May 26, 2017

እንደ መነሻ፣  ምክንያት እየፈለገ የወያኔን ኮቴ እየተከተለ የሚጮኸው ሁሉ በእኩል ደረጃና እምነት የወያኔ ተቀዋሚ መሆን አለመሆኑ ብቻ ሳይሆን  ነጻነት ፈላጊ መሆኑ ራሱ አጠራጣሪ ነው፡፡ ይህ ባይሆን ኖሮ ከምር ሁሉም ነጻነት ፈላጊ ቢሆን ኖሮ የጎሳ አጥር፣ የኃይማኖት ድንበር ወዘተ  እየሰራ በየግል ህልሙ ታጥሮ ለውጥ ሊያመጣ ቀርቶ ሰሚ ሊያገኝ እንኳን ያልቻለ ጩኸት በየመንደሩ በማሰማት ላይ ተወስኖ ሀያ ስድስት አመታትን ባላስቆጠረ ነበር፡፡

ባለትልቅ ራዕይ በትናንሽ ጉዳይ አይለያይም፣

ዓላማው ነጻነት፣ ግቡ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ማየት የሆነ ዜጋም ሆነ ቡድን ከዚህ በመለስ ባሉ ጉዳዮች ልዩነት እየፈጠረ አይወራከብም፣ የየራሱን ነጻ መሬት መስርቶ አይታኮስም( በቃላት)፣ከሚታገለው ወይንም ከሚቃወመው ኃይል አንድ ርምጃ ቀድሞ ያስባል ያቅዳል ይዘጋጃል ይተግብራል እንጂ በትናንት ታሪክ አያላዝንም፣ ወያኔን መዝለፍና ማውገዝን የትግሉ መነሻም መድረሻም አያደርግም፡፡

ወያኔ የደደቢቱን እኛ የእለት የእለቱን” በሚል ርዕስ ከአመት በፊት ይመስለኛል በዚሁ መድረክ ባቀረብኩት ጽሁፍ    “ወያኔ የደደቢቱን ዓላማውን በተለያየ መንገድና ዘዴ ተግባራዊ ሲያደርግ እኛ  አንድ ዓላማ ኖሮን፣ ዓላማችንን ተግባራዊ ለማድረግ ወደሚያስችለን ግባችን ለመጓዝ የሚያስችለንን ስትራቴጂ ነድፈን፣ በቂ ዝግጅት አድርገንና ጥንካሬ ፈጥረን ከመንቀሳቀስ ይልቅ ተራርቀን የወያኔን አግር እየተከተልን ከምናደርገው ተቃውሞ አልወጣንም፡፡ ይህም ሕዝብን ለመስዋዕትነት ወያኔንም ለበለጠ እብሪትና አንባገነንነት ያበቃው በመሆኑ ኢትዮጵያ ዛሬም  የግፍና የጅምላ ግድያ እያስተናገደች ነው፡፡ ፖለቲከኞች ይህ አስቆጥቶአቸውና ቁጭት አሳድሮባቸው  ከዚህ በኋላ ሌላ እልቂት ማየት የለብንም በቃ በማለት ተጠራርተው ሸንጎ ተቀምጠው መላ ሊመቱ፣ እቅድ ሊያወጡና ስንዴና እንክርዳዱ ተለይቶ በአጭር ግዜ ከተከታይነት ወደ ቀዳሚነት መሸጋገር የሚያስችል ስትራቴጂ መንደፍ በጀመሩ ነበር፡” የምትል ሀሳብ አስፍሬ ነበር፡፡ ከዛ በኋላ ወያኔ ብዙ ነገሮችን ከወነ፣ ተቀዋሚውም የትናንቱን እየረሳ ለዛሬው እየጮኸ፣ ከለመደው መጎነታተል ሳይላቀቅ፣ ከእኔ እበልጥ እኔ እበልጥ ልክፍቱ ፈውስ ሳያገኝ ለመተባበር ቀርቶ ለመከባበር የሚያበቃ ህሊናዊ እድገት መፍጠር ተስኖት እንዳለ አለ፡፡ እያንዳንድ ድርጊት ለዋናው ግብ ትንሽም ቢሆን አዎንታዊ ድርሻ የሚያበረክት መሆን አለበት፤የጠራ በግልጽ የታወቀና የታመነበት ግብ ከሌለ ግን በብዙዎቹ ዘንድ እንደሚታየው በእለት እለት ጉዳዮች ብቻ መጠመድ ይሆናል፡፡

