Posted on February 23, 2017

 

በቦረና ዞን ድርቅ በከብቶች ላይ ጉዳት እያደረሰ ነው

Wednesday, 22 February 2017 11:39

 በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን የተከሰተው ድርቅ በከብቶች ላይ ጉዳት እያደረሰ ነው። በዞኑ የበርካታ አርብቶ አደሮች እንስሳት ድርቁን መቋቋም ተስኗቸው የሞቱ መሆኑን የተመለከትን ሲሆን ከአርብቶ አደሮቹ ጋር ባደረግነው ቆይታም በርካታ ከብቶች የሞቱባቸው መሆኑን ገልፀውልናል። በዞኑ ዋና ከተማ ያቢሎ ምዕራባዊ አቅጣጫ ባለው መንገድ ግራ ቀኝ በርካታ ከብቶች ሞተው ተመልክተናል።

አንዳንዶቹ ከብቶች የቆዩ በመሆናቸው አጥንታቸው ብቻ የቀረ ሲሆን ሊሎቹ ደግሞ ከሞቱ ብዙም ቀናት ያላስቆጠሩ በመሆናቸው ቆዳቸው እንኳን ያልበሰበሰ ነው።

አካባቢው ከፍተኛ ሙቀት ያለው ሲሆን በአካባቢውያሉ ዛፎች ደርቀዋል። ምንም አይነት የሳር አይነትም አይታይም። አርብቶ አደሮቹ ለከብቶቻቸው ውሃና ግጦሽ ፍለጋ ከብቶቻቸውን በመንዳት በርካታ ኪሎ ሜትሮችን አቋርጠው ቢጓዙም በሄዱባቸው ቦታዎች በሙሉ ምንም የተሻለ ነገር ያላገኙ መሆኑን ይገልፃሉ። በርካታ አርብቶ አደሮችም ግጦሽና ውሃ ለመፈለግ በሚያደርጉት ጉዞ ከብቶቻቸው በርሃብ ተዳክመው በየመንገዱ ቀርተውባቸዋል። ሁኔታው በዚህ ከቀጠለም ለእነሱም ሆነ ለከብቶቻቸው ከፍተኛ ሥጋት መሆኑን አርብቶ አደሮቹ ገልፀውልናል። በህይወት ያሉ ከብቶችም በከፍተኛ ሁኔታ ከስተው ከመንቀሳሰቅ ይልቅ መተኛትን መርጠው ይታያሉ።

በመንግስት በኩል የድርቆሽ ሳር መኖ እየቀረበ ቢሆንም በአንድ መልኩ የድርቁ አካባቢ ሰፊ መሆኑ እንደዚሁም የሚቀርበው የድርቆሽ ሳር አይነትም ከከብቶቻቸው ጋር ባለመስማማቱ ችግር የገጠማቸው መሆኑን አርብቶ አደሮቹ ገልፀውልናል። በሌላ መልኩ አርብቶ አደሮቹ ቀሪ ከብቶቻቸውን ለማዳን እንደዚሁም ለቀለብ ሸመታ የሚሆናቸውን ገንዘብ ለማግኘት ከብቶቻቸውን ቢሸጡም በአካባቢው ገበያ ዋጋ ሊያጡላቸው ባለመቻላቸው ሸጠው መጠቀም ያልቻሉ መሆናቸውን አመልክተዋል። ቀደም ሲል ከአምስት እስከ ስድስት ሺህ ብር ይሸጥ የነበረው የቀንድ ከብት ዋጋ በአሁኑ ሰዓት ከአንድ ሺህ ብር ብዙም የማይዘል እንደሆነ አርብቶ አደሮቹ ይገልፃሉ።

በድርቁ የተጠቁት አርብቶ አደሮች የከብቶቻቸውን ህይወት ለማቆየት የተወሰኑ ከብቶቻቸውን በመሸጥ የፉርሽካ መኖ ከከተማ ቢገዙም አንዳንድ ነጋዴዎች ፉርሽካውን ከጣውላ ፍቅፋቂ ሰጋቱራ ጋር ቀላቅለው በመሸጣቸው በርካታ ከብቶች የሞቱባቸው መሆኑን ገልፀውልናል።

የቦረና ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የአርብቶ አደር ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብዱሰላም ማርዮ ለድርቁ መከሰት ዋነኛው ምክንያት ከኤሊኖ የአየር ለውጥ ጋር በተያያዘ የክረምት እንደዚሁም በአካባቢው ሀገየ ተብሎ የሚጠራ የዝናብ ወቅት ያለዝናብ በማለፉ ድርቁ የተከሰተ መሆኑን አመልክተዋል። ይህም በመሆኑ ዞኑ በያዛቸው አሰራ ሦስት ወረዳዎች የድርቁ ችግር በስፋት የታየ መሆኑን ገልፀዋል።

የከብቶቹንም እልቂት ከውሃና ከመኖ እጥረት ጋር የተያያዘ መሆኑን ምክትል አስተዳዳሪው ጨምረው ገልፀዋል። ከዚሁ ጋር በተያያዘም የውሃ እና የግጦሽ ችግር የተከሰተ መሆኑን ያመለከቱት ሀላፊው፤ ችግሩንም ለመቋቋም በኦሮሚያ አርብቶ አደር ኮሚሽን እንደዚሁም በኦሮሚያ አደጋ መከላከል ፅህፈት ቤት በኩል ችግሩን ለመከላከል ጥረት ሲደረግ የቆየና መሆኑንና አሁንም በመደረግ ላይ መሆኑን ገልፀውልናል። በአካባቢው በነበረን ቆያታም ለአርብቶ አደሮቹ የስንዴ እርዳታ ሲታደል ተመልክተናል።

ስንደቅ