት ውስጥ የመጠመድ ዕድላቸው እየሰፋ በመምጣቱ ምክንያት ነው፡፡ በከፍተኛ ትምህርት የመማር ዕድል አለ፡፡ በዛው ልክ ሥነ ምግባር በሌላቸው አንዳንድ መምህራንና ተማሪዎች ትንኮሳ ያጋጥማቸዋል፡፡ ሴት ተማሪችን ከወንድ ጋር ለማገናኘት ድለላን ሥራዬ ብለው የያዙም አሉ፡፡ መንግሥትና ቤተሰቦቻቸው በተማሪዎች ላይ ብዙ ኢንቨስት ማድረጋቸውን ተገንዝበው በማይሆን ቦታ እንዳይወድቁ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ አለ፡፡ ዘር ኢትዮጵያ በይፋ ከመመሥረቱ በፊት ማለትም ካለፉት አራት ዓመታት ጀምሮ ግንዛቤ በማስጨበጡ ላይ እየሠራን ቆይተናል፡፡ በእነዚህ ጊዜያት 20,000 የሚደርሱ ሴት ተማሪዎች ያገኙትን የመማር ዕድል እንዲጠቀሙበትና የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች በጽናት እንዲወጡ የግንዛቤ ማስጨበጫ እየተሰጣቸው ወደ ዩኒቨርሲቲ ተሸኝተዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የግንዛቤ ማስጨበጫው የተሰጠው በአዲስ አበባ ብቻ ነው ወይስ ሌሎችንም  ክልሎች ይጨምራል?

አቶ ያሬድ፡- እስካሁን በአዲስ አበባ፣ በድሬዳዋና በሐረር ነው የተደረጉት፡፡ ከዚህ ዓመት ጀምሮ በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በትግራይና በደቡብ ክልሎች በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ለሚመደቡ ሴት ተማሪዎች የግንዛ ማስጨበጫ ይሰጣል፡፡

ሪፖርተር፡- ሌላው ያያችሁት ችግር ምን ነበር?

አቶ ያሬድ፡- የፋይናንስ ችግር አለባቸው፡፡ ከሀብታም ቤተሰብ የሚመጡ ቢኖሩም ባብዛኛው ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚሄዱት የአርሶ አደርና የደሀ ልጆች ናቸው፡፡ ተማሪዎቹ ዩኒቨርሲቲ በመግባታቸው ድህነትን ለማሸነፍ የሚያስችለውን አቅም እየፈጠሩ ቢሆንም በቤተሰቦቻቸው ምክንያት የሚከፍሉት ዋጋ አለ፡፡ ቤተሰቦቻቸው ሊያግዟቸው አይችሉም፡፡ ረዥሙን መንገድ መጥተው ወደ ዩኒቨርሲቲ ሲገቡ የገንዘብ ችግር እንዳያጨናግፋቸው፣ ወንዶቹ ላይ ችግሩ ቢኖርም ሴቶቹ ላይ የከፋ ስለሚሆን፣ የሴቶችን የገንዘብ ችግር ለመቅረፍ ካለፉት ሁለት ዓመታት ጀምሮ 500  ችግረኛ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን መርጠን በየወሩ ሁለት መቶ፣ ሁለት መቶ ብር እየሰጠን ቆይተናል፡፡ አሁን ላይ ንግድ ባንክ የ500 ተማሪዎችን ወጪ ይሸፍንልናል፡፡ በአጠቃላይ 1,000 ሴት ተማሪዎችን በየወሩ እየረዳን ነው፡፡ 500ውን ደርባ ሲሚንቶ ነው የሚደግፋቸው፡፡ ጥቃቅን ፍላጎቶቻቸው ከዋናው ዓላማቸው እንዳያደናቅፋቸውና ቢያንስ መሠረታዊ ፍላጎቶቻቸውን እንዲሸፍኑ ነው ገንዘቡ የሚሰጣቸው፡፡ ገንዘቡም ቀጥታ ከባንኩና ከደርባ ሲሚንቶ በባንክ አካውንታቸው በየወሩ ይገባል፡፡ ሌላው ያየነው ችግር በትምህርት ተቋማት ሴቶችን ከመጠበቅ አንፃር ችግር መኖሩን ነው፡፡ ትንኮሳና በውጤት የማባበሉ ነገር አለ፡፡ መንግሥት ችግሩን ተረድቶ እየሄደበትም ነው፡፡ እንደ ድርጅት ይህንን ለመሥራት ቢከብደንም ግንዛቤውን እየፈጠርን ነው፡፡ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማተ የሥነ ምግባር ደንብ ላይ ተማሪዎች እስከምን መሄድ እንደሚችሉ ስለተቀመጠ፣ ይህንን ተረድተው ከተማሪዎችና ከመምህራን ጋር ያላቸው ግንኙነት በሥርዓት የሚመራ እንዲሆን ግንዛቤ እንሰጣለን፡፡ ሕግን የማስከበሩና ሥርዓት የመፍጠሩ የመንግሥት ሥራ ሲሆን፣ እኛ ደግሞ ግንዛቤ  እናስጨብጣለን፡፡

ሪፖርተር፡- በሴቶች ላይ በምትሠሩት ሥራ የወንዶችን ተሳታፊነት እንዴት ታዩታላችሁ ?

አቶ ያሬድ፡- የሴት ልጅ ብቃት ከፍተኛ ነው፡፡ የትውልድ መገኛ ከመሆን አንስቶ የሁላችን አካል ነች፡፡ በመሆኑም ለሴቶቹ መድረክ ስናዘጋጅ ግማሹን ቀን ለወንዶች ነው የምናውለው፡፡ የሴትና የወንድ ግንኙነትን አዳብረን መሄድ ነው ዓላማችን፡፡ የወንዶቹ ግንኙነት የሴቷን ሕልም በማያደናቅፍ መሆን አለበት፡፡ ወንድ ተማሪዎች በሴቶች ላይ ያላቸው አመለካከት ላይ ክፍተት ተመልክተናል፡፡ ይህ የማኅበረሰቡም ችግር ነው፡፡ በመሆኑም ሴት ልጅ ወደ አመራር እንድትመጣ ወንዶች መደገፍ አለባቸው፡፡ ሴቷ ውስጧ ያለውን አቅም እንድታወጣ ዕድል ልንፈጥርላት ይገባል የሚል አጠቃላይ ግንዛቤ ነው የምንሰጠው፡፡ ኃላፊነት እንድትቀበል፣ አገሯንና ሕዝቧን እንድትወድ፣ መልካም ሚስትና እናት እንድትሆን ዕድል ማመቻቸት አለብን፡፡ እንቅፋት የሆኑባቸውን ችግሮች በቻልነው ያህል ለመፍታት ነው የምንሠራው፡፡

ሪፖርተር፡- ሴት ተማሪዎች በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚገጥማቸው ፈተና ከተለያየ አቅጣጫ ነው፡፡ ከውጭ ደላሎች ከወንድ ጋር ለማገናኘት ይወተውቷቸዋል፣ ከውስጥ ትንኮሳ ያጋጥማቸዋል፡፡ በራሷ ደግሞ የፋይናንስ ችግር አለባት፡፡ ችግሮቹን በተቀናጀ መልኩ ለመፍታት የምታደርጉት ጥረት ምን ይመስላል?