ተመሳሳይ ጠላት ያላቸው ጓደኛሞች ይሆናሉ፡፡

የአሜሪካ ፕሬዝዳንት አብርሀም ሊንከን የተናገሩት ይህ ቃል እውነት ቢሆንም ለእኛ ሀገር ፖለቲከኞች ለብዙዎቹ ግን አይሰራም፡፡ሁሉም ወያኔ ሲያወግዙ ሲኮንኑ ብሎም ጠላታችን ሲሉ ይሰማሉ፣በተግባር ግን ጠላታችን ከሚሉት ወያኔ በላይ በመካከላቸው ያለው ጠላትነት ያይላል፡፡ይህም በመሆኑ እርስ በእርሳቸውም አይሸናነፉ ወያኔንም አያሸንፉ፡ ብቻ ሲያላዝኑና ብሶት ሲያወሩ መኖር፡፡           

ሰሞኑን አብሮ ለመስራት ትብብር ከፈጠሩት ድርጅቶች የአንዱ የኦጋዴ ብሔራዊ ነጻ አውጪ ግንባር ሊቀመንበር ነጻ እናወጣዋለን የምንለው ህዝብ እኮ እያለቀ ነው በማለት መገንጠል ወቅታዊ ጉዳይ አለመሆኑን ገልጸው በኢትዮጵያ ሀገራዊ አንድነትና  ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን በመመስረት ችግሮችን መፍታት እንደሚቻል በማመን ከአርበኞች ግንቦት ሰባት ጋር አብረው ለመስራት መስማማታቸውን የገለጹበት አነጋገር ወቅታዊውን ችግር የተገነዘበ መፍትሄውንም የተረዳ  በተግባር እንያችሁ  ከማለት ውጪ  እሰየው የሚያሰኝ ነው፡፡

ከዚህ ቀድሞ የተመሰረተው ሀገራዊ ንቅናቄም በምስረታው ሰሞን አቶ ሌንጮ ለታ 25 አመት ሙሉ ወያኔን በየኤምባሲው እየዞርን አማን ውጤት አላመጣንም አሁን የትግሉ መንገድ መለወጥ አለበት ( ቃል በቃል አልገለጽኩ ይሆናል) እንዳሉት ተበታትኖ ከማማትና እንዲህ ሆንን እንዲህ ተፈጸመብን እያሉ ከማላዘን ነጻነት በትግል እንጂ በጩኸት እንደማይገኝ ተገንዝቦ ትብብር መስርቶ አቅምን አቀናጅቶ ለለውጥ መታገሉ ነውና የሚበጀው ይህንኑ መንገድ መያዛቸው ተገቢና ወቅታዊ ርምጃ ነው፡፡ ታዲያ በዚህ አድራጎታቸው አራቱን ድርጅቶች ስናደንቃቸው ከአንዱ በስተቀር የተግባር እንቅስቃሴ  አላየንም አልሰማንምና ቃል የእምነት እዳ እንጂ የእናት አባት እኮ አይደልም የሚለውን የሎሬት ጸጋዬ ገብረመድህን አባባል በማስታወስ ቃላችሁን ተግብሩት ማለት ይኖርብን ይመስለኛል፡፡

