By ሳተናው
May 23, 2017 22:21

በመጀመሪያ ሁላችንንም እንኳን ደስ አለን!! በአላማ የተቃወማችሁትም እውነቱን ስትረዱ ትደሰቱ ይሆናል፡፡ ማንም ሰው ከአላማና በትክክልም በሚረዳው ስለመሰለውና ስላመነበት ቢቃወምም ቢደግፍም ስላመነበት ጉዳይ ነውና እቀበላለሁ፡፡ በአሁን ጊዜ በኢትዮጵያውያን የማየው ግን አደገኛ የሆነ የዘረኝነት ልክፍት የተጠናወተው ተቃውሞ ወይም ድጋፍ ነው፡፡ ትግሬ ስለሆነ የቴድሮስ ደጋፊ አማራ ስለሆነ ተቃዋሚ የሚሆንበት አንደም አመክንዮዋዊ ስሌት የለውም፡፡ ተቃውሞና ድጋፉ ከአለመረዳትም ከሆነ መልካም፡፡ እውነቱን ሲረዳ ትክክል አልነበረኩም ለማለት አእምሮው ብቃት አለውና፡፡ ቴድሮስ የወያኔ ኣባል መሆኑ ብዙዎች እንደ አብዛኛው( ቀንደኞቹ) ወያኔ አረመኔ ሰው አድርጎ አስቦት ይሆናል፡፡ ሌሎች ደግሞ ቴድሮስ የሰራቸውን ብዙ ተግባራት አይተው ሊወዱት ይችላሉ፡፡ ሆኖም በአረመኔዎቹ ጋር መቀላቀሉን አስበን ከተቃወምን እሱ በአረመኔው ተግባር የሌለበት ይልቁንስ በዚህ አረመኔዎች በበዙበት አጋጣሚውን ተጠቅሞ ለሕዝብና አገር ባለውለታ እንደሆነ ስንረዳ አዎ ተሳስቼ ነበር፡፡ ይህ ሰው መልካም ሰው ነው ለማለት እድል አለን፡፡ አንዳንድ ከላይ ከላይ የሰራቸውን ሥራዎች አይተን የደገፍንም የውስጥ እኩይ ማንነት ካለው የንን እኩይነቱን ስንረዳ ተሳስቼ ነበር ይህ ሰው እንዲህ ያለ እኩይ መሆኑን አላውቅም ነበር ብለን እራሳችንን እንወቅሳለን፡፡ እነዚህ እንግዲህ ምክነያታዊ ስንሆን ነው፡፡ ዘረኞች ከሆን ተቃውሟችንም ድጋፋችንም በቃ የእኛ ያልንው ጎሳ ምን አረመኔ ቢሆን ደጋፊው የኛ ያልሆነውን ደግሞ ምን የተቀደሰ ቢሆን ተቃዋሚ ነን፡፡ ሕሊና ይህን አይፈቅድም፡፡

