By ሳተናው
May 17, 2017 15:19

ፕ/ር ዓሥራት ወልደየስ

እውቁ የቀዶ ህክምና ባለሙያ ፕ/ር ዓሥራት ወልደየስ የወያኔ አብዮት ማግስት በዜጎች ላይ የተፈጸመው ኢሰብአዊ ድርጊት የህሊና እረፍት ነስቷቸው በሙያቸው ከበሽታ ሲፈውሱት የኖሩትን ኢትዮጵያዊ በፖለቲካ ትግል ከወያኔ የበቀል ደባ ለመታደግ የመላው አማራ ህዝብ ድርጅት ፕሬዝዳንት ሆነው ለወያኔ የውስጥ እግር እሳት በመሆናቸው በእስር ተሰቃይተው ከሞቱ(ከተገደሉ ማለት ሳይሻል አይቀርም) እነሆ ግንቦት 2009 18 አመት ሆናቸው፡፡
በዚህ ወቅት በቀጥታ ከእርሳቸው ጋር የተገናኘ ሁለት ነገር ተጽፎ እያነበብን እየሰማንና እያየንም ነው፡ የመጀመሪያው ሆን ተብሎ ይህ ወቅት ተመርጦ የተዘጋጀ ስለመሆን አለመሆኑ መረጃ የሌለኝ የአማራ ዓለም አቀፍ ጉባኤ ነው፡፡ በዚህ ጉባኤ አዳራሽ የዓሥራት ፎቶ ተሰቀሎ ተናጋሪዎች አውቀው በድፍረት ይሆን ሳያውቁ በስህተት ወይንም ለዓላማቸው ስኬት ዓሥራትን መንጠላጠያ ማድረግ ይበጃል ብለው አልመው ባይገባኝም የዓሥራትን ትግላቸውን የአማራ መስዋዕነታቸውን ክልላዊ  በማድረግ ሲናገሩ ሰምተናል፡፡ የዚህ ጽሁፍ መነሻ አላማም ሆነ መድረሻ ግብ ይህ ባለመሆኑ ኢትዮጵያዊነትን ተላብሶ ለነጻነት ታሎ በክብር ያለፈውን ዓሥራት በእናንተ ደረጃ አውርዳችሁ አታሳንሱት የታገለለትን ዓላማ አታኮስሱት፣ መስዋዕትነቱን አታርክሱ ከማለት ያለፈ የምለው አይኖረኝም፡፡
ሁለተኛው ጉዳይ ባለወልድ ቤተክርስቲያን ሊታደስ ነው በሚል የዓሥራት ሀውልት ሊፈርስ፣ አስክሬኑ ሊነሳ ነው የሚለው ነው፡፡ በርግጥ አንደተባለው ቤተክርስቲያኑ የሚታደስ ከሆነ የዓሥራት ቀብር በቅርበት ነውና የሚገኘው መፍረሱ ግድ ነው፡ከተግባር ርቀን ምክንያት እየፈለጉ መጮህን ስራችን በማድረጋችን አንጂ ይህ ጉዳይ ተቃውሞ የሚሰማበት ባልሆነ ነበር፡እንደውም ከመቃወምና የሚሆን የማይሆን ከመጻፍና ከመናገር አስክሬናቸው እንዳያርፍበት የተከለከለውን  ቅድስት ስላሴ በዚህ አጋጣሚ እንዲያገኝ መስራቱ ነበር የሚሻለው፡፡
ወደተነሳሁበት ጉዳይ ልመለስ፣የዚህ ጽሁፍ ዓለማ ዓሥራትን ከብዙ በጥቂቱ መዘከር ነው፡፡ሀኪሙን ዓሥራት ሳይሆን ፖለቲከኛውን ዓሥራትን፣
1-ከማን ጋር ነው የምሰራው፤
