Posted on May 9, 2017

“ቅባትና ደረቅ” በአማኑኤል የአዕምሮ ህክምና ሆስፒታል ታካሚዎች እንደ ደረጃ መዳቢ የተሰጠ ስም ነው። ታሪኩ ዘግናኝ፣ ኅሊናን የሚፈትን፣ ወዴት እያመራን እንደሆነ ግራ የሚያጋባ፣ መፈጠርን የሚያስጠላ፣ ሲሰሙት ግራ የሆነ፣ ቃላት ሊገልጹት የማይችል የክሽፈታችን ሁሉ ከሽፈት ነው። አማኑኤል ሆስፒታል ተኝቶ ለመታከም አርባ ሺህ ብር እንደሚከፈል ከመስማት በላይ ዘግናኝ ጉዳይ የለም። ጎልጉል ባሰባሰበው መረጃ ሌሎችም ጉዳዮች አሉ።

ወ/ሮ ፋጡማ ሐሰን (ስማቸው ለዘገባው የተቀየረ) ከደሴ ከተማ የመጡ አስታማሚ ናቸው፡፡ በሃያዎቹ አጋማሽ ዕድሜ ላይ የምትገኝ የአዕምሮ ህመምተኛ ልጅ አለቻቸው፡፡ ልጃቸው በ2006 ዓ.ም. የሳውዲ አረቢያ መንግስት ኢትዮጵያዊያን ስደተኞችን “ህገ-ወጥ” በሚል በግፍ ሲያባርር የሰራችበትን ደመወዝ እንኳ ሳታገኝ ባዶ እጇን የተመለሰች ኢትዮጵያዊት ነች፡፡ በወቅቱ ስትመለስ ከፍተኛ የሆነ የመንፈስ ጭንቀትና መረበሽ የነበረባት ቢሆንም፣ የአዕምሮ ህመሟ አሁን ባለበት ደረጃ አልነበረም፡፡ “በሂጃብ ፊቷን የሸፈነች ሙስሊም ሴት ባየች ቁጥር ‹ብሬን! ብሬን! . . . › እያለች ትጮኻለች”

በአማኑኤል ሆስፒታል ሴት የአዕምሮ ህመምተኞች መደፈራቸውን፣ ሲያረግዙ ጽንስ የሚቋረጥበት ክሊኒክ በውስጥ በተደረገ ስምምነት ይሰጥ እንደነበር ይፋ በተሰማ ጊዜ ጫጫታ ተሰምቶ ነበር። ጉዳዩን በወቅቱ ይፋ ያደረጉት አንድ የሆስፒታሉ ነርስ ነበሩ። ዛሬ ያ ግፍ ተመርምሮ መልስ ሳያገኝ ተጨማሪ ጉድ እየሰማን ነው። የሟቹ መለስ ዜናዊ ባለቤት የበላይ ጠባቂ ሆና ስትመራው በነበረው ሆስፒታል ያለውን የቁሳቁስና የጽዳት፣ እንዲሁም የአልባሳትና ተመሳሳይ ችግሮች ሳያነሱ፣ ከሰውነት ደረጃ በወረደ የሚፈጸመውን ጉድ “ህሊና” ያላቸው ወገኖች እንዲያውቁት እንደሚከተለው አቅርበነዋል።

ለአማኑኤል የአዕምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ግንባታ ከኮንትራት ውጭ 82 ሚሊየን ተከፈለ

የሚያሳዝነው አማኑኤል ሆስፒታልን ያዩ “ባለሃብቶች፣ ታዋቂ የሚባሉ የጊዜው ባሮች፣ ሃብት ካፈሩ በኋላ መሬት ለቆለሉት ሃብት ሲሉ የሚልከሰከሱ “ወገኖች” እንዲሁም ያደፈ ጓዳቸውን ተሸክመው በሚዲያ የሚዘመርላቸው “ለጋሶች” ለመሆኑ የት ናቸው?” ተብሎ ቢጠየቅ መልሱ ምን ይሆን? ለሁሉም ሙሉ መረጃውን እነሆ!

የተዘነጋው አማኑኤል የአዕምሮ ህሙማን ሆስፒታል!

  • አንድ መቶ ሚሊዮን ህዝብ አላት ተብሎ በሚገመተው ኢትዮጵያ አንድ ብቸኛ የአዕምሮ ህሙማን ሆስፒታል አላት!

