Posted on February 22, 2017

ዛጎል ዜና ፡- ልቀቅ፣ ልቀቁን፣ ውጣልን፣ ውጡልን፣ ሂድልን፣ ሂዱልን፣ ጥፋ፣ ጥፉልን፣ ውደም፣ ውደሙ፣ ሙት፣ ሙቱ እለቅ፣ እለቁልን ….. ከንባታ ከጎንደር ወጣ፣ ጉራጌ ከኤርትራ ፈለሰ፣ ኦሮሞ ከኬንያ መጣ፣ ሃደሬ … የድሮው የሚጎትተን ህዝቦች፣ የወደፊታችንን በቀድሞው ጉዳይ የምናመነዥግ… በስደት የማናውቃቸውን ተጠግተን እየለመንን እየኖርን፣ የራሳችን ወገን ላይ ስደት የምናውጅ… አድሮ ማንሰለጥን… ታሪካችን የወደፊት እድላችንን አንቆ እንዲገለው የምንማማል …..
እኛ ጊዜው በትክክል በማይታወቅ የሩቅ፣ በጣም የራቀ፣ በልጆች ቋንቋ እ እ እ እ ሩ ቅ ቅ ቅ ቅ ቅ ዘመን ወደሁዋላ ሄደን እንባላለን። ዛሬ ”አሜሪካዊ” የሚባሉት ቅድመ አያቶቻቸው አውሮፓ ናቸው። ዘር ቆጥረው ሲቧጨቁ ግን አንሰማም። 200 ዓመት ባላስቆጠረ የቅርብ ታሪክ ይኖራሉ። ጸብ የለም። እኛ ከክርስቶስ ልደት በፊት ተፈጸመ ወይም በተመጣጣኝ ጊዜ “ሆነ” በተባለ ታሪክ እንባላለን። “ለወደፊታችን ምን ይጠቅመናል” ብለን ማስብ የምንጀምረው መቼ ነው። 10 ሚሊዮን በላይ ህጻናት ርሃብ እየደፋቸው፤ እኛ ገና በደምና በስጋ ጉዳይ ዘር ቆጠራ …. ማፈሪያዎች ነን። የኢትዮጵያ ችግር በዘር መባላት ይፈታል? ያበደው እንባው አይኑን አጠበው። ሳያስበው አለቀሰ። ገዢ፣ ተገዢ፣ አጎብዳጅ… ሁሉም ከሽፈዋል።
ኢህአዴግ በህግ አገሪቱን እስከመበታተን የሚያደርስ ውሳኔ ያጸደቀ እለት ሁሉም ነገር አብቅቷል። መለስ ዜናዊ ያንተ ቱርፋት ይህ ነው። ዛሬ ተከበናል። ጠላቶቻችን አፍንጫችን ስር ገብተው ጦር እያደራጁ ነው። ጅቡቲ፣ አሰብ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሶማሌ… ተከበናል። መለስ አገሪቱን ባህር አልባ አድርጎ በክብር ተቀበረ። “የገደለሽ ኮራ….” አፍረትህ ብዙ ነው። ያበደው ክጥንት ጀምሮ ለመለስ ክብር የለውም። አጠገቡ ካሉት ባለደረቦቹ ጋር መቅረጫውን እያስቆሙት ተወያይቷል። ብዙዎቹ ያሙት ነበር።
በባለቤትነት ጉዳይ የታመምን፤ አንድ ጥይት ሲተኮስ እኛ፣ እኔ፣ ተኮስኩ፤ ግብግብ፣ ሕዝብ ሲያምጽና ሲቆጣ የኮፒ ራይት ግብግብ፣ በአዝማችነት ስም ለመጠራት ከተተኮሰው ጥይት በላይ የቃላት ጦርነት፣ አንድ አስተያየት ሲሰጥ ጦርነት። ልዩነት የሚባለውን ነገር ለማሳየት ስድብ፣ ውግዘት፣ ርግማን፣ ሰው አስተያየት የመስጠት መብቱን በስድብ መለጎም፤ ጊዜው የነጻነት ነው። ሰው ወደ ግልጽነትና ነጻነት መጓዝ አለበት። በነጋ ቁጥር ነጻና ግልጽ ወደ መሆን መራመድ፣ መቅረብ ግድ ነው። ዘመኑን መሆን ያስፈለጋል ። እዚህም እዚያም አፈና አይሰራም። ዛሬ በነጻነት የማይደረግ ነገር አደሮ ዋጋ ያስከፍላል። ሃይማኖቱም ቤት እንዲሁ ነው። ኢየሱስ እየተሰበከ አደረጃጀት አለ። ያበደው ምራቁ ወፈረ። ማለት የሚፈለገውን ከማለት ሲሸበሸብ አፉ ውስጥ ምራቁ ያብጣል።
ያበደው በዝምታ ሰነበተ። ሲምታታበት በቄጤማና በሃሪቲ እንደተለከፈ ባለ ቆሌ አይንከወከውም። በዘርና በጎሳ ጥላቻ የውቃቢ መንፈስ እንደተጠመቁ እዛም እዛም አይረግጥም። የቦሰናን ምክር ተግባራዊ ያደርጋል። ቦሰና ” የማሪያም ምሩቅ ናት” ራስዋን ” አዋቂ” ከሚሉት ባትደምርም፣ ያበደው ግን ይመካባታል። “ኤጭ” ካለች ነገር አለ። ታወርደዋለች። መገልፈጥ አትወድም። ሰሞኑን እሷም ታማለች። “ምን ቢደረግ ይሻላል” እያለች ማቃሰት ላይ ነች። ” ተወረናል” ትላለች። ሁሉም ነገር ደስ አይልም ባይ ነች።
ያበደው አንድ ሙዚየም ውስጥ እየጠየቀ ጎበኘ። ከዛ ወጣ። ቁጭ አለ። አሰበ። ሰዎቹ ታሪካቸውን ባግባቡ አስቀምጠወታል። ታሪክ ያው ብርዝ ነው። ጽድት ያለ ታሪክ ብሎ ነገር የለም። እዚህ ነጮቹ ሲናገሩ በየጊዜው የሚሻሻል አዲስ ግኝት ካለ ይታከላል። በምንም ምክንያት ግን ታሪክ የወደፊታቸውን እንዲመራ፣ እንዲጫን፣ እንዲጎዳ…. አይፈቅዱም። ለታሪካቸው ክብር አላቸው። ነገር ግን ታሪካቸው በወደፊት ጉዳያቸው ላይ ጥላውን እንዲጥል ….. እኛስ? ያበደው ጠየቀ።
እኛም ገና ጥርብ ነን። በታሪክ ስንጋጭ ይኸው 21ኛው ክፍለ ዘመን ደረስን። በሃያ አንደኛው ክፍለዘመን ገና የጋራ ባንዲራ የለንም። የደቆሰንና የገደልን በሽታ መለየት ቀርቶ፤ ህመሙ የት ጋር እንደሚሰማን ለመረዳት አልታደልንም። ይቅርታ መታደል ብሎ ነገር የለም። አልቻልንም። አቅቶናል።በእድል ታሪኩን ያከበረ የለም። በእድል ድህነትን ያሸነፈ የለም። በእድል በምግብ ራሱን የቻለ የለም። በእድል ፋብሪካ የገነባ የለም። በእድል የምድር ሃብትን የዛቀ የለም። ያበደው ሳቀ። አላሙዲን ሰይፉ ከሚባለው / መቼም ራሱን ጋዜጠኛ አይልምና/ ኢትዮጵያ ችግሯ ተቀርፎ ለማየት ምኞት ሲያልሙ ሰማን። ይዘው ከሚመኙ ለምን የዛሬ 20 ዓመት እሰራዋለሁ ያሉትን አይሰሩም። ለእኛ ሲሉ ሳይሆን ለቢዝነሳቸው… እኛ አገር ለዘፋኝ ሁለት ሚሊዮን ተሰጠ ሲባል ማበድ እንወዳለን። አዝማሪ ማስጮህ አላቸው የሚባሉት ሰዎች ጥበብ ነው አሉ….