ሀኪሙን ኣሥራት ወደ ፖለቲካው መንደር አምጥቶ የመዐህድ ፕሬዝዳንትነት ለመሆን ያበቃቸው አዲስ አበባ ሰሜን ሆቴል ከፍ ብሎ በሚገኘው የወ/ሮ አልማዝ ቤት የተጀመረ ምን እናድርግ ምክክር ነው፡፡ ምክክሩ አድጎ ወደ ድርጅት አስፈላጊነት ደረጃ ሲደርስ ፕ/ር ዓሥራት ለፕሬዝዳንትነት ታጭተው ሲነገራቸው ከማን ጋር ነው የምሰራው ብለው ነበር ተብሎ ሲወራ ሰመቻለሁ፡፡ነገሩ እውነት ይሁን አይሁን ማረጋገጥ ባይቻልም በተግባር የሆነው ግን ተናገሩት የተባለው ነው፡፡ርሳቸው ሲታሰሩ ም/ል ሊቀመናብርቱ ገሸሽ አሉ፣ መአህድም ቀኛዝማች ነቅዐጥበብ እጅ ላይ ወደቀ፣ ቀኝዝማቹ ደግሞ በወቅቱ የደህንነቱ ኃላፊ በነበረው ክንፈ ገብረመድህን መዳፍ ውሥጥ ገቡ፡፡
2 ከአንግዲህ የዋስ ክምችት በባንክ ማስቀመጥ ሊኖርብኝ ነው፤
መዐህድ ተመስርቱ ብዙም ሳይቆይ ያገኘው የህዝብ ተቀባይነት ያሰጋው ወያኔ ዓሥራት ደብረ ብርሀን ህዝባዊ ሰብሳ ላይ ከተናገሩት ቃላት ተመዞ፣ ነገር ተመንዝሮ ህዝብን ለአመጽ የሚያነሳሳ ጦርነት ቀስቀሳቀዋል የሚል ወንጀል ለጥፎ ክስ መሰረተባቸው፡፡ ይህ አልበቃ ብሎም  ከጎጃም ከመጡ አርሶ አደሮች ጋር በጽ/ቤታቸው ስለ አመጽ መክረዋል የሚል ክስ ታከሎባቸው በየፖሊስ ጣቢያ እየተመላለሱ ዋስ እየጠሩ መመለስ ሲሰለቻቸው እንግዲህ የዋስ ክምችት በባንክ ማስቀመጥ ሳይኖርብኝ አይቀርም አሉ፡፡
3-አስወስጄ መጠሁ፣
በየፖሊስ ጣቢያ እየተጠሩ በዋስ መለቀቁ ዓሥራትን ሸብረክ የሚያደርግ  የወያኔዎቹንም ፍላጎት የሚያረካ አልሆነምና ሰኔ 1986 ዓ.ም ዋረንት ተቆርጦ ላይመለሱ ወህኒ ተላኩ፡፡ በዚህ ግዜ ነበር ጸጋዬ ብረ መድህን አርአያ በሚለው የብዕር ስሙ የሚታወቀው  ሙሉጌታ ሎሌ ድጋፍ ጭብጨባችን እስከ ወህኒ በር ድረስ ሸኝቶ ለመመለስ እንደሆነ ያሳየበትን አስወስጄ መጣሁ የሚል ርዕስ የሰጠውን ጽሁፍ ጦቢያ መጽሄት ላይ ያስነበበን፡:
ስለ ፕ/ር ዓሥራት ሲነሳ የሚቆጭና የሚያሳዝነው ጸጋየ የገለጸው እስከ እስር ቤቱ በር ሸኝተን መመለሳችን ብቻ አይደለም፡፡ ፕሬዝዳንቱ የታሰረበት መአህድ ይፈቱ ማለቱ ቢቀር ህክምና ያግኙ ብሎ ለመጠየቅ ሰላማዊ ሰልፍ አስቦ አለማወቁ ነው፡፡ ይቻላል አይቻልም ላይ ጉዳይ ነው፤ጠይቆ መከልልም ወጥቶ በፖሊስ መበተንም አንድ ነገር ነው፡፡ ቀኛአዝማች ነቅአጥበብ የእኛ ድርሻ ዓሥራ የለኮሳት ሻማ እንዳትጠፋ የከፈተው ቢሮ በር እንዳይዘጋ መጠበቅ ነው ይሉ ስለነበር አይደለም ሰላማዊ ሰልፍ ከቢሮ የሚሰጥ አስራት ይፈቱ ህክምና ያግኙ የሚል መግለጫ እለነበረም፡፡