በሀገራዊ ንቅናቄው ምስረታ ማግስት “መልእክት፤ ለኢትዮጵያ ሀገራዊ ንቅናቄ  መስራቾች” በሚል ርዕስ በጻፍኳት መልእክት “የፊርማ ሥነሥርዓቱን ለመከታተል በአዳራሽ የተገኘው ነጻነት የናፈቀው፣ ዴሞክራሲ በሀገሩ አብቦ ማየት የሚሻው፣(ለሱም ባይደርስ ለልጆቹ )ኢትዮጵያዊ የየድርጅቶቹ መሪዎች ለመናገር ከመቀመጫችሁ ስትነሱና ወደ ወንበራችሁ ስትመለሱ እንዲሁም ስምምነቱን ስትፈርሙ ቆሞ አጨብጭቦላችኋል ፡፣ያጨበጨበው  ለእናንተ ሳይሆን ላነገባችሁት ክቡር ዓላማ ነው፤ ለደረሳችሁበት የመተባበር ስምምነት ነው፤ ቃላችሁን ተግባራዊ አድርጋችሁ ትግላችሁን አስተባብራችሁ ከወያኔ አገዛዝ ኢትዮጵያን ታላቅቋት ዘንድ መልእክት ነው፡፡ እናም ጭብጨባው የአድናቆት መግለጫ ከመሆኑ በላይ አደራ ነው፤ ትልቅ ሸክም፡፡” ነበር ያልኩት፡፡

 በተግባር የሌሉ ለወሬና ለአሉባልታ እኩያ የሌላቸው የህዝቡ እንቅስቃሴ ትንሽ ጎላ ባለ ግዜ አሸጋግረው ምኒይልክ ቤተመንግስትን በማየት አንገታቸውን የሚታመሙ ሰዎች ከሚያስነሱት አቧራ ራሳችሁን አርቃችሁ ወይኔን በሀሜትና በውግዘት ሳይሆን በድርጊት መታገሉን  አላማችሁ፣ ራሳችሁን ለሥልጣን ለማብቃት ሳይሆን የህዝብን የሥልጣን ባለቤትነት ማረጋገጥ ግባችሁ መሆኑን በተግባር አሳዩ፡፡ ይህን የምለው ራሳችሁ የነገራችሁን ቃላችሁ በመሆኑ እንጂ “ውረድ በለው ግፋ በለው” ለማለት ድፍረቱ ኖሮኝ አይደለም፡፡ ከሚስቶቻቸው ጉያ ሳይወጡ ለምን አትዋጉምለምን ነጻ መሬት ይዛችሁ አታሳዩንምለምን ግዳይ ጥላችሁ አታቅራሩምወዘተ  እንደሚሉት ሰዎች ለመሆን አይቃጣኝም፡፡

ወያኔን እየተከተሉ ማላዘን!

ከምር ለነጻነት ከሚታገለው በምን ተቃውሞ ላሰማ፣ በምንስ ልጩኸ፣እንዴትስ ራሴን የአደባባይ ሰው ላድርግ ወዘተ  የሚለው በመብዛቱ እንጂ የእሬቻው እልቂት፣ የባህር ዳርና ጎንደሩ ጭፍጨፋ በአስር ሺዎች የተፈጸመው የገፍና የግፍ እስራት ወዘተ ተረስቶ የሁለቱ ቴዎድሮሶች ጉዳይ መነጋገሪያም መነታሪኪያም ባልሆነ  ነበር፡፡ ምዕራብ ወለጋ ልጇን ገለው አስክሬኑ ላይ አስቀምጠው የተመጻደቁባትና የተሳለቁባት እናት እንዴት ትረሳለች፡፡አሩሲ ላይ የሁለት ጎልማሳ ልጆቻቸውን አስክሬን ጎን ለጎን አጋድመው የጠሩዋቸው እናትና አባት አንዴት ይረሳሉ፡በየእስር ቤቱ በእሳት የጋዩት ወገኖች አንዴት ይረሳሉ፡፡ ሌላም ሌላም፣እኛ ግን  ራዕይ የለሽ ግብ የለሽ ሆንና ይህን ሁሉ ረስተን በእለት በእለቱ ጉዳይ እንጮሀለን፡፡የወያኔ የሀያ ስድስት ዓመታት ድርጊት እያነሳን እናላዝናለን፡፡

