May 18, 2017

የጤና ኤክስቴንሽን ባለሞያዎች በኢትዮጵያ

አድሃኖም ሃገሩን ሳያድን አለምን አያድን

ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ያስጀመረውና በእጅጉ የሚያደንቀው ገዥው ፓርቲ የሚመካበት ገድል ነው-የጤና ኤክስቴንሽን ባለሞያዎች አገልግሎት::
የተጀመረው በሐምሌ ወር  2001 አ.ም በአዲስ አበባ ጤና ቢሮ አስፈፃሚነትና በፌደራል ጤና ጥበቃ የበላይ ተቆጣጣሪነት ነው::
ህወሓት/ኢሕአዴግ በጤናው ዙሪያ እመርታ አስመዘገብኩባቸው ብሎ ከሚላቸውና በውጭ እርዳታ ሰጭዎችም ዘንድ ሞገስን አገኘሁበት ብሎ የሚኩራራበት ይኸው የጤና ኤክስቴንሽን ጥራዝ (ፓኬጅ)ነው::
የጤና ኤክስቴንሽን ጥራዙ አስራ አንድ ዋና ዋና ዘርፎች ሲኖሩት: ለምሳሌም የአካባቢ ንፅህና እንዲጠበቅ ማስቻል: ያልተፀዱ አካባቢዎች ንፁህ ለኑሮና ለጤና ተስማሚ እንዲሆኑ ማስቻል ይገኙበታል::  ከተጠቃሚው ዘንድ የሚሰሙ ጤናን የሚመለከቱ መረጃዎችን እንደግብአት ወስዶ ቅደመ-ጥንቃቄ በማድረግ ማህበረሰቡን ጤናማ ማድረግ ቁልፉ የጥራዙ መርህ ነው::
መሬት ላይ የሚሰራው ግን ሌላ ነው:: ሁሉም አምባገነኖች እንደሚያደርጉት ዜጎቹ እለት በእለት የሚያስቡትን መከታተልና “ ባቄላዋ ሳታድር መቆርጠም ” የሚሻው ህወሓት/ኢሕአዴግ ከህዝብ በሚሰበስበው ግብር የጤና ኤክስቴንሽን ባለሞያዎችን በማሰማራት ሕዝቡን ያፍናል::
የህወሓት/ኢሕአዴጎቹ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሞያዎች ለምርጫ ቅስቀሳና ለፖለቲካ ማስፈፀሚያነት ማገልገል ነው ዋነኛ ተግባራቸው:: እነዚሁ ባለሞያዎች የፖለቲካ ቅስቀሳ በማድረግ: ማህበሮችን (የሴት ልማት ማህበር ለምሳሌ): ሴቶች እርስበርሳቸው ስለጤናቸው እንዲወያዩ ያለመ ቢሆንም የኢህአዴግ አባላት በመመልመል: በእድር ለቅሶ ቤትና ሌሎች ሰዎችን የሚያሰባስቡ ሁነቶች ላይ አገዛዙን በመካብ ህዝቡ ዘንድ ጉጉት እና ቅዤት በመፍጠር ቀላል የማይባል አገልግሎት ይሰጣሉለአፋኙ አገዛዝ::  ሴቶችን በልማት ሊግ ስም በአባልነት መዝግበው የገዥውን ፓርቲ አባልነት መታውቂያ ያድላሉ:: የኢህአዴግ አባላት ቁጥር በአንዴ እንዲያሻቅብ በማድረግ በኩል የጤና ኤክስቴንሽን ባለሞያዎች ድርሻ ቀላል አይደለም-በግዴታ የሚመዘገቡ አባላትን በማበራከት::
በዚሁ የቤት ለቤት ተግባራቸው የመቃወም አዝማሚያ የሚታይበትን እንዲሁም የገዥው ፓርቲ አሰራር ልክ እንዳልሆነ የሚያወራ ማንኛውም ሰው ይጠቆራል: ይታሰራል: ይታፈናል: ማስፈራሪያዎች ይደርሱታል: እንዲሸማቀቅና በቀጣይ ከአፉ ቆጠብ እንዲል ይደረጋል:: በአገርአቀፍ ምርጫ ወቅት  የጤና ኤክስቴንሽን ባለሞያዎች ከምረቃ እንደወጡ ዋና ስራቸው ቤት ለቤት እየዞሩ የስልለላና ኢህአዴግን ምረጡ የሚል ሰፊ ቅስቀሳን ማድረግን እንጅ ከጤና ጋር የተያያዘ ስራ መከወን አልነበረም::  ጎርቤት በጎረቤቱ ላይ እንዲመስክር ይበረታታል:: ህዝቡ እርስ በርሱ ተፈራርቶ በሕብረት እንዳይቆምና መሰረታዊዎቹን የንፁህ መጠጥ ውሃ እና የሽንት ቤት ፅዳትን በተመለከተ እንኳን ማውራትን እንዳይደፍር ማሸማቀቅ ይደርስበታል::
