May 17, 2017 05:50

መስቀሉ አየለ

ፕሮፌሰር አስራት
ፕሮፌሰር አስራት ወንጀለኛ ተብለው በእኩያን ሸንጎ በቀረቡ ግዜ ሁሉየእውነትን ሰይፍ እንደታጠቁ ግርማ ሞገሳቸው አፍ አውጥቶ ይናገር ነበረ።እርሳቸው የጫማቸውን ሶል ያህል ክብር በሌላቸው ሰዎች ፊት ባልተለመደ ሁኔታ በመቶዎች ለሚቆጠር ግዜ በፍትህ ስም ችሎት ቀርበዋል።አስገራሚው እና ሂደቱን አስቸጋሪ ያደረገው እርሳቸው ከመነሻው የተከተሉት አቀራረብ ነበር።
እርሳቸው እንደማንም ተራ ሰው የተከሰሱበትን የፈጠራ ወንጅል አልካዱም። ወይንም ደግሞ የሰሩትን ስራ ሁሉ “ወንጀል” ነው ብለው አልተከላከሉም፥፥ ወይም ይቅርታ አልጠየቁም። ያሉት ነገር “የሰራሁት ሁሉ ለሃገሬ ለህዝቤ መልካም የሆነውን ነገር ነው ” ነው ያሉት። ባጭሩ ወንጀልን በወንጀልነቱ አልተከላከሉትም ወይም ጥፋት ነው ብለው ይቅርታ አልጠየቁበትም ።ይኽ ማለት ብዙ ያልተለመደ አካሄድ ነው።በመጨረሻም በድፍን አዲስ አበባ እርሳቸው ላይ ደፍሮ የሚፈርድ ዳኛ ሲጠፋ መደበኛ ስራው በአክሱም የነበረ ሃጎስ የተባለ የሰሜን ቀያፉ ከአክሱም በቻርተር አውሮፕላን አዲስ አበባ እንዲገባ ተደርጎ መውጫና መግቢያን እንኩዋን በቅጡ በማያውቀው ፍርድ ቤት ውስጥ “ተሰየመ” ተባለና ይዘቱን ለደቂቃ ገልጦ ሳያይፋይል “በተከሰሱበት ወንጀል ጥፋተኛ ሆነው ስለተገኙ ይሄን ያህል አመት ጽኑ እስራት ተፈርዶባቸዋል; መኖና ህክምና ባለበት ይቀመጡ; መዝገቡንም ዘግተን መልሰናል የሚል ነበር።
በሽኮኮ ችሎት ሲተራመስ የኖረው አሳፋሪ የካድሬ ችሎት በዚህ መልኩ ተጠናቀቀ ተባለና እርሳቸውም ወደ ማረሚያ ቤት ወርደው በእስር ሲማቅቁ ኖረው ከጀርባ በተሰራ የእጀሰብ ወንጀል በክፉ ደዌ እንዲለከፉ በተሰራው የተጠና ስራ በሃኪም እጅ እንዲወድቁ ግድ ቢላቸውም እራሳቸው ቆመው ባሰሩት፣ቆመው ባቀኑት፣ ዘመናቸውን ሁሉ ደክመው ስንት ምሁራን ባፈሩበት ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል እንኩዋን የመታከም እድል ተነፍገው ኖረው በመጨረሻም በሞትና በህይወት መካከል በሆኑ ግዜ እስር ቤት እንዳሉ ህይወታቸው ቢያልፍ እፉኝቶቹ ለሚያራምዱት ፖለቲካ የሚረዳ አለመሆኑን ከጥንስሱ የሚያውቀው ብቻ ሳይሆን የሴኪዩሪቲ የምክር አገልግሎት የሚሰጠው እንግሊዝ የተባለ ተውሳካም መንግስት ሽማግሌ መስሎ ቀርቦ ከእስር እንዲፈቱ አደረገና እለቱን ከአገር ወጡ።
ያን ቀን አረጋዊው ፕሮፌሰር ያን ቀን በማንም ህሊና ውስጥ ለዘላለም ህይወት ዘርቶ የሚኖር አንድ ዘላለማዊ እውነት ተናግረዋል። ” ውስጤን አውቍውዋለሁ። ከእስር የወጣሁት ካለቀለኝ እና ሁለት እግሬ እቀብር አፋፍ ላይ እንደቆመ እርግጠኛ ከሆኑ ቦሃላ ነው። ብሞትም የማትሞተው እውነት በውስጤ አለችና ስለእርሱዋ ዘላለማዊ እሆናለሁ።” ለማንኛውም አሉ”
