ሰሞኑን ዶክተር አባ ኃይለ ማርያም ኦርቶዶክሳውያን ካልሆኑ አካላት ጋር ያከናወኑትን ‹የጠበልና እምነት› ጉዳይ በተመለከተ አያሌ ጥያቄዎች ሲነሡ ነበር፡፡ ነገሩን ከየምንጮቹ ብሰማቸውም በቅዱስ ጳውሎስ ዘመን የነበረው የቂሣርያው ገዥ ፊስጦስ ‹ተከሳሹ በከሳሾቹ ፊት ለፊት ሳይቆም፣ ለተከሰሰበትም መልስ ይሰጥ ዘንድ ፈንታ ሳያገኝ ማንንም ቢሆን አሳልፎ መስጥ የሮማውያን ሥርዓት አይደለም› (የሓዋ.25፣16) ብሎ የተናገረውን መሠረት በማድረግ አባ ኃይለ ማርያም ለጉዳዩ የሚሰጡትን መልስና ማብራሪያ ጠብቄ ነበር፡፡ መልስና ማብራሪያውንም ሰጡ፡፡

 

አባ የድርጊቱን መከናወን አምነው የክንውኑን ዓይነት ከተወራው የተለየ መሆኑን አብራሩልን፡፡

መልሳቸውን ስናጠቃልለው፡-

1. መርሐ ግብሩ ‹ውኃ ለሁሉም› በሚል መርሕ እንደተዘጋጀ

2. ፓትርያርኩና ሊቃነ ጳጳሳት እንደተገኙበት

3. ተበጥብጦ ከመጣው ውኃና እምነት ጠቅሰው በተሳታፊዎቹ ግንባር ላይ ምልክት አንዳደረጉ

4. ሰውዬው ጣቱን አስጠጋ እንጂ አንዳልቀባቸው
መርሐ ግብሩ ‹ውኃ ለሁሉም በፍትሐዊነት እንዲዳረስ› ከሆነ እንዴት ነው እምነትና ውኃ በመበጥበጥ ውኃ ለሁሉም ሊዳረስ የሚችለው፡፡ ‹ውኃ ለሁሉም› የሚለው ጉዳይ የዐውደ ጥናት፣ የምክክርና ምናልባትም የጸሎት ርእስ ሊሆን ይችላል እንጂ እምነትን በውኃ በጥብጦ በመቀባት ‹ውኃ ለሁሉም› እንዴት ለማዳረስ  ይቻላል? እምነት በውኃ በጥብጦ መቀባት ለፈውስ ያገለግላል እንጂ እንዴት ከውኃ ፍትሐዊ አጠቃቀም ጋር ተገናኘ? ደግሞስ እኛ ከሌሎች እምነቶች ጋር አንድነታችንን ማምጣት ያለብን በክርስቶስ እንጂ እምነት በውኃ በመበጥበጥ ነው እንዴ?

አባ ኃይለ ማርያም በሰውዬው (የሌላ አምነት መሪ መሆኑ ከፎቶውና ከመረጃው ይታወቃል) ግንባር ላይ ሲቀቡት ምን እንዲያደርግ አስበው ነው? እንዲፈወስ የቀረበ በሽተኛ ነው? ለበረከት የመጣ ደጅ ጠኚ ነው? እንዴትስ ነው የተበጠበጠው እምነት ከ‹ ውኃ ለሁሉም› አስተሳሰብ ጋር የሚሄደው?

ሌላው አስገራሚ ነገር ደግሞ ‹ሰውዬው ጣቱን አስጠጋ እንጂ አልቀባኝም› ብለዋል፡፡ ፎቶዎቹ ሁሉ የሚያሳዩት ግን ሲቀባዎት ነው፡፡ ደግሞስ ሰውዬው ለመቀባት ካላሰበ እጁን ለምን ወደ እርስዎ ያስጠጋል? ሊባርክዎ ነው? አስቀድማችሁ የተስማማችሁበት ሥነ ሥርዓት ይህንን የማይፈቅድ ከሆነስ እንዴት እጁን ወደ እርስዎ አስጠጋ? ‹እጁን አስጠግቶ ነበር› ካሉን ደግሞ ከተበጠበጠው እምነት እንደ እርስዎ ጠቅሶ ነበር ማለትዎ ነው? ለመሆኑ ኦርቶዶክሳዊ ክህነት የሌለው ሰው ከእምነት ጠቅሶ ሌላውን ሰው መቀባት፣ ያውም ቆሞሱን ይችላልን?

ሥነ ሥርዓቱ ሲከናወን ፓትርያርኩና ሊቃነ ጳጳሳቱ እንደነበሩ አባም ነግረውናል፣ ፎቶውም አሳይቶናል፡፡ ምን ወስነው? ምን ሊያደርጉ ሄዱ? ውኃ ለሁሉ እንዲዳረስ ሊጸልዩ ወይስ ውኃ ለሁሉ እንዲዳረስ እምነት በውኃ ሊበጠብጡ? ለመሆኑ ይህንን እንዲያደርጉ ቀኖና ቤተ ክርስቲያን ይፈቅድላቸዋል? ወይስ ሥልጣን ከቀኖና ስለሚበልጥ?

አባን ለዚህ ሁሉ ነገር የዳረጋቸው በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ መርሕ እየተጣሰ ስለመጣ ነው፡፡ ሁለት መሠረታዊ ጥያቄዎችን እናንሳ፡-
ቤተ ክርስቲያናችን ኢኩሜኒካል ግንኙነትን የምትመራበት ፖሊሲና ደንብ አላት?