4-ህክምናውም ቢሆን እኔ ጋር ሲደርስ ነገር አለው፡፡
ዓሥራት በእስር ቤት በሽታቸው ስር ሰዶ ( ምን አልባትም ወያኔ ራሱ መርዟቸው ሊሆን ይችላል) ወያኔ ህክምና ከልክሎ በቁማቸው ከአዳከማቸው በኋላ እስትንፋሻቸው እጁ ላይ እንዳትወቀጣ በማሰብ ይመስላል ሲሰሩበት በነበረው ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል አንዲተኙ ተደረገ፤ በዚህ ግዜ ከአሜሪካ ድምጽ የአማርኛው ክፍል ጋር(ሰሎሞን ክፍሌ ይመስለኛል የአነጋገራቸው፤) ህክምና ሰለ አለማግኘታቸው ሲናገሩ ህክምናውም ቢሆን እኔ ጋር ሲደርሰ ነገር አለው ነበር ያሉት፡፡
5-የበሽታቸው ምንነት እንኳን አልታወቀም፡
ወያኔ ኣሥራት የሞቱት በበሽታ ነው ለማሰኘት ( የተሳካለትም ይመስላል) እንደማይድኑ ሲታወቅ ለህክምና አሜሪካ እንዲሄዱ ፈቀደ፤ ግና ታክሞ መዳን አይደለም በሆስፒታል ብዙም ሳይቆዩ ይህችን አለም ተሰናበቱ፡፡ አስክሬናቸውን ወደ ሀገር ቤት ለመላክ በተዘጋጀው የሽኝት ፕሮግራም ላይ በጠና ታመው መራመድ አቅቶአቸው በሰውና በከዘራ እየተረዱ የተገኙት ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድህን ባሰሙት ዓሥራት አንተ ለእኛ የሚል ንግግራቸው በሽታህ እንኳን ሳይታወቅ በማለት የገለጹት የሚቆጨው፣ የሚቆረቁረው ጠያቂ ባለመኖሩ እንጂ የሚያጠያይቅ የሚያመራምር፣ አስክሬኑ ወጥቶ ይመርመር እስከማለት የሚያደርስ ጥያቄ የሚያስነሳ ነበር፤ግን ከወሬ ተፋቶ ከተግባር ጋር የተጋባ ሰው ጠፋና ምንም አልተባለ፡፡
6-የአስክሬን አቀባበል ከቦሌ እስከ ቤት፤
ዓሥራትን በመግደል ያልረኩት ወያኔዎች አስክሬናቸው የክብር አቀባበልም አሸኛኘትም  እንዳያገኝ ለማድረግ አሲረው ነበር፡ውስጥ አዋቂዎች በወቅቱ አንደገለጹት በክንፈ ገብረ መድህን ቁጥጥር ስር የነበሩት የወቅቱ የድርጅቱ ፕሬዝዳንት ቀኝአዝማች ነቅዐጥበብ በቀለም ለዚህ ሴራ ተባባሪ ነበሩ፡፡ ግና ይህን የሰሙ ወጣቶች በእልህ ባደረጉት እንቅስቃሴ መንገድ ተዘግቶ፣ አጃቢው እጅግ በዝቶ፣ መፈክሩ፣ ዝማሬው፣ የተቃውሞ ጩኸቱ፣ ደምቆ አስክሬናቸው በቀስታ ተጎዞ ቤታቸው ለመድረስ ትንሽ ሲቀረው ለገሀር ስፖርት ኮሚሽን ጋር የአዲስ አበባ ፖሊስ አዛዦች ላስደፈጡት አድማ በታኝ በሉዋቸው የሚል ትዕዛዝ በመስጠት የአስክሬኑን መኪና ላይ ተደፍተው የሚያለቀስትን ሳየቀር እየደበደቡ በተኑ፣ ከፊሎቹንም አፍሰው ኮልፌ በመውሰድ የሚታወቁበትንና የተካኑበትን ተግባር ፈጸሙ፡፡
