May 6, 2017

ዩናይትድ ስቴትስ እስከ ዛሬ ድረስ ለኢትዮጵያ ስትሰጥ የነበረውን የገንዘብ ድጋፍ ቀነሰች፡፡ በቀድሞ የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ዘመነ መንግስት የኢትዮጵያ አጋር የነበረችው አሜሪካ፣ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ ከኢትዮጵያ ጋር ያላት ሁለንተናዊ ግንኙነት ቀንሷል፡፡ የምስራቅ አፍሪካ የጸረ ሽብር አጋር በመሆን አሜሪካን ስታገልግል የቆየችው ኢትዮጵያ፣ አሁን ነገሮች ተለውጠው የትራምፕ አስተዳደር ፊት ነስቷታል፡፡

ከዚህ ቀደም ለኢትዮጵያ ይሰጥ ከነበረው የእርዳታ ገንዘብ ላይ በፕሬዚዳንት ትራምፕ የተቀነሰው ሶስት ቢሊዬን ብር ሲሆን፣ ይህም በህወሓት ባለስልጣናት ዘንድ ከፍተኛ መደናገጥን ፈጥሯል፡፡ ለጋሽ ሀገራት ለመሰረታዊ ነገሮች በሚሰጡት ገንዘብ የጦር መሳሪያ በመግዛት ዜጎቹን ለመግደል የሚጠቀምበት የህወሓት አገዛዝ፣ ዶናልድ ትራምፕ ስልጣን ላይ እስካሉ ድረስ ከአሜሪካ ጋር የሚኖረው ግንኙነት እንደቀድሞዉ የሰመረ አይሆንም ተብሏል፡፡

የ2017/18 የዩናይትድ ስቴትስን በጀት ዓመት አስመልክቶ በወጣው መረጃ መሰረት፣ አሜሪካ ባጠቃለይ እርዳታ በምትሰጣቸው ሀገራት ላይ የ31 በመቶ ቅናሽ ያደረገች ሲሆን፣ ከኢትዮጵያ በተጨማሪም ዩጋንዳ የየበጀት ቅናሹ ተጠቂ ሆናለች፡፡ በአዲሱ የእርዳታ አሰጣጥ መሰረት ዩጋንዳ ወደ 68 ሚሊዬን ዶላር ሲቀነስባት፣ የህወሓት አገዛዝ ደግሞ 132 ሚሊዬን ዶላር ተቀንሶበታል፡፡

ከዩጋንዳ እና ኢትዮጵያ በተጨማሪ ታንዛንያ፣ 12 ሚሊዬን ዶላር ሲቀነስባት ሩዋንዳ ደግሞ 51 ሚሊዬን ዶላር ተቀንሶባታል፡፡ ኬንያ 12፣ ቡሩንዲ 10 እንዲሁም ደቡብ ሱዳን 11 ሚሊዬን ዶላር ተቀንሶባቸዋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ሶማሊያ 36 ሚሊዬን ዶላር ተጨማሪ ድጋፍ የተደረገላት ሲሆን፣ ይህም ብቸኛዋ አፍሪካዊ ሀገር አድርጓታል፡፡ ከአፍሪካ ሀገራት የኢትዮጵያን ያህል ከፍተኛ የገንዘብ ቅነሳ የተደረገበት ሀገር የለም፡፡

Source: BBN News