አፍላቶክሲን አደገኛው የጤና ጠንቅ

 የተለያየ የጥራት ደረጃ የሚወጣላቸው ዛላ የበርበሬ ዓይነቶች በየማዳበሪያው ተሞልተው ተደርድረዋል፡፡ አንደኛ የሚባለውና በኪሎ 60 ብር የሚሸጠው፣ ዛለው ረጃጅምና ደማቅ ቀለም ያለው ነው፡፡ ሁለተኛው በኪሎ 50 ብር የሚሸጠው ሲሆን፣ ከአንደኛው መለስ ያለ ደረጃ የሚሰጠው ነው፡፡ ሌሎቹ የበርበሬ ዘሮች የተሰባበሩ፣ ነጫጭ የሚበዛባቸው ከበርበሬነት ይልቅ በቀለማቸው ወደሌላ የምርት ዓይነት የሚያደሉት በኪሎ እስከ 30 ብር የሚሸጡ ናቸው፡፡

በሾላ ገበያ በርበሬና የተለያዩ ቅመማ ቅመሞችን የሚሸጡት ወይዘሮ ዘመናይ ይርጋ (ስማቸው የተቀየረ ነጋዴ) ፀዳሌ፣ ማረቆና ሃላባ የተባሉት የበርበሬ ዓይነቶች ተመራጭ እንደሆኑ ይናገራሉ፡፡ በአጠቃላይ ግን ቆዳው ወፍራምና ዛላው ትልልቅ ሆኖ ደማቅ ቀለም ያለው አንደኛ ተብሎ በውድ ዋጋ ይሸጣል፡፡ ልቃሚ የሚበዛውና አመድማ ዛላ ያለው በርበሬ በርካሽ ዋጋ እንደሚሸጥ ይገልጻሉ፡፡

‹‹አንደኛው ቀለሙ በጣም ቀይ ነው፡፡ ወጥ ሲሠራበትም ያጣፍጣል፡፡ የመጨረሻው ግን አፈር የመሰለ ነው ቀለሙም አያምርም፤›› በማለት በሁለቱ የበርበሬ ዓይነቶች መካከል ያለው ልዩነት ከቀለም ያለፈ እንዳልሆነ ያብራራሉ፡፡ ልዩነታቸውም ከአለቃቀምና ከምርት አያያዝ የመነጨ እንደሆነም በልበ ሙሉነት ይናገራሉ፡፡ በሁለቱ በርበሬዎች መካከል ያለው ልዩነት በሻጋታ የተፈጠረ እንደሆነ ግን የገባቸው አይመስሉም፡፡

በቅናሽ ዋጋ የሚሸጠው በርበሬ በአብዛኛው ሻጋታ ይታይበታል፡፡ ሻጋታ የሚፈጠረውም ምርት እርጥበቱ ሳይጠፋ በሚከማችበት ጊዜ እንደሆነ የሥነ ምግብ ባለሙያዎች ሲናገሩ ይደመጣሉ፡፡ ‹‹ኪሎ እንዲያነሳ በማለት ገበሬውም ነጋዴውም በርበሬ ላይ ውኃ ያርከፈክፋሉ፡፡ በርበሬ ዕርጥብ ሲሆን ከአንድ ኩንታል እስከ አሥር ኪሎ ትርፍ ይገኛል፡፡ ይህ በርበሬ ቶሎ ካልተሸጠ ግን ስለሚሻግት በቅናሽ ዋጋ እንሸጠዋለን፤›› በማለት ኪሎ እንዲያሳ ሲባል ውኃ የሚርከፈከፍበት በርበሬ ሻጋታ እንዲፈጥር መንገዱን እየጠረጉ ስለመሆኑ ነጋዴዋ ይናገራሉ፡፡ በርበሬ ሲሻግት በጤና ላይ የሚፈጥረው ችግር እንደሚኖር ግን አንድም ጊዜ አልጠረጠሩም፡፡ በሻጋታ ውስጥ ካንሰር አማጭ የሆነው አፍላቶክሲን የተባለው ኬሚካል እንደሚፈጠር የሚያውቁት ነገር የለም፡፡

