Friday, 26 May 2017

 የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ፣ ከግንቦት 1 ቀን ጀምሮ ለዐሥራ አራት ቀናት ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ፤ ሚያዚያ 10 ቀን በሚነበበው ስንክሳርና በፍትሕ መንፈሳዊ መጽሐፍ ላይ የሰፈረው ንባብና ሥርዋጽ አንቀጽ ሕገ ወጥ በመሆኑ ከአሁን በኋላ እንደይነበብና በቀጣይ ሕትመቶችም ከመጻሕፍቱ እንዲወጣ መወሰኑን አስታወቀ። ለውሳኔው እንደ ምክንያት የቀረበው፤ በፍትሕ መንፈሳዊ ላይ፣ “ኢትዮጵያውያን ከራሳቸው ሊቃውንት ጳጳሳትን አይሾሙም” የሚለው በ7ኛው መቶ ዓመት ግብፃውያን አባቶች በሥርዋጽ ያስገቡት ሕገወጥ ጽሁፍ ስለሆነ፤ ምልዓተ ጉባዔው ተነጋግሮ፤ ጽሁፉ የአገራችንና የቤተ ክርስትያናችንን ክብር የሚነካ ሆኖ በመገኘቱ ከአሁን በኋላ ጽሁፉ እንዳይነበብ፤ ከመጻሕፍቱም፣ እንዲወጣ እና ወደፊትም በሚታተሙ መጻሕፍት እንዳይገባ ሲል መወሰኑን አስታውቋል። 

የቅዱስ ሲኖዶሱ ምልአተ ጉባኤ በዓመት ሁለት ጊዜያት እንዲሆን፣ በፍትሕ መንፈሳዊ መጽሐፉ በተደነገገው መሠረት፣ መደበኛ የርክበ ካሕህት ስብሰባውን ከበዓሉ ዋዜማ ከግንቦት 1 ቀን 2009 .ም ጀምሮ ለ14 ቀናት ያካሄደ ሲሆን፤ ባለ አስራ አራት ነጥብ መግለጫም አውጥቷል። አክሎም፤ በሳዑዲ ዓረቢያ የሚገኙ ወገኖች ሕጋዊ ፍቃድ ሳይኖራቸው ለበለጠ ሥቃይ ከመዳረጋቸው በፊት፣ በተቀመጠላቸው ጊዜ ገደብ ውስጥ እንዲወጡም አሳስቧል።

የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባዔ በመግለጫው ያወጣቸውን ባለ 14 ነጥቦች ውሣኔዎች ከዚህ እንደሚከተለው ቀርቧል።

*** *** ***

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ

የተሰጠ መግለጫ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ መደበኛ ስብሰባ፣ በዓመት ሁለት ጊዜያት እንዲሆን በፍትሕ መንፈሳዊ በተደነገገው መሠረት የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የዘንድሮውን መደበኛ የረክበ ካህናት ስብሰባ ከበዓሉ ዋዜማ ከግቦት 1 ቀን 2009 .ም ጀምሮ ለ14 ቀናት ያህል ሲወያይ ሰንብቷል። 

በምልዓተ ጉባዔው የተደረገውን የመክፈቻ ንግግር በተመለከተ፡

1. ከፍ ብሎ እንደተገለጸው ሁሉ በአሁኑ ጊዜ በአገራችን በአንዳንድ አካባቢ በተከሠተው ድርቅ ለረሃብ የተጋለጡ ወገኖቻችንን ለመታደግ መንግሥት እያደረገ ያለውን ከፍተኛ ጥረት በመገንዘብ፣ በተ ክርስቲያናችንም የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ኃላፊነቱን ወስዶ ከእርዳታ ሰጪዎች ጋር በመነጋገርና በማስተባበር የሚገኘውን ርዳታ ድርቁ የተከሠተባቸው የክልል መሪዎች በሚሰጡት አቅጣጫ እንዲፈጸም ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል።

