Wednesday, 10 May 2017 13:13

 የሚዲያ ኢንዱስትሪ፣ ተራ የንግድ ዘርፍ አይደለም፤ በርካታ ባለድርሻ አካላትን ያካተተ ነው። በተለያዩ ፍላጎቶች የታጨቀ ዘርፍ ከመሆኑም በላይ፣ የሚያሳርፈው ተፅዕኖ በቀላሉ የሚገመት አይደለም። የአንድን ሕብረተሰብ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማሕበራዊ መሰረቶችን በመገንባትም በማፍረስም እኩሌታ ያለው ኢንዱስትሪ ነው።

ኢንዱስትሪው በተለይ፣ የተረጋጋና ቀጣይነት በሌለው የዴሞክራሲ ሒደት በሚናጡ ሀገሮች ላይ የበረታ ተፅዕኖ እንዳለው በስፋት ይታመን ነበር። በተመሳሳይ ሁኔታ ሚዲያው፣ ዴሞክራሲያዊ መሰረታቸውና ተቋማዊ አደረጃጀታቸው ከፍተኛ ደረጃ በደረሰባቸው ሀገሮች ላይም፣ የበረታ ተፅዕኖ እንደሚያሳርፍ ብዙ አብነቶች ማቅረብ ይቻላል። 

በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚዲያ ደኅንነትን በተመለከተ ሪፖርት የሚያቀርቡ የተለያዩ ሀገሮች ተቋማት በርካታ ናቸው። እነዚህ ተቋማት ከሚያወጡት ሪፖርት ጋር በተያያዘ፣ ከተለያዩ ሀገሮች ጋር ያለመተማመን፣ አንዳንዴም የመጋጨት ሁኔታዎች ይስተዋላሉ። የአብዛኞቹ ተቋማት ሪፖርቶች፣ ተቋማቱን ስፖንሰር ከሚያደርጉ አካላት ፍላጎት ጋር የተጣባ ነው፤ የሚል ክስ ይሰማል። በተለይ፣ የኒዮሊብራል ፖለቲካ ኢኮኖሚ አቀንቃኞች ጠንካራ ተጽዕኖ ሥር ወድቀዋል፤ የሚለው ተደጋግሞ የሚሰማ አቤቱታ ነው።

ከእኛ ሀገር ተጨባጭ ሁኔታ ጋር በተገናኘ፣ ባለፈው ወር ፍሪደም ሃውስ የተባለ ተቋም፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ሚዲያን በተመለከተ ያለውን ከባቢያዊ ሁኔታ ይገልፃል ያለውን ሪፖርት አስነብቧል። ተቋሙ በሪፖርቱ፤ ከኢኮኖሚ፣ ከፖለቲካ፣ ከህግ አንፃር ያለውን ምኅዳር አስመልክቶ በራሱ መለኪያ የገመገማቸውን ሁኔታዎች በዝርዝር አስቀምጧል። ተቋሙን ማን እንዳቋቋመው፣ ለምን እንደተቋቋመም ብዙ ማጣቀሻዎች አንስቶ ማሳየት ይቻላል። ከተቋሙ አፈጣጠር ጋር በተያያዘ፤ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በተደጋጋሚ በሚያወጣቸው ሪፖርቶች አለመተማመን ብቻ ሳይሆን፣ ከኒዮሊብራል አክራሪ የገበያ አራማጅ ኃይሎች ጋር የተቆራኘ ነው፤ የሚል ክስም ይቀርብበታል። በተቋሙ እና በኢትዮጵያ መንግስት መካከል ያለው አለመተማመን እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ተቋሙ፣ በሪፖርቱ ላይ ያሰፈራቸው ነጥቦች ሙሉ ለሙሉ ሃሰት ነው፤ ከሚል ድምዳሜ ላይ አያደርስም። ሆኖም ግን አጠቃላይ ከባቢያዊ ሁኔታን፣ ተቋሙ፣ በራሱ መነሻ ባስቀመጣቸው ማሳያዎችና መለኪያዎች ብቻ በኢትዮጵያ የሚዲያው ምኅዳር ሙሉ ለሙሉ በአስቸጋሪ ሁኔታዎች እንደተከበበ አድርጐ በጨለምተኝነት ድምዳሜ መስጠቱ፣ የሪፖርቱን ሚዛናዊነት ጥያቄ ውስጥ ይጥለዋል።