በተለያዩ ጊዜያት የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት በርበሬ፣ በቆሎ፣ ለውዝ እንዲሁም ቦሎቄ ከፍተኛ የአፍላቶክሲን ክምችት ሊገኝባው የሚችሉ የቅባት፣ የቅመማቅመምና የእህል ዝርያዎች ናቸው፡፡ በቅርቡ ወደ እንግሊዝ የተላከ ሁለት ኮንቴነር በርበሬ በአፍላቶክሲን ተጠርጥሮ እንዲጣል መደረጉን ሚዲያዎች መዘገባቸው ይታወሳል፡፡

ሞቃታማና እርጥበት አዘል በሆኑ የዓለም አካባቢዎች በተለይም ከሰሐራ በታች በሚገኙ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች ውስጥ በሚመረቱ የእህል ዓይቶች ውስጥ አፍላቶክሲን በብዛት ይከሰታል፡፡ አፍላቶክሲን በሕፃናት ዕድገት እንዲሁም በማስተዋል ችሎታ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ከማሳደሩ ባለፈ ብዙዎችን ለካንሠርና ለተለያዩ ከባድ በሽታዎች እየዳረገ ይገኛል፡፡

አፍሪካ ባላት የአየር ጠባይ ሳቢያ 80 በመቶ የሚሆኑ ሕዝቦቿ ለአፍላቶክሲን ጉዳቶች የተጋለጡ ናቸው፡፡ በአኅጉሪቱ በተለያዩ ጊዜያት በመከሰት ብዙዎችን ከሚያረግፉት የወባና የሳንባ ወረርሽኞች የበለጠ አፍላቶክሲን በርካቶችን ለሞት እየዳረገ እንደሚገኝ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

25 በመቶ በዓለም የሚመረተው ሰብል በአፍላቶክሲን የተበከለ መሆኑም ይነገራል፡፡ በአፍሪካም አንድ ሦስተኛው ለምግብነት የሚውለው ሰብል ከሚገባው በላይ በአፍላቶክሲን የተበከለ ነው፡፡

አቶ ዘሪሁን አበበ፣ በኢትዮጵያ ተስማሚነትና ምዘና ድርጅት የኬሚካል ቴስቲንግ ላቦራቶሪ ቡድን መሪ ናቸው፡፡ እሳቸው እንደሚሉት፣ ቅርፊት ያላቸው እንደ በቆሎና ለውዝ ያሉ የእህል ዘሮች በእርጥበታማ ቦታዎች በሚከማቹበት ጊዜ በቅርፊታቸው እርጥበት የመያዝ ባህሪ ስላላቸው የመሻገት ዕድላቸው ሰፊ ነው፡፡ ቅርፊት ያላቸውን ያህል ባይሆንም ሌሎችም የሰብል ዓይነቶች በእርጥበታማ ቦታ ከተቀመጡ መሻገታቸው አይቀሬ ነው፡፡

ሁሉም ሻጋታ የአፍላቶክሲን መንስዔ ባይሆንም፣ በፍጥነት ማስተካከል ካልተቻለ ግን ወደ አፍላቶክሲን መቀየሩ አይቀሬ ነው፡፡ አፍላቶክሲን ‹‹ኤስፐርጊለስ ፍሌቨስ›› እና ‹‹ኤስፐርጊለስ ፓራሲተከስ›› በተባሉ የፈንገስ ዝርያዎች የሚከሰት አደገኛ ኬሚካል ነው፡፡ b1፣ b2፣ G1፣ G2 የሚባሉ ዝርያዎችም አሉት፡፡ እነዚህ በሰብሎች ላይ የሚከሰቱ ናቸው፡፡ m1፣ m2 የተባሉ በእንስሳት ተዋፅኦዎች ውስጥ የሚገኙ ዝርያዎችም አሉ፡፡