  • አማኑኤል ሆስፒታል 70 ዓመት የአገልግሎት ጊዜ አለው፡፡ ሦስት መቶ አስር አልጋዎች ብቻ አሉ!

  • አማኑኤል ሆስፒታል ውስጥ አልጋ ለማግኘት አስታማሚዎች እስከ 40,000 ሺህ ብር ድረስ ለህክምና ቡድኑ ሙስና ይከፍላሉ!

በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመን 1939 ዓ.ም. የተመሰረተው አማኑኤል ሆስፒታል፤ ለአገሪቱ አንድ ለእናቱ የሚል ስያሜ ያለው የአዕምሮ ህሙማን መታከሚያ ማዕከል ነው፡፡ “የአገሪቱን የጤና ሽፋን መቶ ፐርሰንት አድርሻለሁ” እያለ የሚመፃደቀው ህወሓት ከከፍተኛ ክሊኒክ እና ከሆስፒታል በተለይም በጤና ተቋማቱ ትኩረት የሚሹ የህመም ዓይነቶችን በመለየት የሚደረገው የህክምና ጥረት ሲፈተሽ የ“መቶኛ” ስሌቱ ፕሮፖጋንዳ ራቁቱን ይቀራል፡፡

ከዓለም አገራት ምድረ-ገጽ የጠፋው ኮሌራ ኢትዮጵያ ውስጥ “አተት” የሚል የዳቦ ሥም ተሰጥቶት ዛሬም ድረስ ምስኪኑን እያጨደና እያሰቃየ ነው፡፡ ከበሽታ መዝገበ ቃላት የተፋቀው ኳሺዎርኮር (ወይም በተምዶ ኳሻኳር/kwashiorkor) ኢትዮጵያ ውስጥ የነበረ፣ ያለና ወደፊትም የሚኖር ልዩ ገጸ በረከት ነው፡፡ “ካላዛር” የተባለው ገዳይ ቫይረስም በአገሪቱ ቆላማ ክፍሎች በተለይም በሰሜን ምዕራብ አካባቢ ከወባ በሽታ በላይ ገዳይ ሆኗል፡፡ በአሺሽ፣ ሺሻ፣ ጫትና መሰል የሱስ ዓይነቶች የናወዘ ትውልድ ያፈራው የህወሓት/ኢህአዴግ አገዛዝ በአገሪቱ አንድም ቦታ የሱስ ማገገሚያ ተቋም (Rehab Center) እንኳ የለውም፡፡ የአገሪቱን የጤና ችግሮች በአንድ ፅሁፍ ዘርዝሮ መጥቀስ ስለማይቻል፣ ከዓለም በተለየ መልኩ እኛ ላይ የሰለጠኑትንና የበረቱትን በሽታዎች ከብዙ በጥቂቱ ለመጠቆም ያህል ከላይ ያነሳናቸው ለጊዜው ማሳያ ይሆናሉ።

የዓለም ስጋት የሆነው የካንሰር ጉዳይ በኢትዮጵያ ፍፁም የተዘነጋ ይመስላል፡፡ በየዓመቱ ከዓለም የጤና ድርጅት ካንሰርን በተመለከተ የሚሰጠው የእርዳታ ብር የት እንደሚገባ አይታወቅም፡፡ የህክምና ባለሙያዎች እንደሚሉት የካንሰር ህመም ዓይነቶች 16 ይደርሳሉ፡፡ ኢትዮጵያ ውሰጥ የካንሰር ህሙማን ማስተናገጃ ልዩ ማዕከል አለመኖሩ ሳይሆን የሚደንቀው፤ የካንሰር ህሙማን በአዲስ አበባ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ብቻ መስተናገዳቸው፣ ለህሙማኑ ተለይተው የተዘጋጁ አልጋዎች ብዛት 20 ብቻ መሆናቸው፣ አገሪቱ ውስጥ አለ የሚባለው የጤና ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ሥራ ላይ መሆኑን ብንጠራጠር ታዛቢና ተከራካሪ ይኖራል ብለን አናስብም። ሌሎችንም ችግሮች መጥቀስ ይቻላል።