በእኔ አረዳድ ቴዎድሮስ መልካም ሰው ነው፡፡ ለማግዘፍ አልፈልግም፡፡ አሁን ጥሩ ቦታ ላይ ደርሷልና፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ቴዎድሮስ በተባበሩት መንግስታት ዋና ዳይሬክተርነት ሲወዳደር ስለሱ ብዙ የማይሆኑ ነገሮች መወራት ጀመሩ፡፡ ሁሉንም እከታተል ነበር፡፡ አንዱም ግን ቴደሮስን ከመልካምነቱ የሚያሳንሰው ሆኖ አላገኘሁትም፡፡ በሚኒስቴርነት መስራት እንዲህ ቀላል አይደለም፡፡ ሰሞኑን የኮሌራን ወረረሽኝ ደግቋል ተብሎ ብዙ ሊወራ ታሰበ፡፡ ቴድሮስ ከውስጥ በሆነ ክፋት ይህን ያደርጋል የሚል እምነት የለኝም፡፡ በሆኑ ምክነያቶች ተገዶ ሊያደርግ የሚችልበት አጋጣሚ ሊኖር እንደሚችል ግን እገምታለሁ፡፡ ብቻ ስለሱ ብዙ ማለት አልፈልግም ከዚህ በፊት የራሴን አስተያየት ሰጥቼ ነበር፡፡ አንዳንዶች እኔንም የወያኔ ደጋፊ ሊሉኝ ሞክረዋል፡፡ ሊንኩን ይሄውላችሁ፡፡ http://www.zehabesha.com/amharic/?p=53920 በዚህ ሊንክ ከሞላ ጎደል የእኔን አረዳድ ታዩታለችሁ፡፡ ያም ቢሆን ከአላማና ነገሮችን ከአለመረዳት ወይም ከመረዳት ከሆነ ይሁን፡፡ የእኔ ስጋት ከጭፍን ደጋፊነት ተቃዋሚነት በተለይም ደግሞ ከዘረኝነት ጋር መያያዙ ነው፡፡
ዛሬ ትግሬ በመሆናቸው ቴድሮስ መመረጡ ያስደሰታቸው ትግሬዎች አዝናለሁ፡፡ ቴድሮስ ትግሬ በመሆኑ የተከፋችሁም እንዲሁ፡፡ አላማ ያለው ትግል ነው ነጻነትና ፍትህ የሚያመጣው፡፡ እኛ በተራችን ደግሞ እድሉን ስናገኝ ያው ነው፡፡ በእኔ እምነት አብዛኛው የ60ዎቹ ትውልድ የዚህ ልክፍት ሰለባ ነው፡፡ ዛሬ ላለውም ትውልድ ይህንን እያጋባ ነው፡፡ ልብ በሉ ወያኔ ውስጥ በብዛት አረመኔዎች ተጠራቀሙ እንጂ የኢትዮጵያና ሕዝብ ጠላት በሌሎችም አሉ፡፡ ተቃዋሚ ነን የሚሉትን ጨምሮ፡፡ ሁሉም መሠረታቸው እምነትም፣ ስብዕናውም የሌለው የዛ የተረገመው የ60ዎቹ ትውልድ ነው፡፡ ብዙ ተከታይ አፍረተዋል፡፡ ሌሎች ግን ወይ ፈዘዋል ወይ ደግሞ የማያውቁትን ሂደት ይደግፋሉ ወይ ይቃወማሉ፡፡ ወያኔን እኮ ሙጥኝ ብለው የያዙት ሁሉም ማለት ይቻላል የ60ዎቹ ናቸው፡፡ ጡረታ እንኳን አይወጡም፡፡ በሌሎቹ የወያኔ ቡድን አጋሮች አነሰም በዛም መቀያየር አለ፡፡ በዛም ምክነያት ነው ከሕዝብ ጎን የቆሙ አልፎ አልፎም ቢሆን የሚታይባቸው፡፡ በተለይ ከ60ዎች ትውልድ ውጭ የሆኑት ብዛት የሕዝብ ጉዳይ የሰማቸዋል፡፡ ከ60ዎቹ ጥቂት እንደነበሩ አልረሳሁም፡፡ መረራ አንዱ ናቸው፡፡ ምን አልባትም ቴድሮስ እኔን እስከሚገቡኝ ድረስ የ60ዎቹ አረመኔያዊ ባሕሪ አይታይባቸውም፡፡ አሁን ሙሉ ትኩረት አድርገን መታገል ያለብን ጠላቶቻችንን ነው፡፡ ጠላት ያልሆኑን ሰዎች ባለማወቅም በጭፍንነትም ብንቃወም ለእኛ ውድቀት ነው ብንደግፍም እዳ ነው፡፡
ሥለዚህ ኢትዮጵያውያን ሁሉ (ዘረኞችን አይመለከትም) ቴድሮስን ከፍጹም ኢትዮጵያዊነት ደግፋችሁም ተቃውማችሁም ከሆነ እናንተ በሕሊና አልተሳሳታችሁም በመረጃ ማጣት እንጂ፡፡ እውነቱን ስታውቁ ልትታረሙ ትችላላችሁና፡፡ ቴድሮስ በሞገሱም ይሁን በምግባሩ እስከማውቀው ድረስ የሚያሳፍር ሰው አደለም፡፡ ከተወዳዳሪዎቹ ከዴቪድ ናባሮም ሆነ ከሌላኛዋ ተወዳዳሪም የተሻለ እንደነበር ግልጽ ነው፡፡ እንደሊዛዊው ናባሮ ብዙ አመት የተባበሩት መንግስታት ለመስራት እድል የኖረው ኢንጊሊዛዊ ስለሆነ ነው እንጂ ከቴድሮስ የተሻለ ስለነበር አይመስለኝም፡፡ ይልቁንም ዛሬ ቴድሮስን መቃወም ሳይሆን ከዚህ በኋላ ቴድሮስ እስከዛሬ በወያኔ ውስጥ ሆኖ እንኳን መልካም የሆነውን ሥራውን የበለጠ እንዲያጎለብት መደገፍ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊ በመሆኑ አደለም መልካም መስሎ ስለታየኝ እንጂ፡፡ ቴድሮስ አባይ ጸሀይዬ፣ ስብሀት ነጋ፣ ሳሞራ ዩኑስ፣ ስዩም መስፍን፣ ደብረጽዮን ወይም አባይ ወልዱ ወይም ሀይለማሪያም ደሳለኝ አደለም፡፡ ቴድሮስ ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ ሰውም ነው! ያላወቃችሁ ይህን እወቁ፡፡ እስካሁን ምንም ማለት ያልፈለኩት በነጻነት ሰዎች የመሰላቸውን እንዲናገሩ ነው፡፡ ለነገሩ እኔም ይህን ሀሳብ ባነሳ ያው ወያኔ የሚለው ስያሜ እሰጣለሁ፡፡ በዚህ አጋጣሚ አስመሳዮች እንደልባቸው ይፈነጩብናል፡፡