እንስሳት በአፍላቶክሲን የተበከሉ መኖዎች በሚመገቡበት ጊዜ ኬሚካሉ ወደ ተዋጽኦዋቸው ይተላለፋል፡፡ ነገር ግን ኬሚካሉን ወደሌላ ዓይነት ይዘት እንዲቀየር (ሜታቦላይዝ) ስለሚያደርጉት በቀጥታ እንስሳቱን አይጎዳም፡፡ እነዚህ የአፍላቶክሲን ዝርያዎች የሚያደርሱት የጉዳት መጠን የተለያየ ነው፡፡ b1 የሚባለው የአፍላቶክሲን ዝርያ ከሌሎቹ በተለየ አደገኛ ነው፡፡ የጨጓራ ካንሰር የሚከሰተው በዚሁ b1 በተባለው የአፍላቶክሲን ኬሚካል አማካይት ነው፡፡ M1 የተባለው በእንስሳት ተዋጽኦ ውስጥ የሚገኘው ኬሚካል እንደ b1 ሁሉ አደገኛ የሚባል ነው፡፡

በአንድ ኪሎ ግራም ምግብ ውስጥ መገኘት የሚገባው ከፍተኛው የአፍላቶክሲን ክምችት እንደየ ዝርያው ዓይነት ይወሰናል፡፡ በኢትዮጵያ ስታንዳርድ መሠረት b1 የሚባለው አደገኛው የአፍላቶክሲን ዝርያ፣ በአንድ ኪሎ ምግብ ውስጥ የሚኖረው ክምችት ከአምስት ማይክሮ ግራም መብለጥ የለበትም፡፡ በሕፃናት ምግብ ውስጥ የሚገኘው መጠንም በአንድ ኪሎ ግራም ውስጥ ከሁለት ማይክሮ ግራም በላይ ከሆነ አደገኛ ነው፡፡ በአዋቂ ምግቦች ውስጥ እስከ 20 ማይክሮ ግራም ከተገኘ አደገኛ የሚያስብለው ደረጃ ላይ የሚመደብ ነው፡፡

ሰብሎች በማሳ ሳሉ ሊሻግቱና በአፍላቶክሲን ሊጠቁ ይችላሉ፡፡ በአፍላቶክሲን የተጠቃ ምርት በማሳ ላይ በሚራግፍበት ወቅትም ኬሚካሉ ወደ አፈር ውስጥ በመግባት ማሳውን ሙሉ ለሙሉ ሊያበላሸው ይችላል፡፡ ‹‹በምርት ወቅት ማሳ ላይ ከተሠራጨ ችግር ነው፡፡ ኬሚካሉ አፈር ውስጥ ስለሚገባ በማሳው የሚበቅል ምንም ነገር በአፍላቶክሲን የተበከለ እንዲሆን ያደርጋል፡፡ ይሁንና ይህ ከብዙ ጊዜ በጥቂቱ የሚከሰት ነው፡፡ ሰብሎች ማሳ ላይ ሻግተው ችግር ለመፍጠር ረዘም ያለ ጊዜ ይፈጃሉ፤›› ለማለት ችግሩ በብዛት እየተከሰተ ያለው ከማሳ ተሰብስቦ በሚከማችበት ወቅት መሆኑን አቶ ዘሪሁን ይናገራሉ፡፡

እንደ እሳቸው ገለጻ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ምርት ከመታጨዱ ወይም ከመሰብሰቡ በፊት እንዳይረግፍ እየተባለ በተገቢው ደረጃ ሳይደርቅ የሚታጨድበት ሁኔታ የተለመደ ነው፡፡ በወጉ ያልደረቀው ምርት ጎተራ ከመግባቱ በፊት እንዲደርቅ እየተባለ በአንድ ላይ ይከማቻል፡፡ ይህም ሻጋታ እንዲፈጠር የመጀመሪያውን መንገድ ይከፍታል ያሉት አቶ ዘሪሁን፣ ገለባው ከፍሬው ተለይቶና ተወቅቶ ወደ ጎተራ በሚገባበት ጊዜም ተገቢው ጥንቃቄ ስለማይደረግ፣ በወጉ ያልደረቁ ፍሬዎች ተቀላቅለው ይገባሉ፡፡ በመሆኑም በጎተራ ውስጥ ታፍኖ የሚቀመጠው ምርት የመሻገት ዕድሉ ከፍተኛ እንደሆነ ያብራራሉ፡፡

‹‹አንዳንዴ ገበያ ላይ ጤፍ እምክ እምክ አለ ይባላል፡፡ ይህ የሚሆነው ጤፉ እርጥበት እንደያዘ ጎተራ ውስጥ ታፍኖ እንዲቆይ ሲደረግ ነው፡፡ ሁሉም ሻጋታ አፍላቶክሲን አይደለም፡፡ ቶሎ ካልተደረሰበት ግን ወደ አፍላቶክሲንነት ይቀየራል›› ይላሉ፡፡