ከሁሉ በላይ ግርምት የሚጭረው ጉዳይ በCIA Book Fact መረጃ መሰረት አንድ መቶ ሚሊዮን ህዝብ አላት ተብሎ በሚገመተው ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ብቸኛ የአዕምሮ ህሙማን ማስተናገጃ ሆስፒታል ያላት መሆኑ ነው፡፡ “አማኑኤል ሆስፒታል ሰባ ዓመት የአገልግሎት ጊዜ አለው፡፡ ሆስፒታሉ ብቸኛ የአዕምሮ ህሙማን ማስተናገጃ ቢሆንም ሦስት መቶ አስር አልጋዎች ብቻ ነው ያሉት፤ በየቀኑ ግን ከ720 እስከ 1250 የሚደርሱ ተመላላሽ የአእምሮ ህመም ታካሚዎችን ያስተናግዳል” የሚለን የሆስፒታሉ የህክምና ባለሙያ ሆስፒታሉ ከፍተኛ የሆነ በዘርፉ የሰለጠኑ የአዕምሮ ህክምና ባለሙያዎችና የህሙማን ማስተናገጃ የአልጋ እጥረት እንዳለበት አመልክቷል።

ወ/ሮ ፋጡማ ሐሰን (ስማቸው ለዘገባው የተቀየረ) ከደሴ ከተማ የመጡ አስታማሚ ናቸው፡፡ በሃያዎቹ አጋማሽ ዕድሜ ላይ የምትገኝ የአዕምሮ ህመምተኛ ልጅ አለቻቸው፡፡ ልጃቸው በ2006 ዓ.ም. የሳውዲ አረቢያ መንግስት ኢትዮጵያዊያን ስደተኞችን “ህገ-ወጥ” በሚል በግፍ ሲያባርር የሰራችበትን ደመወዝ እንኳ ሳታገኝ ባዶ እጇን የተመለሰች ኢትዮጵያዊት ነች፡፡ በወቅቱ ስትመለስ ከፍተኛ የሆነ የመንፈስ ጭንቀትና መረበሽ የነበረባት ቢሆንም፣ የአዕምሮ ህመሟ አሁን ባለበት ደረጃ አልነበረም፡፡ “በሂጃብ ፊቷን የሸፈነች ሙስሊም ሴት ባየች ቁጥር ‹ብሬን! ብሬን! . . . › እያለች ትጮኻለች” የሚሉት የወጣቷ አስታማሚ እናት ወ/ሮ ፋጡማ ብቸኛ ልጃቸውን ለማስታመም ከወልዲያ አዲስ አበባ ከመጡ ሁለት አመት እንዳለፋቸው ይናገራሉ፡፡

ወልዲያ ውስጥ መለስተኛ የሸቀጣሸቀጥ ሱቅ ያላቸው እኚህ እናት፤ በልጃቸው የአዕምሮ ህመም የተነሳ ከባለቤታቸው ጋር ተለያይተው ልጃቸውን በተመላላሽ ታካሚነት አማኑኤል ሆስፒታል ያስታምማሉ፡፡ በተለምዶ ሰባተኛ የሚባለው ሰፈር አነስተኛ ቤት ከተራይተው ልጃቸውን ሲጠብቁ ይውላሉ፡፡ በየአስር ቀኑ ልዩነት ልጃቸውን ይዘው አማኑኤል ሆስፒታል ይመላለሳሉ፡፡ “ከልጄ ውጭ ህይወቴ ባዶ ነው” የሚሉት እናት፤ በራሳቸው እውቅና ልጃቸውን ወደ ሳውዲ አረቢያ መላካቸውና በሰላምና በጤና የሄደችው ልጃቸው ዛሬ ላይ የአዕምሮ ህመምተኛ መሆኗ ለፀፀት እንደዳረጋቸው ሳይሸሽጉ ለጎልጉል ተናግረዋል።

“አልጋ የለም!” በሚለው የሆስፒታሉ ምላሽ የተነሳ ሁለት ዓመት ሙሉ አዲስ አበባ ልጃቸውን ይዘው በተስፋ የተቀመጡት የወልዲያዋ እናት፣ የአካባቢው ሰው ችግራቸውን ተረድቶ በተለይም ሙስሊሞች ‹ዘካ› በማውጣት የቤት ኪራይ፣ ቀለብና የመድሃኒት ወጪያቸውን ለወራት ያህል ቢችሏቸውም ልጃቸው አማኑኤል ሆስፒታል ተኝታ ክትትል እንዲደረግላት ማድረግ አልተቸለም፡፡ 24 ወራት ሙሉ “አልጋ የለም!” የሚለው የአገሪቱ ብቸኛው የአዕምሮ ህሙማን ሆስፒታል አቅም ያላቸው አስታማሚዎች ለአዕምሮ ህመምተኛ ዘመዶቻቸው አልጋ ለማግኘት እስከ አርባ ሺህ ብር ድረስ ለህክምና ቡድኑ ሙስና እንደሚከፍሉ የሆስፒታሉ የጎልጉል የመረጃ ምንጮች ጥቆማቸውን ያቀርባሉ።