ይህም ሆኖ በዚህ ጽሁፍ ማንሳት የተፈለገው፣ በፕሬስ ነፃነት መብት ተሟጋቾች እና በኢትዮጵያ መንግስት ባለሥልጣናት መካከል በየዓመቱ የሚስተዋለውን አለመተማመንና ምልልስ ሳይሆን፤ በተለያዩ መድረኮች፣ ስለነፃው ፕሬስ በአስፈፃሚው በኩል የሚሰጡ ገለፃዎች እና ድምዳሜዎች አሁን ካለው ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር ተገቢነታቸው ምን ያህል ነው? የሚለውን ለመፈተሽ ነው። በየዓመቱ ሚያዝያ 25 በሚከበረው የፕሬስ ነፃነት ቀን በዓል ላይ፣ መንግስት በተለይ የግል ፕሬሱን በተመለከተ ያለው አተያየት የግል ፕሬሱ የሕገመንግሥታዊ ሥርዓቱ አደገኛ የአመፅ ኃየል እንደሆነ በተደጋጋሚ በሚያቀርበው ክስ የተቸነከረ ሆኖ ተገኝቷል።

መንግስት ይህን ክስ ለማቅረብ ምንም መነሻ የለውም፤ ብሎ መከራከር አይቻልም። ሚዲያውን በመጠቀም መንግስትን የህዝብ ቅቡልነት እንዳይኖረው የሚሰሩ ፕሬሶች ነበሩ። አከራካሪው ነጥብ ግን፣ ሁሉንም ፕሬሶች በዚህ ማሕቀፍ ውስጥ  አጠቃላይ የግል ሚዲያው መገለጫ አድርጎ ማቅረቡ ነው። ከዚህም በላይ፤ አጠቃላይ የፕሬሱ መገለጫ አደርጎ ያስቀመጠውን ድምዳሜ፣ ዛሬም እንደ ዳዊት መድገሙ፣ መንግስት ለነፃው ፕሬስ እድገት ያለውን ሚዛናዊ እይታ ጥያቄ ውስጥ የከተተ አቀራረብ ተደርጎ ተወስዷል።

ነፃው ፕሬስ፣ ከመንግስት የሥርዓት ለውጥ ጋር ተያይዞ የዳበረ የሙያ ዘርፍ ነበር። ሆኖም ግን፣ በወቅቱ አዲስ መንግስት ሆኖ በመጣው ኢሕአዴግ እና ከመንግስት ስልጣን የተወገዱት የኢትዮጵያ ሠራተኞች ፓርቲ ልሂቃን መካከል በነበረው የሽግግር ሂደት፣ የግሉ ፕሬስ ከሚጠበቅበት ሞያዊ ሥነ ምግባር በእጅጉ ባፈነገጠ መልኩ፤ የጦዘ ፖለቲካ መጫወቻ ሜዳ ሆኖ እንደነበረ፣ ሁኔታውን የገመገሙ የዘርፉ ባለሙያዎች ጥናቶች ያሳያሉ። በድምር ውጤቱም፣ በመንግስት አስፈፃሚዎች እና በፕሬሱ መካከል፣ አለመተማመን እስከ አሁን ዘልቆ ይስተዋላል። የግሉ ፕሬስ፤ “ሕገመንግስታዊ ሥርዓቱን በአመጽና በኃይል ለመናድ የሚሰራ ኃይል ነው”  የሚለው የመንግሥት አተያይና አረዳድ የዚያ አለመተማመን መገለጫ ነው።

አስፈፃሚው አካል የግል ፕሬሱን ይዞታ የሚተነትንበት ሌላው አተያይ፤ ከፖለቲካ ኢኮኖሚ አንፃር መሆኑ አሻሚ አይደለም። ይኸውም፣ “የግል ፕሬሱ የኒዮሊብራል ፖለቲካ ኢኮኖሚ አቀንቃኞች ወይም ተላላኪዎች ናቸው፤” የሚለው ክስ ነው። ይህም ክስ፣ በርካታ የግሉ ፕሬስ እንቅስቃሴዎች መነሻ ከአክራሪ የገበያ ሥርዓት አራማጆች ነው፤ ከሚል ድምዳሜ አድርሶታል። በግሉ ፕሬስ ላይ የሚመሰረቱ ክሶች፣ ከፍሬ ነገራቸው በበለጠ፣ ይኽው የመንግስት አመለካከትና ድምዳሜ የተጫናቸው ናቸው፤ በማለት ክሶቹን የመብት ተሟጋቾች አይቀበሏቸውም።   

