Posted on April 25, 2017 b

በኦሮሚያ ሰፊ ድጋፍ ያለው የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረንስ ኦፌኮ ህልውናውን ጠብቆ የመቆየት እድል እንደሌለው ለምርጫ ቦርድና ለስርዓቱ ቅርበት ያላቸው የኦህዴድ ሰዎች ለዛጎል ገለጹ። እንደ ገለጻው ኦፌኮ እንደ ፓርቲ እንዲቆይ የማይፈለገው በሁለት አበይት ምክንያቶች ነው። የመጀመሪያው ከኦነግ በሁዋላ ኢህአዴግን የፈተነው ኦፌኮ በመሆኑና ሰፊ ድጋፍ ስላለው በዚህ መልኩ ሕዝብ የሚደግፈው ድርጅት በተለይ ኦሮሚያ ላይ እንዲኖር ስለማይፈለግ ነው። ሁለተኛው ምክንያት ቀጣዩን ምርጫ ኦሮሚያ ላይ ማሸነፍ ስለማይቻል ከወዲሁ ቅድመ ዝግጅት ለማድረግ በሚል እንደሆነ የመረጃው ባለቤቶች ያስረዳሉ። በሌላም በኩል ከድርድር የወጣው መድረክም ኦፌኮን ካጣ ባዶ እንደሚሆን በማሰብም ጭምር ነው ሲሉ ያክላሉ። ኢህአዴግ ያቋቋመውንና በቀደሞው የምርጫ ቦርድ ሹም የሚመራው የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ያቀረበውን ሪፖርት ያስታውሱት ክፍሎች፤ በሪፖርቱ ከተወነጀሉት ሶስት ፓርቲዎች መካከል ኦፌኮ አንዱ መሆኑን ይታወሳል። ሰማያዊ ፓርቲና  ኦፌኮ በኦሮሚያና በአማራ ክልል የተነሳውን ህዝባዊ ተቃውሞ “እንዲቀሰቀስና እንዲባባስ አድርገዋል” በሚል የቀረበውን ሪፖርት ሸንጎው አጽድቆ ፓርቲዎች እንዲከሰሱ ወሳኔ አስተላልፎ እንደነበር የሚታወስ ነው።

ለገለልተኛ አጣሪዎችና ለተባበሩት መንግስታት መርማሪዎች በሩን የዘጋው ኢህአዴግ፣ ሕዝባዊ አመጹን ተከትሎ ለጠፋው የሰው ህይውት ነጻና ገለልተኛ አጣሪዎች ምርመራ እንዳያደርጉ ሲከለክል ምክንያት አቅርቦ ነበር። ምክንያቱም ” ሉአላዊነትን የማስደፈር ያህል ነው” የሚል ነበር። ኢህአዴግ ይህንን ቢልም በአገሪቱ ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ተጥሶባቸዋል የሚባሉ አካባቢዎችን ለጋዜጠኞች፣ ለለጋሽ አካላትና ለተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ለምልከታ ሲከለክል ይህ የመጀመሪያው እንዳልሆነ የሚገልጹ አሉ።

የዜናው ሰዎች እንደሚሉት ኢህአዴግ የሚፈራው ከውጪ ያሉ ተቃዋሚዎችን አይደለም። የአንድ ከፍተኛ ባለስልጣን ስም በመጥራት እነዚሁ ክፍሎች እንደተናገሩት ኢህአዴግ አገር ቤት ተነስቶ የነበረው ተቃውሞ አይነት ቀውስ በድጋሚ እንዳይፈጠር “የትኛውንም ርቀት” ይሄዳል።

በዚሁ መነሻ በኦሮሚያ ብቻ ሳይሆን በአብዛኛው የአገሪቱ ሕዝብ ተቀባይነት ያላቸውን የኦፌኮን መሪዎችና ራሱን ፓርቲውን አግዶ ህልውናውን ማክሰም ሆን ተብሎ ሲሰራበት የነበረ ጉዳይ ነው። ይህንኑ እቅድ ተግባራዊ ለማደረግ ደግሞ ” ህግ” የሚባለውን ማደናገሪያ መጠቀም ግድ በመሆኑ ገለልተኛ እንዳልሆነ በየተኛውም የህብረተሰብ ክፍል የሚታወቀውን የ” ኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ጉባኤ” ሪፖርት መጠበቅ ግድ ነበር። ዜናውን የጠቆሙት የኦህዴድ ሰዎች ” ክስ እንዲመሰረት የተወሰነባቸው ፓርቲዎች ሲከሰሱ በጥቅሉ ምን እንደሚወሰንባቸው ባይታወቅም ኦፌኮ ግን እንደሚታገድና፣ የምርጫ ቦርድ የእውቅና ማስረጃን እንደሚነጠቅ፤ በዛውም እንደሚከስም፣ ሌላ ሕዝብ የሚያምናቸው ድርጅቶች እስኪበቅሉ ምርጫውም ያልፋል ” ብለዋል።