“አማኑኤል ሆስፒታል ውስጥ ያለው አልጋ ሆስፒታሉ በየቀኑ ከሚያስተናግዳቸው የአዕምሮ ህሙማን ብዛት አኳያ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም” የሚሉት የሆስፒታሉ የመረጃ ምንጮቻችን “አስታማሚዎች በየቀጠሮው ከመመላለስና የአእምሮ ህመምተኛውን ቤት ውስጥ ከመጠበቅ ሆስፒታሉ ውስጥ አልጋ ፈልጎ እንዲታከም ማድረግ ይመርጣሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ አልጋ ውድ በመሆኑ በአቀባባዮች በኩል አልጋ ለሚፈቅደው የህክምና ቲም የተጠየቁትን መክፈል አቋራጭ መንገድ ሆኗል” ሲሉ ሰብዓዊነት የጎደለውንና ሰሚ ያጣውን ግዙፍ ችግር ያስረዳሉ።

“አማኑኤል ሆስፒታል ውስጥ አንድ የአእምሮ ህመምተኛ አልጋ ይዞ ክትትል እንዲደረግለት የሚያስችል ወጥ የአሠራር ህግና ደንብ የለም፡፡ ከዚህ በፊት ከተመላላሽ የአዕምሮ ህመምተኞች ውስጥ የባሰበት ህመምተኛ የታካሚውን ‹ቻርት› በያዘው ሐኪም ትዕዛዝ አልጋ ተፈልጎ እንዲሰጠው ይደረግ ነበር” የሚሉት የመረጃው ባለቤቶች፣ ይህ አይነቱ አሰራር በዘመድ፣ በእውቅና እንዲሁም ጠቀም ባለ ገንዘብ (ሙስና) አልጋ እንደሚሰጥ የሆስፒታሉ አስተዳደር የደረሰበት በመሆኑ ከ2007 ዓ.ም. ጀምሮ ለአንድ የአዕምሮ ህመምተኛ አልጋ እንዲሰጠው የሚታዘዘው በኮሚቴ (በህክምና ቡድን/ቲም) ውሳኔ መሆኑን ይገልፃሉ፡፡ ይሁንና “ይህ አይነቱ አሰራር አስታማሚዎች አልጋ ለማግኘት የሚከፍሉትን የሙስና (ብር) መጠን ጨመረው እንጂ መፍትሔ አልሰጠም” በማለት የችግሩን በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ መሆን ያመላክታሉ፡፡

አማኑኤል ሆስፒታል ውስጥ አልጋ ይዘው ክትትል የሚደረግላቸው የአዕምሮ ህሙማን ተንከባካቢዎቻቸውና አስታማሚዎቻቸው ነርሶች እንጂ ቤተ ዘመድ አይደለም፡፡ የቤተሰብ አባላት በሳምንት በተፈቀደላቸው ቀናት በነርሶች አጋዥነት (እንደአዕምሮ ህመምተኛው የጤና ሁኔታ) እንዲጠይቁ ይፈቀድላቸዋል፡፡ ከዚያ በተረፈ ያለው የማስታመምና የመንከባከብ ጉዳይ ለሆስፒታሉ የህክምና ክፍል የተተወ መሆኑን የመረጃ አቀባዮቻችን ይገልፃሉ፡፡

ለጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ መረጃ የሰጡ እንደሚሉት አማኑኤል ሆስፒታል ውስጥ አልጋ ተሰጥቷቸው የህክምና ክትትል የሚደረግላቸው የአዕምሮ ህሙማን በሁለት ይከፈላሉ፡፡ “ቅባት” እና “ደረቅ” ይሏቸዋል፡፡ “ቅባት” የሚባሉት የአዕምሮ ህሙማን አስታማሚዎቻቸው ለህክምና ቡድኑ ገንዘብ (ሙስና) በመክፈል አልጋ እንዲይዙ የተፈቀደላቸው ሲሆን፤ “ደረቅ” የሚሏቸው ደግሞ ለዓመታት ወረፋ በመያዝ በብዙ ደጅ ፅናት ያለሙስና አልጋ እንዲያገኙ የተደረጉ የአዕምሮ ህመምተኞችን ነው፡፡ ሆስፒታሉ ውስጥ የሚደረገው የህክምና እንክብካቤም ቢሆን እንደአዕምሮ ህሙማኑ አገባብ የተለያየ ነው፡፡