የሁለቱም መልስ የላትም የሚል ነው፡፡ በሌሎች እኅት አብያተ ክርስቲያናት የኢኩሜኒካል ግንኙነትን የተመለከተ ፖሊሲና ደንብ ሲኖዶሱ ያጸድቃል፡፡ ከነማን ጋር ምን ዓይነት ውይይት ይደረጋል፣ ምን ዓይነት ውይይቶች በምን ደረጃ (በሊቃውንት፣ በጳጳሳት) ይደረጋሉ፣ ስምምነቶች እንዴት ይጸድቃሉ፣ የጸደቁት እንዴት ለሕዝብ ይገለጣሉ፣ የጸደቁትን እንዴት መተግበርና መከታተል ይቻላል፣ ስምምነት እስኪደረስ ድረስ ከሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ጋር ምን ዓይነት ግንኙነቶች ይኖሩናል? በምን በምን እንተባበራለን? በየደረጃው ያሉ አካላት (ጳጳሳት፣ ካህናት፣ ዲያቆናትና ምእመናን) ያላቸው ድርሻ ምንድን ነው፣ የሚሉትን የሚወስን የፖሊሲ መዝገብ አላቸው፡፡ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ግን ይህ ፖሊሲ የላትም፡፡ ፖሊሲውንም መሠረት አድርጋ የምትመራበትን ሕግ አላጸደቀችም፡፡ ስብሰባ ስትጠራ መሄድ ብቻ ነው፡፡

በሌላ በኩልም የኢኩሜኒካል ግንኙነትን የሚያካሂድ፣ ባለሞያዎችን የሚሰባስብ፣ መረጃዎችን የሚመዘግብ፣ በዓለም ላይ የሚደረጉ የኢኩሜኒካል ግንኙነቶችን የሚከታተል፣ ግንኙነቶቹን በፖሊሲውና በደንቡ መሠረት የሚመራ፣ ስሕተቶች ሲፈጠሩም የሚያርም ተቋምም የለም፡፡ ያለው የውጭ ግንኙነት መምሪያ ነው፡፡ እርሱ ደግሞ ብዙ ጊዜ እንግሊዝኛ ይችላሉ ተብሎ ስለሚታሰብ አሜሪካ በኖሩ ሰዎች የሚመራ ነው፡፡ የኢኩሜኒካል ግንኙነት ግን የአሜሪካን እንግሊዝኛ በመቻል ብቻ የሚሠራ አልነበረም፡፡ የውጭ ግንኙነት መምሪያው ወደ ውጭ ለሚሄዱ ሰዎች ሂደቶቻቸውን መከታተል፣ ከውጭ አጥቢያዎች ጋር ‹መገናኘት› የሚላኩ ሰዎችን መላክ እንጂ ራሱ እንኳን የሚመራበት የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ያለው አይመስልም፡፡

ይህ በሆነበት ሁኔታ አባ ኃይለ ማርያም ያንን ነገር ቢያደርጉት የሚገርም አይደለም፡፡  ቅዱስ ሲኖዶሱ፣ በዕለቱ የነበሩት ፓትርያርኩና ሊቃነ ጳጳሳቱ የቤተ ክርስቲያኒቱን መርሕ እየጣሱ ያዘዟቸውን ነው የተገበሩት፡፡ እርሳቸው ቢሆኑም ግን  ፖሊሲና ሕግ በሌለበት ይህንን ተግባር ከሚያከናውኑ ‹ዱክትርናቸውን› ተጠቅመው ፖሊሲውና ሕጉ እንዲዘጋጅ ቢያደርጉ ኖሮ ይመሰገኑ ነበር፡፡ ነገ ጳጳስ የሚሆኑትን አባት ማንም እየተነሣ እጁን ወደ ግንባራቸው አይልክም ነበር፡፡ በሃይማት መሥመር የበላይ ያመጣውን ሁሉ በእምነት መመርመር ያስፈልጋል፡፡ የበላይ አዞኝ ነው ብሎ ቀኖና መጣስና እምነት ማፋለስ ዋጋ ያስከፍላል፡፡ በጉባኤ ኬልቄዶን የክህደቱን ውሳኔ አልቀበልም ያለው ዲዮስቆሮስ በሮም ቤተ መንግሥት ተጠርቶ ‹ለምን አትቀበልም? ልዮንኮ አለቃህ ነው› ሲባል ‹ልክ ነው ልዮን አለቃዬ ነው፡፡ ነገር ግን ከእምነቱ ሲወጣ አልቀበለውም፡፡ ሳጥናኤልም ለቅዱስ ሚካኤል አለቃው ነበር፤ ከእምነቱ ሲወጣ ግን አልተቀበለውም› ያለውን እዚህ ላይ ማስታወሱ መልካም ነው፡፡ አሁንም ቤተ ክርስቲያናችን ኢኩሜኒዝምን የተመለከተ ፖሊሲና መመሪያ ካላወጣች፣ ጠንካራ ተቋምም ካልመሠረተች ነገ ከዚህ የባሰ ነገር ማየታችን አይቀርም፡፡ ከዚህ ተግባር የተማርነው ግን የቤተ ክርስቲያናችንን ጉዳይ በነቃ ኅሊና መከታተል እንዳለብን ነው፡፡ ያሳወቁንን እያመሰገንን፣ ያላወቅነው እንዲገልጥልን እንለምናለን፡፡