2. ከቤተ ክርስቲያናችን እምነትና ሥርዓት ውጭ በመደራጀት የኑፋቄ ትምህርት ሲያካሄድ የነበረው አሰግድ ሣህሊ የተባለ ግለሰብ ለበርካታ ዓመታት የኑፋቄ ትምህርት ሲያሰራጭ መኖሩ በመረጃ የተደረሰበትና የተረጋገጠበት በመሆኑ ከአሁን በኋላ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስም እንዳያስተምር፣ ምዕመናንም እንዳይከተሉት ምልዓተ ጉባኤው ከግንቦት 3 ቀን 2009 .ም ጀምሮ ቃለ ውግዘት አስተላልፏል። ከቤተ ክርስቲያኒቱ ዕውቅና ውጭ ምንም ዓይነት ፈቃድ ሳያገኙ በተመሳሳይ ሁኔታ አዳራሽ ተከራይተው በቤተ ክርስቲያናችን ስም ወንጌል እናስተምራለን፣ ዝማሬ እናሰማለን የሚሉ ሕገወጦች ከእንዲህ ዓይነት ድርጊታቸው እንዲታረሙ፣ ምዕመናንንም በተለይ ወጣቱ ትውልድ እንዲህ ዓይነት ሕገወጦችን ከመከተልና ሃይማኖታችሁን ከሚበርዙ ኃይሎች እንድትጠበቁ ቅዱስ ሲኖዶስ አበክሮ ያሳስባል።

3. የቤተ ክርስቲያኒቱ መገናኛ ብዙሃን ጉዳይን በተመለከተ የሚዲያ ድርጅቱ በሰው ኃይል እንዲጠናከር፣ የሚያስተላልፋቸው መልዕክቶችም ጥራት እንዲኖራቸው ማድረግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ተነጋግሮ ለ2010 በጀት ዓመት ብር 12,000,000.00 (አስራ ሁለት ሚሊየን ብር) ተፈቅዶለት በበጀት ተጠናክሮ ሥራውን እንዲቀጥል ተስማምቷል።

4. በእየሩሳሌም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስለ ዴርሡልጣን ገዳም ችግር ጉዳይ ጉባኤው በስፋት ከተነጋገረ በኋላ ችግሩን አስመልክቶ መፍትሔ ማግኘት እንዲቻል ለኢፌዲሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፣ በኢትዮጵያ ለእሥራኤል ኤምባሲና በእሥራኤል ለኢትዮጵያ ኤምባሲ ደብዳቤ እንዲጻፍላቸው ተወስኗል።

5. ሚያዝያ 10 ቀን በሚነበበው መጽሐፈ ስንክሳርና በፍትሕ መንፈሳዊ መጽሐፍ ላይ ኢትዮጵያውያን ከራሳቸው ሊቃውንት ጳጳሳትን አይሹሙ የሚለው በ7ኛው መቶ ዓመት ግብጻውያን አባቶች በሥርዋጽ ያስገቡት ሕገወጥ ጽሑፍ ስለሆነ ምልዓተ ጉባዔው ተነጋግሮ ጽሑፉ የአገራችንና የቤተ ክርስቲያናችንን ክብር የሚነካ ሆኖ በመገኘቱ ከአሁን በኋላ ጽሑፉ እንዳይነበብ፤ ከመጻሕፍቱም ውስጥ እንዲወጣ ወደፊትም በሚታተሙ መጻሕፍት እንዳይገባ ተወስኗል።

6. ሥርዓተ ምንኩስናና ሥልጣነ ክህነት አሰጣጥን አስመልክቶ ቀደም ባሉት ዓመታት የተወሰኑ ውሳኔዎች በአብዛኛው አፈጻጸም ላይ ችግሮች እንዳሉ ስለሚታይ ወደፊት የሚወስነው ተጠብቆ እንዲሠራበት ጉባኤው ተስማምቷል።

7. ሕጋዊ ፈቃድ የሌላቸው ሰባክያንና አጥማቂዎች በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ አገልግሎት እንዳይሰጡ የተወሰነ ቢሆንም ውሳኔው መከበር ስላልቻለ ችግሮችም በስፋት የሚታዩ ስለሆነ አሁንም በውሳኔው መሠረት የቁጥጥሩ ሥራ ተጠናክሮ እንዲቀጠል ተስማምቷል።

8. በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስም በአዲስ አበባም ሆነ በየአህጉረ ስብከቱ በማኅበር ተደራጅተው ገዳማትን በማስጐብኘትም ሆነ በቤተ ክርስቲያኒቱ ስም በልዩ ልዩ አቅጣጫ የሚንቀሳቀሱ ማኅበራትን መቆጣጠር የሚቻልበት የማኅበራት ማደራጃ ደንብ እንዲወጣ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል።

9. የቤተ ክርስቲያኒቱ ሁለንተናዊ ችግር በባለሙያዎች ተጠንቶ እንዲቀርብ ቀደም ሲል በተወሰነው መሠረት ጥናቱ ተጠናቆ ከቀረበ በኋላ ጉባኤው ተመልክቶ የሕግ ባለሙያዎችና የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ባሉበት ተመርምሮና ተስተካክሎ ለጥቅምቱ 2010 .ም የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ እንዲቀርብ ተወስኗል።

10. የስብከተ ወንጌል መስፋፋት፣ የሰንበት ት/ቤትና የመንፈሳውያን ኮሌጆች መጠናከር የአብነት ት/ቤቶች መደራጀትና በበጀት እንዲደገፉ ማድረግ የቤተ ክርስቲያኒቱ ዓይነተኛ ተግባር መሆኑን ምልዓተ ጉባኤው ተነጋግሮ በስብከተ ወንጌል ትምህርት አሰጣጥና በመንፈሳውያን ኮሌጆች ደቀመዛሙርት አያያዝ ጥብቅ ክትትል እንዲደረግ ጉባኤው ወስኗል።

11. የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የራሷ የሆነውን ሀብትና ቅርስ በባለቤትነት መጠበቅና ማስጠበቅ እንዲቻል ተዘጋጅቶ የቀረበውን ጥናት ቅዱስ ሲኖዶስ ካዳመጠና ከተወያየበት በኋላ የመጨረሻ ውሳኔ ለመስጠት በቅድሚያ በቋሚ ሲኖዶስ ታይቶ እንዲቀርብ ወስኗል።

12. ብፁዓን አበው በሌሉባቸው አህጉረ ስብከት የሚመደቡ ዕጩዎች ቆሞሳት ምርጫን በተመለከተ ከሀገር ውስጥና ከሀገር ውጪ የሚገኙ ቆሞሳትን በማወዳደር 16 ቆሞሳት ለኤጲስ ቆጶስነት ተመርጠዋል፤ በዓለ ሲመታቸውን ሐምሌ 9 ቀን 2009 .ም እንዲፈጸም ተወስኗል።

13. ኤጲስ ቆጶሳት የሌሉባቸውን የውጭ አህጉረ ስብከት በተመለከተም በጥቅምቱ 2010 .ም በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባዔ እየታየና እየተጠና ብፁዓን አበው እንዲመደቡባቸው ለማድረግ ቅዱስ ሲኖዶስ ተስማምቷል።

14. በኦሮምያ ክልል በሰባት ዞኖች በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች የሚማሩ ተማሪዎች መንፈሳዊውን ትምህርት በቋንቋችን እንዳንማር ማኅበረ ቅዱሳን በደል አድርሶብናል በሚል ባቀረቡት አቤቱታ ዩንቨርሲቲዎቹ ያሉበት አህጉረ ስብከት ጉዳዩን ግራና ቀኝ አጣርተውና ተመልክተው መፍትሔ እንዲሰጡና ውጤቱ ለቅዱስ ሲኖዶስ እንዲቀርብ ተወስኗል።

ቅዱስ ሲኖዶስ ከዚህ በላይ በተገለጹት የውሳኔ ነጥቦችና በሌሎችም ዓበይት ጉዳዮች ላይ ለ14 ቀናት ሲወያይ ሰንብቶ ስብሰባውን በጸሎት አጠናቋል።

እግዚአብሔር አምላክ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን።

አባ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ

 ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት

ግንቦት 14 ቀን 2009 .ም 

ስንደቅ