በቅርቡ አሰቃቂ አደጋ በደረሰበት በተለምዶ ቆሼ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ሃያ ሁለት የጤና ኤክስቴንሽን ባለሞያዎች ባለሞያወች ይንቀሳቀሳሉ-እስከአምና በነበረው ቁጥር:: ላለፉት ዘጠኝ አመታት እነዚሁ ባለሞያወች የቆሼን አካባቢ አሰቃቂ አደጋ ሊታደግ የሚችል ዘገባ አላቀረቡም:: ሰውን የሚቀርቡት ለሌላ አላማ ስለሆነ ገዥውን ፓርቲ ለማዳን ብለው ሕዝቡን አደጋ ላይ ጥለውታል::
ህዝቡ ደሞዛቸውን ይከፍላል: በምላሹም ሲሸማቀቅ ይውላል:: በአንድ ለአምስት አሰራር ተጠርንፎ ተቃውሞ ማሰማትን እንደጦር ይፈራል:: አዲስ አበባ አሁን ያለችበት የዝምታ ድባብ አንዱ ምንጭ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሞያዎች ትሩፋት ነው::
የአንዲት የዋህ ፀሐፊ ገጠመኝ
ገዥው ፓርቲ መቶ ከመቶ መድፈን ልምዱ ስላደረገው የጤናው ዘርፍም የቁጥር ጨዋታው በተዋረድ ደርሶታል:: እቅድና ክንውን በሚመዘገብበት ወረቀት ያቀድኩትን በሙሉ አሳክቻለሁ በማለት እንድትሞላ የተነገራት አንዲት ካድሬ ወደ አንድ ጤና ጣብያ በመሄድ ፀሐፊዋን ሁሉንም መስመሮች መቶ ስትል እንድትሞላ: አድካሚ እንዳይሆንባት ግን አንድ ጊዜ መቶን ፅፋ የቀሩትን በአንዳፍታ የምትሞላበትን አሰራር ታሳያታለች:: ነገሩ ወዲህ ነው:  ቤት ውስጥ ስትወልድ የሞትች እናት እና በወሊድ ምክንያት የሞቱ ሕፃናት ቁጥርን በተነገራት መሰረት የታቀደው ከተሳካው  አንፃር መቶ እንደሆነ ሞልታ ዘገባውን ትልካለች:: ታዲያ ስኬት ማለት ሁሌ መቶ መድፈን ሳይሆነ ዜሮም ዋጋ እንዳላት ያልተረጠረችው ሰራተኛ በሌሎች የጤና ባለሞያዎች ዘንድ መደናገጥን ፈጥራ ነበር::
ወደቁምነገሩ ስንመለስ ገዥው ፓርቲ ግብረሰናይ ድርጅቶችን ከአገር በማስወጣቱ በጤናው ዘርፍ እየተከሰቱ ያሉ ክፍተቶችን በሌላ ፅሁፍ የምንመለስበት ቢሆንም የኤች አይ ቪ ከእናት ወደልጅ መተላለፍ: የእናቶች በወሊድ ወቅት መሞትና: የሕፃናት ከአምስት ዓመት በፊት ሞት መበራከት የጤናው ዘርፍል ላይ ከፍተኛ ስጋት ደቅነዋል::
ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ሀገራቸውን ሳያድኑ አለምን ለማዳን የምረጡኝ ዘመቻቸውን ባጧጧፉበት በዚህ ሰዓት የኮሌራ ወረርሽኝን በአተት ስም እያስቀየሩ የፈፀሙት የፓርቲ ታማኝነት ዋጋ ሊያስከፍላቸው እንደሚችል የዚህ ፅሁፍ አርቃቂ ቢያምንም: በቀሩት ጥቂት ቀናትም አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን የግለሰቡን ተያያዥ ወንጀሎች በማጋለጥና ሃገራት ድምፃቸውን ኢንዱነፍጉት ጥረቱ ይቀጥል እላለሁ:

Source         –     ኢትዮሚድያ – Ethiomedia.com