የአፍላቶክሲን ጉዳይ የዓለምን ትኩረት መሳብ የጀመረው እ.ኤ.አ. በ1960ዎቹ ውስጥ በእንግሊዝ የሚገኝ አንድ የዶሮ እርባታ ውስጥ የነበሩ 100,000 ዶሮዎችን እንደ ጤዛ ካረገፋቸው በኋላ ነው፡፡ ይኸው አፍላቶክሲን በኢትዮጵያ መነጋገሪያ ለመሆን የበቃውም ዓለምአቀፉ የእንስሳት ምርምር ኢንስቲትዩት የተባለው ተቋም ተመራማሪዎች ያወጡትን ጥናት ተከትሎ ነው፡፡ ከዓመት በፊት ይፋ የተደረገው ጥናቱ፣ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚገኙ የወተት ላም አርቢዎችን መነሻ ያደረገና በወተት ውስጥ የሚገኘውን የአፍላቶክሲን ክምችት የሚያሳይ ነበር፡፡

በወቅቱ በርካቶችን ያወዛገበና የእንስሳት ተዋጽኦ ገበያን ሥጋት ውስጥ ጥሎ  እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡ ከዚህ ክስተት ወዲህ ስሙ የገነነው አፍላቶክሲን፣ ከእንስሳት ተዋጽኦ ባሻገር በተለያዩ የምግብ ይዘት ባላቸው ነገሮች ውስጥ ለጤና አስጊ በሆነ የክምችት መጠን እንደሚገኝ የሚያሳዩ ጥናቶች ይፋ እየወጡ መጥተዋል፡፡

በዚህ መርዛማ ኬሚካል በእጅጉ እየተጠቁ ያሉትም የለውዝና የበርበሬ ምርቶች እንደሆኑ አቶ ዘሪሁን ገልጸዋል፡፡ አገሮች ካስቀመጧቸው መሥፈርቶች የበለጠ የአፍላቶክሲን መጠን የሚታይባቸውና እንዲመለሱ እየተደረጉ ካሉት ምርቶች ግንባር ቀደም ሆነው ተገኝተዋል፡፡

ከውጭ የሚገቡ ምግብ ነክ ሸቀጦች እየተፈተሹ መሥፈርቱን የሚያሟሉት እንዲገቡ ሲፈቀድላቸው፣ የማያሟሉት ግን ወደየመጡበት እንዲመለሱ ይደረጋሉ፡፡ ወደ ውጭ የሚወጡትም እንደዚሁ እንደየአገራቱ አሠራርና መሥፈርት ተፈትሸው መሥፈርቶቹን ስለማሟላታቸው የማረጋገጫ ሠርተፊኬት እየተሰጣቸው ይላካሉ፡፡

በዚህ መሠረት ለፍተሻ ወደ ተቋሙ ከሚሄዱ የበርበሬና የለውዝ ምርቶች ውስጥ ከፍተኛ የአፍላቶክሲን ክምችት እንደሚያጋጥም አቶ ዘሪሁን የታዘቡትን ጠቅሰዋል፡፡ በኪሎ ግራም ውስጥ እስክ 60 ማይክሮ ግራም የአፍላቶክሲን ክምችት እንደሚያጋጥም አስታውሰዋል፡፡ ሌሎች መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ በአንድ ኪሎ ግራም ለውዝ ውስጥ እስከ 500 ማይክሮ ግራም የአፍላቶክሲን ክምችት የሚገኝበት ክስተትም ይታያል፡፡ በአውሮፓ ስታንዳርድ መሠረት በአንድ ኪሎ ግራም ለውዝ ውስጥ መገኘት የሚገባው የአፍላቶክሲን ክምችት ከአሥር ማይክሮ ግራም መብለጥ የለበትም፡፡