ዶክተር መረራ ጉዲና፣ በቀለ ገርባ ፣ ያለተዘመረለት ኦልባና ሌሊሳ እና በርካታ አመራሮቹን፣ አባላቱን፣ ደጋፊዎቹ እስር ላይ ያሉት ኦፌኮ መጪው ዕድሉ እንደተባለው መክሰም ከሆነ ይህንን ወሳኔ የሚወስኑት ፕሮፌሰር በቃና – የምርጫ ቦርድ “ዋና ሃላፊ” መሆናቸው ታሪኩን፣ አጋጣሚውን፣ እንዲሁም ውሳኔውን ልዩ እንደሚያደርገው ከኦህዴድ ሰዎች የተገኘው ዜና ያስረዳል።
የሰብአዊ መብት ኮሚሽኑንን ሪፖርት በተለያየ መልኩ ከመዘገብ ውጪ በኦፊሳል የተጠቀሱት ፓርቲዎች ላይ ምን ዓይነት እርምጃ እንደሚወሰድ የተባለ ነገር የለም። ይሁንና ተጠያቂ እንዲደረጉ መወሰኑ የዜናውን ተአማኒነት ያጎላዋል የሚል እምነት አለ። ኦፌዴንና ሰማያዊ ፓርቲ የተወሰነባቸውን ውሳኔ አስመልክቶ የሰጡት ” በገለልተኛ ወገን ያልቀረበ ሪፖርት ተቀባይነት የለውም” ሲሉ መመለሳቸው አይዘነጋም።

የዶ/ር መረራ ፓርቲ ቀደም ሲል ስሙ ተነጥቆ ለአቶ ቶለሳ ቢሰጥም በአጭር ጊዜ ውስጥ ክርክሩን አቁመው ኦፌኮን ማቋቋማቸው አይዘነጋም። ኢህአዴግ የሚወዳደረው ፓርቲ ሲፈጠር ስሙን መንጠቅና ለሌላ አሳልፎ የምስጠት፣ አመራሮቹን አስሮ የማዳከም ለዩ ባህሪው እንደሆነ በስፋት የሚከሰስበት ጉዳይ ነው። አሁን በድርድር ላይ ያሉትን ፓርቲዎች ታሪክ ማየትም ይህንኑ ሃቅ ያጎላዋል።

ሪፖርተር የሚከተለውን ዘግቧል

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በኦሮሚያ፣ በአማራና በደቡብ ክልል ጌዴኦ ዞን ተከስተው የነበሩትን ሁከትና ብጥብጦች አስመልክቶ ያቀረበውን የምርመራ ሪፖርት ያዳመጠው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ኃላፊነታቸውን ያልተወጡ አካላት በሕግ እንዲጠየቁ ወስኗል፡፡

የፓርላማው የሕግ፣ ፍትሕና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ያቀረበውን የውሳኔ ሐሳብም ፓርላማው በሙሉ ድምፅ አፅድቆታል፡፡ በሕግ እንዲጠየቁ ከተባሉት መካከል በኦሮሚያ ክልል የኢሬቻ በዓል ከመከበሩ አስቀድሞ ሁከት እንደሚነሳ እየታወቀ፣ ኃላፊነታቸውን ባልተወጡ የክልሉ መንግሥት የማመለከታቸው ኃላፊዎች ይገኙበታል፡፡

በአማራ ክልል በባህር ዳር ከተማ ሰላማዊ ሠልፍ ጠርቶ የነበረው ሰማያዊ ፓርቲ ሠልፉ ሰዓታት ሲቀሩት መሰረዙን ቢገልጽም፣ ሰላማዊ ሠልፉ እንደተካሄደና ወደ ብጥብጥ እንደተቀየረ ከሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ሪፖርት መረዳት በመቻሉ ፓርቲው በሕግ እንዲጠየቅ ሲል ፓርላማው ውሳኔ አሳልፏል፡፡

በኦሮሚያ ክልል በተቀሰቀሱት ረብሻዎች የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) አባላት ተሳትፎ መገኘቱ በሪፖርቱ በመረጋገጡ ፓርቲው እንዲጠየቅ ፓርላማው ወስኗል፡፡ በሦስቱም አካባቢዎች በነበሩት ግጭት አዘል ተቃውሞዎች 669 ሰዎች መሞታቸውን የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ሪፖርት ማድረጉን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

ከእነዚህ ሟቾች ውስጥ 606 የሚሆኑት ሲቪሎች ሲሆኑ፣ 63 የሚሆኑት ደግሞ የፀጥታ አስከባሪዎች መሆናቸው ተገልጿል፡፡ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ባቀረበው ሪፖርት በተለያዩ አካባቢዎች የፀጥታ አስከባሪዎት ከመጠን በላይ ኃይል መጠቀማቸውን፣ በዚህም ሳቢያ በሰዎች ላይ የሕይወት ህልፈትና የአካል ጉዳት መፍጠራቸውን ገልጿል፡፡

ይህንኑ ከግምት ያስገባው ፓርላማው ከመጠን ያለፈ ኃይል የተጠቀሙ የፀጥታ አስከባሪዎት በሕግ እንዲጠየቁ ሲል ወስኗል፡፡

በአማራ ክልል ለተነሳው ግጭት ከወልቃይት የወሰን ጥያቄ ጋር የተያያዘ ሲሆን፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ የተለያዩ የመንግሥት ኃላፊዎች የአማራና የትግራይ ክልል አመራሮችን ለዚሁ ግጭት ሲወቅሱ ነበር፡፡

ይሁን እንጂ በአማራ ክልል ለነበረው ግጭት መነሻ የመልካም አስተዳደርና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ጥያቄዎች መሆናቸውን ኮሚሽኑ በዋና መንስዔነት የጠቀሰና የወልቃይት ጉዳይ አባባሽ በመሆኑ፣ የሁለቱ ክልል አመራሮች በሕግ ሊጠየቁ እንደማይገባ የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትሩ አቶ አስመላሽ ወልደ ሥላሴ ጉዳዩን አስመልክቶ ፓርላማው ውስጥ ለተነሳው ጥያቄ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

ዛጎል