ለእኔ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን የሚያስብ ወዳጄ ነው፡፡ ቴድሮስ በዚህ መስፈርት አልወደቀም፡፡ ኦባማን ጨምሮ የሱ ካቢኔ የነበሩ ብዙዎች ለእኔ ከወያኔ ባልተናነሰ ጠላቶቻችን ናቸው፡፡ ባለፈው ትራምፕ ሊመረጡ ሲሉ ብዙዎች የክሊንተን ደጋፊ ነበሩ፡፡ በጣም ነበር ሕዝቡን የታዘብኩት፡፡ በምን መሥፈርት ቢባል ያው ሁሉም የራሱን የሥደት እድል ማመቻቸት እንጂ በአገርና ሕዝብ ላይ ሊኖር የሚችለውን አደጋ ፍጹም አላሰበም፡፡ ላስተዋለው ግን ሁኔታው ግልጽ ነበር፡፡ ክሊንትን ቀጥላ ቢሆን አሁን የሚናየውን ለውጥ ማየት እንችልም ነበር፡፡ ሱዛን ራይዝ የሳቀችብንን ሳቅ አድሉን ባገኝ መቼም ቢሆን አልረሳውም፡፡ 100 ፐርሰንት ማሸነፉ አደለም ከሳቋ ጀርባ የማነበው፡፡ የኢትዮጵያን ሕዝብ እንዴት በንቀት እንዳየችው ነው፡፡ እነሱ ገንዘብ እየረዱ ነበር ያ ሁሉ ወሮበሎነት በሕዝብና አገር ላይ የተፈጸመው፡፡ አሁን ጥሩ ለውጥ መጥቷል፡፡ ሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝብ ጠላቶች የሆኑ መሪዎች ዛሬ ወረደዋል፡፡ የኢንግሊዙ፣ ዴቪድ ካሜሩንና ብሌር፣ ኦባማ ዋነኛው ነው፡፡  የጀርመኗ ቻንስለር ለእኛ በጎ ነበረች አሁን አለች፡፡ አሁን ትረምፕን መጠቀም ቢቻል ሰውዬው ለኢትዮጵያ ሕዝብ ልዩ እድል እንደሚፈጥር ይሰማኛል፡፡ ሰውዬው ከእነ ኦባማ ቡድን ጋር በአለምአቀፍ ውንብድና ተሰማርተው የነበሩት የተለያዬ ሚዲያዎችና ደጋፊዎቻቸው እንደሚያወሩት አደለም፡፡ ብልጥም ነው፡፡ ልብ በሉ ሳውዲ ሄዶ የፈጸመውን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ድል፡፡ በፖለቲካው የአረብን አገራት ኔቶ ውስጥ ከተተ ነው የተባለለት፣ ለሕዝቡና አሜሪካም ቃል በገባው መሠረት ጠቀም ያለ ዶላር ነው የመጣላቸው፡፡ ንግግሩም ትልቅ ሰበዓዊነትና እግዚአብሔርን ያሰበ ነበር፡፡ ሰው ካለ አሁን ትረምፕ የኢትዮጵያን ሕዝብ ለመታደግ ሁነኛ ሰው ነው፡፡ የጀርመኗ ሜርክል በዚህ ትተባበራለች፡፡ ዝም ብሎ ተቃዋሚ ነን እያሉ በየከተማው እየዙሮ ሳንቲም ከመልቀም ቁልፍ ሥራ መሠራት ያለበት ለእነዚህ መሪዎች በመረጃ የተደገፈ የሕዝብን መከራ ማሳየት ነው፡፡ ለመሆኑ የተቃዋሚ ተብዬዎቹ ሥራ ምንድነው; ኦባማና ቡድኑ ሁለተኛ አይመጣብንም፡፡ የአሜሪካውያን ግብር ከፋዮችን ገንዘብ ነው ኢትዮጵያውያን እንዲሰቃዩበት እየተደረገ ያለው፡፡ ብዙ ገንዘብ ሕዝብ ያዋጣል ግን የሚሄደው ሌላ ሕዝብ ለመጨረስ ነው፡፡
ስለትረምፕ ይህን ተመኝቼ ነበር ሆኗል፡፡ “የትረምፕ መመረጥ በአለም-በአፍሪካ-በኢትዮጵያ ፖለቲካ ያለው አንድምታ” በሚል የጻፍኩጽ ነበር፡፡  ሊንኩን ስላነሱት ፌስቡክ ላይ እንዲህ ይነበባል https://www.facebook.com/Zehabesha/posts/1099672860104919 አዎ እድሉን የሚጠቀምበት ቢገኝ ትልቅ አጋጣሚ ነው!

ለዶ/ር ቴዎድሮስና ትክክለኛ የኢትዮጵያ ልጆች ሁሉ እንኳን ደስ አላችሁ!! መልካም የሥራ ዘመን ለዶ/ር ቴድሮስ አድሀኖም!

አመሰግናለሁ

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይጠበቅ ይባርክ!
አሜን

ሰርጸ ደስታ