   የግሉ ፕሬስ የሚከሰስባቸው፣ “ሕገመንግስታዊ ሥርዓቱን በአመጽና በኃይል ለመናድ” እና “የገበያ አክራሪ ኃይሎች ተላላኪ” የሚሉት ሐረጎች፣ አሁን ካለው ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር ተገቢነታቸው አጠያያቂ ነው። አጠያያቂነታቸው የሚጀምረው፣ ገዢው ግንባር ራሱ፣ በአደባባይ አምኖ እንደተናገረው፤ ሕገመንግስታዊ ሥርዓቱን በአመጽና በሃይል ለመናድ የሚንቀሳቀሱ ሃይሎች አስቻይ መንገድ ያገኙት ገዢው ፓርቲ፣ መልካም አስተዳደርን ለማስፈን ቁርጠኛ እርምጃ ባለመውሰዱና የኪራይ ሰብሳቢ ፖለቲካ ኢኮኖሚ በሥርዓቱ ውስጥ የበላይነት በመያዙ እንደሆነ በተደጋጋሚ ጊዜ ይፋ ማድረጉ ነው።

ለመልካም አስተዳደር እጦት እና ለኪራይ ሰብሳቢ ፖለቲካ ኢኮኖሚ ማገንገን ተጠያቂዎቹ፣ የገዢው ፓርቲ የፖለቲካ አመራሮች ናቸው። በተለይ ሕገ መንግስታዊ ሥርዓቱ እንዲቀነጠስ፣ ከፍተኛውን ሚና እየተጫወቱ የሚገኙት፣ በገዢው ፓርቲ ውስጥ የተሰገሰጉ የኪራይ ሰብሳቢ ፖለቲካ ኢኮኖሚ የበላይነት እንዲይዝ የሚተጉ ካድሬዎች ናቸው። የገዢው ፓርቲ አንዳንድ ካድሬዎች በዚህ መልኩ ሥርዓቱን እንደቅንቅን እንዲበሉት፣ የግል ፕሬሱ አስተዋጽዖ ምን ነበር ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው፤ መልሱም ምንም የሚል ነው። በአንፃሩ፣ እነዚህ በገዢው ፓርቲው ውስጥ የመሸጉ ኃይሎች፣ የግሉ ፕሬስ ለተጠያቂነት ወደ ብርሃን እንዳያጋልጣቸው፣ ዛሬም ድረስ፣ “ሕገመንግስታዊ ሥርዓቱን በአመጽና በኃይል ለመናድ የሚሰራ ኃይል” ነው እያሉ በአደባባይ ሲከሱ ይደመጣሉ።

በሌላ በኩል፣ ገዢው ፓርቲ የሚያራምደው የ“ዴሞክራሲያዊ ልማታዊ መንግስት” ፖለቲካ ኢኮኖሚን፣ ከፅንሰ ሃሳቡ እስከ አተገባበሩ ድረስ ተፈፃሚ እንዳይሆን በርግጥ፣ የግሉ ፕሬስ አሁን ላይ አቅም አለው ብሎ መውሰድ ይቻላል? የአክራሪ የገበያ ሥርዓት አራማጅ ሀገሮች ፍላጎታቸውን ለማራመድ፣ የግል ፕሬስን በዋና መሣሪያነት ይጠቀማሉ ብሎ ማሰብ ተገቢነቱ ምን ያህል ነው? ገዢው ፓርቲ የኢንዱስትሪ ፓርክ እየገነባ በአደባባይ እባካችሁ ኑ እያለ የሚለምናቸው ከበርቴዎች ውግንናቸው ከማን ጋር ነው? ገዢው ፓርቲ የሀገር ውስጥ ባለሃብቶችን እያበቃ ወደ ኢንዱስትሪ ፓርክ ማሸጋገር የሚገባውን ሥራ ከመዘንጋት በላይ፣ የግል ፕሬሱ ለገበያ አክራሪ ኃይሎች ተላላኪ ቢሆን እንኳን፣ ከገዢው ፓርቲ የኢኮኖሚ ባለሟሎች በላይ እንዴት ተላላኪ ሊሆን ይችላል?

የግሉ ፕሬስ፣ “ሕገመንግስታዊ ሥርዓቱን በአመጽና በኃይል ለመናድ” እና “ለአክራሪ የገበያ ኃይሎች ተላላኪ” ተደርጎ ከጅማሮ እስካሁን ድረስ በአስፈፃሚው አካል የተቀመጠው ድምዳሜ የተቸነከረ በመሆኑ፣ መከለስ አለበት። በሀገሪቷ ሕግ ተመዝግቦ የሚሰራ መሆኑ መዘንጋት አይገባም።

ስንደቅ