7-ቀብር፤
የወያኔዎችን አረመኔነት ልዩ የሚያደርገው አሸንፈው የማይተዉ፣ ገድለው የማይረኩ መሆናቸው ነው፡፡ይህም በመሆኑ የዓሥራት አስክሬን በአጀብ እንዳይሸኝ፣ ቅድስት ስላሴ ካቴድራልም እንዳይቀበር ከለከሉ፡፡ የቀብር ቦታው ክልከላ ቢሳካላቸውም የክብር አጀቡን ግን ማስቀረት አልቻሉም፡፡ እንደውም የወያኔዎቹ ክልከላ ሲሰማ የህብረተሰቡ በተለይም የወጣቱ ተቃውሞው ገነፈለ፡፡ የአስክሬናቸው ግብአተ መሬት ሲፈጸም የነበረው ተቃውሞ ለወገን አኩሪ ለወያኔዎች አስደንባሪ ሆነና ፓርላማ በር ላይ በተተኮሰ ጥይት ሁለት የንፋስ ስልክ አካባቢ ልጆች ተመቱ፡፡ አንደኛው ወዲያው ሲሞት ሁለተኛው ወደ ሆስፒታል ተወሰደ፡፡በልጆቹ መገደል መአህድ የያዘው አቋም አሳፋሪ ነበር፡፡
8-አስታዋሽ ማጣት፤
ዓሥራት ከሞቱ ከአመታት በኋላ የአሜሪካ ድምጽ የአማርኛው ክፍል አንዱን ልጃቸውን አግኝቶ ቃለ ምልልስ አድርጎለት ነበር፡፡ ከቃለ ምልልሱ መረዳት የተቻለው ቤት ንብረታቸው አስታዋሽ አጥቶ ቤቱ ተዘግቶ መቀመጡን ነበር፤ከዛ በኋላ ምን እንደሆነ መረጃ የለኝም፡፡ በስማቸው ብዙ ነገር ማድረግ ሲገባና ሲቻል ቤት ንብረታቸውን ዘወር ብሎ የሚያይ አስታዋሽ ማጣት  ያሳፍራል፡፡ ዛሬ ከ18 ዓመት በኋላ በስማቸው ለመነገድ ደፋ ቀና የሚሉ ሰዎች ማየት ደግሞ ያሳዝናል፡፡
ይህም ብቻ አይደለም ዓሥራት ወህኒ ሲወርዱ ተዳሚ ምክትል ሊቀመንበር የነበሩበትን ድርጅት ጥለው ከሀገር የወጡት ኢ/ር ኃይሉ ሻውል ተመልሰው የድርጅቱ ፕሬዝዳንት ለመሆን ከበቁበት 1992 ዓም በሞት እስከተለዩበት 2009 ዓ.ም  ድረስ አንድም ቀን ዓሥራትን በክብር ሊያስታውሱ ቀርቶ  ስማቸውን ሲጠሩ ተሰምተው አያውቁም፡፡ ምክንያቱን ሳናውቀው እርሳቸውንም ሞት ወሰዳቸው፡፡ ስለ ዓሥራት የሚታወሰው ብዙ ቢሆንም ከብዙ በጥቂቱ ይሄ ይብቃን፡፡
9-በዓሥራት አትነግዱ
አሥራት ኢትዮጵያዊ ነው ዘረኝነት ያልነካካው
መአህድ ብሎ መነሳቱ ቢጠበው ቢቸግረው ነው፡፡
የጻፈውን ፕሮግራሙን ፈልጉና ተመልከቱት
ከአንድ አንቀጽ በስተቀር አማራ የሚልም የለበት፤
ለኢትዮጵያ ታግሎ በኢትዮጵያዊነት የሞተውን
አትነግዱበት በስሙ ለቀቅ አድርጉት አሥራትን፤
አታውቁት ሆኖ ነው እንጂ ብታውቁትማ ኖሮ
በአስክሬኑ ሽኝት ላይ ጸጋዬ ያሰማው እንጉርጎሮ
ምስክር ነበር ለአሥራት
ለሱ ኢትዮጵያዊነት