በኢትዮጵያ በለውዝ ምርት የሚታወቁት በምሥራቅ ሐረርጌ የሚገኙት የባቢሌ፣ የፈዲስና የጉርሱም አካባቢዎች ናቸው፡፡ በእነዚህ አካባቢዎች በሚገኝ የለውዝ ምርት ላይ የተደረገ ጥናት እንደመሚያመለክተው፣ ተከማችተው በሚገኙ የለውዝ ምርቶች ውስጥ 85 በመቶ ያህል የአውሮፓ ኅብረት ካስቀመጠው በላይ ከፍተኛ የአፍላቶክሲን ክምችት የሚገኝባቸው ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ የጥራጥሬ፣ የቅባት እህሎችና ቅመማ ቅመም አምራቾችና ላኪዎች ማኅበር ሥራ አስኪያጅ አቶ አሰፋ ዮሐንስ እንደሚሉት፣ ከመጠን ባለፈ የአፍላቶክሲን ክምችት ምክንያት ወደ ውጭ የሚላከው የለውዝ ምርት ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ መጠን እየቀነሰ ይገኛል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2011 ወደ ውጭ ተልኮ የነበረው የለውዝ መጠን 14,424 ቶን ነበረ፡፡ ይሁንና እ.ኤ.አ. ከ2012 እስከ 2016 ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ የተላከው የለውዝ መጠን በእጅጉ ማሽቆልቆሉን ከማኅበሩ የተገኘው አሃዛዊ መረጃ ያሳያል፡፡ 12,609 ቶን፣ 592 ቶን፣ 124 ቶን እያለ ወርዶ እ.ኤ.አ በ2016 የተላከው የለውዝ መጠን ወደ 79 ቶን ሊያሽቆለቁል ችሏል፡፡

አስፈላጊውን የፍተሻ ሒደትና መሥፈርት ሳያሟሉ ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶች ከመጠን ያለፈ የአፍላቶክሲን ክምችት በሚገኝባቸው ወቅት እንዲወገዱ ሲደረግ፣ ጤናማ የሆኑት ደግሞ በላቦራቶሪ ተፈትሸው ደኅንነታቸውም ተረጋግጦ ወደ ውጭ ይላካሉ፡፡ ይሁንና ስለ ጉዳዩ ብዙም ግንዛቤ የሌላቸው ሸማቾች፣ በየዕለቱ የሚመገቧቸው ነገሮች ምን ያህል ለጤና የሚገባውን መሥፈርት እንደሚያሟሉ አረጋግጠው ስለመጠቀማቸው በእርግጠኝነት መናገሩ አጠያያቂ ነው፡፡ በዓይን የማይታዩ የኬሚካሎችን ዝርያ ከመመገብ መጠንቀቁ ቀርቶ ሻጋታን የመጠየፍ ባህሉ እስከምን ድረስ እንደሆነ ጥያቄ የሚጭሩ ልማዶች ይታያሉ፡፡

‹‹Assessment of Mothers Knowledge towards Aflatoxin Contamination›› በሚል ርዕሥ እ.ኤ.አ. በ2016 የተደረገ ጥናት፣ ማኅበረሰቡ ስለ አደገኛው ኬሚካል ያለው ግንዛቤ ዝቅተኛ በመሆኑ ምክንያት ችግሩ አሳሳቢ እንደሆነ ለማመላከት ሞክሯል፡፡ በአማራ፣ በትግራይ፣ በኦሮሚያና በደቡብ ብሔር ብሐረሰቦች የሚገኙ እናቶች በጥናቱ ተካተው ነበር፡፡

ምርት ከማሳው ጀምሮ ለምግብነት እስኪሚውልበት ድረስ ያሉትን ሒደቶች በሚያሳየው በዚህ ጥናት መሠረት፣ 64 በመቶ እናቶች ምርት ከማሳው ከተሰበሰበ በኋላ በተለያዩ ዘዴዎች አድርቆ የማስቀመጥ ልምድ እንዳላቸው ታይቷል፡፡ 68 በመቶዎቹ ምግባቸውን መሬት በማንጠፍ በፀሐይ ይደርቃሉ፡፡ 94 በመቶዎቹ ደግሞ ምርት በጎተራ ውስጥ ከማከማቸታቸው በፊት ጎተራቸውን በፀረ ባክቴሪያ ኬሚካሎች እንደሚያፀዱ ጥናቱ ያሳያል፡፡

የተሻለ ጥንቃቄ በማያደርጉት በኩል ያለው ምርት በሻጋታ የሚጠቃበት አጋጣሚ ብዙ ነው፡፡ በሻጋታ የሚከሰት ባክቴሪያንም እሳት ላይ ሞቅ ሞቅ በማድረግ መግደል እንደሚቻል የሚያምኑም አልታጡም፡፡ ከፊሉን ለእንስሳት መኖነት፣ የተቀረውን ደግሞ ለጠላ መጥመቂያነት እንደሚያውሉትም ጥናቱ ያትታል፡፡

የተበላሸ የሻጋታ ጥራጥሬን ለጠላ መጥመቂያነት የማዋሉ ነገር በአገሪቱ ክፍሎች የተለመደ ነወ፡፡ የሻገተ እንጀራን በምጣድ ሞቅ አድርጎ መብላትም አዲስ አይደለም፡፡ እንዲያውም እንጀራ ሻጋታ መያዝ ሲጀምር ድርቆሽ ማድረግና አቆይቶ መብላት ምግብን ከብክነት እንደመጠበቅ ይቆጠራል፡፡ በሻጋታ ምክንያት የተቋጠረ (የጓጐለ) ዱቄትን አሽተው ለመብል ማዘጋጀት፣ የሻገተ የበርበሬ ዛላን በርካሽ ገዝቶ ለምግብነት ማዋል ሊያደርስ ስለሚችለው የጤና ቀውስ የሚጨነቁ በጣም ጥቂቶች ናቸው፡፡

ምርት ከማሳ ላይ ተነስቶ ወደ ጎተራ እስኪገባ ባሉት ሒደቶች የሚፈጠረው አፍላቶክሲን በቀላሉ መከላከል እንደሚቻል አቶ ዘሪሁን ይናገራሉ፡፡ ‹‹ምርት እስኪደርቅ ጠብቆ ማጨድ፣ ወደ ጎተራ ከመግባቱ በፊትም በፀሐይ ማድረቅ ተገቢ ነው፡፡ በእኛ አገር የአየር ፀባይ ምግብ ያለ ብዙ ልፋት ይደርቃል፡፡ በዚህ የታደልን ነን፤›› በማለት ዋናው ነገር ምርት ጎተራ ውስጥ በሚከማችበት ጊዜ እርጥበት እንዳይነካው ጥንቃቄ ማድረጉ ላይ እንደሆነም ይመክራሉ፡፡

በተፈጥሮ መከላከል የማይቻል ከሆነም ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም እርጥበትንና ሻጋታን መከላከል ይቻላል፡፡ አቶ ራሺም ጀማል የሃይቴክ ትሬዲንግ ሥራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ ሃይቴክ ኩባንያ የተለያዩ የግብርና የኢንዱስትሪ ማሽገሪዎችና ግብዓቶችን ወደ አገር ውስጥ በማስገባት ሥራ ዘርፍ ይንቀሳቀሳል፡፡ ሻጋታን በባህላዊ መንገድ ማለትም በፀሐይ በማድረቅ መከላከል ካልተቻለ፣ የፈንገስን ዕድገት መግታት የሚችሉ አየር ወደ ውጭና ወደ ውስጥ የማያስገቡ ሄርሜቲክና ሜታል ሳይሎ የተባሉ ቴክኖሎጂዎች የተሻሉ አማራጮች መሆናቸውን አቶ ራሺም ይገልጻሉ፡፡ ሜታል ሳይሎ የሚባለው የዓለም የምግብና የእርሻ ድርጅት በብዛት የሚያከፋፍለው፣ አየር እንዳያስገባና እንዳያስወጣ ተደርጎ የሚዘጋጅ እንደ በርሜል ያለ ዘመናዊ ጎተራ ነው፡፡