በቅርብ ጊዜ ቋሚ ሥራዋን ለቃ የወጣችው ነርስ “የህክምና ሙያ ላይ ይፈፀማል ተብሎ የማይገመት ክህደት ሆስፒታሉ ውስጥ ይከናወናል” ስትል ለጎልጉል አስተያየቷን የሰጠችው በምሬት ነው፡፡ “የተሻለ የኢኮኖሚ ደረጃ ላይ ያሉ የቤተሰብ አባላት ያላቸው የአዕምሮ ህሙማን በሆስፒታሉ ውስጥ ልዩ እንክብካቤ ይደረግላቸዋል” የምትለው ነርስ፤ “የአዕምሮ ህሙማኑ በህክምና ቲም በኩል ክትትል የሚደረግላቸው በመሆኑ የቤተሰቡ አባላት ለህክምና ቲሙ ጠቀም ያለ ገንዘብ የሚሰጡ ከሆነ ለአዕምሮ ህመምተኛው የሚደረገው የህክምና ክትትል የተለየ ይሆናል” ስትል በአገልግሎት ጊዜዋ በሆስፒታሉ ውስጥ የታዘበችውን የህክምና ሙያ ክህደት ትናገራለች፡፡ አማኑኤል ሆስፒታል ውስጥ የሚፈፀመው ሙስና አልጋ በመስጠትና በመከልከል ብቻ የተገደበ አይደለም፡፡ አልጋ የተሰጣቸው የአዕምሮ ህሙማን በሆስፒታሉ ቆይታቸው ልዩ እንክብካቤ እንዲደረግላቸው በአቀባባዮች በኩል በየጊዜው ለህክምና ቲሙ እጅ መንሻ ማቅረብ ግድ ይላል፡፡

አቶ አዲስ ይርጋ (የባለ ታሪኩ የተቀየረ ስም) የሁለት ልጆች አባት ናቸው፡፡ በንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩት እኚህ አባወራ፤ ባለቤታቸው በአሰቃቂ የመኪና አደጋ የአዕምሮ ህመምተኛ ሆነው አማኑኤል ሆስፒታል ከገቡ 8 ወር ሆኗቸዋል፡፡ ከአንድ አመት በፊት ባለቤታቸው ላይ በደረሰው የመኪና አደጋ ለህክምና ከክፍለ ሃገር የመጡት የባለቤታቸው እናት በአደጋው ሲሞቱ፤ መኪናውን ያሽከረክሩ የነበሩት የአቶ አዲስ ባለቤት ከባድ ጉዳት ደረሰባቸው፡፡ ከአደጋው በኋላ በወራት ልዩነት ከአካል ጉዳታቸው ያገገሙት የአቶ አዲስ ባለቤት በአደጋው አሰቃቂነት የተነሳ የአዕምሮ ህመምተኛ ሆኑ፡፡ ከአዕምሮ ህመማቸው ጋር በተያያዘ ማንኛውንም ተሽከርካሪ (መኪና) ባዩ ቁጥር መጮህና ራስን መሳት የወ/ሮዋ ባህሪ ሆነ፡፡ ከአዕምሮ ጭንቀታቸው በተጨማሪ የህክምና ባለሙያዎች “Panic Disorder” የሚሉት የመረበሽ ህመም በአቶ አዲስ ባለቤት ላይ ተፈጠረ፡፡