፩፡ ብዙ የተናገርንበትና ጥርስ ውስጥ የገባንበት የእርትራና የወያኔ ጉዳይ በዚህ መልክ መጠናቀቁ
፪፡ ምንም በፍጻሜው ደስ የሚለኝ ሳዲስት ባልሆንም የሚፈርድብኝ በጠፋ ግዜ ከአክሱም ድረስ ተጠርቶ መጥቶ የመዝገቡን የውስጥ ገጽ በምን አይነት እስክርቢቶ እንኩዋን እንደተጻፈ የማያውቅ ሃጎስ የተባለ ሰው አምጥተው እንዲፈርድብኝ ቢያደርጉም በኔ ላይ የፈረደ ቀን ማታውኑ በተኛበት ትንታ ገደለው። እግዚአብሔር አምለኬ የርሱን እውነት ብየ ለምከፍለው ዋጋ ቀድሞ ምስክርነቱን ሰጥቶኝ እንድበረታ ጽናት ሆኖኛል ዕሲሉ በአውሮፕላን ጣቢያ ሆነው የመጨረሻ ኑዛዜያቸውን ተናገረዋል።
እንዲግህ እረፍታቸውን በዚህ ቀን ስናስብ ስማቸውን ተሸክመን ነገር ግን ማተባቸውን ጥለን ሳይሆን ወቅቱ ይዞት በመጣው አማራን የመታደግ ድምጽ ሆነው ብቅ ቢሉም ኢትዮጵያዊ ሆነው ኖረው ለአንዲት አገር ሲዋትቱ ኖረው ኢትዮጵያዊ ሆነው ያለፉ መሆናቸውን ሳንረሳ ነው፤ እርሳቸው በእምነትና በንጸሃ ጠባይ ኖረው ሰውነታቸውን አስቀድሰው ያረፉ እንጅ ያ ከአልባኒያ አሮጌ ዘንቢል እንደተደፋው የባንዳ ልጅ አብዮታዊ ዲሞክራሲ በሚል ቻይና ውስጥ በስብሶ በወደቀ አሮጌ ፍልስፍና ሲቀረሹ ኖረው አልሄዱም።
ፕሮፌሰር አስራት ጻድቅ፡ወሰማእት ናቸው። ሰማእት ሲባል ደግሞ ነፍሱን ስለሌላው አሳልፎ የሚሰጥ ማለት ነው። በተለይም ደግሞ ነፍሱን የሰጠው ግላዊ ባልሆነ ይልቁንም አገራዊ በሆነ ጉዳይ ሲሆን ፣ ህዝባዊ መሰረት ያለው ሲሆን፣ ሃሰትን አንግሸ እውነትን አልቀብርም ብሎ ሲሆን፣ ስለ ብዙዎች የተከፈለ የህይወት ዋጋ ሲሆን፣ መጸሃፈ መንኮሳት እንደሚለው ግዜ በሰቀለው ባለጌና በተገፋ መጻተኛ መካከል ቆሞ ፍርድን የሚያደርግ እርሱ ብጽእ ነው እንዲል፤ ፕሮፌሰር አስራት ማለት ለአንዲት መበለትና ባለታሪክ አገር ከነሙሉ መንፈሳዊ ክብሩዋ መጠበቅና ብሎም ፋኖ ውረድ እያለ ለሶስት ሽህ አመታት ሙሉ ሲጥልና ሲዎድቅ ለኖረ ኩሩ ህዝብ ክብር መጠበቅ እራሳቸውን የተቀደሰ መስዋእት አድርገው በመሰውያ ላይ ያቀረቡ ፤ የወደቀችው ባንዲራ ነገ ስትነሳ ጽላት የሚቀረጽላቸው፤ድርሳን የሚጻፍላቸው፤ ገድል የሚዘከርላቸው ስጋዊ፡ወመንፈሳዊ ፣ ምድራዊ፡ወሰማያዊ በኩረ ሰማእት ናቸው።
በመሆኑም ዛሬ እርሳቸው በብሔረ ሔዋን ከነሔኖክ ጋር በክብር አሉ፤ አስከሬኑን በዋርዲያ ዛሬ ድረስ የሚያስጠብቁለት የዘንዶው እራስ ደግሞ ከሰቃሊያነ ክርስቶሶች ጋር ዋጋውን በገሃንም እየከፈለ ነው፤ ይኽ የስራ ውጤት ነው።
የጻድቅ መታሰቢያ ለበረከት ነው ብሎ የነገረን ወንጌሉ የታመነ ነው፥፥
የፕሮፌሰር አስራት በረከታቸው ይድረሰን!!