ቢጣራ ከክርስቶስ ለደትም በፊት ሊሆን በሚችል ታሪክ መቧቀስ ምን ያደርጋል? እሱንስ ለማወቅ መጎርጎሩ የት ያደረሳል? ቢታወቅስ ምን ይጠቅማል? ወደፊታችንን ከሚያጭደው በቀር ምን ሊፈይድ? የዘር ነገር መቆሚያ የለውም። በተጫጨድ ነው። ከዛ ጥቁር ታሪክ በነበረው ላይ ይታከላል። መጪው ትውልድ ይህንኑ ይወርሳል። መርገምት አውራሽ ከምሆን፣ “ቅድመ አያትህ እንዲህ አድርጎኝ ነበር ” ከማለት ሃስብ እንወጣ!! ሳናስበው የወደፊቱን እያጨደን እዚህ ደረስን። እስከመቼ ነው ወደፊታችንን እያመነዠግን የምንኖረው? ኢህአዴግም ቢሆን ይብቃህ። የሄድክበት መንገድ/ የመለስ ቅዠትና ተራ ፍልስፍና/ ይብቃ። የተዘራው የዘር መርዝ ይለቀም ዘንድ ቁርጠኛ ሁን። ሃዘኑ በሁዋል የሁሉም ነው። አዎ!! በፖለቲካ ዓለም በድንገት የሚሆን ነገር የለም። ከሱዳን ጋር በፍቅር ከማበድ ከምትመራው ህዝብ ጋር ታረቅ። ጊዜ የለም። ነገሮች መስመር ሳይለቁ ሁሉም አገሩን ያድን። ያበደው ጥሪው አንድ ነው። አገር መጀመሪያ!!
ለልጆቻችን የምናወራውና የምናወርሰው ችግር ነው። ቂም ነው። ጥላቻን ነው። አንዳንድ ህጽናት መሸከም እስከማይችሉ ድረስ በተመጣጥኝ ምግብ ፈንታ ክፋት እየጋትናቸው ነው። ያበደው እዚህ አውሮፓ ብዙ ታዝቧል። ገና ያልገባቸውና ከአሳዳሪዎቻቸው ያልተማሩ ይበዛሉ። ዛሬም ያልረጠቡ አሳዎች አሉ። በአስተሳሰብ ሳቪጀሪ ዘመን ያሉ፣ በግብር ከፈረንጅ ጋር የሚኖሩ… እባካችሁ እንመለስ። ሰክን እንበል።
የአገር ቤቱን እንተወው። እዚህ ” ስደት” እሚባለው ዓለም እንዴት ነው ኑሮ። በዘር ፣ በቀለም፣ በባህል፣ በአመለካከት፣ በወግ፣ በልምድ፣ በተፈጥሮ፣ በአመጋገብ… የማንተዋወቅ አስጥገተውን እንኖራለን። ቦሰና እንዲህ ትላለች ” እባካችሁ እናስተውል” አዎ መጽሃፉም ” የማያስተውል ህዝብ ይገለበጣል” ይላል። በውስጥም በውጭም ” ሰከን” በርጋታ መፍትሄ ይፈለግ። እንደቀድሞው በማምታታት አይሆንም። ኦሮሞ ከፊት አድርጎ ከጀርባ እየገፉ፣ ደቡብን ዙፋን ላይ አስቀምጦ፤ ዙፋኑ ስር ሆኖ መግዛት ከአሁን በሁዋላ ብዙም አያስኬድም። አሁንጊዜው የደጎል ነው። ደጎል መብቱ ካልተጠበቀ ይቆጣል። ይረብሻል። አንዳንዴም እቃ ይሰብራል። እናም ያበደው ወደ ደጎል ይበራል። ሰላም እንሁን!! ሰላም!!

Zaggolenews.