አቶ ያሬድ፡– አንዳንድ ሴቶች ሁለት መቶ ሺሕ ቢፈስላቸው የማይመለሱ አሉ፡፡ ለእነዚህ መልካሙን ተመኝቶ እየተንገጫገጩና ዓላማ ኖሯቸው፣ ነገር ግን የወር አበባ መጠበቂያ ፓድ ለመግዛት እንኳን የተቸገሩ ተማሪዎች አሉ፡፡ የምንሮጠውም እነዚህን ተማሪዎች ለመደገፍ ነው፡፡ ዓላማ ካለ እኛ ሁለት መቶ ብር ባንሰጥም ጥርሷን ነክሳ ትምህርቷን እንደምትጨርስ እናምናለን፡፡ ሆኖም ችግሩ ብሶባት ያልሆነ ቦታ እንዳትወድቅ ለመደገፍ ነው የኛ ጥረት፡፡ ወደፊት ድጋፋችን በ200 ብር ብቻ የሚወሰን ሳይሆን፣ የወር አበባ መጠበቂያ ፓድ ማደልና በሁሉም የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ነፃ የፎቶ ኮፒ ማሽን ማቆምን ይጨምራል፡፡ የድጋፉ ዋና ዓላማ፣ ራዕይ ይዘው ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ያሉ ተማሪዎች የተሻለ አቅም ኖሯቸው ትምህርታቸውን እንዲጨርሱ ማድረግ ነው፡፡  ትምህርታቸውን ጥለው ማኅበረሰቡ ፀያፍ ብሎ በሚጠራው ሥፍራ ለሚገኙት የምመክረው በተቻለ መጠን የምክር አገልግሎት አግኝተው ለራሳቸው፣ ለቤተሰቦቻቸውና ለአገራቸው ጠቃሚ  እንዲሆኑ ነው፡፡ ፍራንክ ይዞ መጥቶ ሴትን እንደሸቀጥ ለሚገዛ ሰው መሄድም ፀያፍ ነው፡፡ በአገሪቱ የትምህርት ሥርዓት ለከፍተኛ ትምህርት ይበቃሉ ተብለው ዩኒቨርሲቲ የገቡ ሴቶች በፀያፍ ሥፍራ ሲታዩ ለመሰደብ ምክንያት ይሆናሉ፡፡ ይህ መቀየር አለበት፡፡ ደላሎቹ ደላልነት መደበኛ ሥራቸው ነው፡፡ ሆኖም የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ማዳለል ሥራ አይደለም፡፡ በትውልድ ላይ የተከፈተ ጥፋት ነው፡፡ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የበለጠ ጥበቃ ሊደረግላቸው ይችላል ብዬ አምናለሁ፡፡ መንግሥትና የትምህርት ተቋማት በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አካባቢ ያሉ ሽሻ ቤቶችና ጫት ቤቶች እንዲነሱ ያደርጋል ብዬ አስባለሁ፡፡ መንግሥት ለተቋማቱ በቢሊዮን የሚቆጠር ኢንቨስት እያረገ ያለው ሰው ለማገኘት ነው፡፡ በተቋማቱ አካባቢ ትምህርት ሊያደናቅፉ የሚችሉ ንግድ ቤቶች የተማሪዎችን ራዕይና ዓላማ የሚያቀጭጩ ከሆነ በትምህርቱ ላይ ያለው ኢንቨስትመንት ዜሮ ይገባል፡፡ ስለዚህ ጥበቃ ቢደረግባቸው ጥሩ ነው፡፡ በአገር ልማትና ዕድገት ውስጥ የራሳቸውን አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ ሥነ ምግባር ያላቸው ልጆች እንዲወጡ ማድረግ አለብን፡፡

ሪፖርተር፡- ዘር ኢትዮጵያ ቪዥን 2020 የሚል ራዕይ አለው፡፡ ቢያብራሩልን?

አቶ ያሬድ፡- ዘር ኢትዮጵያ ቪዥን 2020 የሚል ራዕይ አለው፡፡ የ14 ዓመት ስትራቴጂክ ፕላን ሠርተናል፡፡ በቀጣዩ 14 ዓመታት በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ ያሉ እስከ 5 መቶ ሺሕ የሚደርሱ ሴት ተማሪዎችን በግንዛቤ መፍጠሪያ መድረኮች ለማሳተፍ፣ የገንዘብ ድጋፍ እንዲሁም የወር አበባ መጠባበቂያ ፓድ እንዲያገኙ ለማድረግ አቅደናል፡፡ 31 የፎቶ ኮፒ ማሽን በየዩኒቨርሲቲዎች ለማስቀመጥ ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር እየሠራን ነው፡፡ የሕዝብ ውለታ እንዲከፍሉ ዕድሉን እንፈጥራለን፡፡ ተማሪዎቹን ለመርዳት እንድንችልም በቅርቡ የወር አበባ ንፅህና መጠበቂያን ፋብሪካ ለመገንባት አቅደናል፡፡ ጥናቱ አልቋል፡፡ ይህ ዕውን ሲሆን፣ ለ30,000 ሴቶች በየወሩ ፓድ በነፃ ይሰጣል፡፡ የሚተርፈው ምርት ተሽጦ ከሚገኘው ገቢ በአራት ክልሎች በትግራይ፣ በአማራ፣ በኦሮሚያና በደቡብና በአዲስ አበባ አምስት ሴቶች ብቻ የሚማሩበት አዳሪ ትምህርት ቤት እንገነባለን፡፡ ከታች ጀምሮ ትምህርት የሚሰጥበት ይሆናል፡፡ ቪዥን ፎር ጀነሬሽን በሚለው ድርጅታችንም ጎንደር ላይ ትምህርት ቤት እየገነባን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር ያላችሁ ግንኙነት ምን ይመስላል?

