February 20, 2017

በሰማያዊ ጽ/ቤት፣ በአገር ቤት በየሳምንቱ የዉይይት መድረኮች ይደረጋሉ። በተለያዩ አጀንዳዎች ዙሪያ። ይሄ በጽ/ቤቱ የሚደረጉ ዉይይቶች ፓርቲው አባላቱ ከሞላ ጎደል የበሰለ የፖለቲካ ንቃተ ሕሊና እንዲኖራቸው ለማድረግ ታሳቢ ያደረገ ነው።

በዚህ ሳምንት የውይይት ፕሮግራም ላይ አቶ አሰፋ ሀብተ ወልድ የመኢአድ ተቀዳሚ ፕሬዝደንት፣ “መሪነትና እና የተመሪነት ሚና” በሚል ርእስ ጠቃሚ ሐሳቦችን ያቀርባሉ። የሰማያዊ ፓርቲ ይህ አይነቱ የፖለቲክ ዉይይቶችን ከማድረግ ባለፈ፣ የአገር ቤቱን ትግል በማጠናከሩና ጠንካር መሰረት በመጣሉ ዙሪያ፣ በርካታ ስራዎችን እየሰራ ነው። ከነዚህ መካከል የተወሰኑትን በጥቂቲ ለመጥቀስ፡

1) ከዚህ በፊት በሰማያዊ ፓርቲ ውስጥ በአንዳንድ መሪዎች አምባገነንነት ምክንያት የተፈጠሩ ችግሮች እንዳይከሰቱ፣ ግለሰቦችን ሳይሆን ተቋማትን በማጠናከር ዙሪያ ሥራ እየተሰራ ነው። ግለሰቦች ባኮረፉ ቁጥር፣ ድርጅቱም፣ የሚታመስበት ምክንያት መኖር የለበትምና።

2) ከሌሎች ድርጅቶች ጋር በዋናነት ከመኢአድ ጋር በጣም የጠነከረ ግንኙነቶችን እየመሰረቱ ነው። የቀድሞ የሰማያዊ አመራር የአንድነት የለዉጥ ሃይሎችን በማሰባሰብ ዙሪያ የነበረው አቋም አፍራሽ አቋም ነበር። ከሌሎች ድርጅቶች ጋር አብሮ መስራት ሳይሆን ከሌሎች ድርጅቶች ጋር መፎከከር ነበር የተያዘው። አዲሱ የሰማያዊ አመራር፣ የተናጥል ትግል የትም እንደማይደርስ የተረዳ፣ በተለይም የአንድነት የለዉጥ ሃይል መሰባሰብ እንዳለበት አጠንክሮ የሚያምን ነው። በዚህ መሰረት ፓርቲው ከመኢአዶች ጋር ያለዉን ትስስር ከማጠናከር ባሻገር ትግሉን በማሰባሰብ ዙሪያ በጣም አስደሳች ስራ እየሰራ ነው። በቅርቡ በዚህ ረገድ አስደሳች ዜናዎችን እንሰማለንት ተብሎ ይጠበቃል።

3) ሰማያዊ እና መኢአድ በጋራ በመሆን ፣ ከአዲስ አበባ ዉጭ በሌሎች የአገሪቷ ክፍሎች በመንቀሳቀስ መጠነ ሰፊ ድርጅታዊ ስራዎችን ለመስራት እቅድ አወጥተው ጨርሰዋል። ከጽ/ቤት ወደ ህዝብ መዉረዱ የግድ በመሆኑ፣ የሰማያዊ ፓርቲ እና መኢአድ ፣ በዚህ ረገድ ሕዝቡን የበለጠ ለትግል ለማነሳሳት፣ በክፍለ ሃገር ያሉ አባላትንና ደጋፊዎችን ለማበረታታት ተጨባጭ ስራዎችን ለመስራት ተዘጋጅተዋል። ትግሉ ያለው ሕዝብ ጋር ነውና ወደ ሕዝብ መዉረዳ ያልቻል ድርጅት የሞተ ነውና፣ ሰማያዊ እና መኢአድ በዚህ ረገድ ለመንቀሳቀስ መዘጋጀታቸው አስዳሳች ነው።፡

4) ሰማያዊ እና መኢአድ የሕሊና እስረኞች ሁሉ እንዲፈቱ፣ የፖለቲካ ምህዳሩ እንዲሰፋ፣ በአገራችን ያለው ፍጹም አምባገነናዊ አሰራር ተቀይሮ ቢያንስ በአንጻራዊነት የተሻለ ዴሞክራሲያዊ አሰራር እንዲፈጠር አንደኛ የአለም አቀፍ ዲፕሎማቶች ግፊት እንዲያደርጉ በማሳሰብ፣ ሁለተኛም ከሌሎች አገር አቀፍ ድርጅቶች ጋር በመሆን እየተደረገ ባለው ድርድር ላይ አዎንታዊ አስተዋጾ እያደረጉ ነው። ድርጅቶቹ በሕዝቡ የተወከሉ ባይሆንም (በሕዝብ የተወከለ ማንም አካል የለምና) እንደ ድርጅት የሕዝብን አጀንዳ ይዞ የመቅረብ ግን መብት አላቸው።

በዚህ አጋጣሚ አገር ቤት ያለውን ትግል መደገፍ የምትፈልጉ፣ በሰለጠነ ከጥላቻ የጸዳ ዘመናዊ ፖለቲካ የምታምኑ ወገኖች ካላችሁ በ millionsforethiopia@gmail.com ኢሜል አድርጉልን።

መኢአድና ሰማያዊም ጠንካራ ናቸው ብሎ መናገር አይቻልም። በውስጣቸው የነበሩ አመራሮች በፈጠሩት ችግር እና አገዛዙም መሪዎቻቸውን እና አባላቶቻቸውን በማሰር ባደረሰባቸው ጫና ምክንያት ተዳክመዋል። ሆኖም ግን ደካማ ናቸው ብሎ ለነርሱ ጀርባ መስጠት ተገቢ አይደለም። እነርሱን ካልደገፍን ታዲያ ማንን ነው የምንደገፈው ? ዉጭ አገር ያሉ ድርጅቶች ? ዉጭ ያኡ ደጅርቶች በሪሞት ኮንትሮል ነጻ ለዉጥ እንዲያመጡልን ነው የምንጠብቀው ?

ወገኖች አገር ቤት ያሉ ድርጅቶች ተጠናክረው ካልወጡ አሁን ያለው አገዛዝ እንደገና ለ20 አመታት የመግዛት እድሉ በጣም ያያለ መሆኑን መረዳት አለብን። ትልቅነት የደከመዉን ማጠናከር፣ የወደቀዉን ማንሳት፣ የተበታተነዉን ማሰባሰ፣ የተሰበረዉን መጠገን ነው። ትልቅ የትግል ጠላት ደግሞ ተስፋ መቂረጥ ነው። አዎን ወድቀናል፣ ከዚህ በፊኦት ቆስለናል። ግን ከወደቅንበት ተነስተን እንደገና ቆመ መጓዝ መጀመር አለብን።

ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ

Posted by: