ላቲኑ   The Latin

(3       ለ      8)

የግዕዝ አቅሙ ሲፈተን በሰይፉ By Saefu ኣዳነች Adanech ብሻው Bishaw

(4 ለ 7)        (4 ለ 7)      (3 ለ 6)     = 11 ለ 20

የአማርኛ ቋንቋ የግዕዙን ኆኄያት ተውሦ ይጠቀማል። ከባዕድ የወረሣቸውንም ቃላት ያለችግር ለመጠቅም የፊደል ገበታውን አሟልቶ ይገኛል። በዚኽም ምክንያት የባዕድ ቃል የኾነውን “ቨ” ለመጠቀም በ“በ” አናት ላይ ክፍተት ትቶ እንደ “ሸ” ሠረዝ በማድረግ የግሉ አድርጎ እየተጠቀመበት ነው። አማርኛ እራሱን ለማዳበር ድክመት ያሣየበት ጊዜ የለም። ይኽንንም በዚኽ ጽሑፍ እገልፃለሁ። የፊደል ገበታውም 276 ኆኄያትን ይዞ ይገኛል። ሁሉንም ግን በአግባቡ አንጠቀምባቸውም። እነዚኽንም ከነአጠቃቀማቸው አሣያለሁ።

እንግሊዝኛ ላቲኑን ተውሦ በ26 ኆኄያት ይጠቀማል። አናባቢዎች ከሌሉት ግን ሃሣብን ለመግለፅ አያስችልም። ስለዚኽ አናባቢዎች ይጠይቃል። እነሱም “a” “e” “i” “o” “u” በዋናነት “ei”, “ie”, ተደራቢ ኾነው “y” አንዳንድ ጊዜ የሚገቡ ናቸው። እነዚኽን ማራቢያዎች እንደ አማርኛው ግዕዝ፣ ካእብ፣ ሣልስ፣ ራብዕ፣ ሐምስ፣ ሣድስ እና ሣብእ መኾናቸው ነው። አማርኛ እንደ “a” “e” “i” “o” “u” መራቢያዎቹን ወደ ጎን ቢይዛቸውና የእንግሊዘኛው አቅም የማይችላቸውን “ቀ” “ጠ” “ጨ” “ፀ”ንና “ጰ”ን አስወግዶ ተመሣሣይ ድምፅ ያላቸውን ቢሠርዛቸው በ22 የአማርኛ ኆኄያት ብቻ ሃሣቡን መግለፅ ይችል ነበር።

ግዕዝ ራሱን የቻለ ድምፁን በገባበት አሠምቶ ቃላት እንዲፈጠሩ የማድረግ ችሎታ ያለው ፊደል ነው። በኆኄያት አጠቃቀሙም ከላቲኑ ያነሰ ነው የሚጠቀመው። አርዕስቱ ላይ በቍጥር የተገለፁትን አማርኛውንና ላቲኑን ያስተውሉ።

አማርኛ በመጥበቅ ወይም በመላላት ትርጕማቸው በዐረፍተ ነገር ውስጥ ካልኾኑ በስተቀረ ምን ማለት እንደኾኑ ለማወቅ የሚያስቸግሩት ቃላት ዐሉት። ይኽ የቋንቋው ድክመት ሣይኾን መዘንጋት የሌለብን ሃሣብን ለመግለፅ ዐረፍተ ነገር መኖር እንዳለበት ነው። ደረጃው እንደዚኽ ነው። ኆኄያት ቃል ይፈጥራሉ። ቃላት ሐረግን ይፈጥራሉ። ሐረግም ንኡስ፣ ጥገኛና መደበኛ በመኾን ባለቤትና አንቀፅ አልባ፣ ሙሉ ስሜትን የማይሠጥና ሙሉ ስሜትን ለመግለፅ የሚችል ይኾናሉ። ንኡስ ሐረግ ከቃል የበለጠ ኾኖ እንኳን ሙሉ መልእክት ሊሠጥ የማይችል መኾኑ እየታወቀ አንድ ቃል መጥበቅ መላላቱ ስለማይታወቅ ቋንቋው ደካማ ነው ማለት የቋንቋን ባህሪይ አለመረዳት ነው። “ይሠራል፣ ይበላል፣ ይጠጣል፣”…ወዘተ የመሣሰሉት ቃላት አማርኛ ውስጥ መገኘታቸው ቋንቋውን ደካማ አያደርጉትም። የላቲን ተጠቃሚ የኾነው እንግሊዝኛም ተመሣሣይ ተጠቃሽ ቃላት ዐሉት። ለምሣሌ “Live” የሚለው ቃል በዐረፍተ ነገር ካልኾነ  “ሊቭ ወይም ላይቭ” “መኖር” ወይም “ቀጥታ” ማለት እንደኾነ አይታወቅም። “ቱ” የሚለው ቃል ያለ ዐረፍተ ነገር በድምፅ ሲሠማ “to” “too” ወይም “two” ለማለት እንደኾነ ለመለየት ያስቸግራል። ይኽንንም ማጤን ያስፈልጋል። ሌላም ችግር ዐለው። “ሊቭ” በድምፅ ብቻ ከኾነ ያለ ዐረፍተ ነገር “Live” ወይም “Leave” የትኛው እንደኾነ ማወቅ አይቻልም። “Neither” Potato” “Route” እና ሌሎችም ኹለት ዓይነት አነባበብ ያላቸው ዐሉ። እንግሊዝኛም እንደ አማርኛ ሁሉ የመጥበቅና የመላላት ባህሪይ ዐለው። ግን ለየት ባለ መልኩ ነው። የተለያዬ ትርጕም ያላቸውን ተመሣሣይ ቃላት በአጭር ድምፅ አወጣጥና ድምፅን በማስረዘም ይለያቸዋል። ይኽን የላቲን ድክመት ሣናነሣ ብልጫ ያለውን ግዕዙን መተቸት በቂ ምርምር አለማድረግና ግንዛቤን ማሣነስ ነው። ከ“ሀ – ፐ” ግዕዙን ያወቀ ከ”A-Z” ከተማረ ሰው በተሻለ መልኩ ቋንቋውን ለማንበብና ለመጻፍ ይችላል። ቢኾንም ላቲኑ ባለው ድክመትም ቢኾን ተቀባይነትን አግኝቶ ተስፋፍቶ ይገኛል። ምክንያቱ እንደሚከተለው ነው።

የተጻፈውን ማንበብና የተባለውን ለመጻፍ አስቸጋሪ የኾነው እንግሊዝኛ ሦስት ዓይነት የማስተማሪያ ዘዴዎች ዐሉት። የመጀመሪያው “Phonics” በሚሉት ዘዴ ህፃናትን በለጋ ዕድሜ ማስተማር ነው። ኹለተኛው መዝገበ ቃላት ውስጥ በየአንዳንዱ ቃል አጠገብ ቃሉ እንዴት እንደሚነበብ የሚገልፅ ድምፅ ጠቋሚዎች ተጽፈው ይገኛሉ። አማርኛም በትክክል ለመጻፍ የሚያስችሉት የድምፅ ጠቋሚዎች ዐሉት። የ“ሀ”ን ዘር ሃሌታው፣ ሐመሩ፣ ብዙኃን፤ የ“ሰ”ን ዘር እሣቱ፣ ንጉሡ፤ የ“አ”ን ዘር አልፋና ዐይኑ እያለ ያመላክታል። ሦስተኛው ዘዴያቸው ዓመታዊ የቃላት ውድድር ማድረግ ነው። ቋንቋቸው እንዴት እንደሚነበብና እንደሚጻፍ ለማስተማር የማያቋርጥ ጥረት ማድረግ ይጠይቃቸዋልና። ይሁን እንጂ እንግሊዝኛ የራሱ ተጠቃሚ በመኾኑ ላቲኑ ከሚሠጠው በላይ ልዩ ድምፅ የሚሠጡትን እንደ አማርኛ ያሉ ባዕድ ኆኄያትን ለማስተናገድ ይቸገራል።

ፀሐይና ጨረቃን፣ ጴጥሮስንና ጸሎትን በምንም የኆኄያት ድግግሞሽ ላቲኑ እንደ አማርኛው ሊገልፀው አይችልም። መቻል ሲባል ደግሞ ማንም የላቲኑን ኆኄያት የሚያውቅ በትክክል ሊያነበው የሚችለው ማለት ነው እንጂ “Q”ን “ቀ” ብሎ እንደመገመት አይደለም። “Q” በእንግሊዝኛው “Quest” በጣሊያንኛ “Questo” ሲል የሚታወቀው በ”K” ድምፅ እንጂ በ“ቀ” ድምፅ አይደለም። ማንም አንባቢ በሌላ አይገምተውም። የላቲን ባህሪው ከዚኽ ሊወጣ አይችልምና።

“Center” “Canada” “Kampala” “Chance” እና “Character” (34) ሰንተር፣ ካናዳ፣ ካምፓላ፣ ቻንስ እና ካራክተር(19) ተብለው ይነበባሉ። እንግሊዝኛው “C” እንደ “ሰ” እና “ከ” “Cha” እንደ “ቸ” እና “ከ” ዘር ኾኖ ቀርቧል። “a b c d”ን የተማረ ሲንተር፣ ሲነዳ፣ ሲሃንስ፣ ሲሃራክተር ብሎ ለማንበብ የሚቸግረው ነው። ይኽ የሚያሣየው ላቲን ተጠቃሚው እንግሊዝኛ መልኩን እየቀያየረ ካልኾነ እንደ ግዕዙ ያለ አናባቢ ራሱን ችሎ እሱነቱን ሳይቀይር ኆኄያቱ በየገባበት ቃል ውስጥ የአገባብ አቀማመጡ ባህሪውን ሳይቀይሩት ለመነበብ አለመቻሉን ነው። ላቲኑ ችግሩን ሊደብቅ አይችልም። ብዙ ዝርዝር ውስጥ ላለመግባት ነው እንጂ… አናባቢው ቀድሞ ሲገባ፣ መሃከል ላይ ሲኾን፣ መጨረሻ ላይ ሲጻፍ፤ተደራርበው ሲገቡና እነዚኽም ቦታ ሲቀያየሩ ባህሪያቸው ስለሚቀያየር በሚል ደንብ የተወሣሰበ ነው።

ስለዚኽ ነው ተወላጁ ራሱ ይኽንን ቃል እንዴት ነው የምትጽፈው እያለ የሚጠይቀው። ( ከላይ ላቲኑ 34 ኆኄያት የወሰደበትን ግዕዙ 19 ብቻ እንደወሠደበት ይገንዘቡ። )

ቀ፣ ጠ፣ ጨ፣ ጸ፣ ፀ እና ጰ የሚባሉትን ድምፆች ለመጻፍ ከመቻሉም በላይ ግዕዙ ያለውን ጥንካሬ ላሣይ።

ቈ ቍ ቊ ቋ ቌ  ኈ ኊ ኍ ኋ ኌ  ኰ ኵ ኲ ኳ ኴ  ጐ ጒ ጕ ጓ ጔ

እነዚኽን ኆኄያት የፊደል ገበታ ላይ አይተዋቸዋል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። ከ ቋ፣ ኋ፣ ኳ፣ ጓ፣ በስተቀር ሌሎቹን አይጠቀሙባቸውም ይኾናል። ጥቅማቸውን አሁን ሲመለከቱ ሊግርምዎት ይችላል። በእርግጥ የላቲኑን ቃላት ለመጻፍ እንዲያገለግሉ የተፈጠሩ ናቸው። በዚኽም ብልጫቸውን ይገልፃሉ። በላቲን የተጻፉት ቃላት እንግሊዝኛ እና ጣሊያንኛ ቃላት ያሉበት ነው። ከላይ የተደረደሩት ኆኄያት ውስጥ የ“ቀ”ዉ ዘር በላቲኑ ውስጥ ስለሌለ እሱን በመተው ሌሎችን ቀጥዬ አቀርባለሁ።

ኈ HO st         –     ኰ CO ll ect       –    ጐ GOA l
ኊ WHO m    –     ኵ CU shion     –      ጒ GWI nnett
ኍ WHI m      –     ኲ QUEE n      –      ጕ GUI do
ኋ WHA t        –     ኳ QUA lity     –        ጓ GUA rda
ኌ WHE n       –     ኴ QUE st        –         ጔ GWE n

ይኽ ከዚኽ በላይ ያለው ምሣሌ የሚያሣየን ግዕዙ የማናቸውንም ቋንቋ ተቀብሎ የማሣደግ ችሎታ እንዳለውና ወደፊትም ከላቲኑ በተሻለ በረቀቀ መልክ ሊያድግ እንደሚችል ነው።

ላቲኑ በአገራዊ ቋንቋ ላይ እያስከተለ ያለውን ችግር በተመለከተም ቀደም ሲል ከዶክተር ኣበራ ሞላ ጋር ያደረግሁትን ቃለምልልስ ዩቲዩብ ውስጥ ያገኛሉ https://www.youtube.com/watch?v=y4u4t9wcGQw ያዳምጡ።

ግዕዝ ዩኒኮድ (Unicode) ፲፱፻፺፭ ዓ.ም.  (በፍቃድ የተወሰደ)