አቶ ያሬድ፡- ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በተናጠል ግንኙነት ጀምረን ነበር፡፡ ነገር ግን ማዕከልነት ስላልነበረው በምትህርት ሚኒስቴር በኩል አብረን እየሠራን ነው፡፡ ከትምህርት ሚኒስቴር የሥርዓተ ፆታ ዳይሬክቶሬት ጋር ተፈራርመን ወደ ዩኒቨርሲቲ ዘልቀን ገብተናል፡፡ በየዩኒቨርሲቲው ከሥርዓተ ፆታ ቢሮዎች ጋር አብረን እየሠራን ነው፡፡ እነሱ የመንግሥት እኛ የደጋፊነት ሚና ይዘን እየሠራን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- 5 መቶ ሺሕ ሴቶችን ለማብቃት ስታቅዱ ለወንዶችስ ምን አስባችኋል?

አቶ ያሬድ፡– በዘር ኢትዮጵያ በኩል ሴቶች ላይ ነው የምንሠራው፡፡ ሆኖም ለሴቷ ጥቅም እንሥራ ስንል የወንዱ ደጋፊነት ጥያቄ የለውም፡፡ ወንዱ የሴቶችን ሩጫና ሕልም ካልደገፈ የኛ ሩጫ ዋጋ የለውም፡፡ ወንዶች ኃላፊነቱ እንዳለባቸው የማስገንዘቡ ሥራ ይሠራል፡፡ የጀመርናቸው ሥራዎችም አሉ፡፡ ወንዶች ለሴቶች መብቃት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ በተለያዩ መንገዶች ግንዛቤ እንፈጥራለን፡፡

ሪፖርተር፡- 2007 ዓ.ም. እንደገባ 13 ሴት የበጎ ፈቃድ አምባሳደሮችን ዘር ኢትዮጵያ መርጧል፡፡ አምባሳደሮቹ ምን እየሠሩ ነው? ተሳትፏቸው ምን ይመስላል?

አቶ ያሬድ፡– እንደ ተቋም ዕድለኞች ነን፡፡ የዘር ኢትዮጵያ የበጎ ፈቃድ አምባሳደሮች አገሪቱን በተለያዩ መልኩ በሚመሩ ከፍተኛ ቦታ ላይ ያሉ ናቸው፡፡ በከፍተኛ የጦር አመራር፣ በልማት ተቋማት ያሉ ሴቶች ናቸው፡፡ የሴቷ ጉዳይ የነሱ ጉዳይ ነው፡፡ እነሱ ከበርካታ ሴቶች ዕድለኛ ሆነው ለከፍተኛ ደረጃ በቅተዋል፡፡ በርካታ ሴቶች ይህንን ዕድል አላገኙም፡፡ በርካታ ሴቶች ወደ ከፍተኛ ደረጃ እንዲደርሱ የማብቃት ኃላፊነት ስላለባቸው የምንሠራው ሥራ አካል እንዲሆኑ በጠየቅነው መሠረት በኃላፊነት የበጎ ፈቃድ አምባሳደር ሆነው ራዕያችንን እንደሚደግፉ ገልጸውልናል፡፡ ከኛ ጋር ካላቸው ግንኙነት አንዱ ሥራዎቻችንን ግልጽ እንዲሆኑ ማድረግ ነው፡፡ በርካታ ሰዎች ሥራውን በግልጽ እንዲያዩትና አሻራ ጥለው እንዲያልፉ በጎ ፈቃድ አምባሳደሮቹ አጋር ሆነውናል፡፡ በሌላ በኩል አቅጣጫ ይሰጡናል፣ የምንሠራውን ሥራም ያያሉ፡፡ በጎ አድራጎት ድርጅት ሲባል ማወናበጃ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ በዚህ ምክንያት ብዙ መሥራት የሚችሉ ድርጅቶች መንገድ ቀርተዋል፡፡ በተቻለ መጠን የገንዘብ እንቅስቃሴያችን ግልጽ ይሆናል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ 13ቱ በጎ ፈቃደኛ ሴት አምባሳደሮች ምስክር ይሆኑናል፡፡ አምባሳደሮቹ በሕዝብና በመንግሥት ዘንድ ተቀባይነት አላቸው፡፡ በመሆኑም ራዕያችንን በቀላሉ ለማስረጽ እንችላለን፡፡ በኛና በሕዝብ መካከል ያለውን ግንኙነት ጤናማ ለማድረግ ትልቅ ሚና አላቸው እየረዱንም ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የገንዘብ ድጋፍ ከየት ታገኛላችሁ?