ሄርሜቲክ ቴክኖሎጂ የሚባለው ደግሞ ነቀዝን፣ ተባይን፣ እንዲሁም እርጥበትና ሻጋታን ያለምንም ኬሚካልና ርጭት የተፈጥሮ ዘዴን በመጠቀም ማከማቸት የሚያስችል፣ ድርጅታቸው እንደሚያከፋፍለው ያለ የፕላስቲክ ጎተራ ዓይነት ነው፡፡ ይህ የፕላስቲክ ጎተራ ከ60 እስከ 1,500 ኩንታል የሚደርስ እህል የማከማቸት አቅም አለው፡፡ እንዲህ ቴክኖሎጂዎች ምርትን ከአፍላቶክሲን ከመጠበቅ ባሻገር ከፍተኛ የምርት ብክነትን ማስቀረት እንደሚችሉ ይናገራሉ፡፡ ይሁንና ተደራሽነታቸው ውሱን ነው፡፡

የአፍላቶክሲን ምርመራ የሚካህድበት ቴክኖሎጂ ባለመኖሩ በአንድ ወቅት ከፍተኛ ወጪ እየወጣ ባህር ማዶ እየተላ ምርት ይመረመር ነበር፡፡ የኢትዮጵያ የተስማሚነት ምዘና ድርጅት ከ2007 ዓ.ም. አጋማሽ ጀምሮ የአፍላቶክሲን ፍተሻ ማድረግ መጀመሩን የሚናገሩት በድርጅቱ የማርኬቲንግና ኮሙዩኒኬሽንስ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተሩ አቶ ተክኤ ብርሃኑ ናቸው፡፡ ወደ ውጭ የሚወጡና ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ምግቦችን እንፈትሻለን ያሉት አቶ ተክኤ፣ ድርጅቱ ወደ አገር ውስጥ ከሚገቡ በቀር ወደ ውጭ የሚላኩትን በሙሉ የመፈተሽ ሥልጣኑ ውሱን ነው፡፡ ‹‹ስንጠየቅ ብቻ ነው የምንፈትሸው፡፡ ሁሉም ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶች እኛ ጋር ላይመጡ ይችላሉ፡፡ ወደ ሌሎች ተቋማት በመሔድ ሊያስፈትሹ ይችላሉ፤›› በማለት በድርጅቱ ፍተሻ የሚደረገው ጥያቄ ሲቀርብለት ብቻ መሆኑን ያናገራሉ፡፡

ድርጅቱ በአገር ውስጥ በስፋት ለምግብነት የሚውሉ እንደ የእንስሳት ተዋጽኦ፣ ሽሮ፣ በርበሬ ያሉትን የመፈተሽ አቅም ቢኖረውም፣ ለአገር ውስጥ የሚውሉ የምግብ ዓይነቶችን ለማስፈተሽ ሥራዬ ብሎ ወደ ተቋሙ የሚያመራ አለመኖሩም ሌላው አሳሳቢ ጉዳይ ነው፡፡ ከመጠን ያለፈ የአፍላቶክሲን ክምችት ተገኝቶባቸው ተመላሽ የሚደረጉ ምግብና ምግብ ነክ ሸቀጦች አገር ውስጥ ከገቡ በኋላ ገበያ ውስጥ ይግቡ ወይስ ምን ይደረጉ የሚለው ጉዳይም አጠያያቂ ነው፡፡

አቶ አብነት ወንድሙ፣ በኢትዮጵያ የምግብ፣ የመድኃኒት እና የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን፣ የምግብና ጤና ተቋማት የኢንስፔክሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ናቸው፡፡ ተገቢው ፍተሻ ሳይደረግባቸው ወደ ውጭ ከሚላኩ ምርቶች በተለይ በርበሬ በከፍተኛ የአፍላቶክሲን ክምችት ምክንያት በብዛት ተመላሽ እየተደረገ ነው፡፡ ባለሥልጣኑ እንዲመለሱ የሚደረጉ ምርቶች ወደ ሕዝብ ከመድረሳቸው በፊት እንዲወገዱ የሚያደርግበት አሠራር እንዳለው አቶ አብነት ይናገራሉ፡፡

‹‹ትልቁ ሥራ ግብርና ላይ ነው፡፡ ከዚያ ውጭ አገር ውስጥ የሚመረቱ አፍላቶክሲን ሊገኝባቸው ይችላሉ ብለን የምንገምታቸውን ምርቶች በየሦስት ወሩ እንዲፈተሹ እናደርጋለን፤›› በማለት ለጊዜው ባለሥልጣኑ ትኩረቱን በወተትና በለውዝ ምርት ላይ በማድረግ እየሠራ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