“በቤተ ዘመድ ምክረ – ሐሳብ አማኑኤል ሆስፒታል መውሰድ ግድ ሆነብኝ” የሚሉት አቶ አዲስ፤ የባለቤታቸው የአዕምሮ ህመም በተመላላሽ ታካሚነት በተለይም ተሽከርካሪ እያዩ በተሽከርካሪ ውስጥ መጓዝ የማይቻል በመሆኑ “አልጋ መፈለግ ግዴታ ሆነ” ይላሉ፡፡ በዚህ ጊዜ ነበር አማኑኤል ሆስፒታል ውስጥ ተመላላሽ የአዕምሮ ህክምና ክፍል ውስጥ ያሉ “አቀባባይ ነርሶች” ያገኟቸው፡፡ “ከልጆቼ እናት የሚበልጥ ነገር የለም ብዬ የተጠየኩትን አርባ ሺህ ብር ከፈልኩ፡፡ ከአንድ ሳምንት በኋላ አልጋ መገኘቱን ደውለው ነገሩኝ” በማለት ገጠመኛቸውን ለጎልጉል ሲገልጹ ስሜታቸው መጎዳቱ ሊሸሸግ በማይችልበት ሁኔታ ነው። “ነጋዴ ነኝ፤ ስለ ሙስና መስማትም ሆነ መስጠት ለእኔ እንግዳ ነገር አይደለም፡፡ ሆስፒታል ውስጥ ያውም የአዕምሮ ህሙማን በሚስተናገዱበት ቦታ ግን እንዲህ ያለው ሞራል የሚነካ ሙስና ይኖራል ብዬ አልገምትም ነበር” በማለት በገጠመኙ መደናገጣቸውንና ማፈራቸውን ይገልፃሉ፡፡

“ባለቤቴ በሐኪም ትዕዛዝ ከሚሰጣት ታብሌትና መርፌ በተጨማሪ ተከታታይነት ያለው የሳይካትሪስት ክትትል የሚያስፈልጋት በመሆኑ ለሳይካትሪስቱና በየዕለቱ ለሚንከባከቧት ነርሶች በየጊዜው ስጦታ መውሰድ እንደግዴታ ሆኖብኛል” ይላሉ፡፡ በህክምና ሙያ ውስጥ ህሙማንን በዘር፣ በኃይማኖት፣ በፆታ፣ በኢኮኖሚ፣… ደረጃ ሳይከፋፍሉ ያለአንዳች መድሎ ተገቢ የሆነ ክትትልና ድጋፍ መስጠት የሙያው ሰዎች በቃለ-መሐላ የተደገፈ ሙያዊ ግዴታ ቢሆንም የአዕምሮ ህሙማን በሚስተናገዱበት አማኑኤል ሆስፒታል ውስጥ ግን እውነታው የተለየ ነው፡፡ እያንዳንዱ የህክምና ክትትልና ድጋፍ ከሙያ ግዴታ አኳያ ሳይሆን ከንዋይ ጉርሻ (ሙስና) ጋር በተያያዘ የሚከናወን ነው።

የተሻለ የኢኮኖሚ ደረጃ ላይ ያሉ የአዕምሮ ህሙማን ቤተሰቦች የህሙማኑን ልደት በሆስፒታሉ ግቢ ውስጥ ለማክበር እስከ 20,000 ብር ድረስ ወጪ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ “አንዳንድ የአዕምሮ ህሙማን ቤተሰብ አባላት ህመምተኛውን ለማስደሰትና ወደ ቀድሞ ትዉስታዉ ለመመለስ የአዕምሮ ህመምተኛውን ልደት ማክበር የተለመደ ነው” የሚሉን የመረጃ ምንጮቻችን “ልደቱን ለሚያስተባብሩት (ለሚያዘጋጁት) ነርሶች እስከ 20,000 ብር ድረስ መስጠት ግድ ይላል፡፡ በቶርታ ኬክና በለስላሳ መጠጦች ለሚከበረው የአዕምሮ ህሙማኑ ልደት፤ ልደቱን የሚያዘጋጁት ነርሶች ‹ይህን ያህል ገንዘብ ወጪ ያስፈልጋል› በማለት የህሙማኑን ቤተሰብ ኪስ ይበዘብዙታል” ይላሉ፡፡ ባልተፃፉ በርካታ ሕግጋት በሚመራው አማኑኤል ሆስፒታል፤ “በቅርበት የሚከታተል ቤተሰብ የሌላቸው የአዕምሮ ህሙማን በህክምና ቲሙ ስምምነት ከሆስፒታሉ እንዲወጡ ይደረጋል፡፡ በተለቀቀው አልጋ ‹ቅባት› የሆነ የአዕምሮ ህመምተኛ ከተገኘ ቅድሚያ ይሰጠዋል” የሚሉት የጎልጉል ምንጮች የከተማዋ ጎዳናዎች ላይ ለሚታዩት የአዕምሮ ህሙማን መበራከት ይህ አይነቱ ኃላፊነት የጎደለው የህክምና አስተዳደር የራሱ የሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳለው አስተያየታቸውን ይሰጣሉ

ወዴት እየሄድን ነው?  Read more on goolgule