አቶ ያሬድ፡- እስካሁን ላለፉት አሥር ዓመታት የበጎ ፈቃድ የልማት ሥራ ስንሠራ ቆይተናል፡፡ አንድም ጊዜ የውጭ ዕርዳታ አልጠየቅንም፣ አላገኘንም፡፡ የሠራነው ሕዝብ አሳምነን፣ ከሕዝብ ኪስ በምናገኘው ገንዘብ ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲ ላሉ ተማሪዎችም የምንረዳው ኢትዮጵያውያንን አስተባብረን ነው፡፡ የውጭ ዜጋ የሚሰጠውን ዕርዳታ ለተማሪ ኪስ ማዋል፣ ኢትዮጵያዊ ወገናቸው የሰጣቸውን ገንዝብ ማዋል ይለያያል፡፡ ኢትዮጵያውያን ረድተውኛል፣ እኛም መርዳት አለብን የሚል ስሜትና ኃላፊነት ተማሪዎቹ የሚኖራቸው እርስ በርሳችን ስንረዳዳ ነው፡፡ ሌሎች ተቋማት ትውልድ ላይ ሲሠሩ በተቻለ መጠን ከአገር ውስጥ በሚገኝ ገንዘብ ቢሠሩ እንደ እኔ እመርጣለሁ፡፡ በኛ በኩል የፓድ ፋብሪካውን እንኳን በራሳችን አቅም ለመሥራት ነው ያቀድነው፡፡ ራሳችንን በራሳችን አንችላለን፣ እንደግፋለን ብዬ አስባለሁ፡፡ ከውጭ ገንዘብ መውሰድ፣ መጥፎ ነው እያልኩ ሳይሆን በራሳችን ማድረግ የምንችለውን እናድርግ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ለተማሪቹ 200 ብር በየወሩ ከመስጠት በተጨማሪ ትከታተላችኋላችሁ?

አቶ ያሬድ፡– ጂ 12 የሚባል ቡድን አለን፡፡ በየተቋማቱ የሥርዓተ ፆታ ቢሮዎች አሉ፡፡ በኛ የሚረዱ ተማሪዎች ውጤት በየጊዜው ይታያል፡፡ የምንደግፈው የተሻለ ውጤት ያላቸውን ብቻ ነው፡፡ በሌላ በኩል 200 ብር ትርጉም ያመጣል ወይ? ራዕያቸውን ሊያመክን ከሚችል ተግባር ተቆጥበው ይገኛሉ ወይ? ትምህርታቸውን እየተማሩ ነው ወይ? የሚለውን እንከታተላለን፡፡ ከመስመር የወጡ ልጆች ድጋፋቸው ተቋርጧል፡፡ ከግቢ ወጥተው ባልተገባ ተግባር የተገኙ፣ ውጤታቸው ዝቅተኛ የሆኑ ከዕርዳታው አስወጥተናል፡፡ እኛም ለምነን፣ እነሱም ውጤት ካላመጡ አይሆንም፡፡ ልመና ብዙ ዋጋ ያስከፍለናል፡፡ ተማሪዎቹም ራሳቸውን ለማውጣት ጠንክረው መሥራት አለባቸው፡፡ የኛ ተስፋ ተማሪቹ ናቸው፡፡ መክነው መቅረት የለባቸውም፡፡ የምናደርገውን ድጋፍ ከንቱ የሚያደርጉ ከኛ ጋር አይቀጥሉም፡፡ የእንስት ንስሮቹ መድረክ የሚባል አለን፡፡ ታዋቂ ሴቶች ለዩኒቨርሲቲ ሴት ተማሪዎች ልምዳቸውን የሚያካፍሉበት ነው፡፡ ለአዲስ አበባ በአዲስ አበባ፣ በድሬዳዋ ድሬዳዋና ለሐረር በሐረር ልምድ ያካፍላሉ፡፡ በዚህ መድረክ የማይዳሰስ ጉዳይ የለም፡፡ ተማሪዎች ቅድሚያ የሚሰጡን እንዲለዩ፣ እንዲማሩ ካልተማሩ የሚገጥማቸውን፣ አለመማር ዋጋ እንደሚያስከፍላቸው ግንዛቤ ይሰጣል፡፡ ከመድረኩ ባገኙት ግንዛቤ ተለውጠናል ያሉን አሉ፡፡

Leave a Reply