ወያኔዎች ገደሉ፣ አሰሩ፣ ደበደቡ፣ የሀገር ሀብት ዘረፉ ወዘተ እያሉ ሀያ ስድስት ዓመታት ያላባራ ጩኸት  ማሰማት የእነርሱን እኩይ ድርጊት ፈጻሚነት ሳይሆን የእኛን ከንቱነት ነው የሚያሳየው፡፡ ለዚህ ደግሞ ሁለት ምክንያቶችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ አንደኛው ወያኔዎች ለምንና ለማን እንደታገሉ ዛሬ ድረስ መረዳት አለመቻላችንና ከእባብ እንቁላል ርግብ መጠበቅ የሚሉት አይነት መሆናችን ሲሆን ሁለተኛው የምንጮህበት ድርጊት ሁሉ ሲፈጸም እኛ ምን አደረግን በማለት ራሳችንን ለመጠየቅ አለመድፈራችን ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ  ወያኔን ታግለን አሸንፈን ሥልጣን እንይዛለን የሚሉ ሰዎች ወያኔ እየከፋፈልን በማለት በአደባባይ ሲናገሩ ትንሽ እንኳን አለማፈራቸው ያሳዝናል፡፡ እንዲያጠናክራቸው ይሹ ነበር ማለት ነው?

ወያኔ ማድረግ ያለበትን ነው ያደረገው፣ እያደረገም ያለው፣ ወደ ፊትም የሚያደርገው፤ይህን ደግሞ በጩኸትም ሆነ በማላዘን በውግዘትም ሆነ በመኮነን ማስቆም እንደማይቻል ለመረዳት ሀያ ስድስት አመት ሊባን አለመቻሉ ሌላው እንቆቅልሻችን ነው፡፡ ከዚህ በኋላ በዚሁ መንገድ በጩኸትና ዋይታ መቀጠል ደግሞ ተቀዋሚ እየተባሉ መኖርን ከመፈለግ ውጪ ሌላ  ሊሆን አይችልም፡፡ እንደውም ቀን ቀን ወያኔ ይውደም እያሉ በአደባባይ ተቀዋሚ መስለው እየታዩ ማታ ማታ በቤታቸው ለወያኔ እድሜ የሚለምኑ ሳይኖሩ እንደማይቀሩ የአንዳንድ ሰዎች ድርጊቶች ጥርጣሬ ያጭራሉ፡፡ ይህ አይነት ነገር የለም ከተባለ በሁሉም ተዋሚዎች ዘንድ ግለሰብ ድርጅት ሳይባል የወያኔን እግር እየተከተሉ መጮሁ ይብቃ፤ ወያኔ ግዜ እየጠበቀ ወደ ተቀዋሚው ጎራ በሚወረውረው ኳስ መጫወቱም ይብቃ፡፡ ቀድሞ ማሰብ፣ ቀድሞ ማቀድ፣ ቀድሞ መዘጋጀት፣ ቀድሞ መተግበር መቻል ነው በወያኔ ላይ የበላይነት ለመያዝና ወደ ድል ጎዳና ለማምራት የሚያስችለው፡፡ ሲሞቅ ማጋጋል ሲቀዘቅዝ ድራሽን ማጥፋት በፍጹም ታጋይ ሊያሰኝ አይችልም፡፡

ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ጥቅምት 23/1935 ለፓርላማ አባላት ካሰሙት ንግግር የተወሰደው ይህ አባባል መካሪ ሊሆን ከቻለና የቀድሞ ሥርዓት ናፋቂ ካላሰኘኝ እነሆ!  “ የሚመከረው ነገር በዝግታና በጥልቅ ታስቦ በለዘብታ ክርክር ተጣርቶ በትእግሥት እየተመላለሰ ተመክሮ የተቆረጠ ነገር እንዲሆን ነው፡፡” አዎ ወያኔን መታገል በእለት እለት ጎዳዮች በግብታዊነት ጩኸት ሳይሆን በእቅድ በዝግጅት በድርጊት ይሁን፡፡